ፍትሐዊ የመስኖ ውኃ አጠቃቀምን በማረጋገጥ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የውኃ እና መሬት ሀብት ማዕከል አስታውቋል፤ አርሶ አደሮችም በተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ነው የተናገሩት::
በሰሜን መጫ ወረዳ የቆጋ መስኖ ልማት ተጠቃሚ አርሶ አደሮች እንዳሉት ፍትሐዊ የመስኖ ውኃ ተጠቃሚነት በመኖሩ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው:: ለዚህ ደግሞ ከውኃ እና መሬት ሀብት ማዕከል ያገኙት ስልጠና እና ግንዛቤ እንዳገዛቸው አክለዋል:: እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ ያገኙት ስልጠና ኢፍትሐዊ የመስኖ ውኃ አጠቃቀምን ያስቀራል፤ በዚህም የጥቅም ግጭት እንዳይኖር ያደርጋል::
ከተጠቃሚዎቹ መካል አርሶ አደር አበባው አቤ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አርሶ አደሮች አደረጃጀቶችን (የውኃ ኮሚቴ) መፍጠራቸውን ተናግረዋል፤ ኮሚቴው በሚያወጣው ተራ መሠረትም “ያለምንም ችግር የመስኖ ውኃውን በፍትሐዊነት እየተጠቀምን እንገኛለን” ብለዋል::የውኃ እጥረት ሲከሰት ደግሞ የባሰበትን በመለየት ቅድሚያ እንደሚሰጡ ነው የገለጹት::
ሌላዋ ተጠቃሚ አርሶ አደር ትርንጎ ሞላ የውኃ እጥረት አልፎ አልፎ ቢከሰትም በተፈጠረው አደረጃጀት መሠረት በፍትሐዊነት እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፤ የውኃ እና መሬት ሀብት ማዕከል ያደረገላቸው ስልጠና ደግሞ “እገዛው ከፍተኛ ነው፤ እኔም ኑሮየ ተሻሽሏል፤ በደንባችን መሠረት የማይገዛ ካለም ቅጣት ስለሚጠብቀው ኢፍትሐዊ አይኖርም:: ውኃችንን የምንጠቀመው በመተሳሰብ ነዉ ” ብለዋል::
የሰብል ልማት ባለሙያዋ ሻሺቱ ጫኔ የሚለማውን የሰብል አይነት እና የማሳ ስፋት ታሳቢ ያደረገ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል መኖሩን ተናግረዋል::
በውኃ እና መሬት ሀብት ማዕከል የውኃ ሀብት አስተዳደር ስፔሻሊስት ደርበው ሻንቆ ፍትሐዊ የውኃ ሀብት አጠቃቀምን በማረጋገጥ የምግብ ፍላጎትን ማሟላት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፤ ለዚህ ደግሞ በማዕከሉ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: በውጪ ሀገራት የተገኙ የመስኖ ውኃ ሀብት አጠቃቀም ተሞክሮዎች ተቀምረው የመስኖ ተጠቃሚዎች እንዲለማመዱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
(እያያው ተስፋሁን)
በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም