ፖሊዮ እና ተጽዕኖዉ

0
25

ታሪካዊ ዳራው

የዓለም የጤና ድርጅት ፖሊዮ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የነበረ የማኅበረሰብ የጤና ስጋት መሆኑን ጽፏል:: መረጃው ለዚህ አብነት የሚያደርገው በግብፅ ሀገር የተገኘው አንድ እግሩ የሰለለ/በልጅነት ልምሻ የተጎዳ/ ሰው የሚያሳይ ጥንታዊ የድንጋይ ላይ ሥዕልን ነው:: ሥዕሉ የተሳለበት ጊዜ ከ1580 እስከ 1350 ዓ.ዓ መሆኑ ፖሊዮ ብዙ ሺህ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ የዘለቀ በሽታ እንደሆነ ማረጋገጫ ተደርጓል::  የልጅነት ልምሻ በተለይ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም ላይ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ለሽባነት አልፎሞ ለሞት መዳረጉን የድርጅቱ መረጃ ያሳያል::

በማዮ ክሊኒክ የጤና ድረ ገጽ ላይ የወጣው ጽሁፍ ፖሊዮ ምን ያህል የማኅበረሰብ የጤና ስጋት እንደነበር 77 ዓመታትን መለስ ብሎ ቃኝቷል:: በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ልጆቻቸው በፖሊዮ የመያዝ ስጋት አድሮባቸው ስለነበር በተለያዩ ትርኢቶች ከመሳተፍ ጀምሮ ከስፖርታዊ ውድድሮች፣ ከጋራ የመዋኛ ገንዳዎች እና  ሕዝብ ከሚሰበሰብባቸው ቦታዎች መራቅን መፍትሔ አድርገው እንደነበር አትቷል:: አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ከማያውቋቸው ሕጻናት ጋር እንዳይቀራረቡ  ማድረግን በበሽታው ላለመያዝ እንደ መከላከያ መንገድ ይጠቀሙ ነበር:: ከዚህ ባለፈ የበሽታ ምልክት ስለ መኖር አለመኖሩ በየጊዜው ያረጋግጡ እንደነበርም ጽፏል::

በዚያን ዘመን በአሜሪካ ሚኒሶታ የሚገኘው ሴንት ሜሪ ሆስፒታል ብዙ የፖሊዮ ሕሙማንን በተለየ የሕክምና ክፍል ውስጥ አድርጎ ክትትል ያደርግም ነበር:: የመተንፈሻ አካላት ጡንቻዎቻቸው የተጎዳባቸውን ሕሙማን “የብረት ሳንባ” (iron lungs) ተብለው በሚጠሩ ትልልቅ ማሽኖች እንዲታገዙ አድርገዋል::  ማሽኖቹ እንዲተነፍሱ  እና ረዘም ላለ ጊዜ በሕይወት እንዲቆዩ አስተዋፅዖ ያደርጉ እንደነበርም መረጃው አክሏል:: ይህም ታሪክ የፖሊዮን አስከፊነት በግልጽ የሚያሳይ ነው::

ፖሊዮ እያደረሰ ያለው ተጽእኖ ያበቃ ዘንድ የመጀመሪያው የፖሊዮ ክትባት እ.አ.አ በ1955 ይፋ ተደርጓል:: ከዚያ በኋላ በየጊዜው ማሻሻያ እየተደረገበት ዛሬ ላይ ፖሊዮን ከዓለም ለማጥፋት እንደ ዋና መሳሪያ ሆኖ በሁሉም የዓለም ሀገራት እየተሠራበት ነው:: ሆኖም ከጎርጎሪዮሳዊው 1955 ጀምሮ ይፋ የተደረጉ የፖሊዮ መከላከያ መድኃኒቶች የፖሊዮ በሽታ ስርጭት እንዲቀንስ ቢያደርጉም ስጋትነቱ ግን ዛሬም ድረስ አሳሳቢ ሆኖ ዘልቋል::

ፖሊዮ ምንድን ነው?

ፖሊዮ ወይም የልጅነት ልምሻ ለእኛዋ ሀገር ኢትዮጵያም አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኖ በክትባት መከላከል ከሚቻሉ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል:: የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ፣ ከዬኒሴፍ እና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ለብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል::

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ባለሙያ የሺወርቅ አሞኘ የፖሊዮ በሽታ ምንነት፣ የክትባት ዘመቻው ዓላማ፣ የአፈጻጸም ሂደት እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሚናን በተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል:: ፖሊዮ በዐይን በማይታይ ፖሊዮ በተባለ ቫይረስ የሚመጣ በሽታ መሆኑን  ገልጸዋል:: በሽታው በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል:: የመተላለፊያ መንገዱም የተበከለ ምግብ እና ውኃ እንደሆነ አስታውቀዋል::

የጤና አጠባበቅ ትምህርት ባለሙያዋ ፖሊዮ የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት የእጅ፣ የእግር ወይም የሁለቱም መዛል /መዝለፍለፍ/፣ ዘላቂ የሆነ ሽባነት አልፎም ለሞት የሚያበቃ በሽታ ነው ብለዋል:: ፖሊዮ አሁንም ድረስ መድኃኒት አልተገኘለትም:: በመሆኑም በበሽታው ተይዞ የጡንቻ መዛል ያጋጠመው ታማሚ የመዳን ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ወይዘሮ የሺወርቅ ገልጸዋል::

የፖሊዮ በሽታ ምልክቶች

ወይዘሮ የሺወርቅ እንደሚሉት ፖሊዮ በአብዛኛዎቹ ሰዎች  ምንም አይነት ምልክት ላይታይ ይችላል:: በአንዳንዶቹ ላይ ግን አልፎ አልፎ ቀለል ያሉ ምልክቶች ይከሰታሉ:: ከእነዚህ ምልክቶች መካከል ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ማስታወክ፣ ድካም፣ የእጅ እና የእግር ህመም፣ የጡንቻ ድክመት ተጠቃሾች ናቸው::

ፖሊዮ በኢትዮጵያ

የጤና አጠባበቅ ትምህርት ባለሙያዋ ወይዘሮ የሺወርቅ አሞኘ ፖሊዮ በኢትዮጵያ እንዲሁም  በአማራ ክልል አሁን ያለበትን ደረጃ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ገለጻ አድርገዋል:: በዚህም እንደ ሀገር ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ፖሊዮ በስድስት ወረዳዎች መቀስቀሱን አስታውቀዋል:: 40 ሕጻናት በበሽታው ሲያዙ ሁለቱ በአማራ ክልል እንደሚገኙ ጠቁመዋል:: በአሁኑ ወቅትም ለአፋር ክልል አጎራባች በሆኑ በጅቡቲ ወረዳዎች ጭምር ሪፖርት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::

በአማራ ክልል ከ2012 – 2016 ዓ.ም ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ 12 የፖሊዮ ህሙማን መመዝገባቸውን ወይዘሮ የሺወርቅ አረጋግጠዋል::

የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎች

የፖሊዮ ወረርሽኝን በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘላቂነት መቆጣጠር እና መከላከል ላይ ጤና ቢሮን ጨምሮ ሁሉም የጤናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ባለሙያዋ ጠቁመዋል:: የወረርሽኝ ምላሽ የክትባት ዘመቻ ወረርሽኙ  በተከሰተባቸው የክልሉ አካባቢዎች እና በአጎራባች ወረዳዎች ተካሂዷል፤ ይህም ስርጭቱ እንዳይሰፋ ዕድል መፍጠሩን ነው የገለጹት::

ክትባቱን በዘመቻ ከመሥጠት ጀምሮ መደበኛ የክትባት ፕሮግራም እንዲጠናከር የሚያደርጉ ሥራዎች መከናወናቸው፣ የፖሊዮ በሽታ ቅኝት ሥራም በቅንጅት እንዲከናወን መደረጉን አስታውቀዋል::

የፖሊዮ ቫይረስ አሁንም ስጋት ሆኖ ለምን ቀጠለ? ለሚለው ወይዘሮ የሺወርቅ ምላሽ የሰጡት በብዙ ምክንያቶች ያልተከተቡ ሕጻናት ቁጥር ከፍ ብሎ በመገኘቱ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የበሽታውን ተፈጥሯዊ ባህሪ ምክንያት አድርገዋል:: አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሕጻን መኖር ከ200 በላይ ሌሎች ሕጻናትን  ለቫይረሱ ተጋላጭ ማድረጉን ለዚህ አብነት አድርገዋል::

የፖሊዮ በሽታን መከላከል የሚቻለው ሕጻናትን በመደበኛ የክትባት መርሀ ግብር እና በዘመቻ የሚሰጠውን የማጠናከሪያ ክትባት በአግባቡ እንዲወስዱ በማድረግ መሆኑን ደግሞ በዋና መፍትሔነት ጠቁመዋል:: የፖሊዮ በሽታን እንደ ሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማጥፋት እየተተገበሩ ከሚገኙ የተለያዩ ስልቶች መካከል መደበኛ የፖሊዮ ክትባት ሽፋንን ከ90 በመቶ በላይ ማድረስ፣ ተጨማሪ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎችን ማካሄድ፣ የበሽታዎች ቅኝት እና የአሰሳ ሥራዎችን ማጠናከር ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ገልጸዋል::

የፖሊዮ ክትባት ዘንድሮም እንደ ሀገር አማራ ክልልን ጨምሮ በአፋር፣ በሀረሪ፣ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ይሰጣል:: በአማራ ክልልም ከመስከረም 30 – ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይሰጣል:: ሰሜን እና ምስራቅ ጎጃም፣  ደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች፤ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ እና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደሮችም ክትባቱ የሚሰጥባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ወይዘሮ የሺወርቅ አስታውቀዋል::

ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ፖሊዮ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት የሚያጠቃ መሆኑን በመግለጽ ክትባቱም በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናት እንዲወስዱ ምክረ ሐሳቡን አስቀምጧል:: በአማራ ክልል የሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት ግን ዕድሜያቸው ከአሥር ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ያካትታል:: ይህም በሽታው ከአምስት ዓመት በላይ በሆኑ ታዳጊዎች ላይ በመከሰቱ  ነው::  ሦስት ሚሊዮን 533 ሺህ 869 ሕጻናን ክትባቱን ይወስዳሉ ተብሎ ዕቅድ መያዙን ወይዘሮ የሺወርቅ ጠቁመዋል::

ክትባቱ በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት ቤት ለቤት ይሰጣል:: በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎችም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ጭምር እንደሚሰጥ ወይዘሮ የሽወርቅ አስታውቀዋል::

በመደበኛው የክትባት መርሀ ግብር ክትባት ያልጀመሩ እና ጀምረው ያቋረጡ ሕጻናትን በመለየት በጤና ተቋማት እንዲሁም በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ላይ ክትባቱ ይሰጣል:: ክትባቱ ከአንድ ወር በኋላ ቀጥሎ እንደሚሰጥም ታውቋል::

ጤና አዳም

የፖሊዮ ክትባት

የሚሰጥበት ጊዜ

ታሪካዊ ዳራው

የፖሊዮ ክትባት በአማራ ክልል ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ይሰጣል::

ክትባቱ በሰሜን እና ምሥራቅ ጎጃም፣  በደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች፤ በጎንደር፣ በደብረ ታቦር፣ በደብረ ማርቆስ እና በባሕር ዳር ከተማ ይሰጣል::

ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የክትባቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ

ሦስት ሚሊዮን 533 ሺህ 869 ሕጻናትን ለመክተብ ዕቅድ ተይዟል::

ክትባቱ ቤት ለቤት ይሰጣል::

በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም ሕዝብ የሚበዛባቸው አካባቢዎች የክትባት ማዕከላት ይሆናሉ::

መደበኛውን ክትባት የወሰዱም ሆነ ያልጀመሩ ሕጻናት ክትባቱን መውሰድ ይችላሉ::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here