የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤፍን ለምግብነት ማዋል የጀመረው በጠንካራዋ መሪ በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት እንደነበር ጋዜጠኛ ፍስሐ ያዜ “የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ፡- ከኖኅ እስከ ኢሕዴግ” በሚለው ቁጥር አንድ መጽሐፍ ገልጿል:: ንግሥተ ሳባ የነገሰችው በአክሱም አቅራቢያ በጥንቱ አጠራር ሳባ ከምትባለው ከተማ ነበር:: ንግሥተ ሳባ በአባቷ በአጋቦስ (ተዋስያ) እግር ተተክታ ኢትዮጵያን መግዛት እና ማሥተዳደር የጀመረችው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1013 ዓመተ ዓለም ጀምሮ ነው::
ንግሥተ ሳባ የሚለው ስሟ ሳይሆን የሳባዊያን ንግሥት ማለት ነው:: የንግሥተ ሳባ መጠሪያ ስሟ በክብረ ነግሥት ማክዳ፣ በመጽሐፈ ነገሥት በቀዳማዊ እና ካልዕ፣ በዜና መዋል ንግሥተ ሳባ፣ በወንጌል ንግሥተ አዜብ ተብሎ ተቀምጧል::
በንግሥተ ሳባ ዘመን የኢትዮጵያ ወሰን ወይም ግዛት በምሥራቅ እስከ ማዳጋስካር፣ እስከ ፋርስ ባሕር፣ በምዕራብ እስከ ኑቢያ፣ እስከ ምስር (ግብጽ) ጠረፍ፣ በደቡብ እስከ ኒያንዛ ማለትም የቪክቶሪያ ሐይቅ ድረስ ነበር::
በእርሷ የንግሥና ዘመን የዓረብ፣ የግብጽ፣ የሕንድ፣ የእየሩሳሌም እና ሌሎች ሰዎች ሸቀጣሸቀጥ፣ ልብሽ፣ ሽቶ፣ እጣን፣ ወርቅ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ይነግዱ ነበር:: በዚህ ዘመን ደግሞ በእየሩሳሌም የነገሠው የዳዊት ልጅ ጠቢቡ ሰለሞን ነበር::
ንግሥተ-ሳባ ከ3000 ዓመታት በፊት ወደ እሥራኤል እየሩሳሌም ከተማ አቅንታ ንጉሥ ሰለሞንን እንደጎበኘችው ይነገራል። በሺህዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፉ ሠነዶችም ይህንኑ ያጠናክራሉ። እነዚህ ሠነዶች በተለያዩ መልኮች ተሠንደዋል:: በመጽሐፍ ቅዱሥ እና በቅዱስ ቁርአን ንግሥቲቱ የተለያዩ ስሞችን ይዛ ትገኛለች። የንግሥተ-ሣባ ታሪክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነትን ከመሠረቱት አንዱ መሆኑንም የታሪክ ተመራማሪዎች ይመሰክራሉ። የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አየለ በክሪ የዘመነ ደኣማት (ቅድመ አክሱም) የሳባ ንግሥት በኢትዮጵያ ታሪክ እና ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ስላላት ጉልህ አሻራ እንዲሁም እስከ ዛሬ ዘልቆ ስላለው አወዛጋቢው ንግሥታዊ ግዛቷና ማንነቷ ለኤስ ቢ ኤስ ሬዲዮ ማብራሪያ ሰጥተዋል:: የንግሥቲቱ ታሪክ በዓለም ዙሪያ ለበርካቶች የውበት፣ የፍቅር፣ የሠላም ብሎም ዕውቀትን የመሻት ጉጉት ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፤ ለኢትዮጵያውያን ግን የታሪክ የጀርባ አጥንት ነው። የንግሥተ ሳባ ታሪክ በኢትዮጵያ ቢያንስ 700 ዓመታት እንደ ሕገ-መንግሥት ተደርጎ ተወስዷል።
ንግሥቲቱ የተለያዩ ስሞች አሏት። በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ንግሥተ-ሣባ ተብላለች። በአዲስ ኪዳን «የደቡብ ንግሥት» ተብላ ተጠቅሳለች። በቁርአን «ቢልቅስ» ትባላለች። በኢትዮጵያ ቢያንስ ሰባት መቶ ዓመታትን ባስቆጠረው ክብረ-ነገሥት መጽሐፍ ደግሞ «ማክዳ» መጠረያዋ ነው። የግዕዙ ክብረ-ነገሥት ከሰባት መቶ ዓመት በፊት በዐፄ አምደ-ጺዮን ዘመነ መንግሥት እንደተተረጎመ ይነገራል። ከብሉይ ኪዳን፣ ከዓረብ መዛግብት እና ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎች ተውጣጥቶ የተዋቀረው ክብረ-ነገሥት ንግሥቲቱ ንጉሥ ሰለሞን እንዴት እንደጎበኘች በዝርዝር ይተርካል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙት ታላላቅ መጽሐፍት መካከል አንዱ “ክብረ ነገሥት” የኢትዮጵያ ንግሥና በቀጥታ ከንጉሥ ሰለሞን እና ከንግሥት ሳባ ልጅ በሆነው በቀዳማዊ ምኒልክ እንደወረደ እንዲህ ይተርካል “ከጌታ ልደት በኋላ በ325 ዓ.ም በኒቅያ ጉባዬ ለተሰበሰቡት ሮማዊው ፓትሪያርክ ዶሚስዩስ ከቅድስት ሶፍያን ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለው መጽሐፍ ላይ “የኢትዮጵያ ንጉሥ በቀጥታ (በብኩርና) መስመር እና ተርታ ከሰለሞን ንጉሥ ይወርዳል፤ የሮም ንጉሥ ግን በታናሽነት መስመር ይወርዳል” የሚል አለ፤ ይሄው መጽሐፍ ደግሞ የኢየሩሳሌምን ግማሽ እና የዓለምን ደቡብ በሙሉ ለኢትዮጵያ ንጉሥ’ የቀረውን የኢየሩሳሌምን ክፍል እና የሰሜንን ክፍል ለሮም ንጉሥ ይሰጣል ብሎ ለጉባዬው ነገራቸው” የሚል እናነባለን::
ይህ በአስረጅነት ያቀረብነው መጽሐፍ እንደሚለው ንጉሥ ሰለሞንን ለመጎብኘት የሄደችው ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ማክዳ ናት:: የሳባ ነጋዴዎች በባህር እስከ ህንድ፣ በየብስም እስከ ሴኤን (አስዋን የግብጹ) ድረስ እየሄዱ ትልቅ ንግድ ይነግዱ ነበር:: ከነዚህ ነጋዴዎች አንዱ “ታምሪን” የተባለው ነጋዴ ስለ ንጉሥ ሰለሞን እጅግ በጣም የሚያስገርም ነገር ነገራት፤ ይህን በሰማች ጊዜ ንጉሥ ሰለሞንን ሄዳ ለመጎብኘት ተመኝታ ለንጉሥ የሚገባ እጅ መንሻና አምኃ የሚሆን በብዙ ግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ሄደች::
ከብሉይ ኪዳን፣ ከዓረብ መዛግብት እና ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎች ተውጣጥቶ የተዋቀረው ክብረ-ነገሥት ንግሥቲቱ ንጉሥ ሰለሞን እንዴት እንደጎበኘች በዝርዝር ይተርካል። “ንጉሥ ሰለሞን በቤተ-መንግሥቱ ታላቅ ድግስ ደግሶ ራት ጋበዛት። ለእርሱ ቅርብ ከሆነው ቤተ-መንግሥት ውስጥም ቤት ሰጣት። ዘወትርም ትሄድ እና ትመለስ፣ ጥበብንም ትሰማ፣ በልቧም ትጠብቀው ነበር። እሱም ወደ እሷ ይሄድ፣ የጠየቀችውንም ሁሉ ይነግራት ነበር። «እስከ ንጋቱ ድረስ ስለ ፍቅር እዚሁ ተጽናኚ» አላት። «እንዳትደፍረኝ በአምላክህ በእስራኤል አምላክ ማልልኝ» አለችው። «እንዳልደፍርሽ እምልልሻለሁ። ነገር ግን አንቺም በቤቴ ውስጥ ያለውን ሁሉ እንዳትደፍሪ ማይልኝ» አላት። ንጉሡም በአንድ በኩል ወደ መኝታው ወጣ። ለእሷም ደግሞ በሌላው በኩል መኝታ አዘጋጀላት። ንግሥቲቱም ጥቂት ተኛች። እናም ነቃች። በብልሃት የሚያስጠሙ ምግቦችን አስጋብዟት ነበርና በነቃች ጊዜ አፏ በጥማት ደረቀ። ውኃውን ለመጠጣት መሃላዋን አፍርሳለች እና ከሰለሞን ጋር አደረች”።
ንጉሡን ካየች በኋላ ወደ ሀገሯ ተመለሰች:: ዳሩ ግን ሀገርዋ ሳትገባ “በላ-ዘዲዛርያ” አጠገብ አንድ ልጅ ወለደች:: ልጁም “በይነ ለሐኪም” (የሳባ ልጅ በክብረ ነገሥት ላይ “በን ለሐኪም” ብሎ ይጠራዋል:: በን ለሐኪምን በይብራይስጡ “በን ሀሐካም”፣ ዓረቦቹ “ኢብን ኤል ሐኪም” የተባለው ፍቺው “የጠቢብ ልጅ” የሚል ነው:: በግዕዙ “መኑ ይልህቅ” በመጨረሻም “ምኒልክ” ብሎ ይፈታዋል።) በይነ ለሐኪም 22 ዓመት ሲሞላው የንጉሡን ጥበብ ለንግሥቲቱ ከነገራት ነጋዴ ታምሪን ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ:: የሄደበትም ምክንያት ንጉሥ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ንጉሥነት እንዲቀባውና ሀገሪቱንም ከአረመኔነት (ከአረማዊነት) ለማውጣት በማሰብ ነበር፤ አካሄዱም ከንግሥት ሳባ የተላከ መልዕክተኛ ሆኖ ነበር:: ንጉሥ ሰለሞን ግን የመልኩን መምሰል እና ለንግሥቲቱ ማስታወሻ ብሎ የሰጣትን ቀለበት በማየት ልጁ እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ’ “ሮብዓም” የተባለው ልጁ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ስለነበረ በይነ ለሐኪምን (ምኒልክን) በእስራኤል መንግሥት ላይ ወራሹ እንዲሆን ፈልጎ ነበር፤ በይነ ለሐኪም ግን ፈቃደኛ አልነበረም::
የበይነ ለሐኪምን ፈቃደኛ አለመሆን የተቀበለው ንጉሥ ሰለሞን ‘ልጁን ከሸዋ ደቡብ እስከ ሕንድ ምሥራቅ ድረስ በተዘረጋው ምድር ላይ የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎ በጊዜው በነበረው ካህን “ሳዶቅ” አስቀባው:: ንጉሡም በኢየሩሳሌም የሚሠሩትን ታላላቅ ሥራዎች በኢትዮጵያ ከበይነ ለሐኪም ጋር እንዲፈጽሙ በማሰብ ከእስራኤል ትልልቅ ሰዎች የተወለዱትን ጨምሮ ላከው::
አባ ፓስፓራኒ (በጊዜው የአስመራ ኮምቦኒ ኮሌጅ ዳይረክተር ነበሩ) በ1940ዎቹ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል መጽሐፍ ላይ የመንግሥቱን ኃያልነት ሲናገሩ “በን ለሐኪም መንግሥቱን ካደላደለ ከጥቂት ወሮች በኋላ ዘመቻ አደረገ:: ሰፈሩንም “ከማየ አበው፣ የአባቶች ውሃ” (በዓባይ ዙሪያ ላይ ያለ ቦታ እንደሆነ ይገመታል) ላይ አደረገ:: ከዚያ የዞውን እና የሃዲያን መሬትን ያዘ፤ ከዚያ ቀጥሎ ኖባን እና ሶባን ወግቶ እስከ ግብጽ ወሰን ድረስ ዘመተ:: የግብጽ እና የምድያም ነገሥታት በጣም ፈርተው ሰላማዊነታቸውን የሚያስታውቅ መተያያ ላኩለት:: ከዚያ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ከከተማው ገብቶ እንደገና ወደ ሕንድ ቢዘምት ንጉሡ እጅ መንሻ አቅርቦለታል” በማለት የቀዳማዊ ንጉሥ ምኒልክ መንግሥት ምን ያህል ኃያል እንደነበረ ገልጸዋል::
የንግሥተ ሳባ ጠቢቡ ሰለሞንን መጎብኘት እጥፍ ድርብ የሆኑ ዓላማዎችን ያካተተ ነበር፤ ንግሥተ ሳባ የሄደችበት ዓላማ በራሱ እርሷ የኢትዮጵያ ንግሥት እንደነበረች ያመለክታል:: አንድ ሁለቱን እንመልከት:- የመጀመሪያው ዓላማ ተብሎ የሚወሰደው በእንቆቅልህና በምሳሌ የሰለሞንን ጥበብ ለመርመር እና ለመፈተን መጓዟ ነው፤ ንጉሡ ጥበብ አዋቂ በመሆኑ መደነቋም የግብጽ እና የባቢሎን ነገሥታት አስቸጋሪ ጥያቄዎችን (እንቆቅልሾችን) ምሳሌ እየቀረቡ ከሊቃውንት ጋር መነጋገር መውደዳቸውን በታሪክ እናገኛለን፤ ኢትዮጵያም የዚህ አካል ነበረች::
ሌላኛው የንግሥተ ሳባ ዓላማ በእርሷና በሰለሞን መንግሥት መካከል የንግድ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ መፈለጓ ነበር:: እርሷ በሀገሯ የሞላውን ሽቶ፣ ወርቅ፣ ዝባድ እና የተከበሩ ድንጋዮችን በመላክ በሀገሯ የማይገኙትን የንግድ እቃዎች ማስገባት በመፈለጓ ነው::
ንግሥት ሳባ ኢትዮጵያዊ መሆኗን ማስረዳት የሚችለው የንጉሥ ሰለሞን እና የንግሥት ሳባ የንግሥና ዘመናቸው አንድ መሆኑ ነው:: በክብረ ነገሥት ላይ እንደሚገኘው ታሪክ ንጉሥ ሰለሞን ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በኢየሩሳሌም ላይ ለ40 ዓመታት መንገሡን ይነግረናል:: በአንጻሩ ደግሞ ንግሥተ ሳባ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የነገሥታትን ተርታ እና ትውልድ ያየን እንደሆነ ሳባ ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በኢትዮጵያ ላይ ለ25 ዓመታት እንደነገሠች የሚያመለክት የታሪክ ጽሑፍ እናገኛለን:: በመሆኑም ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን እና ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የነገሡባቸውን ዘመናት ያየን እንደሆነ ያለ ጥርጥር ይህች ንግሥት ኢትዮጵያዊት ነች ብሎ መናገር ይቻላል:: በኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ ላይ የሚገኘው ቀዳማዊ ምኒልክም የስሙ ትርጓሜ “የጠቢብ ልጅ” ተብሏል እና ይህም ጠቢብ ታላቁ የኢየሩሳሌም ንጉሥ ጠቢብ ሰለሞን ነው ሲል የታሪክ ተመራማሪው ብሩክ መኮንን “የኢትዮጵያ ታሪክ ንግሥተ ሳባ እና ልዑል ምኒልክ” በሚለው መጽሐፉ ይደመድማል::
ንግሥተ ሳባ ኢትዮጵያን ለ31 ዓመታት ካሥተዳደረች በኋላ በሕይወት እያለች ምኒልክ ቀዳማዊን ተክታ ሕይወቷ አልፏል:: ነገር ግን የዚህች ብልሕ ንግሥት ሥራዋ እና ታሪኳ አፈ ታሪክ ቢመስልም ዘመን ተሻግሮ እዚህ ደርሷል::
ሳምንቱ በታሪክ
የልዑሉ ጉብኝት
በልዑል ራስ አስራተ ካሳ የሚመራ የኢትዮጵያ የፓርላማ ቡድን ከዩናይተድ ስቴትስ አሜሪካ ፕረዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ጋር በዋይት ሃውስ ሐምሌ 18 ቀን 1955 ዓ.ም ተገናኘ፤ ስለ ኢትዮጵያ ልማት፤ የኢትዮጵያ እና የሶማልያ ግጭት እንዲሁም በአፍሪካ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛቶች እና በወቅቱ በአፓርታይድ አገዛዝ ስር ስለነበረችው ደቡብ አፍሪካ ሁኔታ ተወያየ።
የልዑል ራስ አስራተ ካሳ የአሜሪካ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የጠነከረ ግንኙነት ለመመሥረት እንደ ድልድይ ነበር ሲል ሲኤን ኤን ዘግቧል:: በቀጣዩ ዓመትም ጆን ኤፍ ኬኔዲ ቀዳማይ ዐፄ ኃይለሥላሴን ታይቶ በማይታወቅ መንገድ አቀባበል አድርገው ተቀበሉ:: የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም በተለያዩ ዘርፎች እምርታን አሳይቷል:: ቃኘው የተሰኘው የባሕር ላይ ማዘዣ ጣቢያም በቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ግዛት ላይ ተቋቋመ፤ ይህም ኢትዮጵያን በቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጠተቀሜታዋ የጎላ እንዲሆን አድርጓል::
የኮሪያዎቹ ጦርነት ተቋጨ
ኮሪያ ሁለት ሀገር ከመሆኗ በፊት የርስ በርስ ጦርነት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ተደርጎባት ነበር:: ይህ ጦርነት ሐምሌ 20 ቀን 1945 ዓ.ም ተቋጭቷ:: የጦርነቱ ውጤቱም ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ የሚባሉ ሀገሮችን ፈጥሯል::
ጦርነቱ የተለያዩ ሀገራትን ጎራ ለይቶ ያሳተፈ ነበር:: ኢትዮጵያም በወቅቱ ሊግ ኦፍ ኔሽን አማካኝነት ስምሪት ተሰጥቷት በደቡብ ኮሪያዊያን ጎን ተሰልፋ ተዋግታለች:: በአምስት ዙር ኮርያ ከዘመቱት 6037 ኢትዮጵያውያን መካከል 122ቱ በጦርነቱ ሞተዋል:: አንዳቸውም አልተማረኩም::
ምንጭ፡- አይዘንአወር ቤተመጽሐፍት
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም