0
6

በዓለም የአትሌቲክስ መድረክ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ የአበበ ቢቂላ የባዶ እግር ገድል፣ የኃይሌ ገብረሥላሴ የፍጻሜ ሩጫ፣  የቀነኒሳ በቀለ እና የጥሩነሽ ዲባባ  የመጨረሻ ዙር ፍጥነት፣ የገንዘቤ ዲባባ የዓለም ክብረ ወሰኖች እና ወርቃማው የኃይሌ፣ የቀነኒሳ እና የጥሩነሽ ዘመን ሁሌም ከአዕምሯችን  አይጠፋም።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲነሳ ከጥቂት ሀገራት ጋር በቀዳሚነት የሚጠራው የኢትዮጵያ ስም ነው። ከ1983ቱ የመጀመሪያው የዓለም ሻምፒዮና ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ መድረክ ላይ የራሷን ታሪክ በደማቅ ቀለም ስትጽፍ መቆየቷን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስነብባል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጽናት፣ በጀግንነት እና በማይበገር መንፈስ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል። ይህ ታሪክ በላብ እና በደም የተጻፈ ለትውልድ የሚተላለፍ የጀግንነት እና የስኬት ማህደር ነው።

የኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ የሚጀምረው እ.አ.አ. በ1983 በሄልሲንኪ ፊንላንድ በተካሄደው የመጀመሪያው የዓለም ሻምፒዮና ነው። በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ ጥቂት አትሌቶችን ማሳተፏን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ ሀገራችን በመጀመሪያው ተሳትፎዋም ቢሆን ባዶ እጇን አልተመለሰችም። በማራቶን ውድድር የተሳተፈው ከበደ ባልቻ የብር ሜዳሊያ በማግኘት ኢትዮጵያን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ እንድትካተት አድርጓታል። ከአራት ዓመታት በኋላ በ1987 እ.አ.አ በጣሊያን ሮም በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ ደረጀ ነዲ በማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አምጥቷል።

እ.አ.አ. በ1993 ጀርመን ስቱትጋርት በተካሄደው ሦስተኛው የዓለም ሻምፒዮና የምንጊዜም ምርጡ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በዐስር ሺህ ሜትር ርቀት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል። ውጤቱም ኢትዮጵያ በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ያላት ተጽዕኖ በማራቶን ብቻ እንዳልሆነ ያስመሰከረችበት ነበር። ሻለቃ ኃይሌ በስቱትጋርት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን ከማራቶን ባለፈ  በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ መጪው ዘመን የኢትዮጵያ እንደሚሆን  ያወጀበት ታሪካዊ ክስተት ነው።

ኢትዮጵያ በአራት ዐስርት ዓመታት የመድረኩ ተሳትፎዋ  ከፈተኛ ውጤት ያስመዘገበችው እ.አ.አ. በ2013 ሞስኮ በተደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው፡፡

አትሌቶቻችን  አራት ወርቅ፣ ሦስት ብር እና አራት የነሐስ በአጠቃላይ ከ11 ሜዳሊያዎች ጋር  ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በ2022 በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ከሞስኮ ቀጥሎ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር አይዘነጋም። በኦሪገኑ መድረክ  ኢትዮጵያ አራት የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ የሚታወስ ነው፡፡  በድምሩ ዐስር ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከአሜሪካ ቀጥሎ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው።

አነስተኛ ሜዳሊያ የተመዘገበበት መድረክ ደግሞ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እ.አ.አ በ1983 ሄልሲንኪ በከበደ ባልቻ አማካኝነት የተገኘው የብር ሜዳሊያ እና እ.አ.አ በ1987 በሮም በተደረገው መድረክ ደረጀ ነዲ የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፉን ታሪክ ያስታውሰናል። በወቅቱ የነበረውን ልምድ እና ዝግጅት ከግምት ስናስገባ እነዚህ ውጤቶች እንደ “መጥፎ”  የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡  ይልቁንም መሰረት የጣሉ ታሪካዊ ውጤቶች ናቸው እንጂ።

በአፍሪካ ደረጃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁሌም በሁለት ታላላቅ ሀገራት መካከል በሚደረግ ፉክክር ይታወቃል፤ በኢትዮጵያ እና በኬንያ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ኡጋንዳውያንም ፉክክሩን ተቀላቅለዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ግን በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ፍጹም የበላይነት ያላቸው ሲሆን በሜዳሊያ ሰንጠረዡም ተቀራራቢ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጡት።

ኬንያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን፣ ከ60 በላይ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ኢትዮጵያ ከኬንያ በመቀጠል በአፍሪካ ሁለተኛዋ ስኬታማ ሀገር ናት። እስከ 2023 እ.አ.አ ሻምፒዮና ድረስ ኢትዮጵያ 36 ወርቅ፣ 38 ብር፣ እና 30 ነሐስ በድምሩ 104 ሜዳሊያዎችን  መሰብሰቧን የኦሎምፒክ ዳታቤዝ ዶት ኮም መረጃ ያስነብበናል፡፡ እነዚህን ሜዳሊያዎች የሰበሰበችው በ18 የተለያዩ የዓለም ሻምፒዮና መደረኮች  ነው፡፡

ኢትዮጵያ ይህን ሜዳሊያ ያስመዘገበችው በ11 የውድድር ዓይነቶች ሲሆን 55 የተለያዩ አትሌቶችም የሜዳሊያው ባለቤት ናቸው፡፡ የገንዘብ፣ የመሠረተ ልማት እና የመሳሰሉት ከፍተኛ ችግሮች ባሉበት ሀገር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  እንደዚህ ዓይነት ውጤት መመዝገቡ ሀገሪቱ በተፈጥሮ የታደለች መሆኗን እና የአትሌቶቿን ጥንካሬ ያሳያል።

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ በመድረኩ ታሪክ እኩል አምስት የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ ቀዳሚ ናቸው፡፡ በድምሩም  እኩል ስድስት ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ  አራት የወርቅ እና በድምሩ ሰባት ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ አምጥቷል፡፡

እ.አ.አ በ2023 በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአረንጓዳ ጎርፍ ገደል በሴቶች ዐስር ሺህ ሜትር ርቀት መደገሙ አይዘነጋም፡፡ ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ለተሰንበት ግደይ እና እጅጋየሁ ታየ ተከታትለው በመግባት ዓለምን ማስደነቃቸው የሚታወስ ነው፡፡

በዘንድሮው የቶኪዮ 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኦሪገን ስኬት ለማስቀጠል ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ነው ወደ ጃፓን የበረሩት። ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን ለመምረጥ ግልጽ የማጣሪያ ስርዓት ተግባራዊ አድርጓል። ይህም ምርጥ ወቅታዊ አቋማ ያላቸው አትሌቶች ብቻ ሀገራችንን እንዲወክሉ አስችሏል። ሀገራችን በዚህ መድረክ የእርምጃ ውድድርን ጨምሮ ከ800 ሜትር ርቀት እስከ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡ የዘንድሮው  ብሄራዊ ቡድን እንደ ጉዳፍ ጸጋይ እና ለሜቻ ግርማ ያሉ ልምድ ያላቸው የዓለም ሻምፒዮናዎችን  አካቷል፡፡ እንደ ቢኒያም መሃሪ ያሉ ወጣት እና ተስፋ የተጣለባቸው አዳዲስ አትሌቶችንም አጣምሮ ይዟል።

ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተንታኞች እና ተቋማት ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2025 ሻምፒዮና ላይ ከፍተኛ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት መካከል እንደምትሆን ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ለሜቻ በዚህ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ለሜቻ ባለፉት ሦስት የዓለም ሻምዮናዎች   የብር ሜዳሊያ ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡

ጉዳፍ ጸጋይ በአምስት እና ዐስር ሺህ ርቀቶች ላይ ያላት የበላይነት ቢያንስ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ እንደምታመጣ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባታል። ጉዳፍ በ2022ቱ የኦሪገን እና በ2023ቱ የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዐስር ሺህ እና በአምስት ሺህ ሜትር ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ ድርቤ ወልተጂ እና ብርቄ ሃይሎም በሴቶች አንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀት ተስፋ ተጥሎባቸዋል።  ድርቤም ሀንጋሪ ቡዳፔስት በተደረገው 19ኛው ምዕራፍ በአንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀት የብር ሜዳሊያ ማሸነፏ የሚታወስ ነው፡፡

እንደ ትዕግስት አሰፋ እና አማኔ በሪሶ ያሉ የዓለም ምርጥ ሯጮችን የያዘው የሴቶች ማራቶን ቡድን የወርቅ ሜዳሊያውን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በወንዶችም በዐስር ሺህ ሜትር ሰለሞን ባረጋ እና በሪሁ አረጋዊ ከኡጋንዳ እና ከኬንያ አትሌቶች ጋር ጠንካራ ፉክክር በማደረግ ሜዳሊያ ወስጥ ይገባሉ ተብሎ ይገመታል ። ሰለሞን ባረጋ በቡዳፔስት እና በዶሀ የዓለም አትሌቲክስ ሻምዮና የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ማምጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ አሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅትም ለሀገራችን ብርቅየ አትሌቶች መልካሙን ሁሉ ይመኛል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here