የብቻነት ጉልበት

0
28

ለብቻ መሆን በጣም የሚያስፈራ ነገር ነው:: ስልኬን ቤት አስቀምጨ  ካፌ ውስጥ ቡና እየጠጣሁ ሞክሬው አውቃለሁ:: ከስልካችን ጋር ምን ያህል እንደተጣበቅን የተረዳሁት ያንኑ ቀን ነበር:: ሁሉም ሰው ስልኩ ላይ ዓይኑን ተክሏል፤ ይከራከራል፤ ያወራል:: ከጎኔ ከተቀመጡ ሰዎች በየጊዜው የሚቀያየሩ እና የሚደጋገሙ የቲክቶክ ቪዲዮዎች ይሰሙኛል:: ቀና ስል አፍጥጠው ያዩኛል:: አንገቴን አቀረቅራለሁ:: ዓይኔን ማስቀመጫ አጣሁ:: የተደገፍሁትን ጠረጴዛ ብዙ ልቆይበት አልቻልሁም:: ጸጥ ማለት ከባድ ነው:: አስተናጋጇ ጋር ብዙ ጊዜ ተፋጠጥን:: ውስጤ በጥያቄ ተረበሸ:: አዕምሮየ በጥያቄ ተወጠረ:: ውስጤን ማድመጥ እንዴት ልቻል? በብዙ ጥያቄዎች ተወጠርሁ::

“አይዞህ አትተክዝ” ስትል አስተናጋጇ ከሐሳብ ሰመመን መለሰችኝ፤ አፈርሁ፤ ደነገጥሁ::  ደበረኝ:: ከኪሴ ወረቀት አውጥቼ ሐሳቦችን መጫር ጀመርሁ:: ቅዠት የሚመስሉ ሀሳቦችን አሰፈርኋቸው:: ደጋግሜ አነበብኋቸው:: ተጠራጠርሁ:: ቅዠቴን ለማመን ወራት ወሰደብኝ:: ከዓመት በኋላ እነዚያ የቅዠት ሀሳቦቼ ከሀሳብነት አድገው ወደ ድርጊት ተለውጠዋል:: ፍሬም አፈሩ:: ለካንስ የሰብእና ግንባታ እና ገንዘብ ማግኘት አሰልጣኝ እና ደራሲው  ሮበርት ኪዮሳኪ “ቲንኮ ኦን ፔፐር( በወረቀት ላይ አስብ)” የሚለው ለዚህ ነው:: ሀሳብ ጤዛ ነው:: ቶሎ ላስ አድርገው በማስታወሻ ካልያዙት አእምሮ ቦታ እና ትኩረት የሚሰጣቸው ሌሎች ሐሳቦች ሲመጡ ይሰርዘውና ወደ አዲስ ሀሳብ ይሻገራል:: በወረቀት ያሰፈሩት ግን አይረሳም::

የሰብእና ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት እውቅናን ያተረፈው ጂም ሮን “በሕይወቴ ካገኘኋቸው በጣም ስኬታማ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ አንድ አስገራሚ ልማድ አላቸው። የሚያነቡት ነገር አይደለም፣ የሚያውቁት ሰው አይደለም፣ ወይም ደግሞ ምን ያህል ጠንክረው እንደሚሠሩ አይደለም። ሙሉ በሙሉ ብቻቸውን የመሆን እና በዚያ ብቸኝነት ውስጥ የማደግ ችሎታቸው ነው” ሲል ተናግሯል::

እነዚህ ስኬታማ ሰዎች  ታላቅ ኃይላቸው ያለው ከራሳቸው ጋር ሲሆኑ ብቻ ነው ይላል ጂም:: ጂም ሮን አካባቢያችንን እንድናስተውል ይጠይቀናል:: “ዙሪያችሁን ተመልከቱ እናም ዓለም ከዝምታ ሲሸሽ ታያላችሁ፣ ስልኮች ያለማቋረጥ ይጮኻሉ፣ ቴሌቪዥኖች ባዶ ክፍሎች ውስጥ ይጫወታሉ፣ ሰዎች በየደቂቃው ይቀጣጠራሉ” ይላል::

ብቸኛ በመሆን እና ለብቻ በመሆን መካከል ትልቅ ልዩነት አለ:: ጂም እንደሚለው ብቸኝነት የሚያሠቃይ የመለያየት ስሜት፣ መገለል ነው። ጉልበት ያሟጥጣል። በአንጻሩ ብቸኝነት ዓላማ ያለው ሲሆን ለፍሬያማነት ያበቃል:: ለውጥ በመፈልግ ከመንጋው መነጠል ነው። ብቸኛ ሰዎች እንደተተዉ ይሰማቸዋል። ብቸኝነትን በዓላማ  የሚጠቀሙ ሰዎች ነጻ እንደወጡ ይሰማቸዋል። ብቸኛ ሰዎች አንድ ሰው እንዲያድናቸው ይጠብቃሉ። ብቸኝነትን የሚረዱ ሰዎች ደግሞ ራሳቸውን በሚያድን ስራ ተጠምደዋል።

በታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ ብዙ ታላላቅ ስኬቶች የመጡት ብቻቸውን መሆን ከሚያውቁ ሰዎች ነበር። ለብቻ መሆን በራስ ጉልበት እና አቅም የማመን ምርጫ ነው:: ብቻን የመሆን ችሎታ ከፍተኛ በራስ መተማመንን ያሳያል። አብዛኞቻችን የራሳችን ውስጣዊ ሕይወት ስላላዳበርን የራሳችን ድርጅት ማቋቋም አንችልም። የማያቋርጥ ውጫዊ ማረጋገጫ፣ የማያቋርጥ ትኩረት እንፈልጋለን። ሰዎች በሕይወታችን ደርሰው እንዲረዱን እና እንዲደግፉን እንጠብቃለን::

አንድ ስኬታማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ለጂም ሮን ሚስጥሩን አካፍሎት ነበር:: ይህ አስፈጻሚ  በየጠዋቱ ከማንም በፊት አንድ ሰዓት ቀድሞ ወደ ቢሮው ይገባል። ያ ጸጥታ የሰፈነበት ሰዓት፣ ከሌሎቹ ሰዓታት ሁሉ የበለጠ ዋጋ እንዳለው ተናግሯል። ያንን ጊዜ የሚያሳልፈው ማሰብ፣ በማቀድ፣ ራሱን በማረጋጋት ነበር። ተፎካካሪዎቹ ቀኑን ሙሉ ሲደናገጡ፣ እሱ እየመራ ይውላል።  ምክንያቱም ከሀሳቦቹ ጋር ብቻውን ለመሆን ድፍረቱ ነበረው።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ከኤሌክትሪክ ንዝረት የበለጠ የሚሰማቸው ከሃሳቦቻቸው ጋር ለ15 ደቂቃ ብቻቸውን ቁጭ ሲሉ ነው:: ሰዎች ብቸኝነት ውስጥ ምቾት የማይሰማቸው አእምሮ በሚፈጥራቸው ማለቂያ የለሽ ግትልትል ጥያቄዎች ምክንያት ነው። ጂም ሮን ግን “ያ ምቾት አለመሰማት በትክክል እድገት የሚከሰትበት ቦታ ነው። ኃይሉ ያለው እዚያ ነው። ብቻህን ስትሆን፣ የሚያስደምምህ የለም። ጭምብል አያስፈልግም። ከራስህ ጋር ሙሉ በሙሉ ሐቀኛ መሆን ትችላለህ” ብሏል::

ሰዎች ለሌሎች ጥሩ ለመምሰል በመሞከር በጣም ስለተጠመዱ ራሳቸውን በእውነት የመመልከት ልማድ ፈጽሞ አያዳብሩም። ብቸኝነት ግን ማስመሰልን ያራግፋል። በእውነት ማን እንደሆንን፣ ምን እንደምንፈልግ፣ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ምን እንደሆነ በማሰብ  ከጥያቄዎቻችን ጋር እንጋፈጣለን::

ምርጥ ሀሳቦች በተረጋጋን እና በብቻነት ጊዜ የሚወለዱ ናቸው:: በጸጥታ የእግር ጉዞ ላይ፣ ረጅም የመኪና መንገድ ላይ ይከሰታሉ:: ለዚህ ምክንያት አለው። አእምሯችን ግንኙነቶችን ለመፍጠር ቦታ ያስፈልገዋል። የራሳችንን ጥበብ ለመስማት ጸጥታ ያስፈልገዋል። የማያቋርጥ ጫጫታ እና ሁከት  የፈጠራ ሀሳቦችን ያጠፋል።

ለዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያሰለጠነው ጂም ሮን የሚከተለውን ሐሳብ ተናግሯል:: “አንድ ጊዜ አንዲት ሴት ያለችኝን  አስታውሳለሁ፤ ለእሷ የማይመጥን ሰው ጋር ትውውቅ ነበራት። ለምን አብራው እንደቀጠለች ጠየቅኋት። መልሷ የሚያሳዝን ነበር፡ ‘ቅዳሜና እሁድ ብቻዬን መሆን እጠላለሁ’ አለችኝ” ይላል:: ያቺ ሴት ከብቸኝነት ፍርሀት የተነሳ ህይወቷን የሚጎዳ ውሳኔ ነበራት:: ያ ትልቅ የራስን ኃይል ምለሰው መስጠት ነው።

ፓስተር ደራሲና የአስተሳሰብ ለውጥ አስተማሪው ማይልስ ሙንሮ “ብቸኝነት ታላቅ ኃይል” ነው ይላል:: አብዛኛው ሰው ብቸኝነትን እንደ በሽታ እንደሚሸሸው ተናግሯል:: “ታላቅ ኃይላችሁ፣ ጥልቅ ለውጣችሁ፣ ግሩም ጥበባችሁ ሙሉ በሙሉ ብቻችሁን በምትሆኑበት በእነዚያ ጊዜያት ውስጥ ነው” ይላል::

ለብቻ መሆን እንደ ስህተት፣ እንደ ውድቀት ምልክት ተደርጎ ሲነገረን አድገናል:: በሌሎች የተከበብን ሆነን ህልውናችንን እንድናረጋግጥ ተምረናል:: ጸጥታ ምቾት የማይሰማበት፣ ብቸኝነት እንደ ብቸኛነት የሚታይበት፣ ብቻችንን መሆን ከሌሎች ጋር ከመሆን ያነሰ እንደሆነ የሚታይበት ዓለም ተፈጥሯል።

እውነታው ግን ለብቻ መሆን ስንችል ምቾት ይሰማናል፣ ሌሎች እንዲያሟሉልን መጠየቅ እናቆማለን፣ የማይጠቅሙንን ግንኙነቶች ማቆም እጀምራለን። በሚገባን ልክ መቀበል እንጀምራለን። ከሌሎች ጋር ለመስማማት  ብለን እሴቶቻንን መሸራረፍ እናቆማለን። በኃይላችን፣ በጊዜያችን፣ በሕይወታችን ላይ ማን መግባት እንዳለበት መራጭ እንሆናልን።

ሰዎች ለመጋፈጥ በሚፈሯቸው ነገሮች ወስጥ ሕይወታቸውን የሚቀይሩ ቁልፎች አሉ:: እነዚህ ቁልፎች ግን በድንገት ወይም በእድል አይመጡም:: ማይልስ “በብቸኝነት ውስጥ ስትቀመጥ፣ መጀመሪያ ላይ ምቾት ላይሰማህ ይችላል። ስትሸሻቸው የነበሩ ሀሳቦች እና ስሜቶች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ።  ስለራስህ ለመቀበል አስቸጋሪ የሆኑ እውነታዎችን ልትጋፈጥ ትችላለህ። ነገር ግን ይህ ምቾት አለመሰማት ጠላትህ አይደለም። አስተማሪህ ነው። በትክክል የት ማደግ እንዳለብህ፣ ምንህን ማከም እንዳለብህ፣ ምን መለወጥ እንዳለብህ ያሳይሃል” ይላል::

አሁን በከፍተኛ ሁኔታ በቴክኖሎጂ በተሳሰርንበት ዓለም ውስጥ ብቸኝነት ብርቅ ሀብት ሆኗል። ያለማቋረጥ በመረጃ፣ አስተያየቶች፣ ጩኸት እንታወካለን። ስልኮቻችን ሁልጊዜም ይጮኻሉ፣ አእምሮአችን  በሌላ ሰው አጀንዳ ተይዟል። የራሳችንን ሀሳቦች የማሰብ፣ የራሳችንን ልምዶች የማስኬድ፣ የራሳችንን ውስጣዊ ስሜት የማገናኘት ችሎታችንን አጥተናል።

በየጊዜው የሌሎች ሰዎችን ጉልበት፣ የሌሎች ሰዎችን አስተያየት፣ የሌሎች ሰዎችን ተስፋዎች ስናሳድድ፣ ከውስጣችን ጋር ያለንን ግንኙነት እናጣለን:: በልባችን ከምንመኘው ይልቅ ሌሎች ሰዎች ምን እንድንሆን እንደሚፈልጉ አስበን መኖር እንጀምራለን::

የቡድሂዝም እምነት መስራቹ ቡድሃ ጉተማ  አንድ ዝነኛ አባባል አለው:: “ከሞኝ ጋር ከመሄድ ለብቻ መሄድ ይሻላል” ብሏል። ይህ ማለት ግን ከማንም ጋር አትሂድ፣ ጓደኛ አይኑርህ ማለት አይደለም። ነገር ግን አንድ ሰው ደካማ አስተሳሰብ ያለው ከሆነ፣ ብዙ ጉልበት እና ጊዜ ሊወስድብህ ይችላሉ ማለቱ ነበር::

የሕንዱ አስተማሪ ሳድጉሩ የሰው ልጅ አእምሮ ገደብ የለሽ አቅም እንዳለው ይናገራል:: ብቸኝነት የሚሰጠውን አቅም ለመጠቀም  በትንሹ በትንሹ በጸጥታ ከራስ ጋር ጊዜ ማሳለፍ መፍትሔ ነው ይላል ሳድጉሩ:: መጀመሪያ መረበሽ፣ እብድ መምሰል ሊሰማን ይችላል::  አእምሯችን ይነዘንዘናል:: ይጨቃጨቀናል:: ትርምስ ይፈጠራል:: በሂደት የእእምሮ ትርምስ ወጀቡ ያልፋል:: የአእምሯችንን አቅም መረዳት እንችላለን:: ያን ጊዜ የምንፈልገውን ሳይሆን የሚጠቅመንን መምረጥ እንጀምራለን:: ከውጪ ለሚመጡ ሐሳቦች ሳይሆን ለውስጣዊ ሐሳቦች ቅድሚያ እንሰጣለን ይላል ሳድጉሩ::

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም  26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here