የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር ውድድር ተጠናቋል:: ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያውን ዙር በ36 ነጥብ በሊጉ አናት ላይ ተቀምጦ አጠናቋል:: ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ32 ነጥብ ሁለተኛ እና መቻል በ29 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ነው የመጀመሪያውን ዙር የጨረሱት:: ባሕር ዳር ከነማ የሴቶች ክለብ በዐስር ነጥብ ዐስረኛ ደረጃ ላይ ይገኛል:: ልደታ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው:: ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ዳግማዊት ሰለሞን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በ18 ግብ ኮከብ አግቢነቱን እየመራች ትገኛለች:: ረድኤት አስረሳህኝ ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዐስር ግቦች ትከተላለች::
ለዋንጫ ከሚደረገው ፉክክር ባልተናነሰ ላለመውረድ የሚደረገው ፍልሚያ እጅግ ጠንካራ እና ትኩረትን የሚስብ ሆኗል። በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ትግል የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በአዲሱ አሰልጣኝ ዳዊት አጠናፉ እየተመራ በሊጉ ለመቆየት ብርቱ ትግል እያደረገ ይገኛል። ክለቡ በአሁኑ ሰዓት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ከ14 ቡድኖች ዐስረኛ ደረጃን ይዞ የተቀመጠ ሲሆን ከ13 ጨዋታዎች የሰበሰበው ዐስር ነጥብ ብቻ ነው::
ይህም ከወራጅ ቀጣናው ክለቦች ጋር ያለው ልዩነት እጅግ ጠባብ እንደሆነ ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። 11ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ይርጋ ጨፌ ቡና ጋር እኩል ነጥብ ይዟል:: የግዮን ንግሥቶች በሁለተኛው ዙር ውድድር አንድ ጨዋታ ከተሸነፉ ቡድኑ ከፍተኛ የመውረድ አደጋ ይጋረጥበታል። በአጠቃላይ በመጀመሪያው ዙር ካደረጉት 13 ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ አሸንፏል:: በዘጠኙ ሲሸነፍ በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል:: ስምንት ግቦችን ብቻ በተቃራኒ መረብ ላይ ሲያሳርፉ 16 ግቦች ደግሞ ተቆጥሮባቸዋል::
ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር አጋማሽ በተከታታይ የሽንፈት አዙሪት ውስጥ ገብቶ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ:: ሦስት ጨዋታዎችን በተከታታይ በመሸነፍ ትልቅ የመውረድ ስጋት ገጥሞት እንደነበር አይዘነጋም። ነገር ግን አሰልጣኝ እንዳወቀ አጠናፉ ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ያደረጉትን የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን እፎይታን አግኝቷል። አሰልጣኙ እንደገለጹት ይህ ለቡድኑ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጥንካሬ የሰጠ ሲሆን ተጫዋቾቹ ማሸነፍ እንደሚችሉ እምነት እንዲኖራቸው አድርጓል። በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች መነቃቃት ባይኖር ኖሮ ክለቡ ዛሬ በአራት ነጥብ ብቻ የሊጉ የመጨረሻ ግርጌ ላይ በተቀመጠ ነበር። አሁን ግን ይህንን የአሸናፊነት መንፈስ በሁለተኛው ዙርም በማስቀጠል ከወራጅ ቀጠናው የመራቅ ሰፊ እድል እንዳላቸው ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በወራጅ ቀጣና አቅራቢያ የሚገኙ ክለቦች ብዙ ግብ የሚቆጠርባቸው እና ደካማ የኋላ ክፍል ያላቸው ሲሆኑ የግዮን ንግሥቶች ግን ከዚህ የተለየ አቋም ነው ያላቸው። ቡድኑ በ13 ጨዋታዎች የተቆጠረበት 16 ግቦች ብቻ ነው፤ ይህ የሚያሳየው የቡድኑ የኋላ ክፍል የሊጉ መካከለኛ ደረጃ ላይ ካሉ ቡድኖች ጋር የሚመጣጠን አቅም እንዳላቸው ያመለክታል።
የቡድኑ ዋነኛ የራስ ምታት ግን የፊት መስመሩ ድክመት ነው። ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ክለብ በ13 የሊግ ጨዋታዎች ከመረብ ያሳረፈው ስምንት ግቦችን ብቻ ሲሆን ይህም በአማካይ በጨዋታ ከአንድ ግብ በታች (0.61) ማስቆጠሩን ያሳያል። ይህ አፈጻጸም በሊጉ ሦስተኛው ደካማ የፊት መስመር ያለው ክለብ አድርጎታል::
የክለቡ አሰልጣኝ እንዳወቀ አጥናፉ ይህን ክፍተት ለመሙላት በዝውውር ወቅቱ ተጨማሪ አጥቂዎችን ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም ገበያው ላይ ክፍተታቸውን ሊሞላ የሚችል ተጫዋች ባለማግኘታቸው ያሰቡትን ማሳካት እንዳልቻሉ ተናግሯል። “ገበያው ላይ ተጫዋቾችን እንደፈለግን ማግኘት አልቻልንም፤ ብዙዎቹ ውላቸውን የሚጨርሱት በሰኔ ወር በመሆኑ ውል ጨርሳ ያገኘናት አንድ ተጫዋች ብቻ ናት ብለዋል- አሰልጣኙ:: በተለይም ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከሜዳ መራቃቸው እና ቡድኑ በዝውውር ወቅቱ አንድ ተጫዋች ብቻ ማስፈረሙ በሁለተኛው ዙር ያለ በቂ የቡድን ስብስብ እና የተጫዋቾች አማራጭ ውድድሩን ይጀምራል።
ይህንን የተጫዋች ስብስብ ጥራት እና ጥልቀት ችግር ጥር ስድስት በተከፈተው እና እና ይካቲት ሦስት በተጠናቀቀው የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት መቅረፍ እንደማይችል የአሰልጣኞች የቡድን አባላት በመረዳታቸው በተጫዋቾች የአካል ብቃት እና ውህደት ላይ ትኩረት አድርገው ልምምድ በመስራት ሁለተኛውን ዙር ጀምረዋል። ቡድኑ ውድድሩ በሚካሄድበት አዲስ አበባ አስቀድመው በመግባት ለ15 ቀናት ያህል ጠንካራ ዝግጅት አድርጎ ነው ሁለተኛውን ዙር ውድድር የሚጀምረው።
አሰልጣኝ እንዳወቀ አጥናፉ ከአሚኮ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ “ባሉት ክፍተቶች ላይ በተለይም በአካል ብቃት እና በታክቲክ ውህደት ላይ በትኩረት ሠርተናል” ብለዋል:: ይህም ውስን ተጫዋቾችን ይዞ ለሚጫወት ቡድን የተጫዋቾች የመከላከል አቅም እንዳይወርድ እና በድካም ምክንያት ጉዳት እንዳያጋጥም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር ሲያጠናቅቅ ያስመዘገባቸው ሁለት ተከታታይ ድሎች ለሁለተኛው ዙር ትልቅ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ እንደፈጠረላቸው አሰልጣኙ አልሸሸጉም። “ልጆቹ ወደ አሸናፊነት ስነ ልቦና መጥተዋል፤ ይህንን የአሸናፊነት መንፈስ ማስቀጠል ዋናው ሥራችን ነው” ብለዋል።
የዘንድሮው የውድድር ዘመን ዋነኛ እቅዳቸውም ክለቡ ከፕሪሚየር ሊጉ እንዳይወርድ ማድረግ መሆኑን አሰልጣኝ ዳዊት ገልጸዋል። “አሁን ያለንበት ውጤት አነስተኛ ነው፤ ነገር ግን ትልቁ እቅዳችን ቡድኑ እንዳይወርድ ማድረግ ነው” ሲሉ አሰልጣኙ የክለቡን የህልውና ማስጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
ቡድኑ የመከላከል ጥንካሬውን አስቀጥሎ በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ጠባብ ውጤቶችን ማስመዝገብ ከቻለ ከወራጅ ቀጠናው አዙሪት የመውጣት እድሉ ሰፊ ነው። ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ክለብ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ መርሀ ግብሩን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ይጫወታል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


