በአንድ የውድድር ዓመት አራት ዋንጫዎችን ጠራርጎ የመውሰድ ህልም በዘመናዊው እግር ኳስ የማይቻል ተብለው ከሚፈረጁ ተልዕኮዎች አንዱ ነው። የሊጉን ማራቶን፣ የአውሮፓን የንጉሦች መድረክ፣ የካራባዎ እና ኤፍ ኤ የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ጫና ተቋቁሞ በፍጹምነት ማጠናቀቅ እጅግ ፈታኝ ነው። ይህ ስኬት የማይነጥፍ የቡድን ጥልቀትን፣ ከጉዳት ነጻ የሆነ እና የላቀ የትኩረት ደረጃን ይጠይቃል። በተለይም ትንፋሽ በማይሰጠው እና ፉክክሩ ልብን በሚያሞቀው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ይህንን ህልም ማሰብ ብቻ እንደ እብደት እንደሚቆጠር መረጃዎች አመልክተዋል።
በአንድ የውድድር ዘመን የፕሪምየር ሊጉን ግርማ፣ የቻምፒየንስ ሊጉን ክብር፣ የኤፍ ኤ እና የካራባኦ ዋንጫ ድልን አጣምሮ መያዝ ከሰው አቅም በላይ የሆነ ጥንካሬ፣ ዕድል እና እንደ ብረት የጠነከረ ጽናት ይጠይቃል፡፡ ታዲያ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሴናል ዘንድሮ የትኞቹን ዋንጫዎች አሳክቶ የውድድር ዓመቱን ይጨርሳል? የሚለው ከወዲሁ ትኩረትን ስቧል።
መድፈኞቹ በጥር እና በየካቲት ወር ከሚኖረው የጨዋታ መጨናነቅ አንጻር አቋሙ ይወርዳል ብለው ብዙዎች ቢገምቱም አሁን ላይ በሁሉም የውድድር መድረኮች እየተፎካከረ ይገኛል። በተለይም በካራባኦ ዋንጫ (የሊግ ዋንጫ) ውድድር ከባላንጣው ማንችስተር ሲቲ ጋር ለመፋለም በዌምብሌይ ስታዲየም ቀነ ቀጠሮ ይዟል። በተጨማሪም መድፈኞቹ በኤፍ ኤ ዋንጫ አራተኛ ዙር ላይ ይገኛሉ፤ በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ሲሆን በቻምፒየንስ ሊጉም አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ነው ጥሎማለፉን የተቀላቀለው፡፡ ይህም የአርሴናልን የዘንድሮ ጉዞ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የተለየ እና አስደናቂ ክለብ ያደርገዋል።
አርሴናል ባለፉት የውድድር ዘመናት መጨረሻ ላይ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ያደረገው የፕሪምየር ሊግ ፉክክር ምንም እንኳን በዋንጫ ባይታጀብም ለቡድኑ የማይተካ ልምድ እና ትምህርት ግን ሰጥቶታል። ከዚህ ቀደም የነበረው አርሴናል በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ የመሸበር እና ጫናን የመቋቋም ችግር የነበረበት ሲሆን አሁን በሜዳ ላይ የምንመለከተው ቡድን ግን ፍጹም የተለየ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬን የተላበሰ መሆኑን ሜዳ ላይ እየተመለከትን ነው። የሚኬል አርቴታ ልጆች አሁን የሚያሳዩት ብስለት ከዚህ በፊት በትንሽ ድል ከመፈንጠዝ እና በሽንፈት ከመደናገጥ ስሜት የወጡ መሆናቸውን መረጃው ያሳያል።
አሁን የካቲት ወር ላይ ሆነን መድፈኞቹ ለካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ መድረሳቸው ቡድኑ በየትኛውም የጨዋታ መርሀግብር ጫናን የመቋቋም አቅም እንዳዳበረ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ክለቡ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በዌምብሌይ የሚያደርገው የፍጻሜ ጨዋታ ለቀሪዎቹ ሦስት ዋንጫዎች (ፕሪምየር ሊግ፣ ኤፍ ኤ እና ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ) ትልቅ የስነ ልቦና መነቃቃትን የሚፈጥር ይሆናል። አንድ ቡድን እውነተኛ የአራት ዋንጫ አሸናፊ ተብሎ ለመጠራት በአንድ የውድድር ዘመን ውስጥ የክለቡን አህጉራዊ ትልቅ ውድድር (ቻምፒየንስ ሊግ)፣ የሀገር ውስጥ የሊግ ዋንጫ፣ የሀገር ውስጥ ዋና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና ሁለተኛውን የሀገር ውስጥ ዋንጫ (ወይም አቻውን) ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
እንደ እንግሊዝ ባሉ ሀገራት የሻምፒየንስ ሊግን፣ ፕሪምየር ሊግን፣ ኤፍ ኤ እና ሊግ ዋንጫ በአንድ ላይ እንደማንሳት ይቆጠራል። በዚህ መስፈርት ውስጥ እንደ ኮሚኒቲ ሺልድ ያሉ ባለ አንድ ጨዋታ ዋንጫዎች ወይም የፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ አይካተቱም፤ እንዲሁም እንደ ዩሮፓ ሊግ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ የአህጉር ውድድሮችም ተቀባይነት የላቸውም። በእነዚህ ጥብቅ መስፈርቶች ምክንያት ነው ይህንን ድል ማሳካት በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ከባድ እና ብርቅዬ ስኬት የሆነው።
ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት በአውሮፓ የእግር ኳስ ታሪክ ይህንን እውነተኛ የአራት ዋንጫ የተባለውን ክብር ማሳካት የቻለ አንድ ቡድን ብቻ እናገኛለን። እርሱም በ1967 እ.አ.አ የውድድር ዘመን በታዋቂው አሰልጣኝ ጆክ ስታይን የተመራ የኢሮፓ ዋንጫን (የአሁኑ ሻምፒየንስ ሊግን)፣ የስኮትላንድ ሊግን፣ የስኮትላንድ ዋንጫን እና የስኮትላንድ ሊግ ዋንጫን ጠራርጎ በመውሰድ ብቸኛው የአውሮፓ ክለብ ለመሆን በቅቷል። ከአውሮፓ ውጪ ደግሞ በብራዚላዊው ኮከብ ፔሌ የተመራው ሳንቶስ (Santos) በ1962 እ.አ.አ ተመሳሳይ ገድል በመፈጸም ስሙን በታሪክ ማስመዝገቡ ይታወሳል።
ብዙዎች በአንድ የውድድር ዘመን አራት እና ከዚያ በላይ ዋንጫዎችን በማንሳት ይህንን ስኬት ለማድገም ጥረት ቢያደርጉም፣ በዚህ መስፈርት መሰረት የአራት ዋንጫዎች አሸናፊ ሊባሉ ግን አልቻሉም። ለምሳሌ የፈረንሳይ ሀያል ክለብ ፒኤስጂ በተደጋጋሚ የሀገር ውስጥ የሦስትዮሽ እና የሱፐር ዋንጫዎችን በማሳካት በአንድ ዓመት አራት ዋንጫዎችን ወስዷል። ነገር ግን የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ማሸነፍ አለመቻሉ እንዲሁም ውድድሩን ሲያሸንፍ የሀገር ውስጥ የሊግ ዋንጫ ውድድር መሰረዙ ታሪኩን እንዳይጋራ አድርጎታል።
እንደ ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ፣ ባየርን ሙኒክ እና ፖርቶ ያሉ ታላላቅ ክለቦችም በርካታ ዋንጫዎችን በአንድ ዓመት ቢሰበስቡም ይህንን የተሟላ ክብር አላገኙም። በቅርቡ በ2024/25 እ.አ.አ የውድድር ዘመን የብራዚሉ ፍላሜንጎ ስድስት ዋንጫዎችን ቢያሸንፍም አራቱን ዋና ዋና የአህጉር እና የሀገር ውስጥ ውድድሮች ባለማሽነፉ በዝርዝሩ ውስጥ መካተት አልቻለም።
አርሰናል ግን ዘንድሮ በሀገር ውስጥ ያሉትን ዋንጫዎች የመሰብሰብ እድላቸው ሰፊ ቢመስልም ዋናው እና ትልቁ ፈተና የሚሆነው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ነው። አርሰናል ይህንን ዋንጫ በታሪኩ አንስቶ አያውቅም፤ ስለሆነም አሁን ካለው ምርጥ አቋም በመነሳት የአውሮፓን ምርጥ ክለቦች በማሸነፍ ይህንን ዋንጫ ማሳካት ይችላል- የደጋፊዎቹ እና የኦፕታ አናሊሰት ግምት ነው፡፡ መድፈኞቹ ከተሳካላቸው ግን በዘመናዊ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታሉ።
በዘመናዊው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ውስጥ እንደ ማንችስተር ሲቲ ያለ ግዙፍ የሊጉ አውራ በነገሰበት ዘመን ተፎካካሪ ሆኖ መገኘት በራሱ እንደ ድል የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ነገር ግን ለሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሴናል ተፎካካሪነት ብቻውን በቂ የሚሆንበት ምዕራፍ አብቅቷል። “ወደ ቀድሞ ክብራችን እንመለሳለን” በሚል የኤምሬትሱን መንበር የተረከቡት ሚኬል አርቴታ ቡድናቸውን ገንብተው፣ አብስለው እና አደራጅተው ለፍሬ ለማብቃት ወሳኝ የውድድር ዓመት ላይ ይገኛሉ።
የዘንድሮው አርሴናል ከዚህ ቀደም ከምናውቀውና “ውብ እግር ኳስ ይጫወታል ነገር ግን ልፍስፍስ ነው” ተብሎ ከሚታማው ቡድን ጋር ሲነጻጸር ፍጹም የተለየ ነው። የዚህ ቡድን የጀርባ አጥንት የተገነባው በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓ እግር ኳስ የማይደፈረው ምሽግ እየተባለ በሚጠራው የመሀል ተከላካይ ጥምረት ነው።
ዊሊያም ሳሊባ እና ጋብሪኤል ማጋሌስ የፈጠሩት ጥምረት መድፈኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ እጅግ በጣም ጥቂት ግቦች ብቻ እንዲቆጠርባቸው አስችሏቸዋል። አርሴናል ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት የ25ኛ ሳምንት መርሀግብር ድረስ በፕሪሚየር ሊጉ 17 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠረበት፤ ይህም ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ አነስተኛ ግቦች የተቆጠረበት የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ በሻምፕዮንስ ሊጉም አራት ግቦች ብቻ እንደተቆጠረበት አይዘነጋም፤ ይህም እስካሁን በታላቁ መድረክ የማይሰበር እና አስፈሪ የኋላ ክፍል ያለው ቀዳሚ ክለብ መሆኑን አስመስክሯል፡፡
ይሁን እንጂ ከፊታቸው ያለው የጨዋታ ሳምንታት ለአርቴታ እና ለልጆቹ እጅግ ፈታኝ ቀናት ይሆናሉ። የካቲት እና መጋቢት ወራት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች የሚመለሱበት እና የሊጉ ፉክክር የሚግልበት ወቅት በመሆኑ የተጫዋቾች ጉዳት እና የድካም ስሜት የቡድኑን ብቃት ሊፈትኑት ይችላሉ። አርሴናል በቀጣይ በቻምፒየንስ ሊጉ የጥሎ ማለፍ መድረክ ወሳኝ መርሀግብር ይኖረዋል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ደግሞ ከባድ የሆኑ የደርቢ እና ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች እንዳሉት መርሀግብሩ ያሳያል። በተለይም ከቸልሲ፣ ቶትንሀም ሆትስፐርስ፣ ዎልቭስ፣ አቨርተን እና ከመሳሰሉት ጋር የሚያደርጉት ጨዋታዎች ፍጹም ከስህተት የጸዱ መሆን አለባቸው። በዚህ የተጣበበ መርሀ ግብር ውስጥ የአርቴታ ትልቁ የቤት ሥራ የሚሆነው ቁልፍ ተጫዋቾቹን (እንደ ሳሊባ፣ ማጋሌሽ እና ዴክላን ራይስ ያሉትን) ከጉዳት እየጠበቀ የቡድኑን አሸናፊነት ማስቀጠል ነው።
ማንችስተር ሲቲ በፔፕ ጋርዲዮላ እየተመራ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እያሳየ ያለው አቋም ለአርሴናል ትልቅ ስጋት ነው። አርሴናል የሚዘናጋ ከሆነ ሲቲ በተከታታይ ጨዋታዎችን የማሸነፍ ልምድ ስላለው አጨራረሱን ያሳምራል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል። በሌላ በኩል የሊቨርፑል ፈጣን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለዋንጫው ያለውን ፉክክር የሦስትዮሽ አድርጎታል። አርሴናል ከእነዚህ ሁለት ቡድኖች ጋር ያለው ልዩነት በነጥብ ደረጃ ጠባብ ቢሆንም በስነ ልቦና እና ልምድ ረገድ ግን አሁንም መሻሻል ያስፈልገዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት በመጨረሻዎቹ ሳምንታት እንደታየው አይነት ያለመረጋጋት ችግር ዘንድሮም እንዳይደገም አርቴታ ከፍተኛ የስነ ልቦና ሥራ መስራት ይጠበቅበታል።
ዘንድሮ የአርሴናል የአራት ዋንጫ ጉዞ እውን እንዲሆን ያስቻለው ዋነኛው ምክንያት የታክቲክ ለውጥ ብቻ ሳይሆን በጨዋታ ተበልጦም ቢሆን ውጤት ይዞ መውጣት እና የአሸናፊነት ባህልን ማዳበራቸው እንደሆነ የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። ይህ አይነቱ ባህሪ ቀደም ሲል በአርሴናል ቤት ብዙም የተለመደ አልነበረም፡፡
አርሴናል ካለፉት ዓመታት በተለየ ዘንድሮ የተጫዋቾችን ጥራት እና ጥልቀት ከፍ አድርጓል። አምና የዊሊያም ሳሊባ ጉዳት የቡድኑን የዋንጫ ተስፋ እንዴት እንዳጨለመው አይዘነጋም። ዘንድሮ ግን አርሴናል ተቀያሪ ወንበር ላይ እንደ ኤብሪቼ ኢዜ፣ ሞስኬራ፣ ሄንካፔ፣ ሚኬል ሜሪኖ እና ማዶኬን የመሳሰሉ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች ይዟል፤ ይህ የቡድን ስበስብ ክለቡ በካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ፣ በፕሪምየር ሊግ፣ በቻምፒየንስ ሊግ እና በኤፍ ኤ ዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንዲቆይ አስችሎታል።
የዘንድሮው አርሴናል ትልቁ ጥንካሬው የኋላ ክፍሉ ነው። የዊሊያም ሳሊባ እና የጋብሪኤል ማጋሌስ ጥምረት በአውሮፓ ውስጥ እጅግ አስተማማኝ እና ለመሰበር አስቸጋሪ የሆነ ጠንካራ ምሽግ ፈጥሯል። እነዚህ ሁለት የመሀል ተከላካዮች ያላቸው መናበብ፣ ጉልበት እና ጥንካሬ ክለቡ ብዙ ግብ እንዳይቆጠርበት ማድረግ ችለዋል።
ሳሊባ ኳስን ከኋላ በመመስረት እና የተጋጣሚን ኢላማ በማክሸፍ የሚታወቅ ሲሆን ጋብሪኤል ማጋሌስ ደግሞ በአልሸነፍ ባይነቱ እና በአየር ላይ ኳሶች ባለው የበላይነት ይታወቃል። ከኋላ ክፍሉ ጥንካሬው ባልተናነሰ ዘንድሮ አርሴናልን የዋንጫ ተፎካካሪ ያደረገው ሌላኛው ታክቲካዊ መሳሪያ የቆሙ ኳሶች (Set Pieces) አጠቃቀም ነው። በአሰልጣኝ ኒኮላስ ጆቨር የሚመራው ይህ ታክቲክ አርሴናልን በማዕዘን፣ በፍጹም ቅጣት እና በቅጣት ምት በሚገኙ ኳሶች ግብ ያስቆጠረ የፕሪምየር ሊጉ ቁጥር አንድ ቡድን አድርጎታል። በጠንካራ ፉክክር ወቅት እና እንደ ፍጻሜ ባሉ ወሳኝ የጨዋታ መድረኮች በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ (Open play) ግብ ማስቆጠር ሲከብድ የቆሙ ኳሶች እንደ ትልቅ መሳሪያ ያገለግላል።
በመሀል ሜዳውም ቢሆን አርሴናል ትልቅ ለውጥ አሳይቷል። የዴክላን ራይስ እና የማርቲን ዙብሜንዴ ጥምረት ለቡድኑ ትልቅ ሚዛን ፈጥሯል። ማርቲን ዙብሜንዴ ኳስን ከኋላ በመቀበል እና ጨዋታን በማረጋጋት የሚጫወተው ሚና ዴክላን ራይስ አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት በነፃነት ወደ ፊት እንዲሄድ ያግዘዋል። ይህ ጥምረትም አርሴናልን በአራት መድረኮች እንዲፎካከር ጉልበት ሆኖታል። ይህ ሁሉ ጥንካሬ ነው አርሴናልን በያዝነው የካቲት ወር የአራት ዋንጫ እጩ ያደረገው።
አርሴናል አሁን ባለው አቋም ሁሉንም ዋንጫዎች ለማንሳት ከፍተኛ እድል እንዳለው የኦፕታ አናሊሰት መረጃ ያመለክታል። አርሴናል አራት ዋንጫን ባያሳካ እንኳ አሁን ካለው ጥንካሬ አንጻር ቢያንስ የሦስትዮሽ ወይም የሁለትዮሽ ዋንጫ ባለቤት የመሆን ሰፊ ዕድል እንዳለው መረጃዎች ያስነብባሉ። በተለይም የካራባኦ ዋንጫን ማሳካት ከቻለ ለቀሪው የውድድር ዘመን ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥርለታል። በ2025/26 የውድድር ዘመን ጥያቄው “አርሴናልን ዋንጫ ያሳካል ወይ?” የሚል ሳይሆን “ስንት ዋንጫዎችን ያሳካል?” የሚል እንደሆነ የኦፕታ አናሊስት መረጃ ያስነብባል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


