በርካታ ትዳሮች በልጅ ማጣት ምክንያት ተበትነዋል:: የብዙዎች ልብ በቅስም ሰባሪ ንግግር ተሰብሯል:: በተለይም በማሕበረሰባችን በተለምዶ መካንነትን ወይም ልጅ ለመውለድ አለመቻልን የሴት ችግር ብቻ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ አለ:: እኛም ይህን አስተሳሰብ በተመለከተ ሀሳባቸውን እንዲያጋሩን በእያስታ የሕክምና መዕከል የማሕጸን እና የፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ባዘዘው ፈቃድ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ በቆይታችንም ስለመካንነት ምንነት፣ ምክንያቶች እና ሕክምናዎች አውርተናል:: መልካም ንባብ!
መካንነት ምን ማለት ነው?
ዶ/ር ባዘዘው እንደሚሉት ሁለት ጥንዶች ወይም ተጋቢዎች (የሴቷ እድሜ ከ35 ዓመት በታች ሆኖ) ያለምንም የእርግዝና መከላከያ በሳምንት ከሦስት እስከ አራት ጊዜ የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርገው ለአንድ ዓመት ያህል መጸነስ ካልቻሉ ችግሩ መካንነት ተብሎ ይገለጻል:: የሴቷ እድሜ ከ35 ዓመት በላይ ከሆነ ግን የእንቁላል ክምችቱ እያለቀ ስለሚሄድ አንድ ዓመት መጠበቅ ጊዜ ማባከን ስለሚሆን ለስድስት ወር ተሞክሮ ልጅ መውለድ ካልተቻለ መካንነት ተከስቷል ይባላል::
መካንነት በየትኛው ጾታ ይከሰታል?
ዶ/ር ባዘዘው እንደሚሉት በተለምዶ መውለድ መቸገር የሴት ችግር ተደርጎ ይወሰዳል:: ይሄ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው:: ልጅ መውለድ አለመቻል የወንድም የሴትም ችግር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል:: ባለሙያው እንዳብራሩት ወንዶች ከ30 እስከ 40 በመቶ ልጅ ማስጸነስ ሲቸገሩ ሴቶች ደግሞ ከ40 እስከ 50 በመቶ ልጅ ለመጸነስ ይቸገራሉ::
ዶ/ር ባዘዘው እንደሚሉት ወደ ሕክምና ተቋማት መጥቶ የመታየት ችግር ካልሆነ በስተቀር በጥናትም የተደገፈውና በተግባርም የሚታየው ብዙ ወንዶች ልጅ እምቢ አለን ብለው ወደ ሕክምና ስለማይመጡ እንጂ መካንነት በሁለቱም ጾታ የሚታይ ነው:: ያም ሆኖ ወደ ሕክምና የመጡትን ወንዶች በምናይበት ጊዜ ልጅ መውለድ አለመቻል ከሴቶች ባልተናነሰ የወንዶችም ችግር ሆኖ ይገኛል:: ከሞላ ጎደልም ችግሩ በእኩል ደረጃ ይገኛል ማለት እንደሚቻል ነው የጠቆሙት::
ወንዶቹ መካን ሊሆኑ የቻሉበትን ምክንያት ሲያስረዱም አንድ ወንድ ባለቤቱን ለማስጸነስ ከጭንቅላት ጀምሮ እስከ የወንድ የዘር ፈሳሽ ድረስ ያለው ተክለ ሰውነት ክፍል ጤናማ መሆን ይኖርበታል:: ጭንቅላት ውስጥ የሚገኘው ፒዩቲታሪ የሚባል ዕጢ አለ:: ይህ እጢ ከሚያመርታቸው ውስጥ ለመራቢያነት የሚያገለግሉ ሆርሞኖች ማነስ ካለ፣ የዘር ፍሬዎቹ ላይ ችግር ካለ( በኢንፌክሽን፣ በአደጋ ምክንያት ሊከሰት ይችላል)፣ ኢንፌክሽኖች፣ የአባላዘር በሽታዎች፣ አንዳንዴ የዘር ፍሬው ይመረትና በኢንፌክሽን ወይም በአደጋ ምክንያት የዘር ፍሬ መውጣት አለመቻል፣ በስነ ልቦና ችግር ምክንያት ግንኙነት ለማድረግ መቸገር ካለ መደበኛ የሆነ ግንኙነት ስለማይኖር መካንነት ሊከሰት ይችላል::
የሴቶችን በምናይበት ጊዜም ልክ እንደ ወንዶቹ ልጅ ለመውለድ ጤንነታቸው የተሟላ መሆን አለበት:: የፒቱታሪ እጢ ከሚያመርታቸው ለመራቢያ የሚያገለግሉ ሆርሞኖች ማነስ ካለ፣ ሆርሞኖቹ ተመርተው ግን ኦቫሪ የሚባለው የሰውነት ክፍል (የእንቁላል ከረጢቶች) በቂ የእንቁላል ክምችት መያዝ አለባቸው:: ያለው የእንቁላል ክምችትም በቀላሉ ተፈልፍሎ መውጣት ይኖርበታል:: የእንቁላል የመፈልፈል ችግር ካለ፣ ብዙ ጊዜ ባልታከመ ኢንፌክሽን ምክንያት የተፈለፈለው እንቁላልም ወደ ዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ሳይሄድ ከቀረ፣ የእንቁላል መጠን ማነስ፣ ማሕጸን አካባቢ የተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ካሉ የዘር ማስተላለፊያ ትቦዎችን ይዘጋል:: የማሕጸን ግድግዳ ጠባሳ መኖርም መካንነትን ሊያመጣ ይችላል::
በሌላ በኩል ዶ/ር ባዘዘው እንደሚሉት ለሴቷም ሆነ ለወንዱ የመካንነት ምርመራ ተደርጎላቸው ልጅ ላለመውልድ የሚያስችል ምክንያት የሌላቸው ጤነኛ ጥንዶች ለበርካታ ዓመታት አንድ ላይ እየኖሩ ልጅ ለመውለድ ሲሞክሩ ኖረው አልሳካ ሲላቸው በየፊናቸው ሌላ ሰው አግብተው ሲኖሩ ሁለቱም ልጅ ሊወልዱ የመቻል አጋጣሚ ሊኖር ይችላል:: ይህ ግን ከ10 እስከ 20 በመቶ ምክንያት አልባ ክስተት ነው:: ነገር ግን የሁለቱ ተጋቢዎች ዘረ መል ያለመመቻቸት ሁኔታዎች ችግሩን ሊፈጥሩት ይችላሉ::
መካንነት እንዴት ይታወቃል?
አንዲት ሴት ”መካን ነኝ ወይስ አይደለሁም” የሚለውን ልታረጋግጠው የምትችለው ለአንድ ዓመት የወሊድ መከላከያ ሳትወስድ መደበኛ ግንኙነት እያደረገች ልጅ መጸነስ ካልቻለች ነው:: ባለሙያው እንደሚሉት ልጅ መውለድ መቸገር ወይም “ኢንፈርትሊቲ” ይባላል:: ይህ ግን ልጅ መውለድ አለመቻል ማለት አይደለም:: ምክንያቱም መውለድ አለመቻል የሚረጋገጠው በሕክምና ነው:: ታካሚዎቹ ካላቸው የሕክምና ታሪክ፣ በሚደረግላቸው አካላዊ ምርመራ፣ በሚደረጉ የላብራቶሪ፣ የራጅ እና የአልትራሳውንድ ምርመራዎች አማካኝነት ችግሩ ተለይቶ መውለድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን እና አለመኖራቸው ይረጋገጣል:: ተጋቢዎች መውለድ ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለውን ለማወቅ ጉዳዩ በሕክምና ማረጋገጥ አለበት::
የመካንነት ሕክምና
ብዙዎቹ ልጅ እምቢ ያላቸው ጥንዶች መጸነስ እና መውለድ እንደሚችሉ የሚያስረዱት ባለሙያው ሕክምናው ምንድን ነው የሚለውን በተመለከተ የሆርሞን ፣ የአልትራሳውንድ እና የማሕጸን ትሪያጅ ምርመራዎች እንደሚደረጉ፣ የወንድ የዘር ፍሬ ፈሳሽም ምርመራ እንደሚደረግለት ያስረዳሉ:: እነዚህ ምርመራዎች ከተደረጉ በኋላ እንደምክንያቱ እና እንደ ችግሩ ሕክምናውም ያንን መሰረት ያደረገ ይሆናል:: ለምሳሌ የወንዶች የሆርሞን ችግር ነው ተብሎ ከታሰበ ችግሩን ያመጣው ምንድነው የሚለው ተለይቶ ይታከማል፣ ግንኙነት ለማድረግ የስነ ልቦና ችግር ካለም የስነ ልቦና ሕክምና ይሰጠዋል:: የወንድ የዘር ፍሬ ፈሳሹ የመውጣት ችግር ካለበትም በሕክምና ታግዞ እንዲወጣ በማድረግ የሴቷ ማሕጸን ላይ እንዲቀመጥ ይደረጋል::
የሴቶቹን ሕክምና በምናይበት ጊዜ የሆርሞን ችግር ካለ ሆርሞኑ እንዲስተካከል ይደረጋል:: ችግሩ የመነጨው ከክብደት መጨመር የተነሳ ከሆነም ክብደት እንድትቀንስ፣ ክብደት መጨመር ካለባትም እንድትጨምር ይደረጋል:: የእንቁላል ክምችቱ በቂ ሆኖ የመፈልፈል ችግር ካለበትም እንቁላሎቹ እንዲፈለፈሉ የሚያስችሉ መድሃኒቶችን በመስጠት፣ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦዎች ችግር ካለባቸው ደግሞ በቀዶ ሕክምና መስተካከል የሚችሉ ከሆነ በማስተካከል፣ የማሕጸን ግድግዳን እጢዎቹ ዘግተውት ከሆነም እጢዎቹን በማውጣት ማከም ይቻላል::
አንዳንድ ችግሮች ደግሞ ተጨማሪ ቴክኖሎጂ የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ:: ለምሳሌ የወንዱ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦዎች ተዘግተው የዘር ፍሬ ማስተላለፍ ሳይችሉ ከቀሩ፣ የሴቶቹ ቱቦዎችም በተመሳሳይ ከተዘጉና በቀዶ ሕክምና ሊስተካከሉ ይችላሉ ተብሎ የማይታሰብ ከሆነ ”አይ ቪ ኤፍ”(IVF) በሚባል ሕክምና እንዲወልዱ ይደረጋል:: ይህ ማለት የዘር ፈሳሽ ከሴቶቹ እና ከወንዶቹ ይወሰዳል፤ የሁለቱ የዘር ፈሳሾች በሕክምና ላብራቶሪ በአንድ ላይ እንዲገናኙ ይደረግና ከሳምንት በኋላ ከማሕጸን ግድግዳው ላይ ተመልሰው ይቀመጣሉ:: ይህ ዘዴ የተወሳሰበ የሚመስል ነገር ግን በሀገራችን በተለይም በአዲስ አበባ በስፋት እየተተገበረ የሚገኝ ነው:: በዚህም ብዙ ባለትዳሮች ወላጆች መሆን መቻላቻውን ነው ዶ/ር ባዘዘው ያስገነዘቡት::
በመጨረሻም ዶ/ር ባዘዘው “መካንነት አንዳንዴ በእኛ ማሕበረሰብ እንደ አንድ የጤና ችግር አይደለም የሚታየው፤ ይልቁንም ከእርግማን ጋር፣ ከመንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ ነገሮች ጋር የማያያዝ ነገር አለ:: ነገር ግን መካንነት አንድ የጤና ችግር መሆኑን ተገንዝቦ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይገባል::” ሲሉ ነው ያሳሰቡት:: ባለሙያው እንዳብራሩት ልጅ መውለድ አለመቻል በተለይም በእኛ ማሕበረሰብ ላይ ትልቅ ችግር ሲፈጥር ይታያል:: ብዙ ትዳሮች ሲፈርሱ ሀብት እና ንብረት ሲወድም ይታያል:: በዚሁ ትይዩ ከ10 እና ከ20 ዓመታት በኋላ የመካንነት ምርመራ አድርገው ታክመው ልጅ ወልደው ለመሳም የበቁ በርካታ ጥንዶችም አሉ:: አንዳንዴ እንቁላል አልፈለፈል ብሎ እንዲፈለፈል የሚያደርገውን መድሃኒት ከወሰዱ በኋላ መንታ ልጅ የሚወልዱ እንዳሉና ልጅ መውለድ ካስቸገራቸው በኋላ ልጅ መውለድ መቻል የደስታዎች ሁሉ ደስታ መሆኑን ነው ዶ/ር ባዘዘው ያስገነዘቡት::
ጤና አዳም
ልጅ የመውለድ እድልዎን ለመጨመር
*መደበኛ የሰውነት ክብደት ይኑሩዎት፤ የሰውነትዎ ክብደት ከመጠን በላይ ወይም በታች አይሁን::
*የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ::
*ሲጋራ ማጨስ የእርግዝና እድሎችን ይቀንሳል፤ የፅንስ መጨንገፍ አጋጣሚን ይጨምራል::
*አጫሾች ከማያጨሱ ሰዎች ከሁለት ዓመት ቀደም ብለው ማረጥ ይጀምራሉ::
*ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት አይፈጽሙ፤ ዛሬ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ካጋጠመዎ ነገ በወሊድ ወይም የመራቢያ አካልዎ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ::
*ልጆች ለመውለድ ዝግጁ ሲሆኑ አይዘግዩ::
*የሴት ልጅ እድሜ ከማለፉ በፊት (እድሜ ከ35 ዓመት ሳያልፍ) የህክምና እርዳታ ካገኘች የመጸነስ እና ወላጅ የመሆን እድሏ ከፍተኛ ነው::
ምንጭ፡-https://www.ucsfhealth.org/፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


