ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? የአንደኛው ወሰነ ትምህርት ተጠናቆ ሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ጀምሯል፡፡ ከመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት የተሻለ ውጤት ለማምጣት እቅድ እንዳወጣችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ልጆች ቤተሰቦቻችሁን አቅማችሁ በፈቀደው ታግዛላችሁ? ቤተሰቦቹን አቅሙ በፈቀደ የሚያግዝ ልጅ እናስተዋውቃችሁ፡፡
ኃይለሚካኤል ንብረት የሚኖረው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በእንጅባራ ከተማ ነው፡፡ የ12 ዓመት ታዳጊ እና የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በአገው ፈረሰኞች በዓል ላይ እናቱን ሲያግዝ ነው ያገኘነው፡፡ እናቱ ለበዓሉ አብዚ የተባለውን እና ሌሎች የአገው ባሕላዊ ምግቦችን ስታዘጋጅ አግኝተናታል፡፡
እስጢፋኖስም በመላላክ እና የተለያዩ እገዛዎችን በማድረግ ከጎኗ ነበር፡፡ ልጆች በዚህ አጋጣሚ አብዚ ማለት ከሽሮ፣ ከባቄላ፣ ከኑግ፣ ከአይብ እና ሌሎች የሚሠራ፤ በተጠቀሱት የምግብ አይቶች በእንጀራ ላይ ተቀብተው (የሚቀቡት አንድ ላይ ሳይሆን ብቻ ብቻቸውን ነው) የሚቀርብ ምግብ ነው፡፡
ልጆች እስጢፋኖስ በእረፍት ጊዜው የቤተሰቦቹን የአትክልት ቦታ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ያሳልፋል:: ከዚህ ባለፈ ቤተሰቦቹ የሚያዙትን ከእድሜው እና አቅሙ ጋር የሚመጣጠኑ ሥራዎች ይሠራል፡፡
የእረፍት ጊዜ ሲኖር ደግሞ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር አብሮ በመጫወት ነው የሚያሳልፈው:: ልጆችዬ! እስጢፋኖስ ጐበዝ ነው አይደል? አቅም በሚመጥን መንገድ ቤተሰብን መርዳት መቻል ጥሩ ነገር በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል:: እናንተም በአቅማችሁ መሥራት፣ ማጥናት እና እረፍታችሁን በአግባቡ መጠቀም ይገባችኋል እንላለን!።
ተረት
ቀበጧ አህያ
በአንድ ወቅት ከከብቶች ጋር የምትኖር አህያ ነበረች:: ከከብቶቹም ጋር ትበላና ትተኛ ስለነበረ ቀንዶቻቸውን ስታይ ትቀናባቸው ጀመር:: “ቀንዶች ቢኖሩኝ ጅቦችን እከላከልባቸው ነበር::” ብላም አሰበች:: “እናም ወደ ገጠር ወይም ወደ ሌሎች መንደሮች ሄጄ ቀንዶች የማገኝበትን መንገድ መፈለግ አለብኝ::” ብላ በማሰብ ረጅም ጉዞ ላይ እንዳለች ጀርባው ላይ ትልቅ ሸክም ተሸክሞ ይጓዝ የነበረ ነጋዴ አገኘች::
ነጋዴውም “አሃ! አምላክ በጣም ስላሰበልኝ ይህንን ከባድ ሸክም ሊያቀልልኝ ይህችን አህያ ላከልኝ::” ብሎ በማሰብ ሸክሙን አህያዋ ላይ ጫነው:: ሸክሙም ለአህያዋ ከባድ ቢሆንም አብረው ብዙ መንገድ ከተጓዙ በኋላ አህያዋ ማረፍ ስለፈለገች ቀስ ብላ መራመድ ጀመረች:: በዚህ ጊዜ ሰውየው በያዘው ዱላ ደጋግሞ ይመታት ጀመር:: ሸክሙ አሁንም እንደከበዳት ነበርና በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስላልቻለች በመጨረሻ በጉልበቷ ተንበርክካ አልሄደም አለች:: ነጋዴው ቢደበድባትም ተነስታ መራመድ አልቻለችም:: በዚህ ጊዜ ነጋዴው አንደኛውን ጆሮዋን ቆረጠው:: አሁንም በጣም ስለደከማት መንቀሳቀስ አቃታት::
ከዚያም ነጋዴው ሸክሙን አውርዶላት አህያዋን እዚያው የተኛችበት ትቷት መንገዱን ቀጠለ:: አህያዋም ሸክሙ ከወረደላት በኋላ ወደቀድሞው ቦታዋ ወደከብቶቹ ተመልሳ ስትሄድ የምትፈልገውን ቀንድ ለምን እንዳላገኘች ጠየቋት::
“አይይ! እናንተ ቀንድ ስለማግኘቴ ነው የምታወሩት? እንኳን ቀንድ ላገኝ የነበረኝንም ጆሮ አጥቼ መጣሁ:: ዋጋዬንም አግኝቻለሁ::” አለቻቸው:: ከዚያን እለት በኋላ አጉል ምኞት ያላቸው ሰዎች “ቦታችሁን እወቁ:: ካለበለዚያ ቀንድ እፈልግ ብላ ጆሮዋን እንዳጣችው አህያ እንዳትሆኑ::” እየተባባሉ ይመከሩ ጀመር::
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች ስብስብ፡፡
ይሞክሩ
- ብዙ በወሰድክበት ቁጥር እየተለቀ የሚሄድ ምድን ነው?
- ፍሪጅ ውስጥ እንኳን ብታስገባው ማቃጠሉ የማይበርድ ምንድን ነው?
- ሶስት ሙዝ ጠረጴዛ ላይ ቢኖርና ሁለቱን ብትወስዱ ስንት ሙዝ ይኖራችኋል?
መልስ
- ቀዳዳ
- ቃሪያ
- የወሰዳችሁት ሁለት ሙዝ
ነገር በምሳሌ
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ከተባበሩ የማይቻለውም ይቻላል፡፡
ሚስጥር የባቄላ ወፍጮ አይደለም–
ሚስጥር በአደባባይ የሚነገር አይደለም፤
ሲጎርሱ በልክ ሲታጠቁ በጥብቅ
ሁሉም ነገር በወግ በማዕረጉ ያምራል፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


