የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2018 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ዙር ተጠናቋል:: አዲስ አበባ፣ አዳማ እና ሀዋሳ በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ውድድር በአጠቃላይ 190 ጨዋታዎች ተደርገዋል:: በእነዚህ ጨዋታዎች 320 ግቦች በተለያዩ 155 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል፤ 951 ካርዶችም የተመዘዙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 905ቱ ቢጫ፣ 33ቱ በሁለት ቢጫ ቀይ ካረድ የተመዘዘባቸው እና 13 ቀጥታ ቀይ ካርዶች ናቸው። ሦስት ክለቦች እኩል 35 ነጥብ በመሰብሰብ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል። ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከነማ እና ነገሌ አርሲ በግብ ልዩነት ብቻ ተበላልጠው ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ያለውን ደረጃ ይዘው የመጀመሪያውን ዙር ጨርሰዋል:: ይህም የሊጉን የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከነማ እና ነገሌ አርሲ ያሳዩት ወጥ አቋም፣ የመከላከል ጥንካሬ እና የማጥቃት ስልት ከሜዳ ውጪ ያሉ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያረጋገጡበት ነው። የዘንድሮው ፉክክር ከቀደሙት ዓመታት የሚለየው ትልልቅ ስም ያላቸው ክለቦች በሜዳ ላይ የቴክኒክ ብልጫ የተወሰደባቸው መሆኑ ነው። ይህም ሊጉ ምን ያህል አጓጊ እና ያልተገመተ እንደሆነ ማሳያ ነው።
የገንዘብ አቅም ብቻውን ዋንጫ እንደማያመጣ እና ትክክለኛ የክለብ አወቃቀር እና የአሰልጣኝ ታክቲክ ወሳኝ መሆናቸውን የሲዳማ እና የሀዋሳ ከነማ የበላይነት አብነት ነው። ይህ የኃይል ሽግግር የሊጉን ተወዳዳሪነት ከፍ ያደረገው ሲሆን የዋንጫው ግምት ወደ አዲስ ክለብ እንዲያዘነብልም አድርጓል። በመጀመሪያው ዙር የተመለከትነው የነጥብ ልዩነት በጣም ጠባብ መሆኑ በሁለተኛው ዙር ምን ያህል ከባድ ፉክክር ሊታይ እንደሚችል ከወዲሁ አመላካች ነው።
ለዋንጫው የሚደረገው ፉክክር ከወትሮው በተለየ ዘንድሮ አጓጊ ሆኗል። የሊጉን መሪነት የያዘው ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው ዙር ያሳየው ጥንካሬ የትኛውም የሊጉ ክለብ ሊገዳደረው አልቻለም። ሲዳማዎች በተለይ በመልሶ ማጥቃት እና በሽግግር ወቅት ያላቸው ፍጥነት ለተጋጣሚ ቡድን ፈተና እንደነበሩ አይዘነጋም።
በወጣቶች ስብስብ የተገነባው ሀዋሳ ከተማም ወደ ቀደመው ክብሩ ለመመለስ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ጥሩ ጊዜ አሳልፏል። ሀይቆቹ ዘንድሮ የእየተጫወቱት ያለው እግር ኳስ ማራኪ እና ውጤታማ መሆኑን ተመልክተናል:: በተለይ የአማካይ ክፍላቸው የሊጉ ምርጥ ፈጠራ የታየበት እንደነበርም የሚታወስ ነው። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው እና የሊጉ ጥቁር ፈረስ (Dark Horse) የሆነው ነገሌ አርሲ ደግሞ የዘንድሮው ትልቁ አስገራሚ ቡድን ነው። አዲስ አዳጊው ክለብ ሳይጠበቅ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረቡ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ነገሌ አርሲዎች በተለይ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ የሚያሳዩት አልሸነፍባይነት እና ጠንካራ የመከላከል ብቃት አሁን ካሉበት ደረጃ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል።
ምንም እንኳን የነጥብ ልዩነቱ ሰፊ ባይሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ፋሲል እና መቻል የመሳሰሉ ክለቦች ዘንድሮም ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆን አልቻሉም:: የአማራ ክልልን እግር ኳስ የወከሉት ባሕር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማም በዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር በተጠበቀው ልክ መጓዝ አልቻሉም። የጣና ሞገዶቹ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ለዋንጫ ይፎካከራሉ ተብለው ቢጠበቁም የመጀመሪያውን ዙር ግን በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆኖ ነው ያጠነቀቁት።
የባሕር ዳር ከነማ ዋነኛ ችግር ኳስ እና መረብን ማገናኘት ነው:: ቡድኑ ኳስን ተቆጣጥሮ ከመጫወት ባለፈ የተገኙ እድሎችን ወደ ግብ የመቀየር ውስንነት አለበት። ይህም በርካታ ጨዋታዎችን ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ እንዲወጣ አስገድዶታል:: ቡድኑ ካደረጋቸው 19 መርሀግበሮች ያሸነፈው በአራት ጨዋታዎች ነው:: በሦስቱ ሲሸነፍ በ12ቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል:: ይህም ገና ከወዲሁ ከዋንጫው ፉክክር እንዲርቅ አድርጎታል። የኋላ ክፍሉ 13 ግቦች ተቆጥረውበታል::
የፊት መስመሩ ደግሞ 14 ግቦችን ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን ከፕሪሚየር ሊጉ ደካማ የፊት መስመር ካላቸው ክለቦች መካከል አንደኛው ነው:: እናም ቡድኑ በሁለተኛው ዙር የፊት መስመሩን ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል:: ባሕር ዳር ከነማ የፊት መስመር አጥቂዉን አንተነህ ተፈራን ከሸገር ከተማ በማስፈረም የአጥቂ ክፍሉን አጠናክሯል። ከሁለት ዓመት በፊት በልምምድ ላይ እያለ ከባድ ጉዳት ገጥሞት የነበረው አደም አባስም ከጉዳቱ አገግሞ ቡድኑን ተቀላቅሏል::
በተመሳሳይ ፋሲል ከነማዎች ከባለፉት ሦስት ዓመታት በተሻለ ዘንድሮ ጥሩ አጀማመር ቢያደርጉም በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ያሸፉት ግን ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው። ፋሲል ከነማ በመጀመሪያው ዙር ካደረጓቸው 19 ጨዋታዎች ስምንቱን በድል ተወጥቷል፤ ሁለት ጨዋታዎችን ተሸንፈዋል:: በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል::
በተለይ በተከላካይ መስመር እና በአማካይ ክፍል መካከል ያለውን ክፍተት መድፈን ባለመቻሉ ከተፎካካሪዎች አንፃር ሲታይ ደካማ የሚባል የመጀመሪያ ዙር አሳልፏል። ምንም እንኳ የፊት መስመሩ ደከማ ቢሆንም ስምንት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት የኋላ ክፍሉ ግን ከፕሪሚየር ሊጉ በቀላሉ የማይረበሽ እና ግብ የማይቆጠርበት ቀዳሚው ጠንካራ የኋላ ክፍል መሆኑን ቁጥሮች ይመሰክራሉ::
ሁለቱ የአማራ ክልል ክለቦች በክረምቱ የዝውውር ወቅት የገነቡት ስብስብ ሜዳ ላይ ውጤት ማምጣት አለመቻሉ ትልቅ ጥያቄ ፈጥሯል። ፋሲል ከነማ እና በሕር ዳር ከነማ በመጀመሪያው ዙር በነበራቸው አቋም የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድላቸው የጠበበ ነው። ዋንጫውን ለማንሳት እና በአፍሪካ መድረክ የመሳተፍ እድላቸውን ለማረጋገጥ በሁለተኛው ዙር ተአምር መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በገንዘብ አቅም እየተፈተኑ ያሉት እና የአደረጃጀት ችግር ያለባቸው ክለቦች ደግሞ ህልውናቸውን ለማቆየት እየታገሉ ይገኛሉ። በወራጅ ቀጣናው የሚገኙት ክለቦች በተለይ የፊት መስመራቸው እጅግ ደካማ ሆኖ ታይቷል። ወላይታ ድቻ፣ አርባ ምንጭ፣ ወልዋሎ አዲግራት እና መቀሌ 70 እንደርታ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛሉ። የእነዚህ ክለቦች ችግር ሜዳ ላይ ከሚታየው የቴክኒክ ድክመት ባሻገር የተጫዋቾች ደመወዝ መዘግየት እና የአስተዳደር አለመረጋጋት ነው። እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ፍጻሜ ካልተጫወቱ በሁለተኛው ዙር መጨረሻ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸው የማይቀር ይመስላል።
በተለይ በዘንድሮው ዓመት በሊጉ አናት እና ግርጌ ላይ ያሉት ክለቦች ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ለወራጅ ቀጠና ክለቦች ተስፋ አስቆራጭ ነው። ከመውረድ ለመትረፍ የሚያደርጉት ትግል በሁለተኛው ዙር ይበልጥ እንደሚጠነክር ይጠበቃል:: የጥር የተጫዋቾች ዝውውር ወቅትን ተጠቅመው አዳዲስ ተጫዋቾችን ካላስፈረሙ አሁን ባለው ስብስባቸው መቀጠል በውድድር ዓመቱ የከፋ አደጋ ያስከትልባቸዋል። አሁን ላይ ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት የሚደረገው ፉክክር ከዋንጫው ባልተናነሰ አጓጊ ሆኗል፤ እናም የትኞቹ ክለቦች እንደሚሰናበቱ ለመለየት እስከ መጨረሻው ሳምንት መጠበቅ ግድ እንደሚል የደረጃ ሰንጠረዡ ያሳየናል።
በዘንድሮው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ለአንድ ወይም ለሁለት ክለቦች ብቻ የተተወ አለመሆኑን ያሳየ እና የእግር ኳሱን ድባብ ያደመቀ ነበር ማለት ይቻላል። እንዲሁም ወጣቶች እድል ያገኙበት እና አዳዲስ ኮከቦች ብቅ ያሉበት ውድድር ጭምር ነበር። የሸገር ከተማው ዳዊት ካሳው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ሁዘይፋ ሻፊ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል ይገኙበታል። ምንም እንኳን አንዳንድ ጨዋታዎች በግብ ቢመቱም የሲዳማ እና የሀዋሳ አጥቂዎች ባሳዩት ብቃት በአንፃራዊነት የተሻሉ ግቦች ተቆጥረዋል። በአጠቃላይ ግን አብዛኛዎቹ ቡድኖች በመከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወት መከተላቸው የግብ ብዛቱን ገድቦታል።
የመለማመጃ ሜዳ ችግር እና የስታዲየም ጥራት በመጀመሪያው ዙር ውድድር ክለቦችን የፈተነ ችግር ሆኖ ቀርቧል። ውድድሩ በተለያዩ ከተሞች መካሄዱ ለደጋፊዎች ምቹ አልሆነም ተብሎ ቅሬታ ይነሳል፤ ለተጫዋቾችም የድካም እና የጉዳት መንስኤ ሆኗል። እንዲሁም አንዳንድ ክለቦች በገንዘብ እጦት ምክንያት ተጫዋቾቻቸውን ማቆየት አለመቻላቸው የፉክክሩን ድምቀት ቀንሶታል:: ግብ ጠባቂዎች እና ተከላካዮች ጎልተው የወጡበት ነገር ግን ፈጣሪ አማካዮች በቁጥር ያነሱበት ውድድር እንደነበር የቴክኒክ ባለሙያዎች ይስማማሉ።
የዳኝነት ጉዳይ በዘንድሮውም የመጀመሪያ ዙር ውድድር ሌላኛው አነጋጋሪ ጉዳይ እንደነበር አይዘነጋም። ምንም እንኳን ፌዴሬሽኑ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቢሞክርም በበርካታ ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች ክለቦችን ሲያማርር ተስተውለዋል።
በተለይ በሲዳማ ቡና እና በነገሌ አርሲ ጨዋታዎች ላይ የተከሰቱ አከራካሪ ውሳኔዎች ዳኞች በጨዋታው ውጤት ላይ ተጽዕኖ እያሳረፉ ነው የሚል ቅሬታን አስነስተዋል። የኦፍሳይድ እና የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔዎች ወጥነት ማጣት የሊጉን ፕሮፌሽናል ገጽታ ጥያቄ ውስጥ ከቷል። የባሕር ዳር እና የፋሲል ከነማ አቋም መውረድ በሁለተኛውም ዙር የሊጉ ገበያ እና የተመልካች ቁጥር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ስጋቶች አሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ መድንን የመሳሰሉ ክለቦች የሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸው አይዘነጋም። ዘንድሮውስ የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ማን ያነሳል? አዲስ ክለብ ሻምፒዮን ይሆን? ወይስ የቀድሞ ጠንካራ ክለቦች ከተኙበት ነቅተው ውጤቱን ይቀለብሱታል? ጥያቄው በሁለተኛው ዙር ምላሽ ያገኛል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


