መካከለኛው ምሥራቅ

0
172

መካከለኛው ምሥራቅ በፖለቲካዊ ተጽዕኖው ምክንያት የዓለም አጀንዳ የሚወሰንበት ክልል ነው፡፡ በዘመናችን በክልሉ ውስጥ ያለው የስነ-ሕዝብ አወቃቀር ልዩነት፣ በነዳጅ ሀብት መትረፍረፍ፣ በእስያ፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል የሽግግር አካባቢ መሆኑ ግጭቶችን በማቀጣጠል የአሁኑን ያልተረጋጋ መካከለኛው ምሥራቅ ፈጥሯል ሲል በዓለም አቀፍ ትምህርት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርገው የሴንት ክልመንት ዩኒቨርሲቲ  (stclements.edu) ላይ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

 

ታሪካዊ አውድ

 

ዘመናዊው የመካከለኛው ምሥራቅ መንግሥታት ከኦቶማን ኢምፓየር መፍረስ እና ከተከተለው የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ስልጣን የወጣ ነው፡፡ የኦቶማን ኢምፓየር ከ600 ዓመታት በላይ የመካከለኛው ምሥራቅ ክፍልን ገዝቷል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነዳጅ መገኘት የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ገጽታ ለውጦታል፡፡

የአረብ-እስራኤል ጦርነት፣ የሶሪያ የእርስ በርስ ግጭት እንዲሁም እንደ ፓን-አረቢዝም እና ጽዮናዊነት ያሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካን ቀርጸዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም ነዳጅ ዘይት እንዲሁ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡

 

የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ቁልፍ ገጽታዎች የተለያዩ የአስተዳደር ሥርዓቶች ያሉት ነው፡፡ ክልሉ ፍፁም ንጉሣዊ መንግሥታትን (ለምሳሌ፡ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ባሕሬን ኦማን፣ ኢራቅ)፣ ሕገ-መንግሥታዊ ነገሥታት (ለምሳሌ፡ ዮርዳኖስ) እና የተለያየ የስልጣን ደረጃ ያላቸውን ኢራንን እና ሶሪያን ያካትታል፡፡

የአካባቢው ፖለቲካ በሃይማኖታዊ፣ በጎሳ እና በማንነቶች ከፍተኛ ተጽዕኖ የተደረገባቸው የአምባገነን መንግሥታት፣ የንጉሦች እና የሽግግር መንግሥታት ውስብስብ ድርን ከትልቅ ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት ጋር  ያካትታል፡፡

 

የጂኦፖለቲካዊ መልክአ ምድሩ በሳዑዲ አረቢያ (ሱኒ) እና ኢራን (ሺዓ) መካከል ያለው ፉክክር፣ በኢራቅ፣ ሶሪያ እና የመን ውስጥ ካሉ አማጺያኖች ጋር የተያያዘ ነው፡፡  የሀገራቱ የውስጥ ፖለቲካ በወታደራዊ አገዛዝ፣ በአንድ ፓርቲ ሥርዓት እና በተለያዩ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታዎች የሚገለጽ ነው፡፡ ክልሉ በፀጥታ እና ኢነርጂ ምክንያት በማያቋርጥ የውጭ ጣልቃገብነት ይፈተናል፤ ይህም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

የክልሉ የነዳጅ እና የጋዝ ክምችቶች የዓለም ኢኮኖሚን እና ክልላዊ ሃብትን ያንቀሳቅሳሉ፡፡ የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ እንደ ወሳኝ እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ወሳኝ ነጥብ ሆኖ ይታያል፡፡ የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት የክልላዊ አለመረጋጋትን የሚነካ ማዕከላዊ ግጭትም ነው፡፡ የጎሳ ክፍፍሎችም (አረቦች፣ ፋርሳውያን፣ ኩርዶች፣ ቱርኮች) ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ፈጥረዋል፡፡

ሊንክዲን /linkedin.com/ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው አብዛኛውን ጊዜ በግጭት የሚታመሰው የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖን ያሳድራል፡፡ ግጭቶቹም በዓለም አቀፍ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አላቸው፡፡

 

በታሪክ እና በባሕል የበለፀገው ክልሉ ከስልታዊ ጠቀሜታው በተለይም ካለው ሰፊ የነዳጅ ክምችት የተነሳ የዓለም አቀፍ ትኩረት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ኃያላን ዓይናቸውን እንዲያሳርፉበት አድርጓል፤ ለከፍተኛ ጣልቃ ገብነትም ተጋላጭ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ግጭቶች ውስብስብ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ በሃይማኖታዊ፣ በጎሳ እና በጂኦፖለቲካዊ ምክንያቶች የተደበላለቁ እና ችግሮቻቸው ከክልሉ ወሰን በላይ ናቸው፡፡

 

የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ተጽዕኖ

 

የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭቶች በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ላይ ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው፤ ብዙውን ጊዜ ትላልቅ ኃይሎችን ወደ ምህዋራቸው ይስባሉ፡፡ ለአብነትም የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት፣ የሶሪያ እና የመን የእርስ በርስ ጦርነት፣ በኢራን እና ጎረቤቶቿ መካከል ያለው ውጥረት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚያስፈልጋቸው  ናቸው፡፡

እነዚህ ግጭቶች ብዙውን ጊዜ ወደ ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ያመራሉ፡፡ እንደ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና የአውሮፓ ሀገራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመሳተፍ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ለአብነትም በክልሉ ያሉት ግጭቶች በሌሎች ሀገራት ጣልቃ ገብነት የሚዘወሩ ናቸው፡፡

 

ኢኮኖሚያዊ አንድምታ

48 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የነዳጅ ክምችት የሚይዘው መካከለኛው ምሥራቅ ከነዳጅ ዘይት ጋር የተያያዙ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በክልሉ ብሎም በዓለም አቀፍ  ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡

የፔትሮሊየም ላኪ ሀገሮች ድርጅት (ኦፔክ) የነዳጅ ፖሊሲዎችን ለማስተባበር እ.አ.አ በ1960 ነበር የተመሠረተው፡፡ የባህረ ሰላጤው የትብብር ካውንስል (ጂሲሲ) በነዳጅ ዘይት የበለፀጉ ስድስት ሀገሮችን ያጠቃልላል፡፡ እነሱም ሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌት፣ ባህሬን፣ ኳታር፣ ኤምሬትስ እና ኦማን ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሀገራት ላይ ችግር ቢፈጠር ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ያስከትላል፡፡

 

በዚህ ክልል ውስጥ ያሉ ግጭቶች የዓለምን የነዳጅ ዘይት ዋጋን ይለዋውጣሉ፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ የሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ፣ የየመኑ ሃውቲ የሚቆጣጠረው የቀይባሕር ወሳኝ የመርከብ መስመር፣ ውጥረቱ በዓለም የነዳጅ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ታይተዋል፡፡

አብዛኛው የዓለማችን ነዳጅ የሚተላፈው በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል መሆኑ ይታወቃል፤ በተመሳሳይ ከ12 በመቶ በላይ የዓለማችን ንግድ የሚከናወነው በቀይ ባሕር መስመር ነው፤ ይሁን እንጂ የየመኑ ታጣቂ ቡድን በሚያደርሰው የሽብር ጥቃት ምክንያት መስመሩ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛል፡፡ መርከቦቹም በተለዋጭ መስመር ከ17 ሰዓታት በላይ ተጨማሪ ጉዞ እንዲያደርጉ ተገደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ መስመሩ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን አስከትሏል፡፡

 

ደኅንነት እና ሽብርተኝነት

 

በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ግጭቶች ለዓለም አቀፍ ደኅንነት በተለይም ከሽብርተኝነት አንፃር አንድምታቸው ከፍ ያለ ነው፤ እንደ አይ ኤስ አይ ኤስ ያሉ አሸባሪ ቡድኖች  ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ ዓለም አቀፍ ስጋት ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ ክልሉ በርካታ መሰል የሽብር ቡድኖች ማዕከል ሲሆን የአካባው አለመረጋጋት የጦር መሣሪያ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም የአክራሪነት መራቢያ አድርጎታል፡፡

 

ሰብዓዊ ቀውሶች

የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭቶች ከባድ ሰብአዊ ቀውሶችን አስከትለዋል፡፡ ለምሳሌ የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ መፈናቀል እና ስቃይን አስከትሏል፡፡ የስደተኞች ቀውስ የጎረቤት ሀገሮችን ብቻ ሳይሆን ለደረሱት ሰብአዊ ቀውሶች ድጋፍ ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ እንዲሁም የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችንም የሚፈታተን ነው፡፡

ባሕላዊ እና ታሪካዊ ተፅዕኖ

በክልሉ የበለፀጉ ባሕላዊ ቅርሶችም የግጭት ሰለባ ሆነዋል፡፡ በሶሪያ፣ ኢራቅ እና የመን ያሉ ታሪካዊ ቦታዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ይህም ከፍተኛ የባሕል ቅርስ መጥፋትን አስከትሏል፡፡፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here