የሁለት ፈረሶች እሽቅድምድም

0
154

በያዝነው የውድድር ዘመን የስፔን ላሊጋ ፉክክር የሁለት ፈረሶች ግልቢያ ብቻ ሆኗል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት 25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በሁለቱ ኃያላን ክለቦች መካከል የሚታየው ታክቲካዊ ፍልሚያ እና የነጥብ ልዩነት ላሊጋውን እንደ ተከታታይ ልብ አንጠልጣይ የኔትፍሊክስ ፊልም አጓጊ አድርጎታል።  ይህም የሊጉን ፍጻሜ ለመተንበይ አስቸጋሪ አድርጎታል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የካተለኑ ክለብ ባርሴሎና በ61 ነጥብ እየመራ ይገኛል:: በባርሴሎና ጆሮ ተጠግቶ ሲተነፍስ የቆየው ሪያል ማድሪድ  መሪነቱን  ድጋሚ ከተረከበ ውሎ ሳያድር ተነጥቋል። የዋና ከተማዋ ክለብ  ሪያል ማድሪድ በኦሳሱና መረታቱን ተከትሎ ነው መሪነቱን ለተቀናቃኙ ያስረከበው:: ኮከብ ግብ አግቢነቱንም  ኪሊያን ምባፔ በ23 ግብ እየመራ ሲሆን የማዮርካው ቬዳት ሙሪኪ ደግሞ በ16 ግብ ይከተላል።

የ2025/26 የስፔን ላሊጋ ገና ከጅምሩ በጉጉት የተጠበቀ ነበር፤ ሜዳ ላይ የታየው ግን ከግምት ውጭ የሆነ ድራማ፣ ታክቲካዊ ለውጥ፣ ያልተጠበቁ የክለቦች አቋም መውረድ እና መውጣት ነበር። በቀጣይ በአውሮፓ መድረክ እና በሀገር ውስጥ ዋንጫዎች የሚኖረው የጨዋታ መደራረብም በቡድኖች አቋም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። ይሁን እንጂ የተጫዋች ጉዳት፣ የካርድ ቅጣቶች እና የተጫዋቾች ድካም በወሳኝ ሰዓት የዋንጫውን አቅጣጫ ሊቀይሩ እንደሚችል ይገመታል።  የሪያል ማድሪድ ጋላክቲኮስ ስብስብ፣ የባርሴሎና የወጣቶች አብዮት እና የአትሌቲኮ ማድሪድ ያልተጠበቀ አካሄድ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ልዩ አድርጎታል።

ሁለቱ ኃያላን ክለቦች  እየተፈራረቁ እየመሩ የሚገኙበት  የስፔን ላሊጋ በ25ኛ ሳምንት የላሊጋ መርሐ ግብር ከሜዳቸው ውጪ በጂሮና ሁለት ለአንድ የተሸነፉበት አጋጣሚ የሊጉን መሪነት ለተቀናቃኛቸው አሳልፈው እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። ሃንሲ ፍሊክ የገነቡት ይህ ቡድን በ25 ጨዋታዎች ብቻ 67 ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ በማሳረፍ በአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች አስፈሪ የፊት መስመር ያለው መሆኑን የማርካ ዘገባ ያስነብባል። ይህ የግብ ብዛት የሚያሳየው ቡድኑ ያለውን የመስመር እና የመሀል ሜዳ ጥምረት ጥንካሬ ነው። ቡድኑ በየጨዋታው በአማካይ ከሁለት ግቦች በላይ ማስቆጠሩ ተጋጣሚዎች በካምፕኑም ሆነ በሜዳቸው ባርሴሎናን መግጠም ምን ያህል እንደሚያስፈራቸው ማሳያ ነው።

በ2025/26 የውድድር ዘመን ባርሴሎና በቋሚ አሰላለፉ ውስጥ ከስድስት በላይ ከላማሲያ አካዳሚ የወጡ ተጫዋቾችን (ጋቪ፣ ኩባርሲ፣ ያማል፣ ፎርት እና ሌሎች) በማሰለፍ የሊጉን ክበረወሰን ሰብሯል። በመጀመሪያው ዙር ኤል ክላሲኮ ባርሴሎና ከሜዳው ውጭ ሪያል ማድሪድን ሁለት ለአንድ ያሸነፈበት ጨዋታ የሊጉን አቅጣጫ የቀየረ ወሳኝ ቅጽበት ነበር።

የካታላኑ ክለብ ምንም እንኳን የፊት መስመሩ ብዙ የግብ ናዳዎችን በተጋጣሚዎቹ ላይ ቢያወርድም የተከላካይ ክፍሉ ግን አልፎ አልፎ በሚሰራቸው ስህተቶች ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። የኋላ ክፍሉ  በ25 ጨዋታዎች 25 ግቦች ተቆጥረውበታል፤  ይህም በየጨዋታው በአማካይ አንድ ግብ እንደተቆጠረበት የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያመለክታል:: እናም ክለቡ ለዋንጫ በሚያደርገው ጉዞ የኋላ ክፍሉ ትልቅ እንቅፋት ሊሆን ይችላል- የማርካ ግምት ነው።

ሎስብላንኮቹ አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶን በማሰናበት አልቫሮ አርቤሎአ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ከቀጠሩ በኋላ ወቅታዊ አቋሙ  ከባርሴሎና በተሻለ አስፈሪ እና የተረጋጋ ክለብ ይመስላል። ቡድኑ ያለፉትን ስምንት የላሊጋ ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ   ትልቅ ለውጥ ላይ ይገኛል። ዘንድሮ የሪያል ማድሪድ  ጥንካሬ የመጣው ከፊት መስመሩ ሳይሆን  ከኋላ ክፍል አደረጃጀቱ ነው። የተከላካይ ክፍሉ በ25 ጨዋታዎች 21 ግቦች  ብቻ ነው የተቆጠረበት:: ይህ ቁጥራዊ መረጃም ነጭ ለባሾችን በላሊጋው ቀዳሚ የማይበገሩ የኋላ ክፍል  ባለቤት አድርጓቸዋል።  በዘንድሮው የውድድር ዘመን የሪያል ማድሪድ የፊት መስመር ጉዳይ ብዙዎችን ቢያነጋግርም አልቫሮ አርቤሎአ የገነበው ቡድን ውጤታማ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛለ።

ብራዚላዊው ታዳጊ ኤንድሪክ በቂ የመሰለፍ እድል ለማግኘት እና ልምድ ለመቅሰም ወደ ፈረንሳይ ሊግ በውሰት ማምራቱን ተከትሎ የፊት መስመሩ ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ በኪሊያን ምባፔ እና በቪኒሽየስ ጁኒየር ላይ ወድቋል። ይህ ጥምረት በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ጥያቄዎች ቢነሱበትም አሁን ላይ ግን በሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታዎች ላይ እንደታየው  እጅግ አስፈሪ እና ጨራሽ ሆኗል። የሎስ ብላንኮዎቹ የፊት መስመር በድምሩ 54 ግቦችን አስቆጥሯል። ሪያል ማድሪድ ከባርሴሎና በ11 ግቦች ያነሰ ቢሆንም ወሳኝ በሆኑ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ግን እንደማይቸገር ተመልክተናል።

ሪያል ማድሪድ በግማሽ የውድድር ዘመኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግቦችን ቢያስቆጥርም የተከላካይ መስመሩ መሳሳት ግን ዋጋ አስከፍሎታል። በተለይም በህዳር ወር በሜዳቸው ሳንቲያጎ በርናቤው ከቫሌንሲያ ጋር ያደረጉት እና ሦስት አቻ የተጠናቀቀው ጨዋታ የአሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶን የእንጀራ ገመድ የቆረጠ ሲሆን ቡድኑ ኮከቦችን በመሰብሰብ ብቻ እንደማይሳካለት  ማሳያ ነበር።

ባርሴሎና በከፍተኛ የግብ ልዩነት ተጋጣሚዎችን እያሸነፈ የካቲት ወር ላይ ደርሷል። ነገር ግን የባርሰሎና ከፍተኛ የሆነ የማጥቃት ፍላጎት የኋላ ክፍሉን ለመልሶ ማጥቃት እያጋለጠው ይገኛል።  ሪያል ማድሪድ  ደግሞ ውጤት ላይ መሰረት ያደረገ (Pragmatic) የሆነ አካሄድን በመከተል ጨዋታዎችን በጠባብ ውጤትም ቢሆን እያሸነፈ መጓዝን መርጧል። ይህ የአጨዋወት ስልቱም በውድድር ዘመኑ መጨረሻ አካባቢ በሚፈጠረው ጫና ወቅት ትልቅ ጥቅም ሊሰጠው ይችላል ተብሏል። የሊጉ ዋንጫ መዳረሻ የሚወሰነው በኤል ክላሲኮ እና በቀሪዎቹ የሊጉ ፈታኝ ጨዋታዎች ነው።

ዋንጫውን ለማንሳት ከሚደረገው ፉክክር ባልተናነስ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎን ለማግኘት የሚደረገው ፉክክርም እየጠነከረ መጥቷል። ፣ቪያሪያል፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ቢትስ ትንቅንቅ ውስጥ ገብተዋል:: በተለይ የሁለቱ ኃያላን ክለቦች ተፎካከሪ የሆነው አትሌቲኮ ማድሪድ በ25 ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ አቻ መውጣታቸው እና በአምስት ጨዋታዎች  መሸነፋቸው ከዋንጫ ፉክክር በ13 ነጥብ እንዲርቅ አድርጎታል። የዲያጎ ሲሚኒ ልጆች በተለይም ወሳኝ በሆኑ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ የመጣል ልማድ ተጠናውቷቸዋል። እናም አሁን ላይ የያዙት አራተኛ ደረጃ አስተማማኝ አይደለም::ቪያሪያሎች በተመሳሳይ በ48 ነጥብ አትሌቲኮን እግር በእግር እየተከተሏቸው ነው።

ዲያጎ ሲሞኒ ሁሌም በጥብቅ መከላከል የሚታወቁ አሰልጣኝ ናቸው። የዘንድሮው  አትሌቲኮ ማድሪድ ብዙዎችን አስገርሟል።በ2025/26 የውድድር ዘመን ግን  አትሌቲኮ ማድሪድ “ቶታል ፉትቦል” የሚመስል አጨዋወት እየተጫወተ ይገኛል። ጁሊያን አልቫሬዝን ወደ መሃል አጥቂነት በመቀየር እና ግሪዝማንን ወደ ኋላ የመለሱት ሲሞኒ አትሌቲኮን የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ እንዲሆን አስችለውታል።

ቪያሪያል የዘንድሮው የላሊጋ አስገራሚ ክለብ ነው ማለት ይቻላል። 47 ግቦችን ከተጋጣሚ መረብ ላይ በማስቆጠር ከአትሌቲኮ ማድሪድ የተሻለ ወቅታዊ አቋም እንዳለው አስመስክሯል:: በተለይም በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ ለየትኛውም ቡድን ፈተና እንደሆኑ የማርካ መረጃ ያስነብባል። ቪያሪያል እና አትሌቲኮ ማድሪድ ለሻምፒየንስ ሊግ ደረጃ የሚያደርጉት ፉክክር እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ የሚቀጥል ይመስላል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሪያል ቤቲስ እና ኢስፓንዮልም ዘንድሮ የሊጉ ድምቀት የሆኑ ክለቦች ናቸው። የዘንድሮው አስደናቂ ክለብ ኢስፓንዮል ነው። ብዙ ጊዜ በወራጅ ቀጣና ወይም በታችኛው ሊግ የምናውቀው ኢስፓንዮል ዘንድሮ በ35 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ለደጋፊዎቹ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል። ሪያል ቤቲስ በ42 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወቅታዊ አቋሙ ግን አስተማማኝ አይደለም።

በክረምቱ የዝውውር ወቅት ኒኮ ዊሊያምስ አትሌቲክ ቢልባኦን ይለቃል ተብሎ ሲጠበቅ እንደነበር አይዘነጋም፤  ከወንድሙ ኢናኪ ዊሊያምስ ጋር የፈጠሩት ጥምረትም የላሊጋው ድምቀት ሆኗል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ቢልባኦ እስካሁን በሜዳው ሳን ማሜስ  አንድም ጨዋታ አልተሸነፈም። በስፔን እግር ኳስ ትላቅ ስም ያለው ቫሌንሺያም በያዝነው የውድድር ዘመን ከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ ገብቷል።

ትልቅ የመውረድ አደጋ የተጋረጠበት ቫሌንሺያ ከወራጅ ቀጣናው በሁለት ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው የሚርቀው። ክለቡ በሜዳው ሆነ ከሜዳው ውጪ የሚያሳየው አቋም ደካማ ነው፤ ክለቡ በያዝነው የውድድር ዓመት በሁሉም የሜዳ ክፍል እጅግ ተዳክሞ ተስተውሏል:: ራዮ ቫዬካኖ፣ ሌቫንቴ እና ሪያል ኦቪዬዶ ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በቀሪ መርሐ ግበሮች መሻሻል ካልቻሉ በቀጣይ የውድድር ዘመን በላሊጋው የማንመለከታቸው ይሆናል። በአጠቃላይ የ2025/26 የላሊጋ የውድድር ዘመን ገና ብዙ ያልታዩ ድራማዎችን እንደሚኖሩት ይጠበቃል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here