መጨረሻው        

0
302

     ልቦለድ

– – – መብራቱ ሲበራ ከሳሎኑ በስተግራ ጠርዝ ያለው ሶፋ ላይ አቤሜሎክና ሩት ዳርና ዳር በጀርባቸው ጋደሞ ብለዋል፡፡እግራቸው ተነባብሯል፡፡ ከጅፓሱ እየተሰረቀረቀ የሚወጣው የአስቴር አወቀ ዜማ ከሶፋውም ከቴሌቭዥኑም በላይ ለሳሎኑ ውበት ዘርቶበታል፡፡

የኮሲን ባህር ዛፍ አትንኩት ጥላ ነው

የልጅነት ፍቅር ማርሸት ወለላ ነው።

ምን አይነት ምትሃተኛ የሆነ ድምፅ ነው ግን? ለየትኛውም ሙዚቃ ለዜማውም ለግጥሙም ህይወት እኮ ነው የምትዘራበት፡፡ አንዳንዴማ አስቴር ለሙዚቃ ተፈጠረች ወይም ሙዚቃ ለአስቴር ተፈጠረ የሚለውን ሁሉ መልስ የሌለው ጥያቄ ይሆንብኛል፡፡

ይሄ ዘፈን ደግሞ እንደ እኔ የአፍላነት የህይወት ገፁ በፍቅር ታሪክና ትዝታ  ለተሞላ ልዩ ትርጉም አለው የልጅነት ፍቅር እንደምን ይረሳል  እንዴት ይዘነጋል? በእርግጥ የብዙዎችን የልጅነት ፍቅር የሆነ የማይሽር ጠባሳ ነገር ጥሎብን አልፎ ይሆናል፡፡ ሩቅ አስበን እውነታው ግን ከአጭር ልብወለድ አጥሮ ተጠናቆም ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ እስከህመሙ ትዝታው ደስ ይል ይመስለኛል፡፡

ለዚህ የቴዎድሮስ ካሳሁን ሙዚቃ ስሜቴን የሚገልፅልኝ መስሎ ይሰማኛል፡፡

‘’ደስ የሚል ስቃይ’’ አይደል ያለው?

ከሚገባሽ በታች ከምችለው በላይ

እስኪወድሽ ልቤ ደስ በሚል ስቃይ

ፍቅር ካንቺ ይዞ እየደጋገመኝ

ብወድሽ ብወድሽ አልሰለች አለኝ፡፡

እያለ ይወርድና

ይሄን ስቃይ በዚች አለም

የሚገልፀው ቃላት የለም ይለናል፡፡

እውነት ነው የፍቅርን ስቃይ ቃላት አይገልፀውም፡፡ ብቻ የሆነ የሚያም ግን ደግሞ ደስ የሚል ስቃይ አለው፡፡ምናልባት ግን በፍቅር በጣም የተጎዳችሁና ትላንትን ማስታወስ የማትፈልጉ ካላችሁ በሰው ቁስል . . . እንዳይሆንብኝ፡፡

ነገሩ ድምፆዊ ደሣለኝ መላኩ “ምኔ” በተሰኘው ሙዚቃው ለፍቅር ሲባል የሚከፈል ዋጋን በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት አመስጥሮ ገልጾታል።

ኧረ ለምኔ ኧረ ለምኔ

መከራ እያየ ፍቅር ስለ እኔ

ለፍቅር ሲባል የጠፋ ነፍስ

በ3ኛው ቀን የሚመለስ

ህይወት ከሆነ የፍቅር ሞቱ

እኔንም ወስዶ ይስቀለኝ ፊቱ።

ድምፃዊው በዚህ ሙዚቃው ለፍቅር የሚከፈል ዋጋን ትርጉም ይነግረናል።

ለማንኛውም ሙዚቃው ቀጥሏል የአስቴር ማለቴ ነው።

የኮሲን ባህር ዛፍ አትንኩት ጥላ ነው

የልጅነት ፍቅር ማርሸት ወለላ ነው

መደረብ እሳት ነዶ ሰማዩን አይፈጅም

አይ እኔ አላገኝህም ፍቅር አልከጅልም

አይተከል ለልብህ በምር በመጫኛ

አንተም ባለትዳር እኔም የሰው እጮኛ።

አሌክስ አሎምፖያ ነው አይደለ

“ለዘላለም ትኖሪ ይመስል” የሚለው ሙዚቃው ላይ

አሸቅበሽ ምችው ሰማዩን በእንቧይ

የልጅነት ወዳጅ ባል አይሆን ወይ

ያለው? እውነቱን እኮ ነው ግን ለምንድን ነው የልጅነት ፍቅር ትዳር የማይሆነው? አይደግ ተብሎ ተረግሞ ይሆን? ስለ እዚህ ጉዳዩ የሆነ የተነገረ አፈ ታሪክ ነገር የለም ግን? ለማንኛውም በስንቱ አርሲኩርሲ ርዕሰ ጉዳዮች ሳይቀር የመመረቂያ ፅሁፍ ጥናቶች ይሰሩ የለ ከሼልፍ የማይዘል ጥናት በበዛበት ሀገር ምን አለበት በዚህ ርዕስ ጉዳይ ዙሪያ ማለቴ  ‘’የልጅነት ወዳጅ ባል ለምን እንደማይሆን’’ የሚለው ላይ ጥናት ቢሰሩልን። አዎ ቢያንስ እኛ ምክንያቱን ለማወቅ ያህል ቀጣዩ ትውልድ ደግሞ የእኛ እጣ ፈንታ እንዳይደርስበት ይጠቅም ይሆናል ማን ያውቃል፡፡በነገራችን ላይ የልጅነት ፍቅርን ወደ ትዳር ያሳደጉ እድለኞች መኖራቸውን ዘንግቼ አይደለም እያወራሁ ያለሁት ስለብዙሀኑ ስለሆነ ነው፡፡

ለማንኛውም የሳሎን ቤቱን ጉዳይ ዘነጋሁት አይደል፡፡ ነገሩ ይሄን ሁሉ ያስቀባጠረኝ፣ የቆሰቆሰኝና የነካካኝ የአስቴር ሙዚቃም አልቆ ኤፍሬም ቦታውን ተረክቧል፡፡

ሌላ ትዝታ እንዳልቀሰቅስ በሚል ሙዚቃውን ግን አልገግራችሁም፡፡

አቤሜሌክም ሩትም ሞባይላቸው ላይ አፍጥጠዋል፡፡ ሁለቱም በራሳቸው ፊና ውስጥ ጭልጥ ብለው የሄዱ ይመስላሉ፡፡ ሙዚቃውን ጭምር እያዳመጡት አይመስልም፡፡ ሩትማ ጭራሹኑ በአንድ ጆሮዋ ኤርፎን አድርጋለች፡፡ የዲጅታል ሚዲያው ነገር እኮ “አባንከና” ባይ አጥቶ እንጅ እያሳሳቀ ወደማንወጣው ጣጣ ውስጥ እየዘፈቀን አይመስላችሁም? እውነት ለመናገር እኔ ያሳስበኛል፡፡ ባህር ውስጥ አሳ ለመፈለግ ገብተን በአዞ የመበላት ያህል ነው ነገሩ የሚመስለኝ፡፡ብዙዎቻችን በአንድ ጣራ ውስጥ እያኖረን ግን ተነፋፍቀናል፡፡ እውነቴን ነው ማውራት እኮ ትተናል፡፡ሁላችንም እስክሪናችን ላይ ተጥደናል፡፡ እንደ ባቢሎን ቋንቋችን ሳይደበላለቅ ይቀራል ብላችሁ ነው? ደግነቱ ወሬ ስላቆምን፣ ዝም ስለተባባልን የቋንቋችን ስለመደበላለቁም ስላለመደበላለቁም ማወቅ አንችልም ቢደበላለቅም አያስጨንቀንም ምክንያቱም እያወለን አይደለንም፡፡ ወሬዬን ልቀጥል ነበር ጎሽ አቤሜሌክ የእኔን ወሬ የገታ የሳሎኑንም የሙዚቃ ጩኸት የሰበረ የእነሱንም ኩርፊያ የመሠለ ዝምታ የገለጠውን የመጀመሪያ ድምጽ አወጣ፡፡ ሩት ግን አልሰማችውም፡፡ የጅፓሱን ድምጽ         አጠፋውና በድጋሜ “ፍቅር” አለ

ሩት “ጠራኸኝ?”

አቤሜሌክ ”አዎ በእናትሽ አንዴ አድምጭኝ” አለና ከተጋደመበት  ተነስቶ ሶፋው ላይ ተስተካክሎ ተቀመጠ፡፡ እሷ ግን ትኩረቷን እዛው ስልኳ ላይ እንዳደረገች ነች፡፡

አቤሜሌክ ”ፍቅር ስወድሽ አንዴ አድምጭኝ ባይሆን አንብቤ ስጨርስ የማደርግልሽን አታውቂም ደግሞ በእርግጠኝነት ትወጅዋለሽ” አላት።

ሩት “ምንድነው እሱ ልብ ወለድ እንዳይሆን?” አለችው ኤጭ በሚመስል ስሜት፡፡

ፀሀፊዎች እኮ በዚህ ጉዳይ በጣም ነው የሚያሳዝኑኝ። ስንት ተጨንቀው እና ተጠበው ከአርያም አርያም፣ ከአፅናፍ አፅናፍ፣ አንዴ ከምድር አንዴ ከሰማዩ በምናባቸው ወጥተውና ወርደው፣ ኳትነውና ባዝነው ከራሳቸው ጋር ስንት ትግል ገጥመው፣ ግብ ግብ ፈጥረው፣ የሺ አመት ያህል ፅንስን አምጠው ወልደው እስቲ የአብራኬን ክፋይ እዩልኝ ብለው ሲለምኑ አስባችሁታል፡፡

አንድ ሁለት ገጣሚና ደራሲ ጓደኞች አሉኝ፡፡ ከሚፅፉት ሃሳብ ይልቅ የፃፉትን የሚያነቡለት ጆሮ የሚሰጣቸው ሰው ነው የሚቸግራቸው፡፡

አቤሜሊክ ጠጋ ብሎ እየደባበሳት “ደስ የሚል ግጥም ነው ውዴ” ብሎ ከጆሮዋ ላይ ያለውን ኤርፎን አነሳው፡፡

ሩት “ረዥም ካልሆነ እሺ ቀጥል”

አቤሜሌክ “ረዥም አይደለም ብቻ አንዴ ጆሮሽንም ልብሽንም ቀልብሽንም ስጭኝ” ብሎ ስልኩን ለንባብ እያዘጋጀ ጉሮሮውን ጠራረገ፡፡

ርዕሱ “ሁሉም ያንች ሎሌ ይላል” አለ

ሩት “እሺ ቀጥል” ብላ ለማድመጥ እንደመደላደል አለች፡፡ ስልኳንም ከጎኗ ሶፋ ላይ አኖረችው፡፡

በነገራችን ላይ ሩት ፀይም ድንቡሽቡሽ ደም ግባት ያላት ልጅ ከመሆኗ ውጭ ይሄ ነው የሚባል የሚጠቀስ ቁንጅናም ውበትም የላትም፡፡ በተቃራኒው ደራሲና ገጣሚ እጮኛዋ አቤሜሌክ ፀይም መልከ መልካም ወንዳወንድ ከመሆኑም በላይ በግቢ ቆይታቸው በብዙ ሴቶች ተወዳጅ አይነት ልጅ ስለነበር ሩት የእሷ ሆኖ ጭምር የእርግጠኝነት ስሜት አይሰማትም ሲበዛ ትቀናለች፡፡

ለማንውም አቤሜሊክ ግጥሙን ማንበብ ጀምሯል፡፡

ውዴ እኔ ግን ሲመስለኝ

እግዜር ሲፈጥር አንችን

አንድ መርህ ሽሯል

ብዙ ህግን ጥሷል

ፍፁም ህያው አምላክ ላንች ሲል አዳልቷል

ይህ ባህሪው ባይሆንም እኔ ግን መስሎኛል

ስለሚፈራ እንጅ ደግሞም ሁሉም ያምራል

ምንም ሚስጢር የለው ውበትሽ ያወራል

እንደተዳላልሽ ቆሞ ያሳብቃል።

እኔማ ሲመስለኝ

ፀሐይና ኮከብ ባንች ነው የሚያምሩት

በመልክሽ ተገልጿል የጨረቃም ድምቀት

ሜርኩሪና ቬነስ ማርስና ጁፒተር

ያንች ሎሌ ናቸው ተጨምራ ምድር።

ለጣትሽ ቀለበት ለቁንጅናሽ ክብር

ሳተርንን ሰራልሸ በድንቅ ተዓምር

በውብ ቀለበቶች እጅጉን በሚያምር

ዩራኖስ ኔፕቱን ትንሿም ፕሉቶ

የሰራቸው ናቸው እግዜር ላንች ብሎ

ውዴ እኔ ግን ሲመስለኝ – – –

ብሎ  ሊቀጥል ሲል ሩት “አይበቃም?’’ አለች ከተጋደመችበት ተነስታ ቁጭ እያለች::

አቤሜሌክ “እየጨረስኩ ነው ትንሽ ነው የቀረኝ::”

ሩት “በቃ ቢገባህ ከዚህ በላይ የቀረህ እኮ ሳጥናኤል አዳምና ሔዋንን እግዜር እፀ በለስህ አትብሉ ያላችሁ እንዳላቸው . . .”

አቤሜሌክ ንግግሯን አቋረጣት “አትጨርሽ የማይገናኝ ነገር ልታገናኝ አትሞክሪ እኔ እንደዚህ አይነት ንፅፅር ውስጥ አልገባሁም፤ ይልቁንም የአምላክን ድንቅ የእጅ ስራ ውጤት ነው በብዕሬ እያደነኩም እየመሰከርኩም ያለሁት።”

ሩት “አይደል? በጣም እንጅi እኔ ግን ያልገባኝ አንዴ በልብ ወለድ አንዴ በግጥም እንዲህ እያንቆለጳጰስክ የምታሽሞነሙናት ሴት ማነኝ አለች?”

 

አቤሜሌክ “ምን ማለት ነው?”

ሩት “ግልፅ ነው ይህችን ሴት ደጋገምካት። ዛሬ ደግሞ በፅጌረዳም፣ በአልማዝና በእንቁም መመሰሉ አነሰባትና ጭራሽ ከፕላኔቶቹም አናት ላይ አወጣሀት ወቼ ጉድ ምን ታደርግ የኔ ውበት ገረጣብሃ!!!” ፊቷ እየተቀያየረ ነው::

አቤሜሌክ  “ተረጋጊ ሴትዮ!”

ሩት “ይች ነችና ልጅቱ ጭራሽ እኔ ሩትን ሴትዮ?” ከመቀመጫዋ ተነሳች፤ የምታረገው ግራ ገባት እንደመወረጫጨት እያለች . . . አቤሜሌክ ተነስቶ ይዞ ለማስቀመጥና ለማረጋጋት ቢሞክርም እሷ ግን የሆነ ሳትናገረው በውስጧ ስታብላላው የከረመችው የታፈነ ብስጭት እንደሆነ በሚያሳብቅ ሁኔታ ሁለነገሯ ከመቅፅበት ተቀያየረ፤ የታፈነው እውነት ገንፍሎ ወጣባት::

“ልቀቀኝ!” አለችው ለቀቃት።

“ምን ሆነሽ  ነው? ግን ምን ተፈጥሮ ነው? በፍፁም እንዲህ ሆነሽ አታውቂም!”

ሩት “አዎ አላውቅም ዝምታም ልክ አለው፤ ትዕግስትም ልክ አለው፤ አሁን ግን ከአቅሜ በላይ ሆነ። እኔ ሩት ምንም የማላውቅ አሻንጉሊት ነው እንዴ የምመስልህ?” ፊት ለፊቱ እንደ አራስ ነብር ተገታትራ ቆመች::

“ቆይ ግዴለሽም ተረጋጊ ምን ሆነሽ ነው?”

“ትሠማለህ ይህች ሁሌ እየተነሳህ የምትመሰጥባት ቋንቋ እያጠረህ ቋንቋ ከባጥ ከቆጡ የምትበደርላት የምታሽሞነሙናት ሁሉ ነገርህን የተቆጣጠረችው ሸርሙጣ ሴት ማናት?!”

“ኧረ በስመአብ በይ ስለየትኛዋ ሴት ነው የምታወሪው? ደግሞ ብለሽ ብለሽ በምናባዊ ገፀ ባህሪ እየቀናሽና እየተናደድሽ ባልሆነ?”

“እሺ ባክህ ምናባዊ ነው ያልከው? ገፀ ባህሪያት የገሀዱ አለም ሰዎች ፍጡራን ወኪሎች የዚህ አለም እውነታ ተናጋሪ አንደበቶች ናቸው ገለመሌ ትሉ የለም እንዴ? ነው ለዚህችኛይቱ ወይዘሮህ ይሄ አይሰራም?”

“ግዴለሽም ተይው በቃ ስትረጋጊ በሰከነ መንፈስ ብናወራ ይሻላል፤ አሁን ጥሩ ሙድ ላይ አይደለሽም” ብሏት ወሬውን ሊያቆመው ቢሞክርም ሩት ግን ልትረጋጋ አልቻለችም::

“ምነው ነገሩ ሲነቃብህ ልታድበሰብስ እየሞከርክ መሆኑ ነው? እኔ ግን ማንነቷን ሳትነግረኝ አልፋታህም እሺ!” አለችው አሁንም ወደ እሱ እየተጠጋች፤ አይኗን እያጉረጠረጠችበት::” ይሄኔ አቤሜሌክም ትእግስቱ ተሟጠጠ።

“ይብቃሽ! ትሰሚያለሽ?! ይሄ ድርሰት ነው! ድርሰት የማይገባሽ ከሆነ ደግሞ አንችን ከዚህ በላይ የማስረዳበት አቅም የለኝምና አሁን ልትተይኝ ትችያለሽ?!” አላት።

“አልተውህም! እኔን ለማስረዳትማ እንዴት አቅም ይኖርሀል?! እሷን በማሽሞንሞን ቃላቱን ሁሉ ጨርሰኸው!”

“የራስሽ ጉዳይ!!”

“ምን አልክ የራስሽ ጉዳይ?”

“አዎ የራስሽ ጉዳይ” አላት አቤሜሌክ::

“አንተ ራስህ የራስህ ጉዳይ! ትሠማለህ ሲጀመር ደራሲ፣ ገጣሚ ምናምን የምትባሉ ሰዎች ፅሁፍ መደበቂያችሁ ዋሻና ጭምብላችሁ ነው። እያንዳንዷ እያሽሞነሞናችሁ የምትፅፏት ሴት በህይወታችሁ ውስጥ እስከጫማዋ የገባች የምትገለሙቱባት ውሽማችሁ ነች። ትወናህን እዛው ሌላ ሴት ላይ ተውን እሺ!” ብላ ስልኳንና ቦርሳዋን አነሣነች::

“አልሽ?!”

“አልኩ! ትወናህን ከሌላ ሴት ጋር ቀጥል! እኔ ጋር እዚህ ላይ ብንጨርስ የተሻለ አይመስልህም?!”

“እና የእኔና ያንተ ህይወት ተውኔት ነው እያልሽኝ ነው?”

“ አደረከው!… ባይሆን ትራጀዲ ይሁን ኮሜዲ ዘውጉን ካንተ ከተውኔቱ ደራሲ ልጠይቅህ!”

አቤሜሌክ በጣም ተናዷል:: “ካረግሽውማ ቧልት ብትይው አይሻልም?!”

“ልክ ነህ! በተለይ ላንተ የምታስታውሰው አንድም ጠብታ ትዝታ ያልነበረው ተራና ከንቱ የአብሮነት ቆይታ ስለነበረ ቧልት የሚለው ይገልፀዋል። ህመሙ ለእኔ ነው። ለማንኛውም የምናብህን  ሴት ወደ ቤትህ አስገባት፤ እሷም ሌላ ተውኔት እስኪፃፍባት:: የእኔንና የአንተን ግን እንዳይንዘላዘል እዚህኛው ምእራፍ ላይ መውጫውን ‘እቃቃ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ፤ ተፈፀመ’ ብለህ ፃፍበትና ጨርሰው!” ብላው ከቤት መውጣት ስትጀምር እሱም፣ “ልክ ነሽ! አንችም ስልክሽ ላይ እኔም ድርሰቴ ላይ ስለነበርን ‘ሌሊቱን አሳልፈን ቀን አብረን አልዋልንም’ እንዳለው ድምጻዊው አብረን ብንከርምም አብረን አልነበርንምና በመኖርሽም በመሄድሽም መካከል ያለው ልዩነት የቃል ብቻ ስለሆነ አትሂጅ አልልሽም ሂጅ፤ መንገዱን ጨርቅ ያርግልሽ!” አላት። እሷ ከቤት እየወጣች እሱ ወደ ጓዳ እየገባ የመድረኩ መጋረጃ ተዘጋ። እያየነው የነበረው “ውሽማ” የተሰኘው ቲያትር የመጨረሻው ትዕይንቱን በዚህ መልክ አድርጎ ተፈጸመ። እኛም አዳራሹን ለቅቀን ወጣን።

 

(በሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ))

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here