በዓላት እና ማሕበራዊ ትስስራቸው

0
250

መግቢያ

ኢትዮጵያ በርካታ የዓለምን ቀልብ የሚስቡ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላት የሚከበርባት ድንቅ ሀገር እንደሆነች ብዙዎች መስክረውላታል። ስለሆነም በሀገራችን በየጊዜው የሚከበሩ ክብረ በዓላት በዓለም የቅርስ መዝገብ በመስፈር ላይ ናቸው። ለአብነትም የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ይህ መሆኑ ደግሞ የአደባባይ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታይ ያደርገዋል። ክብረ በዓላቱ ማኅበረሰብን የሚያገናኙ በትውልድ መካከል ያለውን ቁርኝት የሚገነቡ መሆናቸው ደግሞ እጅግ አስደናቂ ያደርጋቸዋል።

በዓላት የሰው ልጆች ከመደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴያቸው ወጣ ብለው የሚያርፉባቸው፣ ደስታቸውን የሚገልጹባቸው እና መንፈሳዊ ወይም ባሕላዊ ግዴታዎቻቸውን የሚወጡባቸው ልዩ ቀናት ናቸው። በመሆኑም የበዓላት ፋይዳ ከመብላት እና መጠጣት ወይም ከእረፍት ባሻገር ትልቁ ቁምነገር “ማሕበራዊ ትስስርን” በማጠናከር ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። በዓላት የቤተሰብን፣ የጓደኝነትን እና የአብሮነትን ገመድ የሚያጠብቁ ወሳኝ ኩነቶች ናቸው።

በዓላት የመገናኛ እና የመሰባሰቢያ መድረኮች ናቸው።

በዘመናዊው ዓለም እንደ ሞባይል፣ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም እና መሰል ቴክኖሎጂ ዉጭ የሥራ እና የኑሮ ውጣ ውረድ ቤተሰብን እና ወዳጅ ዘመድን አራርቆት ይገኛል። በዓል ሲመጣ ግን በሩቅም በቅርብም ያሉ ቤተሰቦች በአንድ ጣራ ስር ይሰባሰባሉ። በተለይም በኢትዮጵያ ባሕል ልጆች ወደ ወላጆቻቸው ቤት ሄደው የመገናኘታቸው ልማድ የቤተሰብን ፍቅር ያድሳል። አብሮ መብላት (ማዕድ መጋራት) በራሱ ትልቅ ማህበራዊ ትርጉም አለው። በአንድ ማዕድ ዙሪያ መቀመጥ የልብን ለማውራት፣ ናፍቆትን ለመወጣት እና የቤተሰብን ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል። ይህ የመሰባሰብ ባሕል የብቸኝነት ስሜትን በማጥፋት የስነ-ልቦና ጤንነትን በመጠበቅ ደስታን ይፈጥራል።

የበዓላት ማህበራዊ ፋይዳ ይቅርታ እና እርቅ ነው።

በዓላት የሰላም እና የፍቅር ተምሳሌት ናቸው። በሰዎች መካከል የተፈጠሩ ቅሬታዎች፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች የሚፈቱት ብዙውን ጊዜ በዓላትን ተገን በማድረግ ነው። “እንኳን አደረሳችሁ” የሚለው ቃል የተዘጋን ልብ የመክፈት ኃይል አለው። ሰዎች ያለፉትን ስህተቶች ይቅር በመባባል አዲስ ምዕራፍ ይጀምራሉ። ይህም ማህበረሰቡ ከቂም በቀል የጸዳ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ሌላው የበዓላት ማህበራዊ ፋይዳ  መረዳዳት እና አብሮነት ነው።

በዓላት ሃይማኖታዊም ሆኑ ባሕላዊ ያለው ሰው ለሌለው ወይም ላጣ ሰው እንዲያካፍል ያስገድዳሉ። የተቸገሩትን መርዳት፣ የታመመን መጠየቅ እና የጎደለውን መሙላት የበዓላት አንዱ አካል ነው። ለምሳሌ በክርስትናም ሆነ በእስልምና በዓላት ወቅት ድሆችን መመገብ እና ዘካ ማውጣት እንደ ትልቅ መንፈሳዊ ግዴታ ይታያል። ይህም በሀብታሙ እና በድሀው መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ለጊዜውም ቢሆን በማጥበብ የማኅበረሰብ ፍቅርን ይገነባል። እንደ “ቅርጫ” ያሉ ባሕላዊ ልማዶችም ሰዎች ወጪን ተጋርተው በጋራ እንዲደሰቱ የሚያደርጉ የማኅበራዊ ትስስር ማሳያዎች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች የሚያጠናክሩ ሐሳቦችን ያጋሩን ደግሞ በደብረታቦር ከተማ ቀበሌ ዘጠኝ ነዋሪው አቶ ዋለልኝ አሰፋ ናቸው። ከአቶ ዋለልኝ ጋር የተገናኘነው የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ የንግሥ በዓል ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአጅባር ሜዳ ሲያከብሩ ነበር። በዓሉ ለእርሳቸው ልዩ ትርጉም ያለው እና ደስ የሚል እንደሆነ ያስረዳሉ። በልጅነት ጊዜያቸው በተለይም የገና ጨዋታ እና የጥምቀት በዓል ልዩ ትዝታቸው ነው። አሁን ላይ ደግሞ ከወንድሞቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው እና ከዘመዶቻቸው ጋር በዓላትን በጋራ እንደሚያሳልፉ ያስረዳሉ።  እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ዘመድ ከዘመዱ እንዲሁም ጎረቤቱ ተጠራርቶ እንደሚጫወት ነግረውናል። ይህም ማኅበራዊ መስተጋብሩን ያጠናክራል ብለዋል።

በተመሳሳይ ጥምቀት ከሐይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ ሰው ለሰው የሚሰባሰብበት፣ ወግ ባሕሉን በአደባባይ የሚገልጥበት፣ በዘላቂ ማሕበራዊ መስተጋብር የሚተሳሰርበትም ነው ብለዋል። አቶ ዋለልኝ እንዳሉት ታቦታትን አጅበው ወደ መንበራቸው ከመለሱ በኋላ የተዘጋጀውን ምግብ እና መጠጥ በጋራ ይመገባሉ፤ ይጠጣሉ። ከሩቅ ቦታ የሚመጡ እንግዶችም በተዘጋጀላቸው ድግስ ተቋድሰው ይሸኛሉ። እርሳቸው የበዓላት አከባበር ሲከናወን በጋራ እንደሆነ አጫውተውናል። በበዓል ወቅት የተጣላው ታርቆ የራቀው ተቀራርቦ ክብረ በዓላት እንደሚከበር ነው የነገሩን። የማይተዋወቁት እንዲተዋወቁ፣ ዘመድ አዝማዱ የሚጠራራበት እና ፍቅር የሚመሠርቱበት ነው። ተራርቀው የቆዩት በናፍቆት እንዲገናኙ ያደርጋል። በዓላት ከባሕላዊ ጨዋታው ባሻገር ፈጣሪን ማመስገኛ ናቸው ብለዋል። ስለሆነም ወጉን፣ ባሕሉን፣ እሴቱን እና የአኗኗር ዘይቤውን በጠበቀ መልኩ ሊከበሩ እንደሚገባ አብራርተዋል። የአሁኑ ትውልድ የውጭ ባሕልን ከመናፈቅ ወጥቶ የራሱ የሆነውን ባሕል እና ወግ ሊከተል እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን አጋርተዋል። በዓላት ሲመጣ አብሮ መታሰብ ያለበት የአለባበስ ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በተለይ ሴቶች ሱሪ፣ ሰውነትን ገላልጦ ከሚያሳዩ አጭር ልብስ ከመልበስ እና ወንዶች ደግሞ የተቀደደ ልብስ ከመልበስ ሊቆጠቡ እንደሚገባ መክረዋል።

በበዓሉ ሲታደሙ ያገኘናቸው ሌላው የደብረታቦር ከተማ ነዋሪ ወንድምነው ባይነስ ናቸው። የዘንድሮው የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል ባለፉት ከነበረው ሁለት ሶስት ዓመታት የደመቀ እና ብዙዎች የታደሙበት መሆኑን በምልከታቸው አረጋግጠዋል። በበዓሉ ወቅት ፈረስ ግልቢያ (ጉግስ)፣ ሐይማኖታዊ  አስተምሮዎች እና ባሕላዊ ጨዋታዎች እንደተከናወኑ ተናግረዋል። ክብረ በዓላትን ለማክበር ከትንሽ እስከ ትልቅ በጉጉት የሚጠብቁት መሆኑን ጠቅሰዋል። ክብረ በዓላት በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ጉልህ ሚና የሚሰጣቸው ሲሆን መተሳሰብን እና መረዳዳትን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል። ክብረ በዓላት መሠረታቸው ሃይማኖቶች ሲሆኑ ማኅበረሰቡም እንደ ሃይማኖቱ ትዕዛዝ እና አስተምሮ በመነሳት የሚከውናቸው ሥርዓቶች አሉት። የዘመን መለወጫ (እንቁጣጣሽ)፣ ገና፣ ጥምቀት፣ ፋሲካ፣ ኢዳልፈጥር፣ አረፋ እና የመሳሰሉት በዓላት ማሳያዎች ናቸው። ከአለባበስ፣ ከአጨፋፈር እና ባሕሉን ጠብቆ ከመሄድ አንፃር ትውልዱ ወደ ቀልቡ ሊመለስ እንደሚገባ አቶ ወንድምነው አሳስበዋል።

ወ/ሮ ንግሥት አበበ በደብረታቦር ከተማ ቀበሌ ሁለት የሚኖሩ እናት ናቸው። ሁሌም በዓላት ሲመጣ ምግብ እና ባሕላዊ መጠጥ ለማዘጋጀት ሽርጉድ እንደሚሉ ያስረዳሉ። በተለይ ሴቶች በበዓል ወቅት ዘመድ የሚወደውን ምግብ እና መጠጥ ቀድመው እንደሚያዘጋጁ ነግረውናል። በዓላት ፍቅርን የሚያድሱ፣ ጠብን የሚያረግቡ እና የመረዳዳት ባሕልን የሚያጎለብቱ የማህበራዊ ሕይወት ምሰሶዎች ናቸው ብለዋል። በመሆኑም በዓላትን ስናከብር ይህንን ጥልቅ ማህበራዊ ፋይዳቸውን በመረዳት እና በመጠበቅ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት። ይህ በእንዲህ እንዳለ የባሕል መሸርሸር መኖሩን የታዘቡት ወ/ሮ ንግሥት ትውልዱ ሊታረም እንደሚገባ መክረዋል። የገና፣ የጥምቀት፣ የአስተርዮ ማርያም እና የቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓላትን በጋራ እና በፍቅር እንደሚያከብሩ ነግረውናል። እነዚህ በዓላት ማሕበራዊ ኑሮን ከማጠናከር አኳያ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል። ሁሌም በዓላትን በጋራ በፍቅር፣ በሰላም እና በአንድነት እንደሚያከብሩት ነው የነገሩን።

በዓል አክባሪዎች እንደሚከተሉት ሃይማኖት እና እንደሚኖሩበት አካባቢ ታሪካቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ መተዳደሪያ ጉዳያቸውን ሁሉ መነሻ አድርገው ፈጣሪያቸውን ለመለመን አሊያም ለማመስገን ክብረ በዓላትን ያከናውናሉ ሲሉ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር እና ተመራማሪ ሞገስ ሚካኤል (ዶ/ር)  ናቸው። ተመራማሪው እንዳሉት ሰዎች ባሕላቸው እና እምነታቸው በሚፈቅድ መንገድ በዓላትን በቤታቸው፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በአደባባይ እንደሚያከብሩ ጠቅሰዋል። አብዛኛው የምስጋና በዓላት የአደባባይ ክብረ በዓላት መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ክብረ በዓላት ከሌሎች ክብረ በዓላት የደመቁ ናቸው ብለዋል። ሰዎች ወደ አደባባይ ይወጣሉ ግንኙነታቸውን ያስቀጥላሉ፤ ሌሎች አዳዲስ ትውውቆች እና ግንኙነቶችንም ይፈጠራሉ። እነዚህም ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማትን ለመገንባት መሠረት ናቸው። በክብረ በዓላት ላይ የማኅበረሰብን አስተሳሰብ ፍልስፍና የሚያንፀባርቁ ትዕይንቶች በባሕላዊ ሁነቶች ታግዘው መከበራቸው ልዩ ገፅታ ያላብሳቸዋል። በዓላት ሰዎችን የማገናኘት፣ የማስተሳሰር፣ የማስተዋወቅ አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ሰዎች በተለያዩ መንገድ ትውውቅን ይፈጥራሉ የጥምቀት በዓል ግን ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ነው ያሉት። ይህም በዓሉን በጋራ እና በፍቅር ከማክበር ባለፈ ቤተሰባዊ ግንኙነትን ይፈጥራል።

ለኢትዮጵያዊያን ድምቀት የሆኑት ክብረ በዓላት ከሌላው ጊዜ በተለየ ለማኅበረሰቡ ትልቅ ደስታን የሚፈጥሩ ናቸው። ማኅበራዊ ግንኙነት መፍጠሪያ ብቻ ሳይሆኑ ማጠናከሪያም ጭምር እንደሆኑ ያብራራሉ። ተለያይተው የነበሩ እና በተለያየ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ግለሰቦች ጊዜ እና ገንዘብ መድበው ወገኖቻቸውን ይጠይቃሉ፤ ደስታቸውን ይጋራሉ። እነዚህ ክብረ በዓላት እርስ በርስ የመተሳሰብ፣ የመተጋገዝ፣ የመፈቃቀር፣ ተካፍሎ የመብላት… ማሳያ ናቸው። በዓላት የባሕል እና የማንነት መገለጫዎች ናቸው። ማኅበረሰቡ በጋራ የሚለብሰው ባሕላዊ ልብስ፣ የሚመገበው ምግብ እና የሚጫወተው ጨዋታ የጋራ ማንነትን ያጠናክራል። ይህም ትውልዱ ከታሪኩ እና ከማኅበረሰቡ እሴቶች ጋር እንዲተሳሰር ያደርገዋል በማለት ጠቀሜታቸዉን አዉስተዋል። በአጠቃላይ በዓላት ከመብላት እና ከመጠጣት ባሻገር የማህበረሰቡን ሰላም፣ ፍቅር እና አብሮነት የሚጠግኑበት ልዩ ማህበራዊ ክስተቶች ናቸው።

 

መረጃ

በዓላት በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ዙሪያ ካላቸው ሃይማኖታዊ ወይም ታሪካዊ ትርጉም ባሻገር እጅግ ጠንካራ ማህበራዊ ፋይዳዎች አሏቸው። በዓላት የማህበረሰቡን አንድነት በማጠናከር፣ ባህልን በመጠበቅ እና የስነ-ልቦና እርካታን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

የበዓላት ዋና ዋና ማህበራዊ ፋይዳዎችም፡-

  • የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ትስስርን ማጠናከር
  • ይቅርታ እና ዕርቅ
  • መረዳዳት እና መካፈል
  • ባህል እና እሴትን ለትውልድ ማስተላለፍ
  • የአዕምሮ እረፍት እና መነቃቃት
  • ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር እና ሌሎች ይገኙበታል፡፡

 

( መልካሙ ከፋለ)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here