በአሜሪካ ኢሊኖይስ በሚኖሩ አሳዳሪዎቹ ቤት 33 ዓመታትን ያስቆጠረው ኮካቴል ወፍ ከዝርያዎቹ ሁሉ ረዢም እድሜ መኖሩ በመረጋገጡ በዓለም አቀፉ የድንቃ ድንቅ መዝጋቢ ድረጅት ለክብረወሰን መብቃቱን ዩፒአይ ድረ ገጽ አስነብቧል::
“ሶኒ” የሚል ስም የተሰጠው ወፍ በ32 ዓመት ከ292 ቀናት እድሜው ነው በዓለም አቀፉ የድንቃ ድነቅ መዝጋቢ ድረጅት ለክብረወሰን መብቃቱ የተረጋገጠው:: ከድርጅቱ የምስክር ወረቀት አግኝቶ 33 ዓመቱ የተከበረለትም በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጥር 10/2026 እ.አ.አ ነው::
የኖርዘርንብሩክ ኗሪዋ የወፉ አሳዳሪ ጃኔት ሬይቸር በ1993 እ.አ.አ የጥቂት ሳምንት ጫጩት ሳለ ቤተሰባቸውን መቀላቀሉን ተናግረዋል:: በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሙዚቃ የተለየ ስሜት ያለው መሆኑን መረዳታቸውንም ነው ያብራሩት::
ወፉ የተለያዩ ዜማ ያላቸው ፉጨቶችን በየአጥሩ እና ቁሳቁስ ላይ እየተንጠላጠለ ያሰማ ፣ አሁን ላይ እድሜው ሲገፋ ቢዘነጋቸውም በርካታ ቃላትን ተገንዝቦ ትእዛዝ ይቀበል እና ይፍፅም እንደነበርም ነው ያስረዱት – ጃኔት ሬይቸር::
የወፉ ረዥም እድሜ የመኖሩ መስጢርም ጤናማ አመጋገቡ፣ የቤተሰብ አባላቱ ቀረቤታ እና የሚደረግለት እንክብካቤ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ነው ያስረዱት- አሳዳሪዋ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


