የደም ቀን

0
222

ሀገራቸው በባእዳን ወራሪዎች እጅ ልትወድቅ መሆኗ ያንገበገባቸው አብርሃም ደቦጭ፣ ሞገስ አስግዶም፣ ስምዖን አደፍርስ እና መሰሎቻቸው የካቲት 12 ቀን 1929 በግራዝያኒ እና በባለሥልጣኖቹ ላይ የቦንብ አደጋ አደረሱ:: በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከህጻን እስከ አረጋዊ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎች በዐይናቸው አይተው መስክረዋል::

አዲስ አበባ የነበረው የሀንጋሪ ሀኪም ላዲስላቭ ሳቮ “ተገቢ ያልሆነ ጭፍጨፋ ነበር፤ ሽማግሌዎች፣ ነዲያን፣ እግር የሌላቸው፣ እናቶች ከነልጆቻቸው ነበሩበት:: ከሬሳዎቹ መካከል የሚተነፍስ እንዳለ እያዩ እየመረመሩ ይገድሉ ነበር” ሲል መመስከሩን ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው አትተዋል።

ላዲስላቭ ሳቮ በምስክርነቱ “ይህ ሁሉ ሰራዊት በህይወት ያለ ኢትዮጵያዊን ለመጨፍጨፍ ተሰማራ:: ሱቆች እንዲዘጉ ተደረገ:: የውጭ ዜጎች ወደ ውጭ እንዳይወጡ መልዕክት ተላለፈ:: በተለይ ፎቶግራፍ እና ቪዲዮ መቅረጫ እየተፈተሸ መወሰድ ተጀመረ:: የፖስታ እና ስልክ አገልግሎት ተቋረጠ (ይህም የፋሽስቶቹ ግፍ ለዓለም ሕዝብ ይፋ እንዳይሆን ነው):: በቅጽበትም በቤተ-መንግሥት እና አካባቢው ያሉ መንገዶች በሬሳ ተሞሉ” ብሏል::

ላዲስ ላቭ ከማልረሳው ነገር ብሎ እንደተናገረው በዚያ ሌሊት የጣሊያን መኮንኖች በሚያማምር አውቶሞቢሎቻቸው ከሚስቶቻቸው ጋር ሆነው እየዞሩ ብዙ ሬሳ ከተከመረበት እና ብዙ ቃጠሎ ከሚታይበት ቦታ በሰው ደም ላይ እየቆሙ ያን እልቂት እየተመለከቱ ይስቁ ነበር:: ግራዚያኒም በሆስፒታል ውስጥ ሆኖ የከተማዋን ጭስ እያየ ይስቅ ነበር::

አዲስ አበባ ለሦስት ቀናት የደም እንባ አነባች:: ጭፍጨፋው በሦስት መንገድ ነበር የተፈጸመው:: አንደኛው በመንገድ ላይ የተገኘውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ አበደ ውሻ መግደል ነው:: ሌላው ቤታቸውን እያቃጠሉ ንብረታቸውን እየዘረፉ ሙሉ ቤተሰቡን በእሳት እያነደዱ መግደል ነው:: ሦስተኛው በአካፋ፣ በመዶሻ እና በዱላ እየቀጠቀጡ የተረፈውን በእስር ቤት አጉሮ በረሀብ እና በጥም መጨረስ ነበር:: ቤተ ክርስቲያን እና መኖሪያ ቤቶችን ማቃጠል ሌላው የበቀል እርምጃ ተደርጎ በጣሊያኖቹ ተፈጽሟል::

ዳግማዊ ኔሮ በበኩሉ “በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ከግንባር ቀደሙ ቶር ጋር ቁስለኛ ለማንሳት በአንቡላንስ ውስጥ እሰራ ነበር:: በሌሎች ጦርነቶችም ግልጋሎት ሰጥቻለሁ:: እንደ አዲስ አበባው ያለ እልቂት ግን አላየሁም:: መኪናዎች እየዞሩ ሬሳ ያነሳሉ፤ ባለጥቁር ሸሚዞች ወደ ኢጣሊያ ባንክ እየገቡ ሌሊት የዘረፉትን ብር እና ወርቅ ያስቀምጣሉ:: ዘረፋው ቤት ውስጥ ብቻ አልነበረም፤ ከሚገድሏቸው ሴቶች እጅ እና አንገት የሚያገኙትን ወርቅ ሁሉ ይወስዱ ነበር::

ህክምና በምሰራበት ቦታ ብዙ ጣሊያኖች ይመጡ ነበር፤ የገደሉትንም የሰው ቁጥር በኩራት ይናገሩ ነበር:: አንዳዶች ሰማኒያ ገደልኩ ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ መቶ ገደልኩ ይላሉ:: አንድ ጣሊያን ብቻ እያዘነ ‘እኔስ የገደልኩት ሁለት ብቻ ነው’ ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ:: የማልረሳው ነገር ግድያው እንዲቆም በተደረገ ጊዜ ታላቁ ግራዚያኒ ለህዝብ በማዘን ግድያው ይቁም ብለዋል መባሉ ነው” ሲል የሚያስታውሰውን ተናግሯል::

ደራሲ ተመስገን ገብሬ ከዚህ ክፉ ቀን በተአምር ከተረፉ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ናቸው:: ይህን ዘግናኝ ታሪካቸውን ጽፈዋል:: የደረሰባቸውን ሲተርኩም“…ስምንት የሚሆኑ መትረይሶች በዙሪያችን ተጠምደዋል:: በዚያም ስፍራ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ሀበሾችን አስቀድመው ገድለዋቸዋል:: ሬሳቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ:: እኛንም በዚያው ሊገድሉን ተዘጋጁ:: ለመትረየስ ተኩስ እንድንመችም የአንዳችንን እጅ ከአንዳችን እጅ አያይዘው አሰሩን:: አንድ ታላቅ ሹም መጣ፤ ሰዎችን ከግድያ እያስጣለ ለምርመራ ወደ እስር ቤት ይወስድ ነበር:: እኛም ታስረን ልንገደል ከቆምንበት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስት ረድፍ ወደ ላይኛው መንገድ እንድንሄድ ትዕዛዝ ሰጠ፤ በመንገዳችን ላይ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ነበሩ:: ምራቄ ከአፌ አለቀ::

…ወደ እስር ቤት አስወሰደን፤ ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር:: ከማዘጋጃ ቤቱ ስንደርስ  በአምስት ካሚዮን ያጠራቀመንን ሰዎች በዋናው መንገድ እንድንቆም አዘዘን:: ዙሪያችንንም ከበው በሳንጃ እየወጉ ጭፍቅ ብለን እንድንቆም አደረጉን:: ወደኋላችንም ትልቁን የጣሊያን ካሚዮን በላያችን ነዱብን:: …በአንድ ጊዜ 48 ሰዎች ተጨፈለቁ:: ከካሚዮኑ ወደኋላ ያፈገፈጉትን እስረኞች ዙሪያውን ሳንጃ መዘው የቆሙት ወጓቸው:: እኔንም ካሚዮኑ ጉልበቴን መታኝ:: ያን ጊዜ የቆሰልኩት እስካሁን  ለምጥ መስሏል::…

ወደ ማዘጋጃ ከገባን በኋላ ጥቂት ቆይቶ መራጮች መጡ:: ጥሩ የለበስነው እያወለቅን ሰገራው ውስጥ (መጸዳጃ ቤት) ወረወርነው:: ከሰገራው ውስጥ አምስት ሰዎች ገብተው ለመውጣት ይንፈራገጣሉ:: ግን እያቃታቸው ተመልሰው ይጠልቃሉ::

አብረውኝ ተቀምጠው የነበሩትን አቶ ንጋቱ ገብረጽዮንን እና ሰመረ ጓለጽዮንን ወሰዷቸው፤ ልብሳቸውን አልለውጥም ብለው የጨዋ መልክ ስለነበራቸው ነው:: ክብሪት ለኩሰው አቃጠሏቸው::… እሳቱም እያቃጠላቸው አንደኛው ፋሽስቶችን ተጣራ እና እንዲህ አላቸው ‘ከፋሽስት ጋር ለሚኖሩ አዝናለሁ፤ እኔ ግን ከእንግዲህ ከፋሽስት መንግሥት ነጻ ነኝ’ ብሎ ስቃዩን ችሎ በድፍረት ተናገረ”::

የጣሊያን ወታደሮች በጥም ለሚሰቃየው እስረኛ በጉንጭ ሙሉ ውኃ በአንድ ብር ይሸጡ እንደነበር ደራሲ ተመስገን ገልጸዋል:: ውሃ በስግብግብነት ሲሸጡ የነበሩ ወታደሮች በእስረኛ መገፋፋት ተጨፍልቀው መሞታቸውንም አንስተዋል::

ደራሲ ተመስገን ገብሬ በጽሑፋቸው ያጋጠማቸውን እጅግ ዘግናኝ ለማንሳት የሚቀፉ ክስተቶችን እና ስቃዮችን አስፍረዋል:: እሳቸው ከታጎረው ህዝብ ወደ መሃል በመዝለቅ ፊትለፊት የጣሊያን ወታደሮች ለጥቃት የሚያጋልጠውን ቦታ በመራቅ ህይወታቸውን ማትረፋቸውን ተርከዋል:: በኋላም ወደሆለታ ተወስደው ጫካ ውስጥ በጥይት የተረፈውን እስረኛ ሲደበድቡ በተአምር ሳይመቱ መትረፋቸውን፣ ጣሊያኖቹም ሞተዋል ብለው ትተዋቸው መሄዳቸውን ጠቅሰዋል:: ፋሽስት ጣሊያን ለቅኝ ግዛት አላማው በተለይ የተማረው የህብረተሰብ ክፍል ፈተና ይሆንብኛል ብሎ በማሰብ ዋነኛ ኢላማ እንዳደረገው ከተመስገን ገብሬ ትረካ መረዳት ይቻላል::

ጳውሎስ ኞኞ “እጅግ በጣም የደነቀኝ ነገር ነፃ ከወጣን በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ካሳ አጠያየቅ ነበር:: ይህም ሂሳቡ ሲታሰብ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሺህ ፓውንድ፣ ለአንድ ሰው መቶ ፓውንድ፣ ለቤት 20 ፓውንድ፣ ለአንድ የቀንድ ከብት አምስት ፓውንድ፣ ለአንድ በግ ወይም ፍየል አንድ ፓውንድ እና ለአንድ ግመል 10 ፓውንድ ነበር:: በዚህ ስሌት የጦር መሣሪያ ግዢን ጨምሮ በአምስት ዓመቱ የቀረ የገቢ ግብር ጋር 185 ሚሊዬን ፓውንድ ቢሆንም በመጨረሻው ስምምነት ግን ስድስት ሚሊየን 250 ሺህ እንዲሆን ተወስኗል። “በራሱ እና ለራሱ ከገነባው የእምነት ቤት አስር ጊዜ አንሶ የተገመተው የሰው ልጅ!” ሲሉ ጽፈዋል::

እስከ ጥቂት ዓመታት ድረስ ለየካቲት 12 የደመቀ የትውስታ መርሃግብር ሲሰናዳለት አለመስተዋሉ ሽንፈትን ደጋግሞ ማውሳት ምቾት ስለሚነሳ ነው የሚሉ ተንታኞች አሉ። በአምስት ዓመቱ ወረራ ንጉሡ ከሀገር ውጭ ቆይታቸው ሲመለሱ ማክበሩን አልፈለጉትም። በእሳቸው አልጋ የተተካው ወታደራዊ መንግሥትም ዕለቱን መዘከር ፊውዳልን እንደማወደስ ቆጠረው::

የካቲት 12 በአዲስ አበባ ብቻ ከ33 ሺህ በላይ ንፁሃን ያለጥፋታቸው በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በፋሺስቶች እጅ ተጨፍጭፈዋል። ይህ ዘግናኝ እልቂት በዓለም ታሪክ ውስጥ በዘግናኝነታቸው ከሚታወቁ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ተርታ የሚሰለፍ ነው።

የየካቲት 12 የሰማዕታት ማስታወሻ በዓል ንፁሐን ዜጎቻችንን በግፍ ያጣንበት ቢሆንም የመነሻ ሰበቡ ሀገር ወዳድነት፣ አልገዛም ባይነት፣… መሆኑ ከፍ ያለ ትርጉም እንድንሰጠው ያስገድደናል። በግለኝነት ጽንሰ ሀሳብ ተተብትቦ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚኳትነው የአሁን ጊዜ ወጣት መሰል ታሪኮችን ዞር ብሎ ቢፈትሽ ሀገር ወዳድነትን፣ ለወገን ቅድሚያ መስጠትን እና ለዓላማ መሰዋትን ይማርበታል::

በመጨረሻም “በአድዋ የተገኘው ድል ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ መጥታ በተደረገው የማይጨው ጦርነት ለምን አልተደገመም?” ብለን ብንጠይቅ ከታሪክ ምሁራን የምናገኘው መልስ “ጣሊያን የተከለከለ የመርዝ ጋዝ በጦርነቱ ከመጠቀሟ ባሻገር በዋናነት ግን በዓድዋ ድል ጊዜ የነበረን አንድነት፤ በማይጨው ጦርነት ጊዜ ስላልነበረን” የሚል ነው።

ከማይጨው ጦርነት በኋላ ባለው የአርበኞች ተጋድሎ ላይ ኢትዮጵያውያን በጀግንነቱ ረገድ ከአባቶቻቸው ባይተናነሱም፤ አንድ ሆኖ በኅብረት ጠላትን በመውጋት ላይ ግን በብዙ ይታሙ ነበር። ለዚህም ይመስላል ከግጥሞቻቸው መካከል በአንዱ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ

“…ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣

ነገራችን ሁሉ- የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ…”

ሲሉ ኢትዮጵያውያን ተባብረው የጋራ ጠላታቸውን እንዲዋጉ ጥሪ ያቀረቡት እኚህ ታላቅ የኪነጥበብ ሰው እዚሁ ግጥማቸው ላይ ይህንን የእንተባበር ጥሪያቸውን ሲያቀርቡ በዓድዋ የወደቁትን ጀግኖች ከተቀበሩበት አፈር አውጥተው አጥንት እስከመልቀም የሚያደርስ መሻታቸውን እስከማሳበቅ ደርሰዋል።

“…አጥንቱን ልልቀመው- መቃብር ቆፍሬ፣

ጎበናን ከሸዋ- አሉላን ከትግሬ…”

ብለው የእነሱን ኅብረትና ጀግንነት የያኔው ትውልድ አርበኞች እንዲደግሙት ከሃገር ፍቅር በሚመነጭ ልባዊ ምኞት በስንኞቻቸው የትውልድ አደራ የሚሆን ስንቅ አሸክመዋል። ይህ መልእክት ደግሞ ለያኔው ትውልድ ብቻ ሳይሆን፤ ለእኛ ለአሁኑ ትውልዶችም ታላቅ የሆነ ትርጓሜና እውነታ አለው። አጥንቱን መልቀሙ እንኳ ይቆየን ብንል ለመተባበሩ ግን ልንሰንፍ የተገባ አይደለም።

የካቲት ወር ሁለት ገፆች ያሉት እና ብዙ የምንማርበት ነው። በእኛ በኢትዮጵያውያን መካከል ኅብረት ሲኖር ማንም እንደማያሸንፈን “የዓድዋ ድል” ሲያስተምረን፣ በመሃላችን መለያየት እና ጥላቻ ሲኖር የሚደርስብንን ውርደት ደግሞ የየካቲት 12 የአዲስ አበባ የፋሽስት ጭፍጨፋ በደንብ አድርጎ ትምህርት ይሰጠናል።

 

 

ሳምንቱ በታሪክ

የአንጾኪያ ጦርነት

የአንጾኪያ ጦርነት የተካሄደው የካቲት 16 ወር 1888 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1896) ነው። በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ አድዋ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት፣ ጣሊያኖች የኢትዮጵያን የጦር እንቅስቃሴ ለመገደብና ስንቅ ለማቋረጥ ሞክረው ነበር።

የአንጾኪያ ጦርነት (አንዳንዴም የአንጾኪያ ደፈጣ ተብሎ የሚታወቀው) የኢትዮጵያ አርበኞች የጠላትን እንቅስቃሴ ለመሰለልና ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር የተጠቀሙበት ነው። አንጾኪያ ለደፈጣ ውጊያ አመቺ የሆነ ተራራማና ሸለቆማ ቦታ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት የጣሊያንን ዘመናዊ መሣሪያ በቅርብ ርቀት ውጊያ ለማምከን ተጠቅመውበታል።

በዚሁ አካባቢ የነበሩ የሀገር በቀል ሰላዮች ለምኒልክ ጦር የጠላትን አሰላለፍ በመጠቆም ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል ማድረጉ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለተካሄደው ለታላቁ የአድዋ ጦርነት ለወታደሩ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗል።

ጣሊያኖች የኢትዮጵያን ሠራዊት ብዛትና የውጊያ ዝግጁነት በስህተት እንዲገምቱና እንዲረበሹ አድርጓቸዋል። የጠላትን የስንቅና የመገናኛ መስመር በማቋረጥ የጄኔራል ባራቲየሪ ጦር ግራ እንዲጋባ አድርጓል። በአጭሩ  የአንጾኪያ ጦርነት ለአድዋ ድል “መቀስቀሻ” ወይም “መቅድም” ከሆኑት አነስተኛ ግን ወሳኝ ግጭቶች አንዱ ነው።

ምንጭ፡- አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፦ “ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ” (በ1901 ዓ.ም የታተመ)።

የጀርመን ፓርላማ ሕንጻ ጋየ

በጀርመን በርሊን የሚገኘው የፓርላማ ሕንፃ (Reichstag) የካቲት 20 ቀን 1925 በድንገት በእሳት ጋየ። ይህ ክስተት በወቅቱ ለነበረው የጀርመን ፖለቲካዊ መረጋጋት መናጋት እና ለአዶልፍ ሂትለር ወደ ፍጹም አምባገነንነት መሸጋገር ቁልፍ መንስኤ ሆኗል።

ሂትለር ገና በሥልጣን ላይ እንደወጣ የተከሰተው ይህ ቃጠሎ፣ ናዚዎች ኮሙኒስቶችን ለመወንጀል የተጠቀሙበት መሣሪያ ሆነ። “ኮሙኒስቶች መንግሥትን ለመገልበጥ የሰነዘሩት ጥቃት ነው” በማለት ሕዝቡን አሳመኑ። ቃጠሎውን ተከትሎ በሚቀጥለው ቀን የዜጎችን መሠረታዊ ነፃነት (የመናገር፣ የፕሬስ እና የመሰብሰብ መብትን) የሚገድብ አዋጅ ወጣ ሲል የብሪታኒካ መረጃ ያሳያል።

 

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here