ተሰጥኦ በትምህርት ከሚገኝ ዕውቀት ጋር ሲቀናጅ…

0
288

አሁን ያለው ዘመን የክህሎት ተኮር ትምህርትን ከምንጊዜውም በላይ ይፈልጋል:: ቴክኖሎጂ እና የስራ ዓለም በፍጥነት እየተቀያየሩ ባሉበት በዚህ ወቅት በንድፈ-ሀሳብ ላይ ብቻ የተመሰረተ ትምህርት በቂ እንደማይሆን ትምህርትን በኢንተርኔት ታግዞ የሚሰጠው ዓለም አቀፉ ትምህርት ቤት (21K School) በድረ ገጹ ዘግቧል::

ተፈጥሯዊ ተሰጥኦን በትምህርት ከሚገኝ ዕውቀት ጋር ማቀናጀት ደግሞ ለዚህ ዘመን ፍላጎት ዕውን መሆን ዋነኛው መንገድ ነው:: የተፈጥሮ ዝንባሌ በትምህርት ከሚገኝ ዕውቀት ጋር ትስስር ሲፈጥር ለሀገር ሸክም የሚሆንባት ሳይሆን መፍትሔ የሚሰጣት ትውልድ እንዳላት “ዓለም አሁን ላይ ምን ችግር ሆነባት” ብሎ የተነሳው አሌክሳንደር ዋንግ ምስክር ነው::

አሌክሳንደር ዋንግ ማነው?

እንደ ፎርብስ መጽሄት አሌክሳንደር ዋንግ የተወለደው እ.አ.አ በጥር 1997 በአሜሪካ ኒው ሜክሲኮ ግዛት ነው:: የአሌክሳንደር አስተዳደግ ለቴክኖሎጂ እና ለሳይንስ ባለው ፍላጎት ላይ ትልቅ ሚና እንደተጫወተም የመጽሄቱ ዘገባ ያስረዳል::

ወላጆቹ ከቻይና ወደ አሜሪካ የሄዱ ስደተኞች ናቸው:: ሁለቱም የፊዚክስ ሊቃውንት ናቸው:: አሌክሳንደር ያደገበት አካባቢ (ሎስ አላሞስ) የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ የተሰራበት ቦታ መሆኑ ደግሞ ለቴክኖሎጂ ያለውን አመለካከት ዕውን ለማድረግ ተጨማሪ ገፊ ምክንያት ሆነው::

አሌክሳንደር ገና በልጅነቱ በሂሳብ እና በኮዲንግ ልዩ ችሎታ እንደነበረው በ ‘ሀውስ ዶት ጂኦቪ’ (house.gov) ድረ ገጽ የታተመው ግለ ታሪኩ ያስረዳል:: በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪነት ሕይወቱ ብሔራዊ የሂሳብ እና የፊዚክስ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል:: በትምህርት ላይ እያለ ገና በ17 ዓመቱ በሲሊኮን ቫሊ በሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ በሶፍትዌር መሃንዲስነት ሰርቷል:: ይህም ለቴክኖሎጂ መሰጠቱን ያረጋገጠ ሆነ:: በ19 ዓመቱ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ የከፍተኛ ትምህርቱን የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ለማጥናት የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋምን ተቀላቀለ:: የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ግን ሁለተኛ ዓመቱንም ሆነ የዩኒቨርሲቲ ቆይታውን ለማጠናቀቅ አልፈለገም::

ለምን?

አሌክሳንደር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ያቋረጠው ትምህርት ሰልችቶት ሳይሆን የተማረው እውቀት በክፍል ውስጥ ተቀምጦ ከሚባክን ይልቅ ወደ ስራ ተቀይሮ ዓለምን ቢቀይር እንደሚሻል በማመኑ ነው:: አሌክሳንደር “እውቀት ዋጋ የሚኖረው ችግር ሲፈታ ብቻ ነው” ብሎ ያምናል::

ኤ አይ እና ስኬል ኤ አይ

የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ስኬል ኤአይ ተግባራቸው የተለያዩ ግን ደግሞ አንዱ ያንዱን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት የሚሰሩ መተግበሪያዎች መሆናቸውን ሀርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው ያስረዳል:: የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃላይ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ስም ነው። ኮምፒውተሮች እንደ ሰው እንዲያስቡ፣ እንዲማሩ እና ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያስችል ጥበብ ነው። ዋና ተግባሩም መረጃን መተንተን፣ ምስል መለየት፣ ቋንቋ መተርጎም፣ እንደ ChatGPT ያሉ ንግግሮችን ማድረግ እና ሌሎችንም ነው::

ስኬል ኤአይ ደግሞ ኩባንያ ሲሆን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤታማ እንዲሆን የሚያስፈልገውን ስልጠና ወይም መረጃ ያዘጋጃል:: ተግባሩ ደግሞ ለሰው ሰራሽ ሞዴሎች የሚሆን ጥራት ያለው መረጃን ማዘጋጀት ነው::

በአጠቃላይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቱ ሲሆን ስኬል ኤአይ ደግሞ ያ ውጤት እንዲመጣ ግብዓቱን የሚያዘጋጅ ፋብሪካ ነው::

ስኬል ኤአይ

አሌክሳንደር ዋንግ ስኬል ኤአይን ለመመስረት ያነሳሳው በወቅቱ የነበረው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ትልቁ እንቅፋት ምን እንደሆነ በስራ ልምዱ መረዳቱ ነው:: የመረጃ ክፍተት፣ የራሱ የቤት ውስጥ ሙከራ እና የወደፊቱ ዓለም በመረጃ ላይ የተመሰረተ መሆን ዋነኞቹ ናቸው:: ሰዎች እውቀታቸውን በሚያካፍሉበት፣ ጥያቄና መልስ በሚለዋወጡበት ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ድረ-ገጽ (Quora) እንዲሁም በሀብት አስተዳደር እና በኢንቨስትመንት ቴክኖሎጂ ላይ በተሰማራው ታዋቂው የአሜሪካ የሶፍትዌር ኩባንያ (Addepar) ውስጥ በሶፍትዌር መሐንዲስነት ሲሰራ የ ኤአይ ሞዴሎችን መገንባት በጣም ከባድ እንደሆነ መገንዘቡ ወደ ፈጣራ እንዲገባ አድርጎታል::

አሌክንደር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓለምን እንደሚቀይር በሚገባ ይረዳ እንደነበር የስኬል ኤአይ ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል:: ነገር ግን ያ ለውጥ እንዲመጣ መሠረተ ልማቱ መገንባት እንዳለበት በመረዳቱ ቴክኖሎጂውን ከጓደኛው ሉሲ ጉዎ ጋር በመሆን በፈረንጆቹ 2016 አበሰረ:: ኩባንያው አሁን ላይ ከጽሁፍ እስከ ወታደራዊ መረጃዎች ድረስ እጅግ ሰፊ የሆኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ግብዓትን ያዘጋጃል::

ታሪኩ ለተማሪዎች

በገንዘብ አያያዝ፣ በስራ ስኬት፣ በቢዝነስ እና በቢሊየነሮች የሕይወት ተሞክሮ ላይ የሚያተኩሩ መረጃዎችን ይፋ የሚያደርገው የሲኤንቢሲ ድረ ገጽ ተማሪዎች ከአሌክሳንደር ምን ሊማሩ እንደሚገባ በስፋት ጽፏል:: ተማሪዎች የእሱን ፈለግ በመከተል ችግር ፈቺ ዜጋ ለመሆን የችግር አነፍናፊ መሆን ይገባቸዋል የሚለውን ጽሁፉ በቀዳሚነት አስቀምጧል:: አሌክሳንደር ስኬታማ የሆነው አዲስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጥሮ ሳይሆን ቴክኖሎጂው እንዳያድግ እንቅፋት የሆነውን ትልቁን ችግር በመለየቱ ነው:: በመሆኑም ተማሪዎች በአካባቢያቸው ያለው ችግር ለይተው መፍትሄ ማፈላለግ ላይ ትኩረት በማድረግ ዕውቀትን ተግባር ላይ ማዋልን ከቴክኖሎጂ ፈጣሪው መማር እንደሚችሉ ዘገባው ጠቁሟል::

ተማሪዎች የረጅም ጊዜ ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባ የሲኤንቢሲ ዘገባ ያስረዳል:: በየቀኑ ትንሽ ትንሽ እውቀት ማከማቸት በረጅም ጊዜ ውስጥ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ የአሌክሳንደርን የሕይወት ጉዞ መነሻ አድርጓል:: ተማሪዎች ዛሬ የሚያነቡት አንድ ገጽ መጽሐፍ ወይም የሚሰሩት አንድ ጥያቄ ቀላል ሊመስል የሚችል ቢሆንም ነገር ግን በየቀኑ ማድረግ ትልቅ የፈጠራ ሰው እንደሚያደርግ ሲኤንቢሲ አረጋግጧል::

አሌክሳንደር አለመሳካትን እንደ ትምህርት ነው የሚመለከተው:: ፈጣሪው የሚመክረው ስህተት መስራት መሸነፍ ሳይሆን የማይሰራውን መንገድ መለየት ነው ብሎ ነው:: በመሆኑም ተማሪዎች ፈተና ሲከብዳቸው ወይም የሞከሩት ፈጠራ ሳይሳካ ሲቀር ተስፋ ቆርጦ ከመተው ይልቅ “ምን ተማርኩበት?” ብሎ መጠየቅን መልመድ ለብቁነት እንደሚያበቃ የአሌክንደር ግለ ታሪክ እማኝ ነው::

በትምህርት ቤት የሚገኝ ዕውቀት ትርጉም የሚኖረው በተግባር ሲፈተን እንደሆነም ቴክኖሎጂ ፈጣሪው ያምናል:: ተማሪዎች በትምህርት ቤት ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው ትናንሽ ፕሮጀክቶችን መጀመር፣ ኮዲንግ መለማመድ ወይም በፈቃደኝነት አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ እንደሚገባቸው የቴክኖሎጂው ገጽ ላይ የተለጠፈው ጽሁፍ ይጠቁማል::

አሌክሳንደር ትክክለኛውን ጊዜዬ ነገ ነው ብሎ በተስፋ መጓዝን እንደማበረታታ የሲኤንቢሲ ሀተታ አስታውቋል:: ብዙዎች ትልቅ ሥራ ለመሥራት ዲግሪ መያዝን ወይም መመረቅን ይጠብቃሉ:: ሐሳብህን ለመሞከር የግድ ትምህርት መጨረስ የለብህም:: እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው ትምህርት ማቋረጥ የለበትም፤ ነገር ግን በትምህርት ቤት እያሉ የጎንዮሽ ሥራዎችን መጀመር ለወደፊት ስኬት መሠረት እንደሚሆን አሌክሳንደር አረጋግጧል::

ተሰጥኦ ብቻውን በቂ አለመሆኑን የሚናገረው አሌክሳንደር ከሌሎች ጋር የመግባባት፣ ሰዎችን የመምራት እና በቡድን የመሥራት ክህሎት ለስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በራሱ አረጋግጧል::

የአሌክሳንደር የመጨረሻው ወሳኝ ምክር የጊዜ ኃያልነትን መረዳት ነው ብሎ ያምናል:: “ጊዜህን የምትሰጠው ለሰው ሳይሆን ለግብህ መሆን አለበት፤ ዛሬ የምታጠፋት እያንዳንዷ ደቂቃ ነገ ለምትሆነው ሰው የምትከፍላት ዋጋ ናት” በማለት ጊዜ ሁሉም ዳኛ መሆኑን አስገንዝቧል:::

 

ኮሮጆ

 

የተፈጥሮ ተሰጥኦን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

ተሰጥኦ ማለት ያለምንም ከፍተኛ ጥረት የምናከናውነው እና ውጤታማ የምንሆንበት ነገር ነው፡፡ ይህንን ለማወቅም የሚከተሉትን ምልክቶች ይከታተሉ፦

አዲስ ነገር ስትጀምሩ ከሌሎች በበለጠ በፍጥነት የምታከናውኑት ከሆነ

አንድን ስራ ስትሰሩ ጊዜው እንዴት እንደሄደ የማታውቁ ከሆነ እና ስራው የማይሰለቻችሁ ከሆነ ውስጣዊ ፍላጎት አለ ማለት ነው ነው።

ሰዎች በተደጋጋሚ በሆነ ዘርፍ የተሻላችሁ እንደሆነ የሚነግሯችሁን በትኩረት መመርመር

አንድ ሥራ ስትሰሩ የሚሰማችሁ ጥንካሬ እና እርካታ ከፍተኛ ከመሆኑ የተደበቀ ተሰጥኦ ሊኖራችሁ ስለሚችል አጠናክራችሁ አስቀጥሉ፡፡

ምንጭ፡- https://themeaningmovement.com

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here