የወዳጄ ወግ

0
213

ከረዥም ጊዜ መለያየት በኋላ ከወዳጄ ጋር ድንገት ተገናኘን:: ወዳጄ በቀላሉ አይገኝም፤ ከተገኘ ግን ደርዘኛ ወጉ አይጠገብም:: እናም ድንገት ሳገኘው ደስ አለኝ:: እሱም እኔን በማግኘቱ ደስ ሳይለው አልቀረም፤ ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጥን::

ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ  ሻይ ቡና እያልን ወጋችንን ቀጠልን:: የዛሬው ወጋችን ያተኮረው በተአማኒነት ላይ ነው:: ርዕሱን የመዘዘው ወዳጄ ነው:: ብዙ ጊዜ እንደማደርገው እንዲያወጋ ዕድል ሰጠሁት፤ ከማዳመጥ ብዙ ቁም ነገር እንደሚገኝ በማመን:: ወዳጄ ታማኝነትን በመበየን ወጉን ጀመረ፤  “ታማኝነት እውነትን ይዞ መጓዝ፣ የሚያምኑበትን መናገር፣ በተናገሩት መጽናትና ቃልን በተግባር ማዋል፣  ለምስክርነት መብቃት ነው…”  የታማኝነትን ምንነት ረጋ ብሎ አብራራልኝ::

ባንክሮ እያዳመጥሁት እያለ፣ “መታመን ለራስ ነው፤ ወንድሜ ለሕሊናህ ታማኝ ሁን!” ሲል ወጉን ቀጠለ:: ‘ይሄ ሰው ምን አይቶብኝ ነው? ለሕሊናህ ታማኝ ሁን የሚለኝ?’  ስል አሰብሁና፣ “ምነው ወዳጄ? ስታምነኝ ከዳሁህ እንዴ?” ስል ጥያቄ አቀረብሁለት::

“ታማኝ ሁን ስልህ አትታመንም ማለቴ አይደለም፤ ለሕሊና መታመን ስላለው ከፍ ያለ ዋጋ ላጫውትህ ስለፈለግሁ ለመንደርደሪያነት የሰነዘርሁት ሀሳብ ነው” የቀረበለትን ሻይ እያማሰለ ወጉን ቀጠለ::  “መታመን ለራስ ነው ሲባል ቀልድ ይመስለኝ ነበር::  ሆኖም በነገሮች ግጥምጥሞሽ አባባሉ ለእኔ የተነገረ እስኪመስለኝ ድረስ ቁም ነገሩ ገዝፎ ታየኝ፤ በውስጡ ትልቅ ቁም ነገር ይዟል” አለ::

እኔም ቡናየን ፉት አልሁና፣ ‘የዛሬ ዘመን ሰው ታማኝ ሆነህ ቢያገኝህ ታማኝ ነው ብሎ ያንተን ፈለግ በመከተል ፋንታ መታመንህን ከሞኝነት ነው የሚቆጥርብህ’ ልለው ካፌ አድርሼ ማዳመጤን ቀጠልሁ፤ “በዚህ ዓመት መጀመሪያ ነው፤ ያለችኝን ትንሽ ብር ላወጣ ወደ ባንክ ቤት ሄድሁ:: ባጋጣሚ ወረፋ አልነበረም:: እናም እንደገባሁ  በወጪ መጠየቂያ ቅጹ ላይ ሦስት ሺህ ብር ወጪ ጽፌ በመፈረም ለገንዘብ ከፋይዋ ሰጠኋት:: ገንዘብ ከፋይዋ የወጪ መጠየቂያ ቅጹን ተቀብላ የኮምፒዩተሯን ቁልፎች ስትነካካ ቆይታ ገንዘቡን  ከመሳቢያ አውጥታ ቆጥራ ሰጠችኝ:: ገንዘቡን ተቀብየ ወደ ኪሴ ላስገባ ካሰብሁ በኋላ ድንገት ቀና ስል ዓይኖቼ፣ “ገንዘብዎን ከመክፈያ መስኮቱ ፊት ለፊት ቆጥረው ይረከቡ” ከሚል ጽሑፍ ላይ አረፉ:: ማሳሰቢያውን ሳይ ‘ለማንኛውም መቁጠር አይከፋም’ በሚል የሰጠችኝን ገንዘብ  መቁጠር ጀመርሁ:: ቆጥሬ ስጨርስ  ሦስት ሺ ብር መሆን ሲገባው አምስት ሺህ ብር ሆነ::  ‘ወጪ የጠየቅሁ ሦስት ሺህ ብር ነው፤ እንዴት አምስት ሺህ ብር ሰጠችኝ?  ስቆጥር ተሳስቼ ይሆን?’ ብየ እንደገና መቁጠር ጀመርሁ፤ አልተሳሳትሁም፤ አምስት ሺህ ብር ነው::

ሁለት ጊዜ ቆጥሬ አምስት ሺህ ብር ሲሆንብኝ፣  “እናት ስንት ብር ነው የሰጠሽኝ?” ስል ጠየቅኋት::

“አምስት ሺህ ብር ነው የሰጠሁህ” አለችኝ፤ በጥያቄየ ግራ ተጋብታ እያስተዋለችኝ::

“እኔ እኮ ወጪ መጠየቂያ ቅጹ ላይ የጻፍሁት ሦስት ሺህ ብር ነው” አልኋት::  ይህን ስላት ድንግጥ ብላ ወጪ የጠየቅሁበትን ወረቀት ከመሳቢያው መዝዛ አወጣችው:: ወረቀቱን እያነበበች፣  “የቆረጥሁት እኮ ሦስት ሺህ ብር ነው” አለችኝ:: እኔም  ቆጠርሁና ትርፉን ሁለት ሺህ ብር መለስሁላት” በማለት ስለፈጸመው የታማኝነት ተግባር አጫወተኝ::

ታላቅነቱን አግዝፎ ያሳየኝን ይህን  ታሪክ ወዳጄ ሲነግረኝ፣ “ታማኝነት፣ የአዕምሮ ልዕልና፣ ለራስ ክብር መስጠት፣ ራስን ማሸነፍ፣ ገንዘብን መናቅ… ይሉሀል እንዲህ ነው! እንኳንም ጓደኛየ ሆንህ!…”  ስል ቀበጣጠርሁ:: ወዳጄም በአባባሌ ተገርሞ ይስቅብኝ ጀመር:: እሱ ሲስቅ፣ “ለመሆኑ ገንዘብ ከፋይዋ ወድዳና ፈቅዳ የሰጠችህን ገንዘብ ወደ ኪስህ በማስገባት ፋንታ ትርፍ ነው ብለህ ስትሰጣት ምን አለችህ?” ስል አድናቆት እንዲሁም ትችት የተቀላቀለበት ጥያቄ አቀረብሁለት::

“በድርጊቷ ደንግጣ ስለነበር ምንም  አላለችም፤ ባንጻሩም አጠገቤ ቆሞ የነበረ ጎልማሳ  ባድናቆት እየተመለከተኝ፣ “‘በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ታማኝ ሰው መገኘቱ የሚገርም ነው!’” በማለት አድናቆቱን ቸሮኛል” አለኝ::

“እንኳን ወደውና ፈቅደው እንካ ብለው የሰጡትን ገንዘብ ትርፍ ነው ብሎ ሊመልስ ሰው የደከመበትን ገንዘብ አንድ ሺህ አንድ የማታለያ፣ የማፍዘዣ እንዲሁም የማደንዘዣ ዘዴ እየፈጠረ  የሚመነትፈው በበዛበት በዚህ ዘመን ተሳስታ ጨምራ የሰጠችህን ገንዘብ በታማኝነት ስትመልስላት ብትደነግጥም አመሰግናለሁ ማለት ነበረባት”  ስል ገንዘብ ከፋይዋን ካንገት በላይ ወቀስሁ::

ሆኖም ወዳጄ ለሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ምስጋናን የሚሻ ሰው አልነበረምና፣ “ገንዘቡን የመለስሁላት ለራሴ መታመን ስላለብኝ፣ ለራሴ ክብር ስለምሰጥ እንጂ እሷ እንድታመሰግነኝ  አይደለም” አለኝ፤ ድርጊቱን አሁን የፈጸመው ያህል የደስታ ጸዳል በፊቱ ላይ እየበራ::

“ቢሆንም ምስጋና አይከፈልበት፤ ለሚደረግልን መልካም ነገር አመሰግናለሁ ብንል ምን ይጎዳናል?” በሀሳቤ ገፋሁበት::

“ትህትና መልካም ነው፤ ለሰው ትሁት በሆንን ቁጥር ውስጣዊ ደስታን፣ ርካታን፣ ሰላምን ነው የምናገኘው፤ ትልቅ ሰው መሆናችንን ነው የምናስመሰክረው:: ሆኖም ሁሉም ሰው ለሚደረግለት መልካም ነገር አመሰግናለሁ ማለት አልለመደበትም ወይም ለዚህ አልታደለም፤ ትህትናችንን ከፍርሃት፣ ታማኝነታችንን ከጅልነት የሚቆጥርብንም አይታጣም:: ስለሆነም ለሰዎች መልካም ነገር በፈጸምን ወይም ታማኝ ሆነን በተገኘን ቁጥር ከሰዎች ምስጋናን መጠበቅ የለብንም:: አንድ ጥሩ ነገር አድርገን ጥሩ ነገር ያደረግንላቸው ሰዎች እንዲያመሰግኑን የምንጠብቅ ከሆነ ሳያመሰግኑን በቀሩ ቁጥር  መልካም ነገር ከመፈጸም እየራቅን ነው የምንሄደው” ሲል አሳማኝ ሀሳብ አቀረበልኝ:: እኔም፣  “ለነገሩ አልሁህ እንጂ እሷ አመሰገነችህ አላመሰገነችህ የሚጨመርልህ ወይም የሚጎድልብህ ነገር የለም” በማለት ሀሳቡን መቀበሌን አረጋገጥሁለት::

“ለነገሩ እሷ ባታመሰግነኝም ለእሷ ያደረግሁት መልካም ነገር ከሁለት ወራት በኋላ ለእኔም ተፈጽሞልኛል” አለኝ፤ ወዳጄ በፈገግታ እያስተዋለኝ::

“መቼም ጫወታ አያልቅብህ፤  ምንድነው ደግሞ ላንተ የተፈጸመልህ?”  በፈገግታ ተውጬ ጠየቅሁት::

“ከሁለት ወራት በፊት ነው:: የግድግዳ ሰዓት ልገዛ ወደ ሱቅ ጎራ አልሁ፤ ዓይኔ ያረፈበትን ሰዓት በጣቴ እየጠቆምሁ፣ ያ ሰዓት ዋጋው ስንት ነው?” ስል  ጠየቅሁ::

“ሁለት ሺህ ብር ነው” ሻጯ ሰዓቱን እየተመለከተች መለሰችልኝ::

“ሁለት ሺህ ብር ውድ ነው፤ ቀንሽልኝና ልግዛው” አልኋት::

“አይቀንስም!” በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ሰጠችኝ::

እንደማትቀንስልኝ ስረዳ፣ “እሽ አውርጅው!” አልኋትና  አውርዳ ሰጠችኝ:: ከዚያም ባለ ሁለት መቶ ብር ሀያ ኖቶች ቆጥሬ ሰጠኋት:: ብሩን ተቀብላ ቆጠረችና፣ “ኧረ ይሄ ነገር በዛብኝ!” አለችኝ:: እኔም፣  “ሁለት ሺህ ብር ነው እኮ የሰጠሁሽ” አልኋት:: እሷ ግን በድጋሜ ቆጠረችና፣ “አራት ሺህ ነው የሰጠኸኝ” ብላ ሁለት ሺህ ብሩን መለሰችልኝ:: ሁለት መቶውን በመቶ ብር አስቤ በስህተት የሰጠኋትን  ትርፍ  ብር በታማኝነት ስለመለሰችልኝ ደጋግሜ  አመሰገንኋት::  በታማኝነቷ ደጋግሜ ሳመሰግናት እሷ ምን እንዳለችኝ ታውቃለህ?” ወዳጄ ሀሳቡን በጥያቄ ገታ አደረገ::

“ምን አለችህ?” ያለችውን ለመስማት ጓጉቼ ጠየቅሁት::

“የሰው ገንዘብ ምን ያደርግልኛል፤  የሰውን ገንዘብ ከገንዘቤ ጋር ብጨምረው የእኔንም ጭምር ነው ይዞብኝ የሚጠፋ ነው የሚመስለኝ” በማለት መለሰችልኝ::  እኔም ፈጣሪ እንደ እሷ ያሉትን ታማኝ ሰዎች እንዲያበዛልን እየተመኘሁ ገንዘቤንም ሰዓቴንም ይዤ ወደ ቤቴ ሄድሁ” አለና በርካታ ተነፈሰ::

ይሄ ደስ የሚል ታሪክ ነው:: እንደ ወዳጄና ሰዓት ሻጯ ነጋዴ ያሉ ታማኝ ሰዎች ዛሬም ቢሆን አልጠፉም:: ለሕሊናቸው ያደሩ፣ ለራሳቸው ክብርን፣ ለአእምሯቸው ልዕልናን ያልነፈጉ፣  የሰውን ገንዘብ የሚጠየፉ፣ ጥረው ግረው በላብ  በወዛቸው መኖርን የመረጡ ታማኞች ቁጥራቸው በጣት ቢቆጠርም አለመጥፋታቸው በእጅጉ ደስ ያሰኛል::

እነዚህን የመሳሰሉ ጥቂት ታማኝ ሰዎች መኖራቸውን ሳስብ በሀሴት ተሞልቼ፣  በስህተት ወደ እኔ የመጣን ገንዘብ በታማኝነት የእኔ አይደለም ብየ መልሼ እንደማላውቅ ሁሉ በወዳጄ መንፈሳዊ ቅናት እያደረብኝ ከመቀመጫየ ተነሳሁና ባድናቆትና ባክብሮት እያስተዋልሁት፣ “ነገ እልፍ ትሆናላችሁ!” አልሁት:: ጓደኛየም ሰዓቱን አየት አደረገና ከመቀመጫው በመነሳት እጁን ለስንብት እየዘረጋልኝ፣ “ጥርጥር የለውም፤ እንዳልከው ዛሬ በጣት የምንቆጠር ታማኞች ነገ እልፍ እንሆናለን!” አለኝ፤ በተስፋ ተሞልተን ደስ ተሰኝተን ተለያየን::

(አባትሁን ዘገየ  (ቦ.ዘ.አ.))

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here