ከዓለም አቀፉ የእንስሳት ሀብት ምርምር ተቋም (ILRI) የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የቁም እንስሳት ሀብት ልማት በተለይም በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሁለንናዊ ዕድገትን ለማምጣት መሠረት ነው። ዘርፉ ከቤት ውስጥ የምግብ ፍጆታ አልፎ እስከ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ አለው።
የበርካታ ሀገራት ዜጎች በቁም እንስሳት እርባታ በመሠማራት እንስሳትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል። ዘርፉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜገጎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ጊዜ ሲከፋ ደግሞ (በጎርፍ፣ በበረዶ፣ በድርቅ በርሃብና በሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምርት ሲወድም) እንስሳት ለአርሶ አደሩ የችግር መሻገሪያ መሰላሎች ናቸው፤ ለዚህም ነው እንስሳት ለገጠሩ ማሕበረሰብ “ተንቀሳቃሽ ባንክ” ናቸው የሚባለው።
በእንስሳት ሀብት ልማት የላቀ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት መካከል ብራዚል አንደኛዋ ናት። እንደ ብራዚል ፋርምስ ዶት ኮም መረጃ ብራዚል ሰፋፊ የግጦሽ መሬቶችን በሥርዓት ትጠቀማለች።፣ ከሀገሪቱ የአየር ንብረት ጋር የሚስማሙ የተሻሻሉ የከብት ዝርያዎችን በማላመድና በማራባትም ትታወቃለች። ዘመናዊ የእርድና የሥጋ ማሸጊያ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባትም ቀዳሚ ናት።
ብራዚል በዓለም ላይ የከብት ሥጋን በከፍተኛ መጠን ለውጭ ገበያ (Beef Export) በማቅረብ የዓለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን፣ ከ20 በመቶ በላይ የዓለምን የሥጋ ፍላጎትም ትሸፍናለች።
በግብርናው ዘርፍ ካላት ጠቅላላው የሀገር ውስጥ ገቢ (GDP) 30 በመቶ የሚሆነው ድርሻ ከእንስሳት ሀብት የሚገኝ ነው። ሀገሪቱ በዘርፉ ውጤታማ እንድትሆን ደግሞ ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፤ ቢሊዮን ዶላሮችን በመመደብ ዘርፉን ሳይንሳዊ ማድረጓ፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ልዩ ማበረታቻ (በዝቅተኛ ወለድ እና ሙሉ የመሠረተ ልማት ግንባታ) መስጠቷ እና ካደጉ ሀገራት ጋር ጠንካራ የገበያ ትስስር በመፍጠር የእንስሳት ሀብቷን ማስተዋወቅ መቻሏ ናቸው።
የብራዚል የእንስሳት ፕሮቲን ማሕበር እንዳስታወቀው ብራዚል በዓመት እስከ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን የከብት ሥጋ ወደ ውጭ ትልካለች። ሀገሪቱ በዶሮ ሥጋም የዓለም መሪ ስትሆን፣ በዓመት አምስት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የዶሮ ሥጋ ወደ ውጭ ገበያ ትልካለች።
በተመሳሳይ በዓመት እስከ ስድስት መቶ ሺህ የቁም ከብቶችን (በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ቱርክዬ) ትልካለች። በአጠቃላይ ብራዚል ከእንስሳት ተዋጽኦ የምታገኘው ገቢ በዓመት እስከ 20 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል። በአጠቃላይ ብራዚል በቁም እንስሳት ሀብት ልማት “የዓለም የሥጋ ቤት” እስከመባል ደርሳለች።
በእንስሳት ሀብት ልማት የላቀ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት መካከል ሌላኛዋ አውስትራሊያ ናት። ለቁም እንስሳት ግጦሽ የሚውል ሠፊ መሬት ካላቸው ሀገራት ቀዳሚዋ ናት። 330 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው (43 በመቶ የሀገሪቱ መሬት) መሬት ለእንስሳት ግጦሽ ይውላል።
ኤክስቴንሲቭ ግሬዚንግ (Extensive Grazing) የተባለውን ዘዴ ትጠቀማለች። ጥቂት ከብቶች በጣም ሰፊ በሆነ የግጦሽ መሬት ላይ ተለቀው እንዲሰማሩ የሚደረግበት ዘዴ ነው።
የአውስትራሊያን ልምድ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ካትል አውስትራሊያ ዶት ኮም አስገንዝቧል፤ ብሔራዊ የቁም እንስሳት መለያ ሥርዓትን መጠቀሟ ዋናው የስኬት ምስጢር ነው።
እያንዳንዱ እንስሳ ገና እንደተወለደ በጆሮው ላይ ኤሌክትሮኒክ ቺፕ (Microchip) ይገጠምለታል። የእንስሳውን የዘር ሐረግ፣ የወሰደውን መድኃኒትና የተሰማራበትን የግጦሽ ቦታ መረጃን በዝርዝር ይይዛል። መንግሥት እያንዳንዱ እንስሳ የኤሌክትሮኒክ መታወቂያ እንዲኖረው ሕግ አውጥቷል። ይህ ሥርዓት በእንስሳት ላይ በሽታ ቢከሰት እንኳ በደቂቃዎች ውስጥ ከየትኛው የግጦሽ መሬት እንደተከሰተ በመለየት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያስችላል።
የአውስትራሊያ መንግሥት ከምንም ነገር በላይ “የሀገሪቱን መልካም ገጽታ (Brand Image) ለመጠበቅ ሳይንሳዊ ቁጥጥርን ይጠቀማል። መንግሥት ሚት ኤንድ ሊቭስቶክ (Meat & Livestock Australia) የተባለ ተቋም እንዲመሠረት አድርጓል። ይህ ተቋም አዳዲስ የማድለቢያ ዘዴዎችንና የሥጋ ጥራት መለኪያ ሳይንሶችን በየጊዜው ይፈጥራል።
በተመሳሳይ ሀገሪቱ የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ በመላክም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች። በተለይ ወደ እስያና መካከለኛው ምሥራቅ በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ በጎችንና ከብቶችን በትልልቅ መርከቦች በመላክ ከፍተኛ ገቢ እንደምታገኝ ካትል አውስትራሊያ ዶት ኮም ላይ ያኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዓለም ቀዳሚዋ የበግ ሥጋ አቅራቢ (ኤክስፖርተር) ስትሆን፣ እ.አ.አ በ2024 359 ሺህ ቶን የፍየል እና 255 ሺህ ቶን የበግ ሥጋ ወደ ውጭ ኤክስፖርት አድርጋለች። ኢንዶኔዢያ ደግሞ 70 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን የቁም እንስሳት በመግዛት ቀዳሚዋ ሀገር ናት።
አውስትራሊያ የእንስሳት ሀብቷን በውድ ዋጋ ለመሸጥ የመንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደ ትልቅ የሽያጭ ወኪል ይሠራል፤ እንደ ቻይና፣ ጃፓን፣ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ካሉ ሀገራት ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ተፈራርሟል። ይህም ባለሀብቶቿ ምርታቸውን በዝቅተኛ ቀረጥ ወይም ከቀረጥ ነጻ እንዲልኩ ረድቷቸዋል።
እ.አ.አ በ2024 አውስትራሊያ አጠቃላይ ወደ ውጭ ከላከችው የሥጋ ምርትና የቁም እንስሳት 19 ነጥብ አምስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች።
ኔዘርላንድስ የእንስሳት ሀብት ልማትን በአግባቡ በመጠቀም ሌላኛዋ ተሞክሮ የሚወሰድባት ሀገር ናት፤ የሀገሪቱ መሬት በጣም ውድና አነስተኛ የሆነባት በመሆኗ፣ እያንዳንዱን ሴንቲ ሜትር መሬት በከፍተኛ ጥንቃቄ ትጠቀማለች። 900 ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት ለቁም እንስሳት ግጦሽ የሚውል ነው። ይህም ከሀገሪቱ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 22 በመቶ አካባቢ ነው፤ ከጠቅላላው የእርሻ መሬቷ ደግሞ ግማሹን ይይዛል።
በመሬት ስፋቷ አነስተኛ ብትሆንም በወተትና በወተት ተዋጽኦ በዓለም ሁለተኛዋ ኤክስፖርተር ናት። በጣም ከፍተኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም (ላሞችን በሮቦት ማለብ) እና የአንድን ላም የወተት ምርት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የላቀ ተሞክሮ አላት።
ኔዘርላንድስ በዓለም ላይ በተለይም በቅቤና አይብ ምርት የምትታወቅ ሀገር በመሆኗ የወተት ተዋጽኦ ንግሥት ወይም ዘ ዲዬሪ ፓወር ሐውስ እያሉ ይጠሯታል። በዓመት ከወተት ተዋጽኦ ኤክስፖርት ብቻ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች።
“ሮቦቲክ” የተሰኘ የእርባታ ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም የመጀመሪያዋ ሀገር ናት። ላሞቹ የሚታለቡት፣ የሚመገቡትና ጤናቸው የሚረጋገጠው በሮቦቶችና በሴንሰሮች (Sensors) አማካኝነት ነው።
በኢትዮጵያ አንዲት የሐበሻ ላም በቀን ከአንድ እስከ ሦስት ሊትር፣ በኔዘርላንድስ ደግሞ አንዲት ላም በቀን በአማካይ 30 ሊትር ወተት ትሰጣለች። ኔዘርላንድስ የእንስሳት ኩበትን መልሳ ማዳበሪያ በማድረግ መኖ ታመርትበታለች። ሁሉም ተረፈ ምርት ጥቅም ላይ ይውላል።
ኔዘርላንድስ ከሥጋ፣ ከወተት፣ ከእንቁላልና ከእንስሳት ዘር ሽያጭ በዓመት በአጠቃላይ ከ 25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች። ወተቱን ብቻውን ከመሸጥ ይልቅ፣ በዓለም ታዋቂ የሆኑ የ”ጉዳ” (Gouda) እና “ኤዳም” (Edam) አይቦችን በማምረት ዕሴት ጨምራ በውድ ዋጋ ትሸጣለች።
የሀገሪቱ መንግሥት “ትሪፕል ሄሊክስ” የተባለ የትብብር ሥርዓት ዘርግቷል፤ የተለያዩ ሕጎችን አውጥቷል። እነዚህ እና በሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች መመራቷ የስኬቷ ምስጢር ናቸው።
መንግሥት እያንዳንዱን ላም የሚከታተል ብሔራዊ የመረጃ ማዕከል አቋቁሟል። ማዕከሉ አንድ አርቢ ወይም አድላቢ የእንስሳቱን ጤንነት፣ የሚበላውን የመኖ መጠን እና የሚሰጠውን የወተት መጠን በተንቀሳቃሽ ስልኩ (በሞባይሉ) እንዲከታተል የሚያስችል ነው።
ኔዘርላንድስ ለገበያ ትስስር የምትጠቀመው የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ነው። ማኅበራቱ በአርሶ አደሮች ባለቤትነት የተያዙ በመሆናቸው የራሳቸውን ምርት ራሳቸው እንዲያቀነባብሩና ትርፉን እንዲካፈሉ አስችሏቸዋል።
የወተት ተዋጽኦን ጨምሮ የእንስሳት ዘርፉ ለሀገሪቱ በዓመት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪን ያስገኝላታል።
ኔዘርላንድስ በስፋቷ ከኢትዮጵያ በ25 እጥፍ የምታንስ ሀገር ናት፤ ይሁን እንጂ በ100 እጥፍ የሚበልጥ የሥጋ ገቢ ታገኛለች።
ኢትዮጵያ ልክ እንደ ብራዚል ሰፊ መሬትና ከፍተኛ የከብት ቁጥር አላት። ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሀብት በአፍሪካ ቀዳሚውን ቦታ ትይዛለች። ከሥጋ ኤክስፖርት የምታገኘው ገቢ ግን ከ100 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም። ይህም ብራዚል ካላት ገቢ ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ ገቢ ከብራዚል በ100 እጥፍ ያነሰ ነው።
ኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማትን በአግባቡ ለመጠቀምና ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጠቀሜታ እንዲኖረው ለማድረግ እንደ ብራዚል በብዛት ማምረት፣ ወይም እንደ አውስትራሊያ በጥራት መመራት አልያም ደግሞ እንደ ኔዘርላንድስ በማቀነባበር ላይ ማተኮር አለባት። የተቀናጀ የመኖ ልማትን ማሳደግ፣ የዝርያ ማሻሻልና ምርምር ተቋማትን ማጠናከርና ማስፋት፣ ዘመናዊ እንስሳት ጤና እና የክትትል ሥርዓትን መዘርጋት፣ ዕሴትን መጨመር፣ የኢንዱስትሪ ትስስር መፍጠር፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የግል ባለሀብቱን ማበረታታት ይገባል። ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር የገበያ ትስስርን መፍጠር ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
ሲ ጅ ቲ ኤን፣ ፍራንስ 24፣ አልጀዚራ እና የዓለም ባንክ ተጨማሪ የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።
መረጃ
ኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማትን በአግባቡ ለመጠቀም የተቀናጀ የመኖ ልማትን ማሳደግ፣ የዝርያ ማሻሻልና ምርምር ተቋማትን ማጠናከር፣ ዘመናዊ እንስሳት ጤና እና የክትትል ሥርዓትን መዘርጋት፣ ዕሴትን መጨመር፣ የኢንዱስትሪ ትስስር መፍጠር፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር የገበያ ትስስርን መፍጠር ይገባታል።
በተመሳሳይ ከብራዚል በብዛት ማምረትን፣ ከአውስትራሊያ በጥራት መመራትን እና ከኔዘርላንድስ ደግሞ ማቀነባበርን መሠረት ያደረጉ ተሞክሮዎችን መውሰድ ይገባታል።
(ቴዎድሮስ ደሴ)
በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


