ምርጫ የአንድን ሀገር የወደፊት አቅጣጫ፣ ሰላም እና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚወስን ትልቁ የፖለቲካ መድረክ ነው። ስልጣን በመሣሪያ ሳይሆን በድምፅ ወረቀት ብቻ እንዲሸጋገር በማድረግ ሀገርን ከትርምስና ከጦርነት ለመታደግ የዴሞክራሲ መሠረትም ነው። በተመሳሳይ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ በር ይከፍታል::
በአጠቃላይ ምርጫ ሕዝብ ድምጽን በመስጠት ለአምስት ዓመታት ሀገርን እንዲመራለት ይሁንታ የሚሰጥበት ኮንትራት እንደሆነ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት:: በርካታ ሀገራት ስኬታማ ምርጫን በማከናወን በአብነት የሚጠቀሱ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ ትጠቀሳለች።
ደቡብ አፍሪካ ለብዙ ዓመታት በዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት እና በከፍተኛ ግጭት ውስጥ ነበረች። እ.ኤ.አ በ1994 የተደረገው የመጀመሪያው ሁሉን አቀፍ ምርጫ ግን የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ እንደቀየረው የደቡብ አፍሪካ የታሪክ ትምህርት እና ምርምር ተቋም የሆነው ‘ሳውዝ አፍሪካ ሂስትሪ ኦንላይን’ (sahistory.org.za) በድረ ገጹ አስፍሯል::
ምርጫው የነጮች የበላይነት አብቅቶ ሁሉም ዜጋ እኩል ድምፅ እንዲኖረው ማድረጉንም መረጃው ያስገነዝባል:: የምርጫ ሂደቱም ሀገሪቱ ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ ታድጓታል። ለዚህም ነው ምርጫ ታሪካዊ ቁስሎችን ለመፈወስ፣ አዲስ ሀገራዊ ስምምነት ለመፍጠር እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ሁነኛ መሣሪያ ነው የሚባለው::
ምርጫ የሕዝብ ፍላጎት እና የመንግሥት አቅርቦት የሚገናኙበት ድልድይም ተደርጎ ይወሰዳል:: የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ለመያዝ ሲሉ የተሻለ ትምህርት፣ ጤና፣ ውኃ እና መሠረተ ልማት እንደሚያቀርቡ ቃል ይገባሉ። ይህ ውድድር አገልግሎቶች ጥራት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ተሞክሮ መሆን ትችላለች:: ሀገሪቱ ምርጫን ለኢኮኖሚ እና ዲሞክራሲ ግንባታ ማጠናከሪያ አድርጋ በመጠቀም በአርዓያነት ተጠቃሽ ናት::
ኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት (The Library of Congress) ድረ ገጽ እንዳስነበበው ደቡብ ኮሪያ እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ነበረች። ይሁን እንጂ በ1987 የተደረገው የዴሞክራሲ ሽግግር እና ተከታታይ ምርጫዎች ሀገሪቱን ወደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ኃያልነት ቀይረዋታል።
በምርጫ የሚመጡ መሪዎች ለሕዝብ ተጠያቂ መሆናቸው ሙስና እንዲቀንስ እና ግልጸኝነት እንዲሰፍን አድርጓል። ይህም የሀገሪቱ የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደረዳት የኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት መረጃ ያሳያል::
ምርጫ በኮሪያ መንግሥት ለማኅበራዊ ተቋማትና አገልግሎቶችም ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል። ተማሪዎች እና ሠራተኞች በምርጫ አማካኝነት ባደረጉት ግፊት መንግሥት ለትምህርት እና ለጤና ዘርፍ ከፍተኛ በጀት እንዲመድብ አስገድዷል።
የሀገራቱ ተሞክሮ የሚያሳየው ምርጫ ሰላምን ለማምጣት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት፣ በዓለም ላይ ተሰሚ (ተጽዕኖ ፈጣሪ) ሀገርን ለመፍጠር እንዲሁም ሰላማዊ ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር የሚያገለግል የሕጋዊ መሠረት ምሰሶ መሆኑን ነው::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያም 7ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በመጪው ግንቦት ወር ታካሂዳለች፤ ለዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረጉን አስታውቋል::
ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሲሆን ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ ዕምነት ይኖራቸዋል፤ ይህ ደግሞ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያም ለምርጫ የምትሰጠው ቦታ ከፍ ያለ መሆኑን ያለፉት ምርጫዎች ማሳያዎች ናቸው::
ኢትዮጵያ በሕዝብ በተመረጠ መንግሥት መመራት የጀመረችው ከንጉሣዊ ሥርዓት ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: መደበኛ ምርጫ መካሄድ የጀመረው ግን ከ31 ዓመታት በፊት እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል::
ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ፣ የመራጮች ምዝገባ እና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ:: በተለያዩ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎችም ለጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠናል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል::
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ድግሴ መንግሥት ሁሉም ዜጋ ድምጹ የሀገርን ዕጣ ፋንታ የሚወስን መሆኑን በማመን ያለ ማንም ቀስቃሽነት በንቃት መሳተፍ እንደሚገባው ተናግረዋል:: እርሳቸውም ለምርጫው አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል:: ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ሁሉ የምርጫ ካርድ በማውጣት ይወክለኛል የሚለውን መምረጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት:: ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል::
የአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበር የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፤ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት በድሩ ወንድሙ ታዛቢዎችን በማዘጋጀት አባላቱ በሚመደቡበት የምርጫ ጣቢያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲከናወን የበኩሉን እየሠራ እንደሚገኝ ነው የተናገረው::
ከዚህም ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች በተወዳዳሪነት እና በመራጭነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርቧል:: በምርጫ ወቅት ከሚተላለፋ ሃሰተኛ መረጃዎች መጠንቀቅ እና እውነተኛ መረጃን በመያዝ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከወጣቶች እንደሚጠበቅም መልዕክት ተላልፏል::
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለምርጫ የመወዳደር ምዝገባቸውን አጠናቀው ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት እያስተዋወቁ ይገኛሉ:: በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የካቲት 06 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ተወያይቷል፤ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ በኢትዮጵያ ታሪክ ሥልጣን ከካርድ የሚመነጭበት ልምድ እምብዛም ነው ብለዋል:: በመሆኑም ሥልጣን ከካርድ እንጂ ከጠብመንጃ የሚቀዳ አለመሆኑን በመረዳት ለሰላማዊ ምርጫ መሥራት ቀዳሚው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል:: “የምርጫ ውድድራችን የሕዝባችን ሰላም እና የሀገርን አንድነት እንዳያደፈርስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል”ም ብለዋል::
አቶ ተስፋሁን አክለውም “ምርጫ ካለ አሸናፊ እና ተሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ ይኖራል፤ ነገር ግን አሸናፊ ሀገር እና አሸናፊ ዴሞክራሲ መኖር አለበት፤ ለዚህ ደግሞ በጋራ መሥራት አለብን” ብለዋል። በመሆኑም ለምርጫው የሚደረግ ውድድር እና ቅስቀሳ ሰላምን የሚያደፍርስ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል::
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ማኒፌስቶውን እና የምርጫ ምልክቱን ይፋ አድርጓል:: የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የፓርቲው ራዕይ እና ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል:: ለብዝኀነት እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል::
“ያለፉት ዘመናት የኢትዮጵያ ትልቁ ጥማት ዴሞክራሲ ነበር” ያሉት አቶ ይርጋ ቋሚ እና የጸና የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት:: ፓርቲው ኢትዮጵያ ኋላቀርነትን፣ ድህነትን፣ ግጭትን እና ጦርነትን ተሻግራ ከፍ ብላ እንድትታይ እየሠራና፣ ሕዝብንም በፍትሐዊነት እያገለገለ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል::
አቶ ይርጋ ሲሳይ እንዳሉት ፓርቲው አንድነትን አጥብቆ የያዘ፣ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጅ ሕግን ለማስከበር እና ፍትሕን ለማስፈን እየሠራ ይገኛል:: በተጨማሪም ሰብዓዊ ልዕልናን፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እና የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገርን መፍጠር የፓርቲው አሁናዊ እና ቀጣይ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል::
በ7ኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲ ምልክት የስንዴ ነዶ መሆኑን አስታውቀዋል:: ስንዴ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ፣ ነዶውም የአንድነት እና የመተባበር ምልክት ስለመሆኑ አብራርተዋል:: ምርጫው ችግሮች የሚታረሙበት፤ አካሄዱም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል::
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊነትን እና ሀገራዊ አንድነትን በመላበስ ከድህነት እና ኋላቀርነት ለመላቀቅ፣ ግጭት እና ጦርነትን ለማስቀረት፤ ጸረ ዴሞክራሲ ሥነ ምኅዳርን በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ለመተካት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል:: “መጪው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና የሕዝብ ድምጽ የሚከበርበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት ይሠራል”ም ነው ያሉት::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ከቦርዱ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል:: ምርጫ ቦርድ 48 የፖለቲካ ፖርቲዎችን የምርጫ ምልክት አስተዋውቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከማድረግ ጀምሮ ዜጎች በዕውቀት ላይ ተመሥርተው ድምጻቸውን እንዲሰጡ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት ግንዛቤ ለመፍጠር ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል:: በተመሳሳይ በተዋረድ አስፈላጊ ጽ/ቤቶችን መክፈቱንም ቦርዱ አስታውቋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


