አማላይዋ ከተማ – ፓሪስ

0
255

ፓሪስ በዓለም ውቧ ከተማ ናት፤ “የብርሃን ከተማ” በመባል የሚታወቀው ዝናዋም ዓመቱን ሙሉ ቱሪስቶችን ይስባል። በፈረንሳይ ዋና ከተማ ውስጥ የሚታዩ እና የሚደረጉ ነገሮች እጅግ ብዙ በመሆናቸው ጥቂት ሰዓታት ብቻ አይበቁም። ታሪካዊ መታሰቢያዎች፣ ሙዚየሞች፣ የገበያ ስፍራዎች፣ መናፈሻዎች እና የምግብ አዳራሾች ለጎብኚዎች ሰፊ አማራጭ ያቀርባሉ። በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ በእግር በመንሸራሸር ወይም የተለየ ጭብጥ ባላቸው ጉብኝቶች ፓሪስን ማሰስ ይቻላል ።

የታላቋ ፓሪስ መታሰቢያዎች

ፓሪስ በመጠን ብቻ ሳይሆን በበለጸገ የሕንፃ ቅርሶቿም እፁብ ድንቅ ናት! የዋና ከተማዋ አንዱ ምልክት እና በጣም ታዋቂው ሐውልት በእርግጥ የኢፍል ታወር (Eiffel Tower) ነው ። ይህ ልዩ የሆነው “የብረት እመቤት” (Iron Lady) ለጎብኚዎች ተወዳዳሪ የሌለው እይታን ይሰጣል። ብዙም ሳይርቅ በተመሳሳይ መልኩ ታዋቂ የሆነው አርክ ደ ትሪምፍ (Arc de Triomphe) ይገኛል። በታሪክ የታሸገው ይህ ሐውልት  ፀሐይ በትልቁ ቅስት ውስጥ ስትጠልቅ በምታዩበት ብሩህ ቀናት ውስጥ እጅግ ያብረቀርቃል ።

ሌላው መታየት ያለበት የኖትር ዳም ደ ፓሪስ (Notre-Dame de Paris) ካቴድራል አስደናቂ ትርኢት ያቀርባል ። በዚህ የጎቲክ ስነ-ሕንፃ ጥበብ ውስጥ ያሉት ቅርጻ ቅርጾች፣ ግንቦች እና ምድር ቤት (crypt) እንኳን ሊደነቁ የሚገባቸው ናቸው ። በተመሳሳይ ሁኔታ ቀስቃሽ እና የጸሐፊዎች እንዲሁም የፊልም ባለሙያዎች መነሳሻ የሆነው የሳክሬ-ኩዌር ባሲሊካ (Sacré-Coeur Basilica) በፈረንሳይ ውስጥ ትልቁ የሞዛይክ ጥበብ መገኛ ሲሆን በሞንትማርት (Montmartre) ሰፈር አናት ላይ አስገራሚ እይታን ይሰጣል።

 

የፓሪስ ገናና አደባባዮች

ፕላስ ደ ላ ኮንኮርድ (Place de la Concorde): ሁለት ምንጮች፣ የአምድ ምሰሶዎች እና አስደናቂው የሉክሰር ኦቢሊስክ (Luxor Obelisk) የሚገኝበት። ፕላስ ደ ላ ባስቲል (Place de la Bastille): የታዋቂው የጁላይ አምድ (የአብዮቱን ቀናት የሚያስታውስ) እና በጣም ዘመናዊው የፓሪስ ብሔራዊ ኦፔራ መገኛ ነው።

ፓሪስ ከሚያስደንቁ ሐውልቶቿ በተጨማሪ የብዙ ሙዚየሞች መኖሪያ ናት። ከዓለማችን ስለ ሉቭር (Louvre) ያልሰማ ማን አለ? ይህ አስደናቂ ሕንፃ በሚያስደንቅ ስነ-ሕንፃው እና በመስታወት ፒራሚዱ ለሁለት ክፍለ ዘመናት በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ ሙዚየሞች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። በ8 ክፍሎች ውስጥ 35 ሺህ የጥበብ ስራዎች ያሉት ሲሆን 652,000 ስኩዌር ጫማ ስፋት ያላቸው ክፍሎች ለቋሚ ስብስቦች ተመድበዋል።

የሙሴ ዲ ኦርሴ (Musée d’Orsay) በቀድሞ የባቡር ጣቢያ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በትልቁ ሰዓቱ እና በኢምፕሬሽኒስት የጥበብ ስብስቦቹ ይታወቃል። የበለጠ እንግዳ የሆነ ነገር ይፈልጋሉ? ከ420,000 ስኩዌር ጫማ በላይ ስፋት ያለው እና የአፍሪካ፣ አሜሪካ፣ እስያ እና ኦሺኒያ ሀገር በቀል ጥበብ እና ባህሎችን የሚያሳየው ዱ ኳይ ብራንሊ (Musée du Quai Branly) ሙዝየም ደግሞ ሌላው የፓሪሰ ሀብት ነው።

ሲቴ ዴ ሳይንስ ወጣቶችንም ሆኑ አዋቂዎችን የሳይንስን ምስጢራት እንዲያውቁ ወደሚጋብዘው ላ ቪሌት (La Villette) ያምሩ። ሙዚየሞቹ በጣም የተለያዩ እና ብዙ በመሆናቸው ስለእነሱ በጥቂት መስመሮች ብቻ መጻፍ አስቸጋሪ ነው።

 

የፓሪስ የኑሮ ዘይቤ

ፓሪስ ለመጎብኘትም ሆነ ለመኖር ማለፊያ ስፍራ ናት። ልዩ የኑሮ ዘይቤዋን ሳያጣጥሙ ከፓሪስ አይወጡም። በፓሪስ ቢስትሮ በረንዳ ላይ ቡና መጠጣት የሕዝቡ የተለመደ እና የተወደደ ልማድ ነው። በቢራ ፋብሪካ ውስጥ ምሳ መብላት ከሕዝቡ የተለመደ እና ተወዳጅ ተግባራት አንዱ ነው።

በታወቁ ሬስቶራንቶች ውስጥ እራት መመገብ ወይም የዓለማቀፍ ምግቦችን የሚያቀርቡ ቦታዎችን መቃኘት እና እንደ ሩ ዴ ሮዚየር (Rue des Rosiers) ፋላፌል ወይም ሞንትፓርናስ የብሬተን ጋሌት ያሉ የሀገር ውስጥ ምግቦችን በጉዞ ላይ መቅመስ የእለት ተለት ተግባር ነው።

በፋሽን ዋና ከተማዋ ፓሪስ ከተማ ውስጥ ለገበያ (Shopping) ጊዜ መድበው ግብይት ሳያደርጉ መውጣት አንዳች ነገር እንዳጎደሉ ይሰማዎታል። እንደ ሌስ ሃልስ (Les Halles) እና ሞንትፓርናስ ያሉ የገበያ ማዕከላት፣ እንዲሁም እንደ ለ ፕሪንታምፕ (Le Printemps) እና ጋለሪ ላፋዬት (Galeries Lafayette) ያሉ ትላልቅ መደብሮች ብዙ አማራጮችን ይሰጣሉ።

በመጨረሻም ፓሪስ ወደ 330ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች እና ወጣት ባለሙያዎች ያሏት የወጣቶች ከተማ ናት። ይህ በታሪክ፣ በዘመናዊነት እና በጊዜ የማይገደብ ውበት የተሞላች አስማታዊ ከተማ ሁሉንም ሰው ትማርካለች። ልምዱ መቼም ቢሆን አንድ ዓይነት ባለመሆኑ ደጋግሞ ወደ ፓሪስ ለመመለስ ብዙ ምክንያቶች አሉ።

ምንጭ: ኦል ስዊትስ (All Suites)

አጫጭር እውነታዎች

አጫጭር እውነታዎች ስለ ፈረንሳይ

  • ፈረንሳይ በዓለም ላይ በጣም ብዙ ጎብኚዎች የሚመጡባት ሀገር ናት። በየዓመቱ በአማካይ ከ80 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይጎበኟታል።
  • ፈረንሳይኛ ቋንቋ በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በ29 ሀገራት ውስጥ የሥራ ቋንቋ ነው። እንዲሁም ከእንግሊዝኛ ቀጥሎ በሁሉም አህጉራት የሚነገር ብቸኛው ቋንቋ ነው።
  • በፈረንሳይ በየዓመቱ 10 ቢሊዮን ገደማ “ባጌት” (Baguette) የተሰኙ ረጅም ዳቦዎች ይመረታሉ።
  • ሀገሪቱ ከ1,600 በላይ የተለያዩ የአይብ አይነቶችን ታመርታለች።
  • በፈረንሳይ ሱፐርማርኬቶች የተረፈ ምግብ መጣል በህግ የተከለከለ ነው። በምትኩ ለድሆች መርጃ ድርጅቶች መስጠት አለባቸው።
  • ፈረንሳይ በተለያዩ የባህር ማዶ ግዛቶቿ ምክንያት 12 የተለያዩ የሰዓት ቀጠናዎች አሏት። ይህም ከአለም አንደኛ ያደርጋታል።
  • የፈረንሳይ ንጉሥ የነበሩት ሉዊስ 19ኛ ለ20 ደቂቃ ብቻ በመንገሥ የአለማችን አጭር የንግሥና ጊዜ ባለቤት ናቸው።
  • መጀመሪያ ላይ ለ20 ዓመታት ብቻ እንዲቆይ ተደርጎ የተሠራ ቢሆንም፣ አሁን ግን የሀገሪቱ ዋነኛ ምልክት ሆኖ ቀጥሏል።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here