የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ዳኝነት ማን ይታደገዋል?

0
169

በዘንድሮው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ውድድር ተጀምሯል። የመጀመሪውን ዙር  ፉክክር ያደበዘዘው የዳኝነት ስህተት ጉዳይ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ከስታዲየም እስከ ማህበራዊ ሚዲያ  መነጋገሪያ አድርጎት እንደነበር አይዘነጋም። በመጀመሪያው ዙር ውድድር በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ የታዩ ግልጽ የዳኝነት ስህተቶች የክለቦችን ልፋት፣ የአሰልጣኞችን ስልት እና የደጋፊውን ተስፋ አበላሽቶት አልፏል። በሀገሪቱ ትልቁ የሊግ እርከን የዳኝነት ችግር ተፈጥሯዊ ስህተት ከመሆን አልፎ ወደ ስርዓታዊ ቀውስ የተሸጋገረው ለምንድን ነው? የሚለው አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ጥያቄ ነው።

በመጀመሪያው ዙር የታየው የዳኝነት አፈጻጸም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የሊግ አክሲዮን ማኀበሩ ቆም ብለው ማሰብ ያለባቸው ደረጃ ላይ መድረሱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ስህተት የሰው ልጅ ተፈጥሮ አካል ቢሆኑም በተደጋጋሚ እና በወሳኝ ሰዓት የሚፈጠሩ የዳኝነት ክፍተቶች ግን የውድድሩን ተአማኒነት እየሸረሸሩት ይገኛሉ። የእግር ኳስ ሜዳዎች የደስታ እና የክህሎት ማሳያ መሆን ሲገባቸው በዳኞች የውሳኔ ግድፈት ምክንያት የውዝግብ ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል። በተለይም በመጀመሪያው ዙር ውድድር አስራ ሰባተኛው ሳምንት  ድረስ በነበሩት መርሐ ግብሮች ላይ በዋና ዳኞች እና በረዳት ዳኞች መካከል የነበረው የሃሳብ መለያየት እና አለመግባባት በግልፅ ሲታይ ተመልክተናል:: ይህ የዳኞች ስህተት በእጅጉ ጎልቶ መታየቱ የብዙ ክለቦች፣ የተጫዋቾች፣ የአሰልጣኞች እና የሚሊዮኖች የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዋነኛ የቅሬታ ምንጭ ሆኖል።

ክለቦች ለወራት የለፉበት፣ አሰልጣኞች ሌት ተቀን ስልት የነደፉበት እና ተጫዋቾች ላባቸውን ያፈሰሱበት ውጤት በአንድ ዳኛ የተሳሳተ ፊሽካ ሲቀለበስ ማየት እጅግ አሳዛኝ መሆኑን አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ከጨዋታ በኋላ በሚሰጡት አስተያየት መረዳት ይቻላል። እናም በርካታ ትልልቅ ክለቦች ትዕግስታቸው ተሟጦ በዳኞች ውሳኔ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ በይፋ እና በፅሁፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ለፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር እስከማሳወቅ ደርሰዋል።

ለአብነት አንጋፋው የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ በተደጋጋሚ በጨዋታዎቹ ላይ በሚታዩ የዳኝነት ስህተቶች ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ካሰሙት ክለቦች አንዱ ነው። ክለቡ በተለይም በቅርቡ በውጤቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የፈጠሩ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን አጥብቆ በመቃወም ለብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ይፋዊ አቤቱታ አቅርቧል። ከዚህ ቀደምም ክለቡ በሸገር ደርቢ ላይ በነበረው ደካማ የዳኝነት አፈፃፀም ምክንያት አቤቱታ በማቅረቡ በዳኞች ላይ የእገዳ እርምጃዎች መወሰዳቸው የሚታወስ ነው።

ሌላው  የዘንድሮው የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነው ፋሲል ከነማ የዳኝነቱን ጥራት አጥብቆ ከኮነኑ እና ቅሬታቸውን በይፋ ካሳወቁ ክለቦች ውስጥ ቀዳሚው ነው። የፋሲል ከነማ አመራሮች የዳኞች ስህተት የክለቡን ነጥብ እያሳጣ፣ የተጫዋቾችን ስነ ልቦና እየጎዳ እና የደጋፊውን ልፋት መና እያስቀረ መሆኑን በመጥቀስ ፌዴሬሽኑ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ማሳሰባቸው አይዘነጋም።

መቐለ 70 እንደርታ በበኩሉ የዳኞች የውሳኔ አሰጣጥ ወጥነት የጎደለው መሆኑን እና ተደጋጋሚ ስህተቶች በክለቡ ላይ እየተሰሩ መሆኑን በመቃወም ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቷል። በአስራ ሰባተኛው ሳምንት መርሀግብር ኳስ በእጅ ተገጭቶ የተቆጠረን ግልፅ ህገ ወጥ ግብ ዳኞች ሳያዩት ቀርተው በማፅደቃቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ሳይቀር ያስቆጣ እና አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ያስገደደ አነጋጋሪ ክስተት መፈጠሩ አይዘነጋም። ይህ የዳኝነት ችግር በተለይም ፋሲል ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ በዳኝነቱ ደረጃ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ቅሬታ እና ተቃውሞ በይፋ እንዲያሰሙ እና ትዕግስታቸው መሟጠጡን እንዲያሳውቁ ገፊ ምክንያት ሆኗል።

የዲስፕሊን ግድፈቶቹን መበራከት እና የክለቦችን ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ከቁጥጥር ውጪ መሆንን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዝምታውን በመስበር ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ከዳኞች ጋር አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ተገዷል። የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከዚህ በኋላ ለሚፈጠሩ ግልፅ የዳኝነት ስህተቶች ተቋማቸው ምንም ዓይነት ትዕግስት እንደሌለው  በማያሻማ ቋንቋ ተናግሯል። አቤቱታ የቀረበባቸው እና ግልፅ ስህተት የሰሩ ዳኞች ጨዋታ እንዳይመሩ እና ወደ ቤታቸው እንዲመለሱም እርምጃ ተወስዷል።

በጎንደር ዩንቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪው አቶ አዲስዓለም ምህረት ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ በመጀመሪያው ዙር ችግሩ ከዳኞች አቅም ማነስ አልፎ በስርዓቱ እና በውሳኔ ሰጪ አካላት ላይ ጭምር የሚታይ መሆኑን አስረድቷል። አቶ አዲስዓለም “ቀልቤን የሳቡኝ የዳኝነት ጨዋታዎችን አላውቅም” በማለት በመጀመሪያው ዙር ውድድር በነበረው የዳኝነት ውሳኔዎች ቅር መሰኘቱን ተናግሯል። በሜዳ ላይ የሚታዩት የዳኝነት ውሳኔዎች ተመልካችን ጭምር ግራ የሚያጋቡ እና ከእግር ኳስ ሕግጋት ያፈነገጡ መሆናቸውንም ያስረዳል።

ስህተቶች ሲፈጠሩ በቪዲዮ ታግዞ ለማረም እና ውሳኔዎችን ለመቀልበስ ኮሚቴው በራሱ ሕግ መታሰር እንደሌለበት ሞግተዋል። የዳኞች የአካል ብቃት፣ የጨዋታ ንባብ እና በሜዳ ላይ ያላቸው አቋቋም ዋነኛ ችግሮች ናቸው። ዳኝነት የሕግ እውቀትን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ አዕምሯዊ ንቃት እና አካላዊ ጽናትን የሚጠይቅ ሙያ ነው። ነገር ግን አብዛኛዎቹ የፕሪሚየር ሊጉ ዳኞች ኳስን በቅርበት የመከታተል ትልቅ ክፍተት እንዳለባቸው የስፖርት ሳይንስ መመህሩ ይመሰክራል። “አብዛኛዎቹ ዳኞች ኳስ አይከታተሉም (አያዩም)፤ በቅርበት ሆነው ጨዋታን ለመምራት ሲሞክሩም አይስተዋሉም። በአምስት ወይም በስድስት ሜትር  ካልሆነ ደግሞ እስከ ስምንት እና ዐስር ሜትር ቀርበው ዘጠና ደቂቃ መጨረስ አለባቸው” ይላል አቶ አዲስዓለም።

የአብዛኞቹ ዳኞች አካላዊ አቅም በጨዋታው መገባደጃ ላይ በእጅጉ እንደሚዳከም እና ለከፋ ስህተት እንደሚጋለጡም የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አልሸሸገም። የዳኞች ከሜዳ ውጪ ያለው የግል ህይወት እና ራሳቸውን በዘመናዊ እውቀት ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት ጨዋታን የመምራት ብቃታቸው ላይ ቀጥተኛ እና የማይካድ ተጽዕኖ አለው ተብሎ ይታመናል። ዳኞች አሁንም የዳኝነት ሥራን እየሰሩ ያሉት በትርፍ ጊዜያቸው አነስተኛ በሆነ ክፍያ ነው። ዳኞች ከኑሮ ውድነት እና ከአነስተኛ ክፍያ ጋር እየታገሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ዋጋ ያላቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ትኩረት እና በንጽህና እንዲመሩ መጠበቅ ችግሩን አግዝፎታል። የደመወዝ ማነስ እና ሙያው የሙሉ ጊዜ አለመሆን ለአጭበርባሪዎች (Match Fixers) ኢላማ ሊሆኑ ይችላል የሚል ስጋትን ይፈጥራል።

የውሳኔ ስህተቶች የሜዳ ላይ ጭቅጭቆችን ከማብዛት ባለፈ የጨዋታውን ውበት ያጠፋሉ።  ዳኞች  በጥርጣሬ እና በውጥረት ውስጥ ሆነው እንደሚዳኙ ጭምር ያብራራል። ዳኝነት አካላዊ ብቃትን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ስነ ልቦናን ይጠይቃል። በጨዋታው መጀመሪያ ላይ ጥሩ ሆነው ይጀምሩ እና የተመልካች ጩኸት ወይም የተጫዋቾች ተቃውሞ ሲበዛባቸው የመደነባበር፣ ውሳኔ የመቀልበስ እና ሚዛናዊነት የማጣት ችግር ውስጥ ይገባሉ። ከስታዲየም ደህንነት ጥበቃ ማነስ ጋር ተያይዞ በደጋፊዎች ጸያፍ ስድብ እና ዛቻ ሲሸማቀቁም በተደጋጋሚ ይታያሉ። አንድ ዳኛ “ፍጹም ቅጣት ምት ብሰጥ ከስታዲየም በሰላም እወጣ ይሆን?” የሚለው ጥያቄ እንደሚያስጨንቃቸውም አቶ አዲስዓለም ተናግሯል።

በሀገራችን እግር ኳስ የፍትሃዊ ጨዋታ እሴት መጥፋትም ለዳኞች ሥራ መክበድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። “ፍትሃዊ ጨዋታ (Fair play) የሚባለው እኮ እኛ ሀገር የለም፤ ጥፋት ሳይሰራባቸው ወድቀው የማስመሰል እና ውሳኔ የማስቀየር አዝማሚያ ምን ያህል ስር እንደሰደደ እንደመጣ የአደባባይ ሀቅ ነው። በአውሮፓ እግር ኳስ ተጫዋቾች የራሳቸውን ስህተት ሲገነዘቡ የሚያሳዩት እርጋታ እና በሀገራችን ተጫዋቾች ዘንድ የሚታየው ያልተገባ ጩኸት ፍጹም ተቃራኒ መሆኑንም የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ያስረዳል።

ስህተት የሚሰሩ ዳኞችን ለሳምንታት ከውድድር ማገድ እስካሁን ችግሩን አልፈታውም፤ ወደፊትም አይፈታውም። ቅጣቱ ዳኞችን ከማረም ይልቅ በራስ መተማመናቸውን እያጠፋ ለባሰ ስህተት ይዳርጋቸዋል ተብሏል። ዳኞች እርስ በእርስ የሚግባቡበት የመገናኛ ወይም የኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች አለመኖር ሥራቸውን በእጅጉ አክብዶታል። አሁን ግን የዳኞችን ሥራ ለማቅለል እና ስህተትን ለመቀነስ ፌዴሬሽኑ ዘላቂ መፍትሄዎችን መፈለግ ጀምሯል። የኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች ወይም የመገናኛ ሬድዮኖች ግዢ ሂደት እንዲፈጸም መደረጉን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል። በተጨማሪም ዘመናዊ እግር ኳስ እጅግ ፈጣን እና በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ውስጥ ውሳኔ የሚፈልግ ዘርፍ በመሆኑ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል ነው የተባለው። “እውን  የስታዲየሞቻችን የመሰረተ ልማት ደረጃ ለዚህ ዝግጁ ነው ወይ?” የሚለው መዘንጋት የለበትም ባይ ነው- የስፖርት ሳይንስ መምህሩ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ሲጀመር ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ላለመግባት ግልጽ እና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መፍትሄዎች ያስፈልጉታል። ክለቦች ትኩረታቸውን ከዳኛ ውሳኔ ላይ አንስተው በራሳቸው አቅም፣ ታክቲክ እና ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ ላይ እንዲያደርጉ አቶ አዲስዓለም ይጠቁማል። የዳኞችን ክፍያ ማሻሻል፣ ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ ማሳደግ እና የስልጠና አሰራሮችን መዘርጋት ይገባልም ብሏል አቶ አዲስዓለም። ዳኞች ራሳቸውን በአካል ብቃት፣ በቋንቋ እና በቴክኖሎጂ እውቀት ሊያጎለብቱም ይገባል- የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አስተያየት ነው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here