እግር ኳስን የተጠናወተው በሽታ

0
169

የአውሮፓ እግር ኳስ በዓለማችን ላይ እጅግ ተወዳጅ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚንቀሳቀስበት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን በየሳምንቱ ከቴሌቪዥን መስኮት እና ከስታዲየም ጋር የሚያስተሳስር ግዙፍ ኢንዱስትሪ ነው። በዚህ ተወዳጅ ስፖርት በግልጽ በወረቀት ላይ ያልሰፈረ ነገር ግን በሚሊዮኖች ዘንድ በተግባር የሚታይ አንድ  ክብረ ነክ እና ስውር ተግባር አለ። ይህ ተግባር ከዘረኝነት  የሚመነጭ ነው፡፡ በዘመናዊው የእግር ኳስ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ጥቁር የዘር ሐረግ ያላቸው ተጫዋቾች የሚከበሩት በዕለታዊ አቋማቸው ጥሩ ውጤት ካሳዩ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ጥሩ ውጤት ካላሳዩ  በተለያየ መንገድ ክብራቸው ይነካል፡፡ ነጭ ተጨዋቾች ግን በጨዋታ ወቅት ብቃት ኖራቸውም አልኖራቸውም ክብራቸው በፍጹም አይነካም፡፡

በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ በተለይም በጥቁር እና አፍሪካውያን ተጫዋቾች ላይ የሚደርሰው ይህን መሰሉ የዘረኝነት ጥቃት የዘመናዊው እግር ኳስ ትልቁ ጥቁር ነጥብ ሆኖ ቀጥሏል። ምንም እንኳን ስፖርቱ በዘመናዊነት፣ በቴክኖሎጂ እና በፋይናንስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም ዘረኝነት እስካሁን ሊጠፋ ያልቻለበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው  በብዙዎቻችን አዕምሮ የሚመላለስ ጥያቄ ነው። እግር ኳስ  የማህበረሰቡ ትልቁ መስተወት ነው፡፡ እናም ጉዳዩን ከስፖርታዊ ብቻ ሳይሆን  ከማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ስነ-ልቦናዊ አቅጣጫዎች መመርመር ግድ እንደሚል የኪክ ኢት አውት መረጃ ያስነብባል።

መረጃዎችን አገላብጠን የችግሩን ስር መሰረት ስንመረምር በስታዲየም ውስጥ የሚሰማው የጥላቻ ድምፅ ከስታዲየሙ ውጭ ካለው እውነተኛው ዓለም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን እንረዳለን። በስታዲየም ውስጥ የሚታየውን ዘረኝነት ጥቂት ስነ ምግባር የጎደላቸው እግር ኳስ ደጋፊዎች  የፈጠሩት ጊዜያዊ ወይም ድንገተኛ ክስተት ብቻ አድርጎ ማሰብ ትልቅ የዋህነት ነው። ጉዳዩ ከዚህም የጠለቀ እና በአጠቃላይ በአውሮፓ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ነባራዊ የፖለቲካ እና የማህበራዊ  እውነታ የሚያንፀባርቅ ነው።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  በብዙ የአውሮፓ ሀገራት እያደገ የመጣው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ፣ የፀረ ስደተኛ አመለካከት እና የብሔርተኝነት ቀጥተኛ ነፀብራቅ መሆኑን ዘ አትሌቲክ ዘግቧል። በአሁኑ ወቅት አውሮፓ በከፍተኛ የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ማዕበል እየታመሰች ነው። እግር ኳሱ ደግሞ ከሰፊው የአውሮፓ ፖለቲካ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።  በጣሊያን፣ በፈረንሳይ፣ በኔዘርላንድስ እና በጀርመን “ሀገራችንን እናስመልስ” የሚሉ   ስደተኞችን እንደ ጠላት የሚመለከቱ ፓርቲዎች ስልጣን እየያዙ ነው።

የእግር ኳስ ስታዲየሞች ደግሞ የዚህ ፖለቲካዊ ስሜት ማስተንፈሻ መድረኮች ሆነዋል። አንድ ደጋፊ ስታዲየም ገብቶ ጥቁር ተጫዋች ላይ ሙዝ ሲወረውር እየወረወረ ያለው በተጫዋቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገሩ ውስጥ እየበዙ ነው ብሎ በሚያስበው ስደተኞች ላይ ጭምር ነው።

በብዙ የአውሮፓ ከተሞች ስደተኞችን እና የውጭ ዜጎችን እንደ ስጋት የሚቆጥረው የፖለቲካ ትርክት ደጋፊዎች  በተጋጣሚ ቡድን ጥቁር ተጫዋቾች ላይ የፈለጉትን ያደርጉ ዘንድ ድፍረት ሰጥቷቸዋል። ዘረኝነት በደማቸው ሰርጾ ያሰከራቸው የእግር ኳስ ደጋፊዎች የተጫዋቾችን ድንቅ ተሰጥኦ፣ ጥረት እና ሜዳ ላይ የሚያፈሱትን ላብ ወደ ጎን በመተው በቆዳ ቀለማቸው እና የመጡበትን ሀገር መሰረት አድርገው ብቻ ጥቃት ያደርሱባቸዋል።

ጥቁር ተጫዋቾች ግብ በማስቆጠር ክለቦች ለድል ሲበቁ “ጀግናችን” ይባላሉ፡፡  ትንሽ ስህተት ሲሰሩ፣ ኳስ ሲበላሽባቸው፣ ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት ሲስት ወይም ቡድኑ ሲሸነፍ በአስነዋሪ ተግባር ምላሽ ይሰጣቸዋል። ማንነታቸውን ከዝንጀሮ አሳንሰው ስደተኛ እና መጤ መሆናቸውም ይነገራቸዋል።   እ.አ.አ በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ  እንግሊዛውያኖቹ ማርከስ ራሽፎርድ፣ ጄደን ሳንቾ እና ቡካዮ ሳካ የፍፁም ቅጣት ምት በመሳታቸው ስቴዲየም ውስጥ እና በማህበራዊ ሚዲያ የደረሰባቸው የዘረኝነት ጥቃት ትልቅ መነጋገሪያ እንደነበር አይዘነጋም። ጥቁር ተጫዋቾች ከሌሎች ነጭ አቻዎቻቸው በተለየ መልኩ እንከን አልባ እንዲሆኑ እና ስህተት የማይሰሩ መሆን እንዳለባቸው አውሮፓውያን ዘረኞች ያምናሉ፤ ይህም በማህበረሰቡ ያለውን የተዛባ እና ፍትሃዊ ያልሆነ ሚዛን በጉልህ ያሳያል።

እንደ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዩኤፋ) እና የተለያዩ የሀገር ውስጥ የሊግ አስተዳዳሪዎችን የመሰሉ አካላት በተደጋጋሚ “ለዘረኝነት ቦታ የለንም” (No to Racism) የሚል ዘመቻ ቢያደርጉም ለውጥ ሊመጣ ግን አልቻለም። በዘረኝነት ድርጊት በሚሳተፉ ደጋፊዎች እና ክለቦች ላይ የሚጣልባቸው ጥቂት የአስር ሺህ ዩሮዎች ቅጣት ወይም  ጨዋታዎችን በዝግ ስታዲየም እንዲካሄዱ ማድረግ አጥፊዎችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና እንዲጸጸቱ አላደረገም። በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ታላላቅ ክለቦችን ጥቂት ሺህ ዩሮዎችን መቅጣት ቀልድ እና ስላቅ ከመሆን አያልፍም። አጥፊዎችም ይህን የላላ እና ለታይታ ብቻ የሚደረግ ሕግ ስለሚያውቁ ድርጊታቸውን በተለያዩ ስታዲየሞች በድፍረት እየደገሙት እንደሚገኙ የኪክ ኢት አውት መረጃ ያስነብበናል።

አንድ ክለብ ደጋፊዎቹ ለሚያሳዩት ፀረ ሰብአዊ ባህሪ ዋጋ እንደሚከፍል፣ በነጥብ ቅነሳ ምክንያት ከሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ እንደሚወድቅ ወይም የሊግ ዋንጫ እንደሚያጣ ካወቀ ራሱ ክለቡ ዘረኛ ደጋፊዎችን ከስታዲየሙ ጠራርጎ ለማስወጣት እርምጃ ይወስዳል። ነገር ግን ተቋማቱ ይህንን ለማድረግ የሚያቅማሙት ከፋይናንስ፣ ከስፖንሰርሺፕ እና ከቴሌቭዥን ስርጭት መብቶች ጋር በተያያዘ የራሳቸው ጥቅም እንዳይነካ በመስጋት መሆኑ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ፣ ግብዝነት የተሞላበት እና ተቋማዊ ድጋፍ ያለው አስመስሎታል።

የዚህ ሁሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ድክመት ቀጥተኛ ሰለባ የሚሆኑት ደግሞ ሜዳ ውስጥ የሚገቡት ተጫዋቾች ናቸው። በተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ የሆኑ ተጫዋቾች የሚገቡበት የስነ ልቦና ጫና እና ውጥረት እጅግ ከባድ እና በቃላት ለመግለፅ የሚከብድ ነው። የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ቪኒሺየስ ጁኒየር በተለያዩ ስታዲየሞች ሲጫወት የሚደርስበት የተደራጀ የዘረኝነት ጥቃት፣ በጣሊያን ሴሪ ኤ ሮሜሉ ሉካኩን እና ካሊዱ ኩሊባሊን ጨምሮ በርካታ አፍሪካውያን እና ጥቁር ተጫዋቾች በየሳምንቱ የሚያሳልፉት የስነ ልቦና ጦርነት እግር ኳስ የስርዓቱ ውድቀት ማሳያ ነው።

ይህ የስነ ልቦና ጫና በተጫዋቾቹ የሜዳ ላይ ብቃት፣ የውሳኔ አሰጣጥ እና የፈጠራ ችሎታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከማሳደሩም ባለፈ በውስጣቸው በቀላሉ የማይሽር አደገኛ ቁስል ፈጥሮ ያልፋል። አንዳንድ ተጫዋቾቹ ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሜዳ ላይ እንባ ሲያነቡ፣ አልያም ለጥቃቱ በምልክት ወይም በንግግር ምላሽ ሲሰጡ ደግሞ ራሳቸው ዳኞች በቢጫ ወይም በቀይ ካርድ ሲቀጧቸው መመልከት የሕጉን መዛባት በግልፅ ያሳያል። ሰለባውን መልሶ ወንጀለኛ የሚያደርገው ይህ አሰራር የተጫዋቾችን የአዕምሯዊ ጤና ክፉኛ እየጎዳ ይገኛል።

የዘረኝነት ጥቃት ሲደርስ ጥቃቱ የደረሰበት ተጫዋች ብቻውን የሚታገልበት፣ የሚያዝንበት እና ለዳኛ የሚያመለክትበት አሰራር ማብቃት እንዳለበት የማርካ መረጃ አመልክቷል። ይልቁንም አብረውት ያሉ የቡድን አጋሮቹ (በተለይም ነጭ ተጫዋቾች እና የቡድን አምበሎች) እንዲሁም የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ጭምር ጉዳዩን በጋራ  ማውገዝ እንደሚያስፈልግ ያስነብባል- መረጃው። ጨዋታዎች በዘረኝነት ምክንያት ከተቋረጡ፣ ስታዲየሞች ባዶ ከሆኑ፣ የቴሌቪዥን ስርጭቶች ከተስተጓጎሉ እና ማስታወቂያዎች አየር ላይ ካልዋሉ ስፖንሰር አድራጊዎች እና ባለሀብቶች ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ከደረሰባቸው ስፖርቱ ጫና ውስጥ መግባቱ አይቀርም። ይህ ከሆነ ደግሞ ጉዳይ በቀላሉ ትኩርት ያገኛል ተብሏል።

በተጨማሪም ዘረኛ ደጋፊዎችን ስታዲየም ውስጥ በጅምላ ከመጠየቅ እና ክለቡን በገንዘብ ከመቅጣት ይልቅ ግለሰባዊ ተጠያቂነትን ማምጣት ሌላኛው መፍትሄ ነው። ለዚህ ደግሞ የፊትን ገጽታ መለየት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም በስታዲየም ውስጥ የሚገጠሙ የድምፅ መቅረጫዎችን በመጠቀም ግለሰቦቹን በትክክል ለይቶ ማውጣት ይቻላል።

ጥፋተኛ ሆነው የተገኙትን ግለሰቦች ከስፖርታዊ ተቋማት ውሳኔ ባለፈ በቀጥታ በወንጀል ሕግ ፊት ማቅረብ የጥላቻ ንግግር ክስ መመስረት፣ እስራት እንዲበየንባቸው ማድረግ እና ከማንኛውም የእግር ኳስ ስታዲየም ለዕድሜ ልክ ማገድ ትልቁ መፍትሄ መሆኑን  የማርካ ዘገባ ይጠቁማል። በተጨማሪም ክለቦች በውስጣቸው የተሰገሰጉ የቀኝ አክራሪ እና አድሎአዊ አመለካከት ያላቸውን አደረጃጀቶች መበተን አለባቸው። የትምህርት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከታች ከታዳጊዎች አካዳሚ ጀምሮ መሰራት ይኖርባቸዋልም- ይላል መረጃው።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here