የፊልሙ ንጉሥ

0
294

ኃይሌ ገሪማ የተወለዱት በ1938 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ ነው። አባታቸው አባ ገሪማ ታፈረ የታወቁ የቲያትር ፀሐፊ፣ የታሪክ ተመራማሪና መምህር ነበሩ። ይህ የአባታቸው ስራ ለኃይሌ የኪነ-ጥበብ ፍቅር መነሻ ሆኗቸዋል።

በልጅነታቸው አባታቸው የሚጽፏቸውን ተውኔቶችና የህይወት ታሪኮችን እያዩ ማደጋቸው  በኋላ ላይ ለሰሯቸው የታሪክ ፊልሞች ትልቅ ግብዓት ሆኖላቸዋል። መደበኛ ትምህርታቸውን በጎንደርና በጅማ የተከታተሉ ሲሆን ወደ ጥበብ ዓለም ያዘነበሉት ገና በወጣትነታቸው ነበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ

በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ወደ አሜሪካ በማቅናት መጀመሪያ በችካጎ “Goodman School of Drama” ውስጥ ትወናን አጠኑ። ሆኖም ግን በልጅነታቸው ቲያትር የማጥናት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በሆሊውድ የላቲን አሜሪካውያኑን ፊልም ማየታቸው ወደ ፊልም እንዲያዘነብሉ እንዳደረጋቸው በሎስ አልጀለስ ለታይም መፅሄት በሰጡት ቃለ ምልልሳቸው ገልፀውታል።

በመሆኑም በ1960ዎቹ ወደ ካሊፎርኒያ በመሄድ የፊልም ትምህርታቸውን በመከታተል በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል። በዚያ እያሉ “LA Rebellion” ተብሎ የሚጠራውና ጥቁር የፊልም ባለሙያዎች ንቅናቄ መስራች እና አባል ሆኑ፤ ንቅናቄው አባላት የራሳቸውን ታሪክ በራሳቸው እይታ እንዲሠሩ ይቀሰቅስ  ነበር።

እናም ገና ተማሪ እያሉ “Child of Resistance” (1972) እና “Bush Mama” (1975) ፊልሞቹን በመስራት በወቅቱ የነበረውን የጥቁር አሜሪካውያን ጭቆና አጋልጠዋል።

ኃይሌ ገሪማ “የሆሊውድ አሽከር አልሆንም” በሚለው አቋማቸው ይታወቃሉ። ፊልሞቻቸውን በራሳቸው የገንዘብ ምንጭና ነፃነት መስራትን መርጠዋል። ለምሳሌ ከባለቤታቸው ከሽሪካና አይንዛ ጋር በመሆን በዋሽንግተን ዲሲ “Sankofa Video and Bookstore” የተባለ ተቋም አቋቁመዋል። ይህ ቦታ ዝም ብሎ መሸጫ መደብር ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝብ ታሪክ የሚጠናበት፣ ወጣቶች የሚመካከሩበት እና የፊልም ስራዎቻቸውን በነጻነት የሚወያዩበት ማዕከል ነው።

በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የሳንኮፋ መጽሐፍት መደብር ለቤተሰቡ የሥራ ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ጭምር የሚሳተፉበት የባህል ማዕከል ነው። ይህም ቤተሰቡ ለጥቁር ሕዝብ ታሪክና እውቀት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ከጎንደር ተነስተው ዓለም አቀፍ እውቅናን ቢያገኙም ሁልጊዜ ልባቸውና ስራዎቻቸው ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ማንነት ጋር የተቆራኙ ናቸው።

የፕሮፌሰር ኃይሌ ሕይወት ከጥበብ ጋር የተቆራኘው ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲሆን፣ ትዳራቸውም የዚሁ ጥበብ አካል ነው። ሽሪካና አፍሪካ-አሜሪካዊት የፊልም ባለሙያ ስትሆን፣ የኃይሌ የሕይወትም የሥራ አጋርም ናት። ጥንዶቹ “Mypheduh Films” የተባለ የፊልም ማከማቻና አከፋፋይ ድርጅት በጋራ አቋቁመዋል።

አምስት ልጆች አሏቸው። ልጆቻቸውም በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው። ለምሳሌ ልጃቸው ካህሊል ገሪማ በፊልም ቀረጻና በፈጠራ ስራዎች ላይ አባቱን እየተከተለ ይገኛል።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በአድዋ ዙሪያ ዘጋቢ ፊልም ሰርተዋል፤ “አድዋ፦ የአፍሪካ ድል” የተሰኘ  ፊልም፡፡ ይህ ፊልም በ1999 (እ.አ.አ) ለአድዋ ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያነት የቀረበ ሲሆን ከአድዋ ጦርነት በላይ የአፍሪካውያንን የነፃነት መንፈስ የሚዘክር ታላቅ ስራ ነው።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ይህን ፊልም የሰሩት በተለመደው የታሪክ መጽሐፍት አጻጻፍ ሳይሆን በአፋዊ ትውፊት (Oral Tradition) ላይ ተመስርተው ነው። በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ አባቶችና እናቶች ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው የነገሯቸውን ታሪኮች ከሽማግሌዎች አንደበት በመቅዳት ታሪኩ በህዝብ ዘንድ እንዴት እንደሚታወስ አሳይተዋል። ፊልሙ የታሪክ ምሁራንን ትንታኔ ብቻ ሳይሆን፣ የተራው ህዝብ ስሜትና ተሳትፎ ምን እንደሚመስል በዝርዝር ያሳያል።

ፊልሙ አድዋን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ ድል አድርጎ ያቀርበዋል። አድዋ ለሌሎች አፍሪካውያንና በዲያስፖራ ለሚገኙ ጥቁሮች የነፃነት ተምሳሌት (Beacon of Hope) መሆኑን በስፋት ይዳስሳል። የአውሮፓን ቅኝ ገዥነት ኃይል ሰብሮ የጣለ ብቸኛው የጥቁር ህዝብ ድል መሆኑን በማጉላት፣ የአፍሪካውያንን ክብርና ማንነት ከፍ ያደርጋል።

በፊልሙ ውስጥ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል እና የሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶች በጦርነቱ ወቅት የነበራቸው ሚና በከፍተኛ ሁኔታ ተወስቷል። ሴቶች በስንቅ ዝግጅት፣ ወታደር ማበረታታትና በጦር ሜዳ ስልት ላይ የነበራቸውን አስተዋጽኦ በማጉላት የታሪኩን ሚዛን ይጠብቃል።

የጣሊያን ወረራ ሙከራ እና ኢትዮጵያውያን ለሀገር ዳር ድንበር ጥበቃ ያደረጉት ክተት አንዱ የፊልሙ አካል ነው። ስልታዊ ውሳኔዎች እና የጀግንነት ውሎዎች በስዕላዊ መግለጫዎች የታገዙ ናቸው። ድሉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የሰጠው የሞራል ስንቅ መሆኑ ተተርኮበታል።

ፊልሙን በጣም አስፈላጊ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ፕሮፌሰር ኃይሌ ይህን ፊልም የሰሩት ምዕራባውያን ስለ አፍሪካ ያላቸውን “የተሸናፊነትና የድህነት” ትረካ ለመስበር ነው። ፊልሙ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ብልሃትና አንድነት ታሪክን እንዴት እንደቀየሩ ለዓለም ያሳዩበት አንዱ መሳሪያ ነው። ፕሮፌሰር ኃይሌ ይህን ፊልም ሲሰሩ ብዙዎቹን ምስሎችና ትረካዎች የሰበሰቡት ከቤተ ክርስቲያን ስዕሎች፣ ከባህላዊ ዘፈኖች እና ከቤተሰብ ትውስታዎች በመነሳት መሆኑ ደግሞ አስገራሚ ያደርገዋል።

ፕሮፌሰር ኃይሌ በረጅም የሙያ ዘመናቸው በርካታ ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፉ ፊልሞችን ለተመልካች አብቅተዋል። ከእነዚህም መካከል፦ ሀርቨስት: 3000 ይርስ) አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ የፊውዳል ሥርዓት ውስጥ የነበረውን የገበሬውን ጭቆናና የነፃነት ፍላጎት በረቀቀ ጥበብ ያሳዩበት ቀደሚ ሥራቸው ነው።

ሳንኮፋ (Sankofa) ሌላው ድንቅ ስራቸው ሲሆን በአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን፣ ጥቁር ሕዝቦች ወደ ኋላ ተመልሰው ታሪካቸውን በማወቅ ለወደፊቱ ማንነታቸው ጥንካሬ እንዲያገኙ የሚመክር ድንቅ የጥበብ ውጤት ነው።

ጤዛ (Teza) ፊልም በደርግ ዘመን የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት፣ የተማሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የደረሰባቸውን እንግልትና የማንነት ቀውስ የሚተነትን፣ በቬኒስ ፊልም ፌስቲቫል ትልቅ ሽልማት ያስገኘላቸው ፊልም ነው።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ሽልማቶችና እውቅናዎችን አግኝተዋል። ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ለሆሊውድ የንግድ ቀመር እጃቸውን ባለመስጠታቸው፣ ያገኟቸው ሽልማቶች በሙሉ ለጥበብ ጥራታቸው የተሰጡ እውነተኛ እውቅናዎች ናቸው። በ2021 ቪንቴጅ አዋርድ የተሰኘው በኦስካር አዘጋጅነት የሕይወት ዘመን ክብር ተጎናጽፈዋል። ለ “ጤዛ” (Teza) ፊልም Golden Stallion of Yennenga የተባለው በአፍሪካ ትልቁ የፊልም ሽልማት (FESPACO) በ2009 እንዲሁም  Special Jury Prize በቬኒስ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል (ጣሊያን) 2008 ተበርክቶላቸዋል። Best Screenplay   ለ “ጤዛ” – በቬኒስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለተጻፈው ምርጥ ድርሰት 2008፣ Grand Prize የተባለ ሽልማት ለ “ሳንኮፋ” (Sankofa) – በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የጥቁር ፊልሞች  ፌስቲቫል ላይ     በ1993 ተበርክቶላቸዋል። Interfilm Award ለ “ምርት ሦስት ሺህ ዓመት” – በበርሊን ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል (ጀርመን) በ1976 መሸለማቸውን ታሪካቸው ያስረዳል።

በተጨማሪም ካገኟቸው ልዩ ታሪካዊ ክብር (The Vantage Award) ውስጥ በ2021 እ.ኤ.አ የአሜሪካው የፊልም አካዳሚ (Academy Museum of Motion Pictures) ለፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የሰጣቸው ሽልማት ነው። ሽልማቱን የሰጧቸው ታዋቂዋ የፊልም ዳይሬክተር አቫ ዱቨርኔይ (Ava DuVernay) ስትሆን፣ በንግግሯ ላይ፦ “ኃይሌ ገሪማ ለእኛ መንገድ የጠረገልን፣ የጥቁር ሕዝብ ታሪክ በራሱ እይታ እንዲነገር የተዋጋ ታላቅ መምህር ነው” ስትል ገልጻቸዋለች።

የአፍሪካ ሲኒማ አባት ናቸው፤ ምክንያቱም አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክ “ከቅኝ ገዥዎች እይታ ውጭ” እንዲተርኩ አርአያ ሆነዋል። ጥሩ መምህርነትን አሳይተዋል፤ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ለ40 ዓመታት በማስተማር አዳዲስ የፊልም ባለሙያዎችን አፍርተዋል። ፊልሞቻቸውን ለመስራት ገንዘብ ሲያጡ ቤታቸውን እስከማስያዝ የደረሰ መስዋዕትነት በመክፈል የመንፈስ ፅናትን አውርሰዋል።

በተለይ ፕሮፌሰር ኃይሌ በንግግሮቻቸው ላይ “የራሳችሁን ታሪክ ካልተረካችሁ፣ ሌላው መጥቶ በፈለገው መንገድ ይተርክባችኋል” የሚሉት አባባል ለብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መነሳሳት ሆኗል።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ለብዙ ዓመታት በማስተማር አዳዲስ የፊልም ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን ሲኒማዊ ቋንቋ እንዲፈጥሩ ትልቅ አርአያ ሆነዋል። ሥራዎቻቸው ዛሬም ድረስ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የሥነ-ጥበብ መድረኮች እንደ ዋቢ ይጠቀሳሉ። በአሁኑ ወቅትም “የአንበሳ ፕሮጀክት” በሚል ስያሜ አዲስ የአድዋን ታሪክ የሚዘክር ፊልም ላይ በማተኮር የጥበብ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡

መረፊያ

የሀይሌ ገሪማ. ዘጋቢ ፊልሞች (Documentaries)

  • ቻይልድ ኦፍ ሬዚስታንስ (Child of Resistance, 1974) ፡ ስለ ጥቁር ሴቶች ትግል የሚያሳይ አጭር ፊልም።
  • ቡሽ ማማ (ቡሽ ማማ፣ 1975) ፡ በአሜሪካ የከተማ ኑሮ ውስጥ የጥቁር ሴቶችን መከራና ንቃት የሚያሳይ።
  • ዊሊሚንግተን ቴን (ዊልሚንግተን 10 – USA 10,000, 1979) ፡ ስለ ፍትህ መወለድና እስራት የሚያትት።
  • ኢትዮጵያ፡ ትውልድ ካልሞተ (Ethiopia: Imperfect Past, 1994) ፡ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ የሚቃኝ ነው።
  • አድዋ (አድዋ፣ 1999) ፡ የኢትዮጵያን የአድዋ ድል ለዓለም የሚያስተዋውቅ ታሪካዊ ዘጋቢ ፊልም።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here