የትናንቱን ድል ለዛሬ

0
153

መግቢያ

የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛት ጭቆናን ለመስበር የተመዘገበ፤ የኢትዮጵያውያንን ፅናት፣ አንድነት እና ጀግንነት የሚያሳይ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደማቅ ከሆኑ ድሎች መካከል አንዱ ነው። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ማርች 1 ቀን 1896) በኢትዮጵያ እና በጣሊያን ወራሪ ኃይሎች መካከል የተካሄደው የዓድዋ ጦርነት፣ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል ያላቸውን የአንድነት ጥንካሬ እና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ታላቅ ምስክር ነው። ድሉ ለኢትዮጵያውያን እና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ነጻነትን ከማጎናጸፍም ያለፈ ትርጉም ያለው ሆኖ በየዓመቱ ሲታሰብ ይኖራል::

የጦርነቱ መነሻ

ዋናው የጦርነቱ መንስኤ የጣሊያን ቅኝ የማድረግ ፍላጎትና በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመው የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 የተሳሳተ ትርጉም ነው:: በአማርኛው ቅጂ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ግንኙነት ማድረግ ስትፈልግ በጣሊያን በኩል ማድረግ “ትችላለች” ሲል፣ በጣሊያንኛው ግን “ማድረግ አለባት” በማለት ኢትዮጵያን የጣሊያን ሞግዚት ለማድረግ መሞከሩ ጦርነቱ እንዲፈነዳ አደረገው:: ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ውሉ እንዲታረም ቢጠይቁም ጣሊያኖች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እና የኢትዮጵያን ግዛት በመውረራቸው ጦርነቱ መጀመሩን የብሪታኒካ ጽሁፍ ይገልጻል:: ጦርነቱም በኢትዮጵያ የበላይነት ተቋጨ::

የድሉ ትርጉም ሲገለጥ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር መምህር ገረመው እስከዚያ (ዶ/ር)፣ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ በርካታ የክብር ታሪኮች መካከል ቀዳሚውና ዋናው መሆኑን ገልጸዋል። ድሉ ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም መድረክ ትልቅ ቦታ እንዲኖራት ከማድረጉ ባለፈ፣ አፍሪካውያን ከዘረኝነት አስተሳሰብ ተላቀው በኩራት እንዲኖሩ ፋና ወጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። ወራሪውን የቅኝ ግዛት ኃይል ድል አድርጎ የመለሰው የሕዝቡ የጸና ትብብር መሆኑን የጠቀሱት የታሪክ ባለሙያው፣ በዘመቻው ላይ ሴቶች፣ ቀሳውስትና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ በመሳተፍ ለአሁኗ ኢትዮጵያ መዋደቃቸውንና ይህም የታሪኩ ልዩ ገጽታ መሆኑን በዝርዝር አብራርተዋል።

በአሜሪካ ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ጌታቸው መታፈሪያ (ዶ/ር)፣ የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት ከመሆኑም በተጨማሪ ለአፍሪካውያን የነፃነት ተጋድሎ ፋና ወጊ መሆኑን ያምናሉ:: ዓደዋ ባርነት እና ጭቆና የአፍሪካውያን ግብር አለመሆኑን ያረጋገጠ፤ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ብዝበዛዎች እልባት እንዲያገኙ መፍትሄ የሆነ ድል መሆኑን ያምናሉ::

ዓድዋ የጥቁር ሕዝብ ትንሣኤ፣ የኢትዮጵያዊነት ማኅተም እና የማይቻል የሚመስለው የታቸለበት እና የአብሮነት ሕብረት ዕውን የሆነበት መሆኑንም መስክረዋል። አውሮፓውያን “ጥቁር ሕዝብ በሥልጣኔ እና በጦር መሣሪያ የበላይ የሆነን ነጭ ኃይል ሊያሸንፍ አይችልም” ብለው በሚያምኑበት ዘመን ዓድዋ ምላሽ የሰጠ የታሪክ ግድግዳ ሲሉም አሞካሽተውታል::

በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር  ሬሞንድ ጆናስ ‘የአድዋ ጦርነት’ በተሰኘው መጽሀፋቸው የዓድዋ ድል በዘመናዊው ታሪክ ውስጥ አፍሪካዊ ሉዓላዊነት የተረጋገጠበት ታላቅ ክስተት መሆኑን ጽፈዋል:: የዚህ ይዘት የሚያስረዳው ዓድዋ በወቅቱ የነበረውን “ጥቁር ሕዝብ ነጭን አያሸንፍም” የሚለውን ዓለም አቀፍ የውሸት ትርክት መስበሩን ነው:: የዛሬው ትውልድ ደግሞ ካለበት የድህነት እና የኋላ ቀርነት አዙሪት ለመውጣት አይቻልም ከሚል የሽንፈት ተረት እንዲወጣ ዓድዋ ትልቅ ትምህርት ነው:: የዛሬው ትውልድ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚችል ዘመናዊ ጦር ታጥቆ በጦርና በጎራዴ ድል የተነሳው ጣሊያን ታሪክ እማኝም ነው::

የአሸናፊነት ምስጢራት

ዓድዋ ኢትዮጵያውያን መሸነፍ ዕጣ ፈንታቸው እንዳልሆነ፣ ለመላው ጥቁር ሕዝብም የኩራት እና የነፃነት አርማ የሆነው በመሪ እና በህዝብ መካከል በነበረው ጠንካራ ትስስር ነው:: አሜሪካዊው የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን የዓድዋን ድል ከወታደራዊ ድል ባለፈ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ አድርገው እንደሚመለከቱት “The Victory of Adwa: An African Victory” በሚለው ጽሑፋቸው ጠቁመዋል::

እንደ ሌቪን ድሉ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ከመቶ ሺህ በላይ ጀግኖች በአንድነት የገነቡት አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው። ዓድዋ የተለያየ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና ባህል ያላቸው ኢትዮጵያውያን (ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወላይታና ሌሎችም) ለአንድ ዓላማ ቆመው  “ኢትዮጵያዊነትን” የፈጠሩበት ትልቅ ማኅበራዊ ክስተት ሲሉ ገልጸውታል:: ይህም የፕሮፌሰሩ ሀሳብ ዓደዋ አሁን በኢትዮጵያ ላለው ውስብስብ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የማንነት ፈተናዎች መፍትሄ መሆን እንደሚችል ነው:: ለዚህም ወደ ኋላ መለስ ብሎ የዓድዋን መንፈስ እና በዚያ የተፈጠረውን አዲስ አድማስ በጥልቀት መፈተሽ ይገባል የሚል መልእክትን የሚያንጸባርቅ ነው::

የመሪዎች ብቃት እና ስትራቴጂ ሌላኛው የድል መሠረት ተደርጎ ሲነሳ የአፄ ምኒልክ ዲፕሎማሲያዊ ጥበብና የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ስልታዊ አመራር (ለምሳሌ የጣሊያንን የውኃ ምንጭ በማስያዝ ያደረጉት አስተዋጽኦ) ለድሉ ወሳኝ መሆኑንም ከብሪታኒካ ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል::

ዓድዋ ለዛሬው ትውልድ

ቀደምት አባቶች ያለ ዘመናዊ መሣሪያ በቅንነትና በትብብር ኢትዮጵያን አስከብረው ማቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ መምህር ገረመው እስከዚያ (ዶ/ር) ናቸው:: የአሁኑ ትውልድም ከዚህ ታሪክ የአገር ፍቅርንና አንድነትን ሊማር እንደሚገባ አሳስበዋል። አገር ሊያድግ የሚችለው በልማት መሆኑን ወጣቱ ተገንዝቦ በየተሰማራበት የሥራ መስክ ሊተጋ እንደሚገባ የጠቆሙት ምሁሩ፣ በተለይም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ሕዝባዊ መነሳሳትና ተሳትፎ ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና ለቀጣናዊ ትስስር ያለውን ፋይዳ በዝርዝር አስረድተዋል። ድህነትን በማሸነፍ ሌሎች ተግዳሮቶችን መሻገር እንደሚቻልና ቴክኖሎጂን መጠቀም ደግሞ የዘመኑን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለማስከበር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ትውልዱ ከከፋፋይ አስተሳሰቦች በመራቅ ለአንድነት በመቆምና በልማት ሥራዎች ላይ በንቁ ተሳታፊነት በመሰማራት የዓድዋን ገድልና ራዕይ በተግባር ሊያሳካ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

“ያለፈውን ታሪክ መዘከር የዓድዋ ድል ዳግም እይታ” በሚል ርእስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር  ከበዱ መኮንን ገብረማርያም የተጻፈው እና በኢትዮጵያ የሳይንስና የሰብአዊነት (Ethiopian journal of the science and humanities) መጽሔት ላይ የወጣው ይህ ጽሁፍ “ዓድዋ እግራችን የቆመበት መሬት እና በትክክለኛው መንገድ እንድንኖር የሚገፋፋን ነበልባል ነው” ሲል ይገልጸዋል:: ዓድዋ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ይቅርታ እና ክብር የተገለጠበት፤ ጥቁር እና ነጭ በጦር ሜዳ እኩል መሆናቸውን፣ አልፎ ተርፎም ጥቁር ማሸነፍ እንደሚችል በተግባር ያሳየ ክስተት መሆኑን  ጠቁመዋል::

የማኅበራዊ ትስስራችንን በሚፈትኑ ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የዓድዋ ትውስታ የጀግናውን ጉዞ እንድንከተል ሊያነሳሳን ይገባል የሚለውን ደግሞ ለቀጣዩ ዓድዋ መሠረት አድርጎ መውሰድ እንደሚገባ ጸሀፊው ጠቁመዋል:: የዓድዋ ድል በሁሉም ኢትዮጵያዊ አእምሮ ውስጥ የሚኖር “የጋራ ትውስታ” በመሆኑ ዛሬም ድረስ ለብሔራዊ ኩራት እና ለሉዓላዊነት መከበር መሰረት መሆኑን ማሰብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል::

የዓድዋ ድል የማይቻል የለም የሚል መንፈስን ይፈጥራል። ታሪክን ወደ ኋላ መመልከት ብቻ ሳይሆን ያንን ድል ለዛሬው ችግር መፍትሄ (ለልማትና ለዲፕሎማሲ) እንደ መነሻ መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል::

የዓድዋ ድል የተገኘው በጉልበት ብቻ ሳይሆን በብልሃት ጭምር መሆኑን ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “A History of Modern Ethiopia 1855–1991” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ከትበውት ይገኛሉ:: የእቴጌ ጣይቱ የመቀሌውን ውኃ የመቁረጥ ታክቲክ እና የዳግማዊ ምኒልክ የዲፕሎማሲ ጨዋታ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊውን ድል እንድትቀዳጅ አድርጓታል:: ይህም ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: ሀገር አሁን ከገባችበት ቀውስ በማውጣት ከፍታዋን ለማረጋገጥ ከጠመንጃ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት እንደሚገባ የዓድዋ መሪዎች የድል ምስጢር ይናገራል:: በመሆኑም ትውልዱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት እና የሀገሩን ጥቅም በዓለም መድረክ የማስከበር ጥበብን በዓድዋ መንፈስ መመርመር ይኖርበታል::

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት  የ130ኛውን የዓድዋ የድል በዓል ምክንያት በማድረግ “ከዓድዋ ተራራዎች እስከ ጉባ፤ ዓድዋ በልኩ ሲዘከር” በሚል መረጃ አጋርቷል:: የዓድዋ ድል የጦር ሜዳ ስኬት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በራሷ እንደምትወስን ለዓለም የታወጀበት ታሪካዊ አዋጅ መሆኑን ገልጿል። የጀግኖች አባቶችና እናቶች መስዋዕትነት የሚዘከረው በትላንትናው ግርማ በመኖር ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬውን አሻራ በማሳረፍና በዓድዋ መንፈስ እየተመራን የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ መሆን እንዳለበት ተመልክቷል። በዚህም መሠረት ከዓባይ ወንዝ የተነሳው ‘ሁለተኛው ዓድዋችን’ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ያለፈውን ዘመን የምንዘክረው የአሁኑን ጊዜ በአሸናፊነት በመምራት መሆኑን ሕያው ምስክር መሆኑ ተገልጿል። ኢትዮጵያም ይህንን የድል መንፈስ መሠረት በማድረግ የብልጽግና ጉዞዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል በመረጃው ተመላክቷል።

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here