ግብር የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እና መንግሥት ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ የሚያስችለው ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው። ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ፣ ከሚያካሂዱት ንግድ ወይም ከሚገዙት ላይ ለሀገር የሚከፍሉት ሕጋዊ ግዴታ ነው፡፡ የዚህ ክፍያ ዋና አስፈላጊነት ደግሞ ተመልሶ ለራሳቸው ለዜጎች እና ለሀገር ልማት ለማዋል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች አብራርተዋል።
የግብር ዋነኛው እና የመጀመሪያው አስፈላጊነት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እና የማህበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ነው። መንግሥት ዘመናዊ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ ተቋማትን እና የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎችን የሚያከናውነው ከሕዝብ በሚሰበሰበው ግብር ነው። በተጨማሪም ለኅብረተሰቡ እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን በመገንባት ዜጎች ጤናማ እና የተማረ አምራች ኀይል እንዲሆኑ ለማድረግ የግብር ገቢ ወሳኝ ነው። በሌላ በኩል ግብር የሀገርን ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ትልቅ ፋይዳ አለው።
ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ለራስ፣ ለቤተሰብ እና ለመጪው ትውልድ የተሻለች እና የበለፀገች ሀገርን የመገንባት መሰረት ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ግብሩን በታማኝነት ሲከፍል እና መንግሥትም የተሰበሰበውን ሀብት ለታለመለት የልማት ዓላማ ሲያውል የሀገርን ዕድገት ያፋጥናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከገቢዎች ሚኒሥቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ የካቲት 7 ቀን 2018 ዓ.ም የዕውቅና እና የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። በዕለቱም በገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ደመመ የክልሉን የገቢ አቅም በአግባቡ ለመሰብሰብ የተቀናጀ አሰራር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው በዚህም በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ውስጥ ሆነንም በገቢ አሰባሰብ የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ ግብር ከፋዮች ሕግን አክብረው ግብራቸውን በወቅቱ እና በአግባቡ በመክፈላቸው ለነበራቸው አበርክቶም ምስጋና አቅርበዋል። የግብር ከፋዩን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪን የሚቀንሱ እንደ ሀገር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካል የሆነውን መረጃን በበየነ መረብ በመጠቀም ግብር ከፋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር)የገቢ አሰባሰቡ የዲጂታል አሰራርን እየተከተለ በመሆኑና ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋቱ የገቢ መሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዉ ሀገር፣ መንግሥት፣ ሕዝብ እና ግብር የማይነጣጠሉ የአንድ ቤት አራት ምሶሶዎች ናቸው በማለት አዉስተዉ ከዚህ በተጨማሪም ግብር የፍትሕ፣ አገልግሎት የማግኘት የመሠረተ ልማት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የተመቻቸ መንገድ አቅርቦት እና የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል እንደ ክልል መንግሥታት በ1985 ዓ.ም ሲመሰረት 86 ሚሊዮን ብር የገቢ ግብር በመሰብሰብ ጀምሮ ከ32 ዓመታት በኋላ ማለትም በ2017 ዓ.ም 60 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ በሚችልበት ቁመና ላይ መድረሱን አመላክተዋል። በተለይ የአማራ ክልል በፀጥታ መታወክ እየተፈተነ ባለበት በዚህ ወቅት በ2012 ዓ.ም ከተሰበሰበው 12 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በአምስት ዓመት ውስጥ በአምስት እጥፍ አድጎ 60 ቢሊዮን ብር መድረሱ እጅግ አስደናቂ ውጤት ነው ብለውታል።
የገቢ አሰባሰቡን ፈጣን እና ቀልጣፋ ለማድረግም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እየተተገበሩ መሆኑንና በዚህም ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል። ይህ ሲባል ግን ከኢኮኖሚ ዕድገቱ፣ ከወጪ ፍላጎታችን፣ ከሌሎች ሀገሮች እና ከአጎራባች አቻ ክልሎች ጋር ሲመዘን ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ አመላክተዋል።
የግብር አሰባሰብ ሥራ ግብር መክፈል ያለበት እና ገቢ የሚያገኝ ሰው ማነው? ብሎ ከማወቅ እና የግብር አጣጣሉ ፍትሐዊ መሆኑን ማረጋገጥን እንደሚገባም ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል። የሒሳብ መዝገብን መመርመርን፣ አቤቱታ ማስተናገድን፣ ክሪላንስ (መልቀቂያ) መስጠትንም ይጠይቃል ነው ያሉት ሃላፊዉ።
ከቅንነት ማነስ እና ቅልጥፍና በማጓደል ብዙ ተገልጋዮቻችን ከቅሬታ ያለፈ ምሬትን የሚያሰሙ እንዳሉ መታዘባቸውን ያስረዱት ሃላፊዉ ገንዘብ ይዞ የሚመጣን ደንበኛ ጎንበስ ቀና ብለን ልናገለግል ይገባል ብለዋል። ባለሙያዎችን በእውቀት፣ በክህሎት እና በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያገለግሉ መንግሥት በጀት መድቦ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል። የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው ባለሙያዎቻችን ላይ አምርረን እርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል።
ገና በጅምር ደረጃ ቢሆንም ዛሬ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በእጅ ስልካቸው ግብራቸውን የሚያውቁበት እና ግብር የሚከፍሉበት መንገድ እየተተገበረ መሆኑን አብራርተዋል። የሚነሱ ቅሬታዎችን እና መጉላላቶችን ለመቀነስ ቢሮው በዲጅታላይዜሽን የታገዘ ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር ሥርዓት (ኢ-ታክስ) የተሰኘ ሲስተም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስለምቶ እየተገበረ ይገኛል። ቴክኖሎጂው የግብር አሰባሰቡን ሂደት ወደ ዘመናዊ ዲጂታል አሰራር በማሸጋገር ለግብር ከፋዩ እና ለገቢዎች ቢሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ በተደረገበት በ2017 ዓ.ም 223 ሺህ አነስተኛ ግብር ከፋዮች በእጅ ስልኮቻቸው ግብራቸውን እንዲያውቁ ተደርጓል። 186 ሺህ ያህሉ ባሉበት ሆነው ግብራቸውን መክፈል መቻላቸው ትልቅ ለውጥ መሆኑን አንስተዋል። በቀጣይም ሁሉም ግብር ከፋይ በሲስተም መጠናቀቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በግብር ከፋዮች በኩል ደግሞ የግብር ሕግ ተገዥነት መጓደል፣ ግብርን በትክክል እና በወቅቱ አለማሳወቅ፣ አለመክፈል፣ ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ ታክስ አልሰበሰብንም፣ ሰርተው አልሰራንም የማለት፣ ሐሰተኛ ደረሰኝ ማቅረብ፣ ተገቢ ያልሆነ አቤቱታ ማቅረብ እና መሰል ችግር አለ ነው ያሉት።
በአመራሩ እና በአጋር አካላት በኩል ደግሞ በበጀት ድልድል ትኩረት የሚሰጡበትን ያክል ለገቢ ትኩረት አለመስጠት፣ የጠራ መረጃ አለማቅረብ፣ የገቢ ድርሻ በበቂ ሁኔታ አለመሰብሰብ እና በሕግ ማስከበር በኩል በቂ ትብብር አለማድረግ የታዩ ችግሮች ናቸው።
በ2018 በጀት ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር (ኢ-ታክስ) ለገቢው መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል። በቀሪ ወራት ቀሪውን በጋራ ተረባርበን ለማሳካት በጋራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ለታማኝ ግብር ከፋዮችም ለነበራቸው አበርክቶ ምስጋና አቅርበዋል።
በመድረኩ ለግብር አሰባሰቡ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ ነጋዴዎች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።
ለበኩር ጋዜጣ አስተያየታቸውን ከሰጡ ምስጉን ግብር ከፋዮች መካከል የአልማኮን ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አቶ ደሳለኝ አንዱ ናቸው። ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከፍተኛ ግብር ከፋይ እና ልዩ ተሸላሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ግብር ለሀገር ግንባታ፣ ዕድገት እና ብልጽግና መሠረት መሆኑንም አንስተዋል። የሕዝብን የልማት (የመንገድ፣ የጤና፣ የት/ቤት፣ የውኃ፣ የመብራት) እና መሰል ጥያቄዎች ለመመለስ ግብርን በወቅቱ መክፈል እንደሚያስፈልግም ነው ሐሳባቸውን ያጋሩን። ይህም ኅብረተሰቡን፣ አካባቢን እና የሀገር ምጣኔ ሀብት በማሳደግ ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል። የተሠሩ ሥራዎችን በአግባቡ በመመዝገብ ግብርን ያለማንም ቀስቃሽነት በወቅቱ እንደሚከፍሉ አስረድተዋል። ስለሆነም ግብር መክፈል ለሀገር ክብር መስጠት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል። ግብርን መክፈል የሥልጣኔ መገለጫ ነው ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው ግብር መክፈል የሰለጠነ አሥተዳደር፣ የሰለጠነ ነጋዴ፣ የሰለጠነ ኅብረተሰብ መገለጫ እንደሆነም አመላክተዋል።
ሌላው በሰሜን ሸዋ ዞን አንሳሮ የሚገኘው ከአይሳነው በፍርዱ እና ጓደኞቻቸው የደረቅ ጭነት አገልግሎት ኅብረት ሽርክና ማኅበር የመጡት አቶ ከተማ አሰግድ ግብራቸውን በታማኝነት እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የተሰጣቸው ዕውቅና ለተሻለ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው እና በቀጣይም ለሀገር የሚጠቅም ግብር መክፈል እንዳለባቸው አስረድተዋል። ግብር ከሌለ ሰላም፣ ትምህርት እና ጤና የለም ያሉት አቶ ከተማ “ማንኛውም ሰው በአግባቡ ግብር መክፈል እና ሀገሩን ማሳደግ ይጠበቅበታል፤ ግብር አለመክፈል የሀገርን ጥቅም እና እድገት የሚጎዳ በመሆኑ ዜጎች በሀቀኝነት እና በታማኝነት ግብርን መክፈል ይጠበቅባቸዋል” ነው ያሉት፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


