አድዋ ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን የታሪክና የስልጣኔ ማዕከል ናት። አድዋ በጥንት ጊዜ ከአክሱም ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው የንግድ መስመር ላይ የምትገኝ ወሳኝ የንግድ ማዕከል ነበረች። የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ደም የፈሰሰባት የኢትዮጵያዊነት የቁርጥ ቀን ሆና ትወሳለች። አድዋ የነፃነት ፋና ወጊ ናት። ለፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፈጠር ትልቁን ድርሻ የምትወስድ፣ የጥቁር ሕዝብ “አልሸነፍ ባይነት” ማረጋገጫ ናት። ዛሬም ድረስ በቱሪዝም፣ በታሪክ ምርምርና በሃይማኖታዊ ስፍራዎቿ የዓለምን ቀልብ እየሳበች ትገኛለች።
ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በታሪካዊቷ አድዋ ከተማ ተገኝተን ነበር- እኔና ጥቂት የአሚኮ የሙያ አጋሮቼ። አድዋ ግሩም የእንግዳ ተቀባይ ደጋግ ሕዝብ መኖሪያ መሆኗን በቆይታችን ለማረጋገጥ ችለናል። ከአድዋ ከተማ፣ ትንሽ ወጣ ብለን የአድዋ ጀግኖች ለነጻነት ተፋልመው ወራሪን ጥለው የወደቁባቸውን የሶሎዳ፣ ሸዊት እና ኪዳነ ምሕረት ተራሮችን በቅርብ ርቀት ተመለከትን። ተራሮቹ ትናንት የተፈፀመውን ታሪክ ይተርኩታል፤ ለሀገር ክብር እና ለነፃነት የተከፈለውን ዋጋ አባቶቻችን በወደቁበት ስፍራ በአካል ተገኝተን የማየት እድል ባገኘንበት በዚህ አጋጣሚ በአባቶቻችን ጀግንነት የተሰማን የኩራት ስሜት ልዩ ነበር። እናም በሽርሽር አምዳችን የአድዋን ተራሮች እና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶቿን ልናስቀኛችሁ ወደድን።
መልካም ንባብ!
የአድዋ ተራሮች
የአድዋ ተራሮች ለጦርነቱ ድል ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው፣ የነበራቸውና ዛሬም ድረስ የቆሙ የሚታዩ ምስክሮች ናቸው፡- እንደ ሰማያታ፣ ሶሎዳ፣ አባ ገሪማ እና ማርያም ሸዊቶ ያሉ ስፍራዎች ለጦርነቱ ወታደራዊ ጠቀሜታ ነበራቸው።
የሰሜታ ተራራ (ደብረ ሰማይ)
ይህ ተራራ በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ ከፍተኛ ግብግብ የተገጠመበት ስፍራ ነው። የጀነራል አልቤርቶኒ ሰራዊት (የጣሊያን የግራ ክንፍ) በስህተት ወደዚህ ተራራ አቅጣጫ ተጓዘ። የኢትዮጵያ ሰራዊት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የጣሊያንን ሰራዊት ከበባ ውስጥ አስገባ። የጣሊያን ጦር ገና ሳይደራጅ ከፍተኛ ድብደባ ደረሰበት። ጀነራል አልቤርቶኒ እዚሁ ተራራ ስር ተማርኳል።
የረቢ አሪየኒ ተራራ
ይህ ተራራ በጦርነቱ መካከለኛ ክፍል ላይ የሚገኝና የጣሊያን ዋና ማእከል ያለበት ስፍራ ነው። ጀነራል አሪሞንዲ በዚህ ተራራ ላይ መሽጎ ነበር። ሆኖም አልቤርቶኒ መሸነፉን እና መማረኩን ሲረዳ ለማፈግፈግ ሞከረ። ሆኖም ዐፄ ምኒልክ 25 ሺህ የሚሆነውን የጥበቃ ሰራዊት (ኢምፔሪያል ጠባቂ) ወደዚህ ተራራ እንዲዘምት ትእዛዝ በመስጠታቸው የኢትዮጵያ ሰራዊት በከፍተኛ ወታደራዊ ብልጫ ተራራውን ተቆጣጠረ፤ ጀነራል አሪሞንዲም እዚሁ ተራራ ላይ ተገደለ።
የማርያም ሸዊቶ ተራራ
ይህ ተራራ የጣሊያን ቀኝ ክንፍ (በጀነራል ዳቦርሚዳ የሚመራው) የተሰማራበት ነበር። ዳቦርሚዳ ከሌላው የጣሊያን ተዋጊ ጋር ግንኙነቱ ተቋርጦ ለብቻው ተነጥሎ ቀረ። የራስ አሉላ፣ የራስ መኮንን፣ የራስ መንገሻ እና የራስ ሚካኤል ሰራዊት በዚህ ተራራ ላይ የጣሊያንን ጦር አይቀጡ ቅጣት የቀጡበት ወሳኝ ስፍራ ነው። ጀነራል ዳቦርሚዳ እዚሁ ተራራ ስር ተገደለ። የጣሊያን ሀይል ዳግም እድል ሊያገኝ የማይችልበትን ሽንፈት የተከናነበው እዚህ ስፍራ ላይ ነው።
የማርያም ሸዊቶ ተራራ ጠባብ ሸለቆና ወጣ ገባ መሬት ያለበት ስፍራ ሲሆን የጣሊያን ዘመናዊ መድፎችና ጠመንጃዎች እንደ ልብ አያገለግሉም ነበር። የኢትዮጵያ አርበኛ ግን “የጨበጣ ውጊያ” በመጠቀም የጣሊያንን ሰራዊት አረገፈው።
ጀነራል ዳቦርሚዳ በዚህ ሸለቆ ውስጥ ተከቦ እያለ ረዳት እንደሚመጣለት ተስፋ አድርጎ ነበር። ሆኖም ግን ረዳት ሳይመጣለት ቀርቶ በውጊያው ላይ ተገደለ። የሱ መሞት የጣልያን ቀኝ ክንፍ ሙሉ በሙሉ እንዲበታተን አድርጓል።
የአድዋ ውጊያ በይፋ የተጠናቀቀው እና የጣሊያን ጦርም “ፈረንጅ አይሸነፍም” የሚለው ትዕቢቱን የተነፈሰውም እዚህ ስፍራ ላይ ነው። በማርያም ሸዊቶ አካባቢ ዛሬም ድረስ የጦርነቱ አሻራዎች፣ ጥንታዊ ምሽጎችና የታሪክ ምልክቶች ይገኛሉ። ስፍራው የጀግንነትና የድል መታሰቢያ ተደርጎም ይቆጠራል።
የሶሎዳ ተራራ
ሶሎዳ ተራራ በአድዋ ከተማ አጠገብ የሚገኝ ለከተማዋ ውበትና ግርማ የሰጠ ታሪካዊ ተራራ ነው። ይህ ተራራ የአድዋ ከተማን ቁልቁል ለመመልከትና ለጦርነቱ መሪዎች እንደ አካባቢ መመልከቻ (Observation point) ያገለገለ ስፍራ ነው። በጦርነቱ መዝገብ ላይ የተረፈው የጣሊያን ጦር ወደ ሰሎዳ ተራራ በመሸሽ ራሱን ለማዳን ሞክሮ ነበር። ነገር ግን ተራራው እጅግ ገደላማ ስለነበር ወታደሮቹ እየተንሸራተቱ እንዲወድቁና ለኢትዮጵያውያን በቀላሉ እንዲማርኩ አድርጓቸዋል። የጣሊያን ጦር ሙሉ በሙሉ መበታተኑ እዚህ ተራራ ስር ተረጋገጠ።
የአባ ገሪማ ተራራ
የአባ ገሪማ ተራራ (ወይም ደብረ መደራ) በትግራይ ክልል አድዋ አቅራቢያ የሚገኝ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ተራራ ነው። ይህ ተራራ ከአባ ገሪማ ገዳም ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው። አባ ገሪማ ተራራ አርበኞች በጀግንነት የተዋደቁበትና የድሉ ዋና መገኛ ነው።
ተራራው የሚገኘው ከአድዋ ከተማ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ ነው። አካባቢው ወጣ ገባና ድንጋያማ ሲሆን ከላይ ሆኖ ሲታይ የአድዋን ተራሮች ሰንሰለት (ለምሳሌ እንደ ተራራው ልዕልት “ሰሎዳ”) በግልጽ ለመመልከት ያስችላል። አባ ገሪማ ከሮም መጥተው ገዳማቸውን ከመመሥረታቸው በፊት በዚህ ተራራ ላይ በብሕትውናና በጸሎት እንደቆዩ ይነገራል።
የአባ ገሪማ ተአምራዊው ምንጭ እዚህ ይገኛል። በተራራው ግርጌ አባ ገሪማ በበትራቸው መሬቱን መትተው እንዳፈለቁት የሚነገርለት “ጸበል” (ምንጭ) ይገኛል። ይህ ምንጭ ዛሬም ድረስ ለገዳሙና ለአካባቢው ማህበረሰብ እንደ ትልቅ በረከት ይታያል።
የአባ ገሪማ ተራራና አካባቢው በ1888 ዓ.ም በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ለተደረገው የአድዋ ጦርነት ስትራቴጂካዊ ቦታ ነበር። የኢትዮጵያ ጦር በቦታው የነበረውን ተፈጥሯዊ ምሽግ ተጠቅሟል። የአባ ገሪማ ታቦትም ወደ ጦርነቱ ግንባር ወጥቶ ለኢትዮጵያውያን ወታደሮች የሞራል ጥንካሬ እንደሰጠ በታሪክ ይዘከራል።
ተራራው ለተፈጥሯዊ ግርማ ሞገሱና ለታሪካዊነቱ ሲባል በጎብኚዎችና በሀጅ ተጓዦች ይጎበኛል። በተራራው ዙሪያ የሚገኙት የጥንት ዛፎችና የብዝሃ ሕይወት ሀብቶች ለቦታው ልዩ ውበት ሰጥተውታል።
ታሪካዊ ቅርሶች
አድዋ የጦር ሜዳ ብቻ ሳትሆን፣ የኢትዮጵያ የጥበብ፣ የሃይማኖትና የሥልጣኔ አሻራዎች በጉልህ የሚታዩባት “ሕያው ቤተ መዘክር” ናት።
ከአድዋ ከተማ በስተምስራቅ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአባ ገሪማ ገዳም፣ የኢትዮጵያ የጥበብ ታሪክ ማሳያ ነው። በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ ጌጣማ ጽሑፎች አንዱ ነው። የካርቦን ምርመራ እንደሚያሳየው በ5ኛው ክፍለ ዘመን (ከ390-570 ዓ.ም) የተጻፈ ሲሆን በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ በቆዳ ላይ የተጻፉ ወንጌላት ቀዳሚው ተደርጎ ይወሰዳል።
ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት የአባ ገሪማ መገልገያዎች፣ የነገሥታት ዘውዶችና ልብሶች በገዳሙ ውስጥ ይገኛሉ።
የአድዋ ድል መታሰቢያ ቤተ መዘክር
በአድዋ ከተማ መሃል የሚገኘው ይህ ቤተ መዘክር የድሉን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ የተገነባ ነው።
በቤተ መዘክሩ ውስጥ በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የተጠቀሙባቸው ጎራዴዎች፣ ጋሻዎች፣ እና የጠላት ምርኮ የሆኑ ጠመንጃዎችና መድፎች ይገኛሉ። የዐፄ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱ እና የሌሎች ጦር መሪዎች ታሪክና ምስሎችም በስፋት ተሰንደውበታል።
በአድዋ ከተማ ዳርቻና በተራሮቹ ግርጌ በጦርነቱ የወደቁ የጣሊያን ወታደሮች መታሰቢያዎችና መቃብሮችም ይገኛሉ። ይህም ጦርነቱ በእውነት የተከናወነ መሆኑንና የድሉን ግዝፈት የሚያሳዩ ቅርሶች ናቸው።
እንደ እምባ ባሪቶ፣ ራየ እና አባ ገሪማ ያሉ ተራሮች ራሳቸው እንደ “ተፈጥሮአዊ ቅርስ” ይታያሉ። እነዚህ ተራሮች የድሉ ታሪክ በውስጣቸው የታተመባቸው በመሆኑ ለቱሪስት መስህብነት ከፍተኛ ዋጋ አላቸው።
አድዋ የጥንታዊ ሥልጣኔ ማከማቻ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የነፃነት አርማ በሆኑት አምባዎቿ የደመቀች ታሪካዊ ቦታ ናት። በእርሷ ውስጥ ያሉ ቅርሶችን መጠበቅና ማልማት ታሪክን ለትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ ከተማዋን የዓለም የቱሪስት መዳረሻ ያደርጋታል!
እንኳን ለ130ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!፡፡
አጭር እውነታ
ስለ አድዋ አጭር መረጃዎች
- የአድዋ ጦርነት በ1888 ዓ.ም (1896 እ.ኤ.አ.) በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ተካሄደ።
- በዚህ ጦርነት አፄ ምኒልክ ሁለተኛ የመሩት የኢትዮጵያ ኃይል ድል አድርጓል።
- ይህ ድል ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንድትጠብቅ አድርጎ በአፍሪካ ታሪክ ታላቅ ምልክት ሆኗል።
- የአድዋ ድል ለብዙ የአፍሪካ አገሮች የነፃነት ተነሳሽነት ሆኗል።
- ዛሬም የአድዋ ድል በኢትዮጵያ በየዓመቱ ይከበራል።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


