ግቦች ቀነሱ? ወይስ ጨመሩ?

0
148

እግር ኳስን ማራኪ እና ተወዳጅ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ዋነኛው መረብ ላይ የሚያርፉ ግቦች ናቸው:: ደጋፊው ወደ ስታዲየም የሚያቀናውም ሆነ በቴሌቪዥን መስኮት ጨዋታዎችን የሚከታተለው ከማራኪ እግርኳስ በተጨማሪ የሚቆጠሩ ግቦችን ለማየት ነው:: ነገር ግን በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር የተቆጠሩ ግቦች አነስተኛ መሆናቸውን በጎንደር ዩንቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪው አቶ አዲስአለም ምህረት ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግሯል:: በመጀመሪያው ዙር ውድድር በተደረጉት የሊጉ ጨዋታዎች በአጠቃላይ 320 ግቦች መረብ ላይ አርፈዋል:: እነዚህን ግቦች 155 የተለያዩ ተጫዋቾች ማስቆጠር ችለዋል:: ይህ ማለት በአንድ ጨዋታ በአማካኝ የተቆጠረው አንድ ነጥብ 68 ግብ ብቻ መሆኑን ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ::

ከአምናው የመጀመሪያው ዙር ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ 53 ተጨማሪ ግቦች ተቆጥረዋል:: ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 20 ከፍ በማለቱ ብቻ መሆኑን የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪው አቶ አዲስአለም ምህረት ተናግሯል:: የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከነበረበት የመከላከል እና ጥንቃቄ ያመዘነበት አጨዋወት ወጥቶ፣ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ እና በርካታ ግቦች ወደ ሚቆጠሩበት መድረክነት እየተቀየረ ቢመጣም አሁንም በሊጉ የሚቆጠረው የግብ መጠን  አነስተኛ መሆኑን የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ያስረዳል::

በመጀመሪያው ዙር ከተከናወኑት 190 ጨዋታዎች ውስጥ 80 ጨዋታዎች  በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት:: 43ቱ ጨዋታዎች ምንም አይነት ግብ ያልተቆጠረባቸው (በዜሮ አቻ) ያለቁ ናቸው:: በ10ኛ፣ 11ኛ እና 15ኛ ሳምንታት ላይ በእያንዳንዳቸው 21 ግቦች ተቆጥረው አንፃራዊ መነቃቃት ቢታይም አጠቃላይ የሊጉ ገፅታ ግን አጥቂዎች የግብ ረሃብ የጠናባቸው እና አብዛኛዎቹ ክለቦች ከመጫወት ይልቅ መከላከልን የመረጡበት ሆኖ አልፏል:: የግብ ድርቁ በከፍተኛ ሁኔታ የታየበት 17ኛው ሳምንት ላይ ሲሆን በዐስር ጨዋታዎች የተቆጠረው 11 ግብ ብቻ ነበር::

ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር ብቻ 33 የፍፁም ቅጣት ምት ግቦች እንዲሁም 13 በራስ ላይ የተቆጠሩ ግቦች መገኘታቸው የግብ መጠኑን ከፍ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ:: በእግር ኳስ የቡድኖች የአካል ብቃት እና የታክቲክ ለውጥ የሚለካው በየአጋማሹ በሚታየው የግብ መጠን ነው:: በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ 151 ግቦች ሲቆጠሩ ከዕረፍት መልስ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ  የግብ መጠኑ ወደ 160 ከፍ ብሏል:: ይህ የሚያሳየው አብዛኛዎቹ ቡድኖች በሁለተኛው አጋማሽ የማጥቃት ኃይላቸውን እንደጨመሩ ወይም የተጫዋቾች የአካል ብቃት መዳከምን ተከትሎ የተከላካይ ክፍሎቻቸው ስህተት እንደሚበዛባቸው ነው ቁጥራዊ መረጃው የሚያመለክተው::

በ2015 ዓ.ም የውድድር ዘመን በዓመቱ መጨረሻ 464 ጠቅላላ ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን በመጀመርያው ዙር 232 ግቦች ተቆጥረዋል:: በወቅቱ ሊጉ ከነበረበት የግብ ድርቅ መነቃቃት የጀመረበት እንደነበር አይዘነጋም:: በ2016 ዓ.ም ደግሞ የክለቦች የማጥቃት ፍልስፍና ይበልጥ ጎልብቶ በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ 483 ግቦች ተቆጥረዋል፤ በመጀመሪያው ዙር ውድድር  241 ግቦች መረብ ላይ አርፈዋል። በ2017 ዓ.ም ደግሞ በአጠቃላይ በዓመቱ 534 ግቦች መቆጠራቸውን መረጃዎች አመልክተዋል:: በዚሁ ዓመት የመጀመሪያ ዙር ውድድርም 267 ግቦች መቆጠራቸውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበሩ ከሚያዘጋጀው መጽሔት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል::

በዚህ ዓመት እንደ አርባምንጭ ከተማ አይነት ክለቦች በ19 ጨዋታ ዐስር ግብ ብቻ በማስቆጠር የማጥቃት ኃይላቸው ምን ያህል እንደተዳከመ አሳይተውናል:: በአንፃሩ ሲዳማ ቡና 24 ግቦችን በማስቆጠር የተሻለ የማጥቃት ክብረወሰን ይዟል:: ይህ ችግር በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን ከአሰልጣኞች የታክቲክ ምርጫ እና ፍርሃት የመነጨ መሆኑን አቶ አዲስአለም ይናገራል::

“የመከላከል እና ውጤት ላይ ብቻ ያተኮረ ፍልስፍና በሜዳ ላይ ከሚያስከትላቸው ተግዳሮቶች አንዱ  የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን በተለይም ወጣት የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች ሚናን ማዳከሙ ነው:: ተጫዋቾች አዳዲስ የፈጠራ መንገዶችን ተጠቅመው ግብ የመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት እና ክህሎት ቢኖራቸውም አሰልጣኞቻቸው በሚጭኑባቸው ውጤት የማግኘት ጫና ምክንያት አቅማቸውን አውጥተው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም:: እናም በመጀመሪያው ዙር በርካታ ግቦች እንዳይቆጠር ይህ አንደኛው ምክንያት ነው::” በማለት ያስረዳል- አቶ አዲስአለም::

ሌላው ከፍተኛ ግብ የማስቆጠር ክህሎት ያላቸው አጥቂዎች እጥረት መኖር በመጀመሪያው ዙር የተቆጠሩ ግቦች አነስተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ተብሏል:: ይሁን እንጂ  ምን ያህል ግብ የሚሆኑ ያለቀላቸው ኳሶች ለአጥቂዎች ይደርሳሉ? የሚለው ጥያቄ መዘንጋት እንደሌለበት የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ተናግሯል::

“ኳስ ከመጀመሪያው የሜዳ ክፍል ከኋላ ተከላካዮች ይመሰረታል፤ የሚቀበሏቸው ግን አማካዮች አይደሉም:: አንድ ሁለት ሦስት አጥቂ ወደ ኋላ ተመልሰው ነው- ወደ ሁለተኛው የሜዳ ክፍል ኳስን ይዘውት የሚሄዱት። ከአንደኛው የሜዳ ክፍል ወደ ሁለተኛው ከዚያም ወደ ሦስተኛው በሂደት የኳስ ሽግግር በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዙ ጊዜ አንመለከትም::” በማለት አንደኛው ፕሪሚየር ሊጉ በግብ ድርቅ እንዲመታ ምክንያት መሆኑን የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ይገልፃል::

እናም ተጫዋቾች በጋራ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ካልገቡ አጥቂው ብቻውን ተዓምር ሊሰራ እንደማይችል የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ያስገነዝባል። ስለዚህ ግቦችን ለማስቆጠር በህብረት ማጥቃት ትልቁ መፍትሄ መሆኑን ያስረዳል:: በመጀመሪያው ዙር ለተቆጠሩ አነስተኛ ግቦች የስታዲየሞች እና የሜዳዎች ጥራት መጓደል ሌላኛው ምክንያት መሆኑን የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ያብራራል::

የኢትዮጵያ ስታዲየሞች ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ ለኳስ ቁጥጥር (Ball control) እጅግ አስቸጋሪ መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ቢሆንም ለግብ ድርቁ ብቸኛ ማሳበቢያ ምክንያት ሊሆኑ ግን አይችልም ነው የተባለው:: “የሜዳዎቻችን ጥራት ግልፅ ነው፣ አስቸጋሪ ነው:: ግን ለተከላካዩም ለአጥቂውም እኩል ነው። እንዲያውም ተከላካዩም  ኳስ ቁጥጥር ለማድረግ ይቸገራል:: መሬቱ ካልተስተካከለ ሲቆም ሚዛኑን ስቶ ይወድቃል::” በማለት ሜዳው ለተከላካይም ስለማይመች አጥቂዎች የሚፈጠረውን ስህተትን ተጠቅመው ግብ ማስቆጠር እንደሚችሉ አመላክተዋል::

በመጀመሪያው ዙር ግቦች በብዛት ከተቆጠሩባቸው ሜዳዎች መካከል የአዲስ አበባ ስታዲየም በ140 ግቦች (17ቱ በፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ) ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል:: በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም 91 ግቦች እንዲሁም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ደግሞ 89 ግቦች ተቆጥረዋል::

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ሲቀጥል አሰልጣኞች የፍርሃት ቆፈናቸውን አውልቀው  በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ማራኪ እግር ኳስን ማለማመድ አለባቸው:: ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ነፃነት መስጠት እና የቡድን የማጥቃት ስልትን በመዘርጋት በርካታ ግቦች እንዲቆጠሩ ግድ ይላል- የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ምክረ ሀሳብ ነው::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here