እግር ኳስ ስፖርት በድራማዊ ክስተቶች የታጀበ መሆኑ በቢሊዮኖች ተወዳጅ አድርጎታል:: ነገር ግን የቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) በእግር ኳስ ስፖርት ከተጀመረ በኋላ የስፖርቱ ተፈጥሯዊ ውበት እየደበዘዘ መጥቷል የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም:: ቴክኖሎጂው ስህተቶችን በማረም እግር ኳስን ፍትሐዊ ለማድረግ ቢጀመርም ዛሬም ከውዝግብ ግን ሊጸዳ አልቻለም:: እናም ቫር እግር ኳስን እያሻሻለው ነው ወይስ እየገደለው ነው? የሚለው ጥያቄ የዘመናችን ተወዳጅ ስፖርት ትልቁ መከራከሪያ ርእሰ ጉዳይ ሆኗል።
የቫር ቴክኖሎጂ በሰው ዓይን በቀላሉ ሊታዩ የማይችሉ እና ከጨዋታው እይታ ውጪ የሚሰሩ አሰቃቂ ጥፋቶችን በመለየት ተጫዋቾችን ከከባድ ጉዳት መታደግ መቻሉ የቴክኖሎጂው ዋነኛ ትሩፋት ነው:: በተጨማሪም በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሚሰሩ ግልጽ የሆኑ የእጅ ኳስ ጥፋቶችን ከማሳየት እና የተሳሳተ ተጫዋች ላይ የሚሰጥን የካርድ ውሳኔ በማረም ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል:: ዳኞች በሜዳ ላይ ከሚኖራቸው ፍጥነት እና የእይታ ውስንነት አንጻር ሊያመልጧቸው የሚችሉ ትልልቅ ስህተቶችን በመቀነስ በኩል ቫር የራሱን አዎንታዊ አሻራ አሳርፏል::
ይሁን እንጂ የቫር ቴክኖሎጂ ስፖርቱን አደጋ ላይ እየጣለው ይገኛል የሚል መከራከሪያ ሀሳብም በስፋት ይነሳል:: አንድ ተጫዋች ግብ አስቆጥሮ ደጋፊው በደስታ ከፈነደቀ በኋላ የተቆጠረው ግብ ድጋሚ በቫር ታይቶ ሲሻር የሚፈጠረው የስሜት መቀዝቀዝ ስፖርቱን እጅግ አሰልቺ አድርጎታል:: አሁን ላይ ደጋፊዎች ግብ ሲቆጠር ሙሉ በሙሉ ደስታቸውን ከመግለጽ ይልቅ እስኪ ቫር ያረጋግጥ ብለው ስሜታቸውን መግታት ጀምረዋል:: እግር ኳስ በፈጣን እንቅስቃሴ የተሞላ ስፖርት ሆኖ ሳለ ዳኛው ውሳኔ ለመስጠት የሚያጠፋው ደቂቃ የተመልካችን ትኩረት የሚሰርቅ ሆኗል። ከዚህም ባሻገር በሚሊሜትር በሚለኩ የጨዋታ ውጪ ውሳኔዎች ግቦች መሻራቸው እግር ኳሱን ከስፖርትነት ወደ ሳይንሳዊ የምርምር ማዕከልነት ቀይሮታል ይላል የቢቢሲ መረጃ።
ይህ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በተለይም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እያመጣ ያለውን ተጽዕኖ ስንመለከት ቫር ክለቦችን አላግባብ እየጎዳ እና እየጠቀመ መሆኑን በግልጽ እናያለን። የ2025/26 የውድድር ዘመን ያለ ቫር የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ምን ይመስል ነበር? የሚለው ቢቢሲ ስፖርት አስደንጋጭ እውነታዎችን አውጥቷል። ለአብነት እንደ ዎልቭስ እና ኖቲንግሃም ፎረስት የመሳሰሉ ክለቦች በቫር ውሳኔዎች ምክንያት በርካታ ነጥቦችን በማጣት ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሆነዋል።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት የ29 ሳምንት መርሀግብር ድረስ ዎልቭስ በተደጋጋሚ በተሻሩበት ግቦች እና በቫር በተነፈጉ የፍጹም ቅጣት ምቶች ምክንያት በውድድር ዘመኑ ሊያገኝ ከሚገባው ነጥብ ላይ በአማካይ ከ አራት እስከ ስድስት ነጥቦችን አጥቷል:: እንደ አስቶን ቪላ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ኒውካስል ዩናይትድ የመሳሰሉ ክለቦች ድጋሚ በቫር ከታየ በኋላ ተጨማሪ ነጥቦችን በማግኘት ተጠቃሚ ሆነዋል። አርሰናል እና ሊቨርፑልን የመሳሰሉ ታላላቅ ክለቦችም ቢሆኑ በቫር ውሳኔዎች የዋንጫ ፉክክራቸው አቅጣጫ ሲቀየር ታይቷል።
ይህ የነጥብ መቀነስ እና መጨመር ቫር ዳኞችን አድሏዊ አድርጓቸዋል የሚል ሰፊ መከራከሪያ ሀሳብ በርካቶች ዘንድ እየተነሳ ይገኛል:: ዋና ዳኞች ከባድ ውሳኔዎችን ለመወሰን ድፍረት በማጣት እንዲሁ ቫር ያየዋል በሚል ሀላፊነትን መሸሽ ጀምረዋል። እንዲሁም በቫር ክፍል ውስጥ ያሉ ዳኞች ለታላላቅ ክለቦች የሚያሳዩት የተንሸዋረረ እይታ ወይንም ድብቅ አድልዎ አለ። ለምሳሌ በኦልድትራፎርድ ወይም በአንፊልድ ላይ ለአንድ ትልቅ ክለብ በቀላሉ የሚሰጥ በቫር የተደገፈ የፍጹም ቅጣት ምት በተመሳሳይ ጥፋት ለትንሽ ክለብ ሲሆን እንደማይሰጥ በተደጋጋሚ ተመልክተናል።
በቫር ክፍል ያሉ ዳኞች የትልልቅ ክለቦችን ደጋፊዎች እና የሚዲያ ጫና በመፍራት ለነሱ የሚያደሉ ውሳኔዎችን መወሰናቸው ቴክኖሎጂው የዳኞችን አድልዎ በቪዲዮ ማስረጃነት ሕጋዊ ሽፋን እንዲያገኝ አድርጎታል። ይህ የዳኞች አድልዎ እና የቫር ውዝግብ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ብቻ ችግር አይደለም። በስፔን ላሊጋም ችግሩ የከፋ ሆኖ እናገኘዋለን። በላሊጋው ቫር ከፍትህ ማስፈኛነት ይልቅ የፖለቲካ እና የሚዲያ ጦርነት ማካሄጃ መሳሪያ ሆኗል። በተለይም በሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና መካከል ባለው ታሪካዊ ፉክክር ውስጥ የቫር ውሳኔዎች የትልልቅ ውዝግብ መነሻ ናቸው።
የባርሴሎናው የኔግሬራ ቅሌት በፈጠረው የጥርጣሬ ድባብ ውስጥ ዳኞች በቫር ክፍል የሚያሳልፉት እያንዳንዱ ውሳኔ እንደ ሴራ ይቆጠራል። በሌላ በኩል ሪያል ማድሪድ በራሱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በዳኞች ላይ የሚያደርገው ተደጋጋሚ የስነ ልቦና ጫና የቫር ዳኞች ውሳኔያቸው ነጻ እንዳይሆን አድርጓል የሚሉ ትችቶች አሉ:: በላሊጋው በተለይ የእጅ ኳስ ሕግ ትርጓሜዎች ከሳምንት ሳምንት የሚለዋወጡ በመሆናቸው በቫር ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሆነ ተብሎ ውጤት ለማዛባት ተግባራዊ የሆነ አድርገው ክለቦች እንዲያምኑ አስገድዷቸዋል::
የጣሊያን እግር ኳስ በባህሪው የመከላከል አጨዋወት ላይ ያተኮረ እና እያንዳንዱ የዳኛ ውሳኔ በከፍተኛ ሁኔታ የሚተነተንበት ሊግ ነው:: ሴሪ ኤ ቫርን ቀድመው ከጀመሩ ሊጎች አንዱ ቢሆንም እንደ ጁቬንቱስ፣ ኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን ላሉት ታላላቅ ክለቦች አሁንም ድረስ የዳኞች አድልዎ አለ የሚለው እሮሮ አልቆመም። በጣሊያን የቫር ትልቁ ፈተና የጨዋታውን ፍጥነት መገደቡ ነው። ዳኞች ውሳኔ ለመወሰን የሚቆዩበት ጊዜ መርዘሙ ስፖርቱን ወደ ክርክር መድረክነት ቀይሮታል። ነገር ግን ጣሊያኖች ከእንግሊዝ አንጻር በቅርቡ ከፊል አውቶማቲክ የኦፍሳይድ ቴክኖሎጂን (Semi-automated offside) ቀድመው በመጠቀማቸው በመጠኑም ቢሆን የሚነሱ ቅሬታዎችን መቀነስ ችለዋል።
በጀርመን ቡንድስ ሊጋ የሚገኙ ደጋፊዎች እግር ኳስ የሕዝብ ነው በሚለው የ 50+1 ሕግ የሚያምኑ በመሆናቸው ቫር በስታዲየም ውስጥ ያለውን የተመልካች ስሜት ስለሚገድል አጥብቀው ይቃወሙታል። የዳኞች አድልዎ ከሌሎቹ ሊጎች አንጻር ሲታይ በቡንደስ ሊጋው አነስተኛ ቢሆንም የቫር የውሳኔ አሰጣጥ ግልጽነት አለመኖር እና ስታዲየም ውስጥ ላሉ ደጋፊዎች ምክንያቱ በቶሎ አለመነገሩ ቴክኖሎጂው የእግር ኳስን ሕዝባዊነት እያጠፋው ነው የሚለውን ሀሳብ አጠናክሮታል።
በፈረንሳይ ሊግ አንድ ያለው የቫር አተገባበር ደግሞ ከሌሎቹ ሊጎች የተለየ የኢኮኖሚ እና የቴክኒክ ፈተናዎች ያሉበት ነው። የፈረንሳይ ሊግ ከሌሎቹ አራት ታላላቅ ሊጎች ጋር ሲነጻጸር የፋይናንስ አቅሙ አነስተኛ ነው:: በሊጉ የካሜራ ጥራቶች እና የዳኞች ስልጠና በተፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ ምክንያት የቫር ስህተቶች በብዛት ይታዩበታል። የፓሪስ ሴንት ዠርመን (PSG) በሊጉ ያለው የገንዘብ እና የተጽዕኖ የበላይነት ዳኞች ሳያውቁትም ቢሆን በቫር ውሳኔዎች ላይ ለክለቡ እንዲያደሉ ያደርጋቸዋል የሚል ወሬ በስፋት ይሰማል:: በተለይ ወራጅ ቀጠና ላይ ያሉ ክለቦች በቫር በሚወሰንባቸው አወዛጋቢ የፍጹም ቅጣት ምት ከሊጉ መሰናበታቸው በፈረንሳይ እግር ኳስ ውስጥ የቴክኖሎጂውን ተአማኒነት አሳጥቶታል።
ታዲያ ይህንን ስፖርቱን እያመሰ ያለውን የቫር ቴክኖሎጂ ፈጽሞ ማጥፋት ነው ወይስ ማስተካከል? የሚለው የዘመናችን ትልቁ የእግር ኳስ መከራከሪያ ሀሳብ ነው:: አብዛኛዎቹ የስፖርቱ ምሁራን ቴክኖሎጂን ወደ ኋላ መመለስ ስለማይቻል አሰራሩን ማሻሻል ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ ይስማማሉ:: የመጀመሪያው መፍትሔ የዳኞችን ምልልስ በቀጥታ ማሰማት (Live Audio Broadcast) ነው::
በራግቢ ስፖርት እንደሚደረገው ሜዳ ላይ ያለው ዳኛ እና የቫር ክፍል ዳኞች የሚያደርጉት ውይይት እና የሚሰጡት ውሳኔ በስታዲየም ለሚገኙ ደጋፊዎች እና በቴሌቪዥን ለሚከታተሉ ተመልካቾች በቀጥታ ሊሰማ ይገባል:: ይህ አሰራር ግልጽነትን ከመፍጠሩም በላይ የዳኞችን አድሏዊነት ይቀንሳል የሚል የመፍትሄ ሀሳብ ተቀምጧል:: ሌላው ቫር አንድን ክስተት ለመገምገም ከ 60 ሴኮንድ በላይ መውሰድ የለበትም የሚል ነው፤ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ግልጽ እና ጉልህ ስህተት መሆኑ ካልታወቀ ዋና ዳኛው በመጀመሪያው ውሳኔ ጸንቶ ሊቀጥል ይገባል የሚል ሀሳብ ይነሳል።
እንዲሁም በቴኒስ እና በቅርጫት ኳስ እንደሚደረገው እያንዳንዱ አሰልጣኝ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ የዳኛን ውሳኔ በቫር እንዲገመገምለት የመጠየቅ መብት ሊሰጠው ይገባል የሚል ሀሳብም አለ። ይህ ዳኞች በራሳቸው ፍቃድ ብቻ ማጣራት እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ያልተገደበ ስልጣን ሚዛናዊ ያደርገዋል ማለት ነው:: በተጨማሪም ከፊል አውቶማቲክ የኦፍሳይድ ቴክኖሎጂን በሁሉም ሊጎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተግባራዊ በማድረግ ስህተቶችን መቀነስ እንደሚቻል ቢቢሲ ስፖርት ያስነብባል:: የቫር ቴክኖሎጂን የተካኑ እና የካሜራ እይታን በሚገባ የተረዱ ገለልተኛ የቫር ስፔሻሊስቶችን በማፍራት የውሳኔዎችን ጥራት መጨመር ሌላኛው መፍትሄ ነው ይላል መረጃው::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


