ከጨዋታ ባሻገር                  

0
147

የብዙዎቻችን ልጅነት በጥሩ ጨዎታዎች የታጀበ ነው። የልጅነታችን ጨዋታዎች የሕይወትን እውቀት የቀሰምንባቸው መማሪያዎች ነበሩ::  ዛሬ ግን ያ ጨዋታ በቴክኖሎጂ (ስማርት ስልክ፣ ታብሌት፣ ቴሌቪዥን) እና በዘመናዊ የከተማ አኗኗር  ተተክቶ  የልጆች ጨዋታ ድምፅ እየቀነሰ መጥቷል::

የልጆች ጨዋታ  በሰው ልጅ እድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ሳይንስ ያረጋግጣል:: ታዋቂው የስነ-ልቦና ባለሙያ  ሌቪ ቬጎትስኪ ጨዋታ እና የልጆችን አዕምሮ እድገት በሚመለከት ጥናት አድርገዋል:: በዚህም ጨዋታ የልጆች የግንዛቤ እድገት  እና የቋንቋ ክህሎት ዋና ምንጭ መሆኑን አስረድተዋል:: በኢትዮጵያ አውድ ደግሞ ባህላዊ ጨዋታዎች የማንነት ግንባታ፣ የማህበራዊ ትስስር እና የባህል ቅርስ መተላለፊያ መንገዶች ናቸው::

የኢትዮጵያ ባህላዊ ጨዋታዎች በዋናነት በሦስት ምድቦች ሊከፈሉ ይችላሉ:: የቡድን ጨዋታዎች፣ የክህሎት እና የጥበብ ጨዋታዎች፣ እና የቃላት/የስነ-ቃል ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ::

የቡድን ጨዋታዎች እና ማህበራዊ ክህሎት

እንደ ገና እና ቀለበት (ልጆች ክብ ሰርተው የሚጫዎቷቸው)  ያሉ ጨዋታዎች ልጆች በቡድን የመስራት፣ የመቻቻል እና የማህበራዊ ህግጋትን የማክበር  ባህልን ያዳብራሉ።

በገና በዓል ወቅት የሚጫወቱት ጨዋታ ከፍተኛ የአካል ብቃት እና የቡድን ስራን ይጠይቃል:: “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” የሚለው ባህላዊ አባባል በጨዋታ ወቅት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በይቅርታ እና በመቻቻል የመፍታት ባህልን ያንፀባርቃል:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ትምህርት ክፍል በመለሰ መኮንን (2010ዓ.ም) የተደረገው “የባህላዊ ጨዋታዎች ሚና ለልጆች እድገት” የተሰኘ ጥናት እንደሚያመለክተው የቡድን ጨዋታዎች ልጆች ማህበራዊ ህጎችን፣ ተራ መጠበቅን እና የቡድን ስራን በተግባር እንዲለማመዱ ይረዳቸዋል:: ጥናቱ አክሎም እነዚህ ጨዋታዎች በልጆች ላይ የሚፈጥሩት ጤናማ ፉክክር አሸናፊነትን በጸጋ መቀበልን እና ሽንፈትን መቋቋምን  እንደሚያዳብር ያብራራል::

ልጆች ክብ ሰርተው የሚያደርጉት ጨዋታ  የትኩረት  እና የፍጥነት ክህሎትን የሚጠይቅ ነው:: ልጆች በቡድን ተደራጅተው ለጋራ ዓላማ እንዲሰሩ ያበረታታል::

የክህሎት፣ የጥበብ እና የሒሳብ እውቀት

ገበጣ፣ ሰኞ ማክሰኞ  እና አኩኩሉ  የአካል ብቃት፣ የአእምሮ ንቃት እና የሂሳብ ስሌትን ያዳብራሉ:: ገበጣ ጥንታዊ ጨዋታ ነው:: በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ይታወቃል:: የስትራቴጂክ አስተሳሰብን እና የሂሳብ ስሌትን ለማዳበር ፍቱን መሳሪያ ነው:: በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአለማየሁ ተቀባ (2013) የተሰራው “ሀገር በቀል ጨዋታዎች እና የሒሳብ ትምህርት”  የሚል ጥናት ገበጣ የሒሳብ ስሌት፣ ስልት መንደፍ እና የሎጂክ ችሎታን እንደሚያዳብር በሳይንሳዊ መንገድ አረጋግጧል:: ጥናቱ ገበጣን እንደ “የአእምሮ ጂምናዚየም” በመግለጽ ልጆች ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት ክህሎታቸውን ከልጅነት ጀምሮ እንዲያዳብሩ እንደሚረዳቸው አመልክቷል::

ሰኞ ማክሰኞ ጨዋታ የአካል ሚዛን መጠበቅን፣ የቅንጅት እና የቁጥር ቅደም ተከተልን ያስተምራል:: ልጆች እየዘለሉ ቁጥሮችን ሲጠሩ፣ የሂሳብ እና የቋንቋ ክህሎታቸውን በተጓዳኝ ያዳብራሉ::

የቃላት፣ ስነቃል እና የግንዛቤ እድገት

እንቆቅልሽ  እና ተረት  የቋንቋ ክህሎትን፣ የአካባቢ እውቀትን እና የስነ-ምግባር እሴቶችን ያስተላልፋሉ:: “ቤት ሰርቶ በር የሌለው…?” ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ እንቁላል ይሆናል:: እነዚህ እንቆቅልሾች የልጆችን የመተንተን፣ የመገመት  እና የፈጠራ አስተሳሰብ ያሳድጋሉ:: ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች” በሚለው መጽሐፋቸው፣ እንቆቅልሽ የልጆችን የአካባቢ እውቀት (ስለ እንስሳት፣ እፅዋት፣ ቁሳቁስ) እንደሚያሰፋ እና የቋንቋ አጠቃቀማቸውን እንደሚያዳብር አስረድተዋል::

ተረቶች የማህበረሰቡን ታሪክ፣ ባህል እና ሞራላዊ እሴቶች (ለምሳሌ ታማኝነት፣ ትጋት፣ ደግነት) ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ:: ተረቶች ልጆች የህይወትን ውስብስብነት በምሳሌያዊ መንገድ እንዲረዱ እና የስነልቦና ዝግጁነት እንዲኖራቸው እንደሚረዱ ተገልጿል::

ማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ተጽእኖ

ባህላዊ ጨዋታዎች ለማህበራዊ ግንኙነት መሰረት ናቸው:: ልጆች አብረው ሲጫወቱ ይተዋወቃሉ፣ ይግባባሉ፣ ይጣላሉ፣ ይታረቃሉ:: ይህ ሂደት የግጭት አፈታት ክህሎትን ያዳብራል:: ጨዋታ የልጆች ማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ እድገት ወሳኝ ነው::  ጨዋታዎች ህግ ማክበርን፣ ተራ መጠበቅን፣ ፍትሃዊነትን እና አመራርን  ያስተምራሉ::

በተጨማሪም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለልጆች ጤንነት ወሳኝ ነው:: ሩጫ፣ ዝላይ እና ጉልበት የሚጠይቁ ጨዋታዎች (ለምሳሌ  አኩኩሉ፣ ሰኞ ማክሰኞ) የልጆችን ጡንቻ ያጠናክራሉ፣ የደም ዝውውርን ያሻሽላሉ፣ እናም ከመጠን በላይ ውፍረትን  ይከላከላሉ:: የአለም ጤና ድርጅት ህጻናት በቀን ቢያንስ 60 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመክራል:: ባህላዊ ጨዋታዎች ይህንን በነጻ እና በደስታ የሚያሟሉ ናቸው::

ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች

ዛሬ ላይ ባህላዊ ጨዋታዎች በዲጂታል አለም እና በዘመናዊነት ተፅዕኖ ስር ወድቀዋል:: የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ትምህርት ክፍል ባካሄደው “የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጽእኖ በአዲስ አበባ የልጆች ባህላዊ ጨዋታዎች ላይ” በሚል የሰለሞን በቀለ፤ 2011 ዓ.ም ጥናት ከመጠን በላይ የስክሪን ጊዜ  እና የቪዲዮ ጨዋታዎች ሱስ የልጆችን የአካል ብቃት፣ የማህበራዊ ክህሎት እና የፈጠራ ችሎታ እየቀነሰ መምጣቱን አሳይቷል:: ልጆች ከጓደኞቻቸው ጋር በአካል ተገናኝተው ከመጫወት ይልቅ በብቸኝነት ስክሪን ላይ ማፍጠጥን እየመረጡ ነው::

በከተሞች የመጫወቻ ቦታዎች እጥረት እና ክፍት ቦታዎች በህንፃዎች መሞላት ልጆች በነጻነት እንዳይጫወቱ እንቅፋት ሆኗል:: አንዳንድ ወላጆች ጨዋታን እንደ ጊዜ ማባከን በመቁጠር ልጆች በትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ መገፋፋታቸው ሌላው ችግር ሆኖ በጥናቶች ቀርቧል::

የልጆችን ሁለንተናዊ ንቃት እና ጤንነት ለመጠበቅ ጥናት አድራጊዎች የመፍትሔ ሀሳቦችንም ጠቁመዋል:: የመጀመሪያው መፍትሔ ያለው ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው:: ባህላዊ ጨዋታዎችን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት፣ በስፖርት ክፍለ ጊዜ እና በክበባት ማስተማር ቀዳሚው መንገድ ነው::

ቀጥሎ የሚመጣው የከተማ ፕላን ጉዳይ ነው:: መንግስት እና የከተማ አስተዳደሮች ለልጆች የሚሆኑ የመጫወቻ ፓርኮች እና ክፍት ቦታዎችን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት አለባቸው:: በሦስተኛ ደረጃ ወላጆች የመፍትሔው አካል ሆነው ይመጣሉ:: ለልጆቻቸው የስክሪን ጊዜ ገደብ ማበጀት እና ከቤት ውጭ እንዲጫወቱ ማበረታታት ይኖርባቸዋል::

የመጨረሻው መፍትሔ ያለው ብዙኀን መገናኛዎች እጅ ነው:: የባህል ጨዋታዎችን የሚያስተዋውቁ ፕሮግራሞችን፣ ዶክመንተሪዎችን እና የልጆች ዝግጅቶችን ማቅረብ ሲችሉ ልጆች ያንን ይማራሉ::

ባህላዊ የልጆች ጨዋታዎች የትዝታ ማህደር ብቻ አይደሉም:: የነገው ትውልድ የማንነት፣ የጤና እና የአእምሮ ብቃት መሰረት ናቸው:: እነዚህ ጨዋታዎች ልጆች ጤናማ፣ ማህበራዊ እና አእምሯዊ ብቃት ያላቸው ዜጎች ሆነው እንዲያድጉ ያግዛሉ:: ዛሬ የምንዘራው የጨዋታ ዘር፣ ነገ የምናጭደው ጠንካራ እና አምራች ዜጋ ይሆናል::

ማረፊያ

 

የማሳበብ መዘዝ

በፍርዱ ሸንጎ ፊት ፣

ስትቆም በክስ ወጥመድ፣

ብርቱ ፀፀት አስሮህ፣

ካቃተህ መራመድ፣

እገሌ ነው ብለህ፣

ማሳበብ አትልመድ።

ሟች ሞቶ እንዲገኝ፣

ሀሳብ አመንጭተህ፣

ግብር አበሮችህን፣

በወኔ አበርትተህ፣

ጥይቱ እንዲተኮስ ፣

ጥይት አቀብለህ፣

የገዳዮች አውራ፣

አንተ ራስህ እያለህ፣

ታድያ በፍርዷ ቀን ፣

“ገዳይ አይደለሁም”

ስለምን ትላለህ?

ይኸውልህ ስማኝ…

ተባብረህ ከነበር፣

ካጥቂዎቹ መሀል፣

የማያልፈው ቅጣት፣

አንተም ይገባሀል።

ዮሐንስ ገርማሜ

(አቢብ በዓለሜ)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here