በሲሲሊ ካታኒያ ከተማ ኗሪው ውሻውን አሰልጥኖ ከቤቱ የሚያወጣውን ቆሻሻ በመንገድ ዳር እንዲጥል ማድረጉ በቁጥጥር ካሜራ በመረጋገጡ መቀጣቱን ዩፒአይ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አበቅቶታል::
ግለሰቡ ቆሻሻን መንገድ ዳር በዘፈቀደ መጣል በህግ የሚያስቀጣ በመሆኑ ውሻውን አሰልጥኖ ተጠራቅሞ በከረጢት የታሰረን ቆሻሻ በተደጋጋሚ በድብቅ እንዲጥል አድርጓል:: በከተማዋ በቀጣናው የተሰቀለ የእንቅስቃሴ መከታተያ እና መቅረጫ ካሜራ በተለያየ ጊዜ ውሻው በከረጢት የታሰረ ቆሻሻ እያወጣ መጣሉን ተቀርጾ መሰነዱ ተረጋግጧል::
የቀጣናው ፖሊስም የውሻውን አሳዳሪ ማንነት ለይቶ ማስረጃዎቹን አሰባስቦ ለህግ አቅርቧል::
የከተማዋ አስተዳደርም ለችግሩ በመፍትሄነት የምስል መቅረጫ ካሜራዎችን ለመትከል ተገዷል:: በመሆኑም በቅርቡ ከተፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶች መካከል በውሻ ቆሻሻ የሚያስጥለው የሲሲሊውኗሪ አንዱ ሆኖ ተገኝቷል::
በመጨረሻም ግለሰቡ ወንጀለኛነቱ ተረጋግጦ ከ1500 እስከ 1800 ፓውንድ ሊቀጣ እንደሚችል ነው ድረ ገጹ በማጠቃለያነት ያስነበበው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


