ፓርኩ በግሪንላንድ የሚገኝ ሲሆን ስፋቱ 972 ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዌር ወይም ካሬ ኪሎ ሜትር ተለክቷል:: የፓርኩ ክልል 80 በመቶ በግግር በረዶ የተሸፈነም ነው::
ፓርኩ በ1974 እ.አ.አ የተመሰረተ ሲሆን በ1988 እ.አ.አ ተስፋፍቶ እንዲከለል በመደረጉ አሁን ያለውን ልኬታ እንዲይዝ አስችሎታል::
የሰሜን ምስራቅ ግሪንላንድ ብሔራዊ ፓርክ በስፋቱ በዓለም ቀዳሚ ነው:: መጠኑን በውል ለማሳየት የፓርኩ ስፋት ከዓለም 195 ሀገራት 166ቱን እንደሚበልጥ ድረገፆች አስነብበዋል::
በፓርኩ ቀጣና ቋሚ ኗሪዎች የሉም:: በበጋ ወቅት ለምርምር በሚያገለግሉ አራት ጣቢያዎች ውስጥ ባለሙያዎች በጊዚያዊነት እንደሚቀመጡ ነው የተጠቆመው:: ለአብነት በ2008 እ.አ.አ በክረምት 31 ሰዎች እና 110 ውሾች ሰፍረው እንደነበር ተመዝግቦ ተገኝቷል::
በፓርኩ ቀጣና ዋና ጽ/ቤቱ ዳንቦርግ፣ የአየር ሁኔታ መከታተያ፣ ወታደራዊ ጣቢያ፣ የሥነ ምህዳር ምርምር ጣቢያዎች ይገኛሉ::
የፓርኩ ቀጣና ከእንስሳት የዋልታ ድብ፣ “መስክ ኦክስን” የአርቲክ ቀበሮ፣ ጥንቸል፣ ተኩላ ከባህር እንስሳት “ሲል” “ዎልሩስ” መኖራቸው ተረጋግጧል:: ከአእዋፍ 60 ዝርያዎች መኖራቸውም ሰፍሯል:: ከነዚህ ውስጥ ባህር ጠላቂ ዝይ፣ ጭልፊት፣ የበረዶ ጉጉት እና ቁራ በቀጣናው እንደሚገኙም ድረ ገፆች አስነብበዋል::
በተናጠል ቀጣናውን ለመጐብኘት በውሾች በሚጐተት የበረዶ ላይ ተንሸራታች ጋሪ መገልገል ይችላል- አገልግሎቱን የሚያቀርቡ ግለሰቦችም ስለሚገኙ:: ከዚህ ባለፈ ባለሞተር ተሽከርካሪም ሆነ ጀልባ ወ.ዘ.ተ አለመፈቀዱ ነው የተገለፀው::
ወደ ፓርኩ ገብቶ ለመጐብኘት ከግሪን ላንድ መንግሥት ፈቃድ ማግኘት ግድ ነው:: ለጐብኝዎች የዓየርም ሆነ የየብስ መጓጓዣ አይሞከርም- ከጀልባ ውጪ::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቪዚት ግሪንላንድ ኦሽንዋይድ ኤክስፒዲሽን፣ ዋይልድ ላይፍ ወርልድ ዋይድ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


