ምርጫ እና ዝግጅቱ

0
132

ምርጫ የዴሞክራሲ መሠረታዊ መሣሪያ ነው። ሕዝብ ፈቃዱን በነፃ እና በሰላም ለመግለጽ የሚጠቀምበት መንገድም ነው። በኢትዮጵያም ምርጫ የሕግ መሠረት ያለው ሂደት ሲሆን በሕገ-መንግሥት እና በሌሎች የምርጫ ሕጎች ይመራል። ሕዝቡ ደግሞ ተወካዮቹን በመምረጥ የምርጫ ቀጥተኛ ተሳትፎውን ያደርጋል።

በአጠቃላይ ምርጫን በተመለከተ በበላይነት የሚመራው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፤ ቦርዱ ዕጩዎችን እና መራጮችን መመዝገብ፣ የምርጫ ጣቢያዎችን ማዘጋጀት እና ውጤቶችን ማሳወቅ እና መሰል ተግባራትን ያከናውናል። ምርጫ በነፃነት፣ በፍትሕና በግልጽነት እንዲካሄድ የሕግ መመሪያዎችም ተዘጋጅተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሊካሄድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀነ ቀጠሮ ተቆርጦለታል፤ ይህን መሥረት በማድረግም ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ:: የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ማኒፌስቷቸውን እና ምልክታቸውን እያስተዋወቁ ነው።

በተመሳሳይ መራጮች መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና መዘናጋት እንዳይኖር ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ቋንቋዎች የምርጫ ኅብረ ዝማሬን ይፋ አድርጓል። “ምርጫችን ነው” የሚል ስያሜ የተሰጠው ኅብረ ዝማሬው በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ እና በሌሎችም ቋንቋዎች መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ እንደተናገሩት ኅብረ ዝማሬው መራጩ ሕዝብ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያደርግ የሚያበረታታ ነው። ከጥር 01 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የዕጩዎች ምዝገባ ሲደረግም ቆይቷል፤ በአሁኑ ወቅትም የማጥራት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል። ኅብረ ዝማሬው ታዲያ መራጮች ግንዛቤ እንዲኖራቸው እገዛው ከፍ ያለ ይሆናል ነው የተባለው::

እንደ ሰብሳቢዋ ማብራሪያ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ነው፤ ይህም ከ45 በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ይከናወናል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ በ17 ሺህ ያህል ምርጫ ጣቢያዎች  የዲጂታል ምዝገባ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በተዋረድ ጽ/ቤቶችን መክፈት እና ሥራ ማስጀመር፣ የምርጫ ቁሶችን ማሰራጨት፣ ለታዛቢዎች ፈቃድ መስጠት እና ማሰማራት ደግሞ ለምርጫው ስኬት እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ናቸው::

ምርጫ ቦርድ የሚያዘጋጃቸው የፓርቲዎች የክርክር መርሐ ግብሮች ደግሞ መራጩ በጉጉት የሚጠብቃቸው እና የተሻለ ግንዛቤ የሚይዝበት ዐቢይ ተግባር ነው፤  ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባቸው። የቦርዱ ሰብሳቢ መገናኛ ብዙኃን በፍትሐዊነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራም ማሳሰቢያም ሰጥተዋል። “መገናኛ ብዙኃኑ ሁሉም ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን እና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ እንዲያስተዋውቁ ያለ አድልኦ ዕኩል ዕድል መስጠት ይጠበቅባችኋል” ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብን ተቀብለው መፈራረማቸው ደግሞ ቦርዱ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ይገኝበታል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን በተገኙበት 48ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ የሚወዳደሩባቸውን ምልክቶች ይፋ መደረጉ ይታወሳል፤ በዚህ ወቅት ነው የሥነ-ምግባር ደንቡ የተፈረመው::

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ የሚከናወነው ሁሉም ፓርቲ ሕግን አክብሮ ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሰባት ምዕራፎችና በ30 አንቀጾች የቀረበውን እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር አስቀድሞ ውይይት ተደርጎበት ሃሳብ የሰጡበትን የሥነ-ምግባር ደንብ አስፈላጊነት፤ እንዲሁም ዝርዝር አንቀጾቹ ምን እንዳካተቱ ጭምር ለመድረኩ ተሣታፊዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንዲፈርሙበት ተደርጓል።

የዋና አሠልጣኞች ሥልጠና መሰጠቱ ደግሞ ለጠቅላላ ምርጫው ስኬት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፤ እነዚህም የመስክ አሠልጣኞችን በተዋረድ የሚያሰለጥኑ ዋና አሠልጣኞች ናቸው። በስልጠናው ሦስት መቶ ያህል ዋና አሠልጣኞች ተሳትፈዋል፤ እነዚህም በየሥልጠና ማዕከላቱ በመሰማራት ከአምስት ሺህ በላይ የመስክ አሰልጣኞችን ያሰለጥናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የመስክ አሰልጣኞች ደግሞ በተዋረድ ከ214 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ስልጠናውን እንደሚሰጡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

መረጃ

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት በ1987 ዓ.ም ከፀደቀ በኋላ እስካሁን ስድስት ሀገራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። እነርሱም፡-

 

1ኛው ሀገራዊ ምርጫ፦ በ1987 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1995)

2ኛው ሀገራዊ ምርጫ፦ በ1992 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2000)

3ኛው ሀገራዊ ምርጫ፦ በ1997 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2005)

4ኛው ሀገራዊ ምርጫ፦ በ2002 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2010)

5ኛው ሀገራዊ ምርጫ፦ በ2007 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2015)

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ፦ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2021)

ማስታወሻ:- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ልብ ይሏል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here