የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቀው የቤት ሥራ

0
118

ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በቀውስ ውስጥ እያለፈ የሚገኘውን የአማራ ክልል የትምህርት ዘርፍ ከገጠመው ችግር በማውጣት በውጤታማነት ለማስቀጠል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር መፍትሔ ተኮር ውይይቶችን እያደረገ ይገኛል። ቢሮው የትምህርት ዘመኑን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል፤ ትምህርት የሁሉም ሥራዎች መሠረት መሆኑን በማንሳት ዘርፉን ከችግር ለማውጣት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ነው ትኩረት አድርጎ የተወያየው፡፡

የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ የስጋት ደሴ በዞኑ በትምህርት ላይ ያለውን ተጨባጭ ተግዳሮት እና ተስፋ በጥልቀት አብራርተዋል። ዞኑ ከፍተኛ የትምህርት ተሳትፎ የነበረበት ቢሆንም ባለፉት ሦስት ዓመታት በሰላም እጦት ምክንያት ትልቅ ፈተና እንደገጠመው ተናግረዋል። በተለይም በ2016 ዓ.ም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ችግር እንደነበር በማንሳት በ2018 ዓ.ም አንጻራዊ መሻሻል ታይቶ 109 ሺህ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ መቻሉን አስታውቀዋል፡

ይሁን እንጂ አሁንም ከ350 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ መሆናቸው እና 169 ትምህርት ቤቶች በደረሰባቸው ጉዳት አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸው አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል ነው ያሉት። የሰላም እጦቱ በፈጠረው ሥጋት ተማሪዎች ወዳልተፈለገ ዓላማ እንዳይሰማሩ እና ማኅበረሰቡ “ሀብቴ ትምህርት ነው” የሚለውን የቆዬ ዕሴቱን እንዳያጣ ትምህርትን ከማንኛውም ፖለቲካዊ አጀንዳ ነጻ አድርጎ ማስቀጠል ይገባል፤ ይህ ደግሞ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ርብርብ የሚጠይቅ ብሔራዊ የቤት ሥራ መሆኑን አቶ የስጋት አስገንዝበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ በከፍተኛ ትኩረት እየተከናወነ ይገኛል። ተማሪዎች በክልል እና በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርቶች እየተሰጡ መሆኑን መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተለይ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ይዘቶችን እንዲከልሱ፣ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተፈታኞችም ቀድሞ የነበሩ የክፍል ደረጃ ይዘቶችን እንዲያጠኑ የተሻለ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የዘንድሮ ተፈታኞች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መያዝ ግዴታ ነው፤ በመሆኑም በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ጨምሮ ሁሉም ይህንን መረጃ እንዲያሟሉ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነጋልኝ ተገኘ በበኩላቸው በዞኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ሂደት በአሁኑ ወቅት ማገገም እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ትምህርት በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ አጀንዳ እንዲሆን የተሠራው ሥራ ለመሻሻሉ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በዚህም 90 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ሥራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከ50 በመቶ በላይ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን ነው የጠቆሙት፡፡ መምህራን እና ተማሪዎች ከደረሰባቸው ሥነ-ልቦናዊ ጫና እንዲወጡም ከዩኒቨርሲቲዎችና ከባለሙያዎች ጋር በመተባበር የምክር አገልግሎትና ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል።

60 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸውና የተጎሳቆሉ መሆናቸውን ያስታወቁት መምሪያ ኃላፊው፣ መልሶ ለመገንባት እና ለመጠገን 283 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም እና “ቀበሌ አንድ” የተሰኘው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ማስፋፊያ ንቅናቄም የዘርፉን ትንሣኤ የሚያበስሩ አዳዲስ ተነሳሽነቶች ሆነው ተጠቅሰዋል። የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ፣ ባለሀብቶች እና መንግሥት በቅንጅት እንዲረባረቡ ጥሪ ቀርቧል።

በአሁኑ ወቅት ከ248 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ ነጋልኝ፣ እነዚህን ተማሪዎች ለማብቃት ልዩ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የክፍለ ጊዜ ብክነት ከመቀነስ ጀምሮ የማጠናከሪያ ትምህርት በስፋት እየተሰጠ ነው፡፡ በተለይም ለ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ልዩ የማብቃት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ፋይዳ ብሄራዊ መታወቂያን ለትምህርት ጥራት እና ለተፈታኞች ተደራሽ ለማድረግ በተሰጠው ትኩረት እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች መታወቂያውን ማግኘታቸው ገልጸዋል።

በመጨረሻም ምንም እንኳን አበረታች ለውጦች ቢታዩም ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት ቤት የመመለስ ጉዳይ ልዩ ትኩረትን ይሻል። ትምህርት ቤቶች ከማንኛውም ጫና ነፃ ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እና ተማሪዎች በሰላም ተገቢውን ዕውቀት እንዲገበዩ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የትምህርት ሥራዎች ግምገማ የተካሄደ ሲሆን፣ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ የመመለስ ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገልጿል። የብሔረሰብ አስተዳደሩ የትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ማኔ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት 34 በመቶ ብቻ የነበረው የተማሪዎች ተሳትፎ በአሁኑ ወቅት ወደ 62 በመቶ አድጓል። ይህ አበረታች ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በአካባቢው ሰላም ከሰፈነ በኋላ በተከናወነ የተቀናጀ ሥራ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው የቀሩ ተማሪዎችን ለመካስ እና ተፈታኝ ተማሪዎችን ለማብቃትም በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በትምህርት ቢሮው በተቀረጸው የተፋጠነ የትምህርት አደረጃጀት አማካኝነት ተማሪዎች ከመደበኛው ክፍለ ጊዜ ውጭ ባሉ ሰዓታት እንዲማሩ በማድረግ ከጓደኞቻቸው ጋር እኩል እንዲራመዱ እየተሠራ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም ለ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች በተመረጡ መምህራን ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ነው ያሉት።

ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት እንዲያውሉ ታስቦ የተጀመረው የአዳሪ ትምህርት ፕሮግራም ሌላው ተጠቃሽ ስኬት ነው። ይህ አሠራር ተማሪዎች በትምህርት ቤት ወይም ወላጆች ባመቻቹላቸው ስፍራ በጋራ እንዲያጠኑ የሚያስችል ሲሆን ባለፈው ዓመት በተተገበረባቸው አካባቢዎች የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ እስከ 80 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ለዚህም እንዲረዳ ቤተ-መጻሕፍት ከሰኞ እስከ እሁድ ክፍት እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳን አበረታች ውጤቶች ቢታዩም፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱ ተማሪዎችን ለማምጣት መረባረብ እንደሚገባ መምሪያው አሳስቧል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ ከማኅበረሰቡ ጋር በተፈጠረ መግባባት ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት የመመለስ ምጣኔ 60 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡ ሰባት ሺህ አዳዲስ የመማሪያ እና የአስተዳደር ክፍሎችን የያዙ ከ218 በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ መሠረተ ልማቶች በጦርነት እና በቀውስ ለተጎዳው የክልሉ ትምህርት ዘርፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ አክለዋል።

ክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎችን ለሚወስዱ ተማሪዎች የተጀመሩ የዝግጅት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የጠቀሱት ቢሮ ኃላፊው፣ በቀጣይም ተወዳዳሪ እና በሥነ-ምግባር የታነጸ የሰው ኃይል ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ክትትል እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል። የትምህርት ጉዳይ የማኅበረሰቡ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ማኅበረሰቡን በማስተባበር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የትምህርት ዘመኑን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ኮሮጆ

ተማሪዎችን ለውጤት የሚያበቁ መንገዶች፦

 

ተማሪዎች የጥናት ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ እና እርስ በእርሳቸው እንዲረዳዱ የአዳር ፕሮግራምን እና የጋራ ጥናትን መከተል ይኖርባቸዋል፡፡

መደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሳይባክን ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የሚሰጡ የማጠናከሪያ ትምህርቶችን መከታተል ለውጤታማነት ወሳኝ ነው።

የቤተ-መጽሐፍት አገልግሎትን ማዘውተር

በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት ያመለጣቸው ተማሪዎች “የተፋጠነ የትምህርት አደረጃጀትን” በመጠቀም የጠፋውን ጊዜ መተካት እና ከጓደኞቻቸው ጋር እኩል መድረስ ይችላሉ።

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here