ኮንትሮባንድ- የእድገት ጠንቅ

0
134

  ምርቶች ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ከሀገር ማስወጣት እና ማስገባት/ኮንትሮባንድ/ እንዲሁም ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ  በንግድ ላይ መሰማራት በሕጋዊ ነገዴዎች ላይ የገበያ ሽሚያ ከመፍጠር ባሻገር  የአንድን ሀገር ምጣኔ ሀብት፣ የዜጎችን ደህንነት እና ጤንነት በእጅጉ የሚጎዱ አደገኛ ተግባራት ናቸው። እነዚህን አደገኛ እንቅስቃሴዎች ለመከላከል መንግሥት፣ ኅብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ጠንከር ያለ ምክረ ሐሳባቸውን እያጋሩ ነው።

ለኢኮኖሚው እድገት ማነቆ የሆኑትን እነዚህ ችግሮች ለመከላከልም ግብረ ኀይል አቋቁሙ ወደ ሥራ ገብቷል:: የአማራ ክልል ምርትና ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ የሕገ ወጥ እና ፀረ- ኮንትሮባንድ ጥምር ግብረ ኀይል የወንጀል ጉዳዮች ቴክኒክ ኮሚቴ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል።

የገበያ ሥርዓቱን ከሕገ- ወጥ እንቅስቃሴ ነፃ ለማድረግ እና ሕጋዊ የገበያ ሥርዓትን ለማጠናከር የወንጀል ጉዳዮች ክትትል ቴክኒክ ኮሚቴ ተደራጅቶ ሥራዎችን ሲያከናውን  እንደቆየ ተገልጿል። በዚህም ሕገ- ወጥነትን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራ፣ በሕገ ወጥ ተግባር በተሰማሩት ላይም ሕጋዊ የቅጣት ርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል። ሕገ – ወጥ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ መስመሩ እንዲገቡ መደረጉም ተመላክቷል።

በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ ለበኵር እንደተናገሩት የቴክኒክ ኮሚቴው ከ13 ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን አቅፎ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። አቶ ሙሉጌታ እንዳሉት ኮሚቴው በስድስት ወራት ሥራው  ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠሩን፣ ሕገ- ወጥ ተግባራት እንዳይከሰቱ ክትትል እና ቁጥጥር አድርጓል።

ይህን ተከትሎም የቴክኒክ ኮሚቴው ባለፉት ስድስት ወራት በ190 ሺህ 150 ነጋዴዎች፣ የንግድ ማኅበራት እና ድርጅቶች ላይ አሥተዳደራዊ ርምጃዎች ተወስደዋል። በዚህም ለ37 ሺህ 615 ነጋዴዎች፣ የንግድ ማኅበራት እና የንግድ ድርጅቶች የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል:: ቀሪዎቹ 30 ሺህ 709 የንግድ ድርጅቶች ታሽገዋል፣ 3 ሺህ 695ኙ ታግደዋል፣ 283 የንግድ ማኅበራት ፍቃዳቸው ተሰርዟል፣ 98 ሺህ 451 ነጋዴዎች ደግሞ ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ ተደርጓል።

የወንጀል ምርመራ በማካሄድ ከሕገ-ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በማጣራት 739 መዝገቦች ለፍርድ ቤት ቀርበው 141 ውሳኔ ማግኘታቸውን ዳይሬክታሩ  ጠቅሰዋል:: በውሳኔዎችም በሕገ ወጦች ከኤግዚቢት፣ ከመቀጮ እና ከአሥተዳደራዊ ውሳኔ በጥቅል 3 ቢሊዮን 245 ሚሊዮን 786 ሺህ 284 ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል።

በስድስት ወራት ውስጥ በደሴ እና ባሕር ዳር ከተማ ሕገ ወጥ የቤንዚል ዝውውር፤ በመተማ መስመር እና ምዕራብ አርማጭሆ ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ዝውውር፤ ሰሜን ጎጃም፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ማርቆስ የመጠቀሚያ ጊዚያቸው ያለፈባቸው የለስላሳ መጠጦች፤ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በአነደድ ወረዳ ከባዕድ ጋር የተቀላቀለ ቅቤ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን የተበላሸ በርበሬ በኮሚቴው   ተወግዷል:: የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ የንግድ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት በዜጎች ደህንነት ላይ ችግር እየፈጠሩ በመሆናቸው የወንጀል ተጠያቂነት እንዲሰፍን እየተሠራ ነው።

የመጠቀሚያ ጊዚያቸው ያለፈባቸው እና በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ 13 ሚሊዮን 471 ሺህ 165 ብር  ግምት ያላቸው የንግድ ዕቃዎች መወገዳቸውንም ዳይሬክተሩ አንስተዋል:: ከእነዚህም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የምግብ ሸቀጦች እና የለስላሳ መጠጦች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል::

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኮሚቴው ያከናወነው ተግባር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው:: የቴክኒክ ኮሚቴው በየሩብ ዓመቱ የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ መቻሉም በጥንካሬ ታይቷል::

የቴክኒክ ኮሚቴው በክልል ደረጃ የተጠናከረውን ያህል በወረዳ እና በዞን በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘቱ፣ የበጀት እጥረት እና የዞን ቴክኒክ ኮሚቴን የመስክ ድጋፍና ክትትል አለማድረግ ደግሞ በስድስት ወሩ የታዩ ድክመቶች ናቸው።  በቀጣይ ቀሪ ጊዚያት ከወረዳ እስከ ክልል ያለውን በተመሳሳይ ጥንካሬ ውጤት ለማስመዝገብ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ/ር) ቅንጅታዊ አሠራሩ ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ባለሀብቱ ምርቱን በሰላም ገዝቶ አጓጉዞ ወደ ውጭ ልኮ የተሻለ ምንዛሬ እንዲያገኝ ጠንካራ ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የንግድ ሥርዓቱን የሚያዛቡ ተግባራት ላይም አምርሮ መታገል እና ሥርዓት ማስያዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፈንድቃ ከተማ፣ በምዕራብ ጎንደር መተማ፣ ዳንሻ እና ጠረፍ አካባቢ የተለየ ጠንካራ ቁጥጥር የሚሹ አካባቢዎች እንደሆኑ አመላክተዋል። ሥራው የንግድ ቢሮ፣ የጉሙሩክ፣ የፖሊስ፣ የፍትሕ ቢሮ አሊያም የሌሎች ተቋማት እና ግለሰቦች ብቻ እንዳልሆነም ቢሮ ኃላፊው አስገንዝበዋል::

የቴክኒክ ኮሚቴው ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮችም አንስተዋል፤ ከእነዚህም መካከል ኬላዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ፣ የገቢ እና ወጪ ኮንትሮባንድ ንግድ ምርቶችን ለይቶ በማወቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ  ተናግረዋል። ለአብነትም የቀንድ ከብቶች ለሀገር አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ እየወጡ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነዳጅ ነው። በቅርቡ በተከናወነ ኦፕሬሽን በሕገ ወጥ መንገድ ነዳጅ ከማደያዎች ሲያወጡ የነበሩ 34 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል። የእነዚህ ተባባሪ የነበሩ 121 ግለሰቦች ተይዘው የእርምት ቅጣት ተወስዶባቸዋል። በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ባሕሪውን እየቀያየረ የሚከሰተውን ሕገ- ወጥነት ለመከላከል የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ነዳጅን ያለ አግባብ ማዘዋወር፣ ባልተፈቀደ ዕቃ ይዞ መገኘት፣ ከተፈቀደለት ሰው ውጪ ይዞ መገኘት በእስራት እና በገንዘብ እንደሚያስቀጣም ኃላፊው  አስገንዝበዋል::

ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የክልሉን ኢኮኖሚ ቋት ማሳደግ እና በትክክል መግባቱንም መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በቀጣይ ከዚህ በተሻለ በመሥራት የክልሉን ኢኮኖሚ ጤናማ ሆኖ  እንዲንቀሳቀስ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል::

ሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ፣ የሕዝቡ ምሬት እንዲጨምር እና መኖር እንዲያቅተው እያደረገ መሆኑ፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የተለያዩ ሸቀጦች እና መድኃኒቶች በሕገ ወጥ መንገድ መዘዋወር፣ መረጃ እና ማስረጃ መደበቅ፣ ምርቶችን ለረጅም ጊዜ ደብቆ ማስቀመጥ፣ ክልሉ ላይ እየታየ ያለው ቁርጠኝነት በወረዳና ዞን ላይ አጠናክሮ አለመሥራት በተሳታፊዎች የተነሱ ነጥቦች ናቸው።

በተለይ በኬላዎች እና በነዳጅ ማደያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል። ሕግን በጣሱ እና የሥነ ምግባር ጉድለት ባሳዩ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ጠንከር ያሉ፣ የማያዳግሙ እና ለሌሎች ትምህርት በሚሆን መንገድ መሆን እንዳለበት ተነስቷል። በክልሉ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴን ማስፈን፣ የሸማቹን መብት እና ጥቅም መጠበቅ፣ ሕገ-ወጥነትን መከላከል እና ሕጋዊ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የግብረ ኀይሉ ቀዳሚ ተግባር  ሊሆን እንደሚገባም ተመላክቷል። ይህ ሲሆን የክልሉ ኢኮኖሚ ያድጋል፤የዜጎች ተጠቃሚነትም ይረጋገጣል:: እናም የቁጥጥሩ ተግባር የተወሰኑ ተቋማት እና ግለሰቦች ሳይሆን የጋራ ሊሆን እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው አረጋግጠዋል::

መረጃ

የኮንትሮባንድ ዋና ዋና ጉዳቶች፡-

በኢኮኖሚው፡- መንግሥት ከቀረጥ ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ ስለሚያሳጣ ሀገር እንድትጎዳ ያደርጋል፡፡

በሕጋዊ ነጋዴዎች፡- ሕጋዊ ነጋዴዎች ቀረጥ ከፍለው ሲሸጡ፣ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ቀረጥ ስለማይከፍሉ በርካሽ ይሸጣሉ፤ በዚህም ሕጋዊው ነጋዴ ከገበያ እንዲወጣ እና ኪሳራ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል።

በኅብረተሰቡ ጤና እና ደህንነት፡- ጥራታቸውን ያልጠበቁ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ የለስላሳ መጠጦች እና ምግቦች እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ስለሚገቡ በህዝብ ላይ ትልቅ አደጋ ይፈጥራሉ።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here