ከቀያይ ዓለቶች የተወለደችው የጥንቱ ዓለም ድንቅ ከተማ

0
167

በዮርዳኖስ በረሃማ ተራሮች መካከል በነፋስና በዝናብ የተገረፉ ቀይ ዓለቶች አንድ ታላቅ ምስጢር ይዘዋል። ይህ ምስጢር ለዘመናት ከአውሮፓውያንና ከዘመናዊው ዓለም ተሰውሮ የቆየው በዓለም ላይ ካሉ ሰባት አዳዲስ ድንቅ ነገሮች አንዷ የሆነችው ፔትራ ከተማ ናት። ፔትራ ተራ ከተማ አይደለችም፤ ይልቁንም የሰው ልጅ ጥበብ፣ የጽናት እና ከተፈጥሮ ጋር የመስማማት ትልቁ ማሳያ ናት። ፔትራ በዮርዳኖስ በረሃማ ተራሮች መካከል የምትገኝ ከዓለት ተፈልፍላ የተሠራች እጅግ አስደናቂ ጥንታዊ ከተማ ናት። “የሮዝ ከተማ” (The Rose City) እየተባለችም የምትጠራው ይህችው ስፍራ ከአለት ተፈልፍላ የወጣች የኪነ-ጥበብ ሙዚየም ትመስላለች። “የሮዝ ከተማ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጣትም ድንጋዮቹ ባላቸው ቀይ፣ ሮዝ እና ብርቱካናማ ቀለም ምክንያት ነው።

ፔትራ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የሚጀምር ታሪክ አላት። በወቅቱ ናባቲያዊያን የተባሉ የአረብ አርብቶ አደሮች አካባቢውን ተቆጣጥረውት ነበር። እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ላይ በድንኳን የሚኖሩ ከብት አርቢዎች ቢሆኑም በሂደት ግን በዓለም ላይ ወደር የማይገኝላቸው መሃንዲሶችና ነጋዴዎች ለመሆን በቅተዋል።

ፔትራ የተገነባችበት ስፍራ ስትራቴጂያዊነት በዘመኗ ተመራጭ አድርጓት ነበር። ከጋዛ፣ ከደማስቆ፣ ከቀይ ባህር እና ከፋርስ ባህረ ሰላጤ የሚመጡ የንግድ መስመሮች መገናኛ በመሆኗ ናባቲያዊያን እጅግ ባለጸጋ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በከተማዋ በኩል የሚያልፉት የቅመማ ቅመም፣ የሐር እና የዕጣን ነጋዴዎች ለጥበቃና ለውሃ አገልግሎት የሚከፍሉት ግብር ከተማዋን ወደ ታላቅ የንግድ ማዕከልነት ቀይሯታል።

ወደ ምስጢራዊቷ ከተማ ፔትራ የሚደረግ ጉዞ የሚጀምረው “ሲቅ” በተባለ ጠባብ ገደል ውስጥ በማለፍ ነው። ይህ ገደል በተፈጥሮ የተሰነጠቀ ግዙፍ ዓለት ሲሆን ርዝመቱ 1.2 ኪሎ ሜትር ያህል ነው። በገደሉ በኩል ስትጓዙ በሁለቱም በኩል ያሉት ቀይ ዓለቶች እስከ 80 ሜትር ከፍታ አላቸው። መንገዱ እየጠበበና እየተጠማዘዘ በሄደ ቁጥር ተጓዡ በአድናቆትና በጉጉት ይሞላል።

በዚህ ጠባብ መንገድ መጨረሻ ላይ በድንገት ወለል ያለ ብርሃን ይፈነጥቅና አንድ እጅግ አስደናቂ ህንፃ ይታያል። ይህም “አል-ካዝነህ” (The Treasury) ወይም ግምጃ ቤቱ በመባል የሚታወቀው የፔትራ መለያ ነው። ከ40 ሜትር በላይ ቁመት ያለው ይህ ህንፃ በቀጥታ ከቀይ ዓለቱ ተፈልፍሎ የተሰራ ነው። የህንፃው ዝርዝር ቅርጾች፣ የምሰሶዎቹ ጥራትና የአሰራር ጥበቡ ረቂቅነት ዛሬ ባለው ዘመናዊ መሣሪያ እንኳን ለመስራት እጅግ አስቸጋሪ የሚባል ነው።

የውሃ መሃንዲስነት ጥበብ

በበረሃ መሃል እንዲህ ያለ ግዙፍ ከተማ እንዴት ሊኖር ቻለ? የሚለው ጥያቄ የብዙዎችን አዕምሮ ይሞግታል። ናባቲያዊያን “የውሃ ጌቶች” ነበሩ። በዓመት ውስጥ ጥቂት ቀናት ብቻ በሚዘንበው የዝናብ ውሃ ተጠቅመው ከተማዋን ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ያደርጓት ነበር።

በዓለቶች ላይ ተፈልፍለው የተሰሩ የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች (Aqueducts)፣ ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች (Cisterns) እና ግድቦች በረሃውን ወደ ገነት ቀይረውት ነበር። ይህ የውሃ አያያዝ ስርአታቸው ዛሬም ድረስ በዘመናዊ የሃይድሮሊክ መሃንዲሶች ዘንድ በአድናቆት ይጠቀሳል። ያለዚህ ጥበብ ፔትራ ለሺህ ዓመታት ጸንታ መቆየት ባልቻለች ነበር።

የከተማዋ ድንቅ ስፍራዎች

ከግምጃ ቤቱ (The Treasury) አልፎ ከተማዋ እየሰፋች ትሄዳለች። በውስጧም የሚከተሉትን ዋና ዋና ስፍራዎች እናገኛለን፦

የሮማውያን ቲያትር ማሳያ ስፍራ አንዱና ታሪክ ነጋሪው የከተማዋ ገፅ ነው። ከዓለት ተፈልፍሎ የተሰራና ከ8 ሺህ በላይ ተመልካቾችን መያዝ የሚችል ግዙፍ ስታዲየም ነው። ናባቲያዊያን ከሮማውያን ጋር የነበራቸውን የባህል ትስስር ያሳያል።

የነገስታት መቃብሮች በከተማዋ የሚገኝ መጎብኘት ያለበት አንዱ የታሪክ አሻራ ነው።  በተራራው ግድግዳ ላይ የተሰሩ ግርማ ሞገስ ያላቸው መቃብሮች ሲሆኑ የከተማዋን ባለጸግነትና የነገስታቱን ክብር ያንጸባርቃሉ።

አድ-ደይር (The Monastery) የተባለው ገዳም በከተማዋ ይገኛል። ወደ ከተማዋ ጫፍ ላይ የሚገኝና 800 ደረጃዎችን በእግር በመውጣት የሚደረስበት ስፍራ ነው። ከግምጃ ቤቱ በበለጠ ስፋት ያለው ይህ ህንፃ ከተራራው ጫፍ ላይ ሆኖ የሚሰጠው እይታ ወደር የለውም።

“የጠፋችው ከተማ” ዳግም መገኘት

በ7ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በደረሰ የኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ እና የንግድ መስመሮች መቀየር ምክንያት ፔትራ ነዋሪዎቿን ማጣት ጀመረች። ለብዙ መቶ ዓመታትም በአካባቢው ከሚኖሩ ጥቂት ዘላን ቤዱዊኖች (Bedouins) በስተቀር የውጭው ዓለም ስለ እርሷ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

እ.ኤ.አ. በ1812 ዮሃን ሉድቪግ ቡርክሃርት የተባለ ስዊዘርላንዳዊ ተጓዥ ራሱን እንደ ሙስሊም ነጋዴ በመሰወርና የአካባቢውን ቋንቋ በመማር ምስጢራዊቷን ከተማ ዳግም ለዓለም አሳወቀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፔትራ የዓለም አቀፍ ቱሪስቶችና የአርኪኦሎጂስቶች መዳረሻ ሆናለች።

ፔትራ የድንጋይ ክምር አይደለችም፤ እርሷ የሰው ልጅ አስቸጋሪውን ተፈጥሮ ተቋቁሞ ዓለቱን አሸንፎና በረሃውን ገዝቶ የገነባት የድል አክሊል ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። እያንዳንዱ የድንጋይ ቅርጽ፣ እያንዳንዱ የውሃ መስመር እና እያንዳንዱ የቀለም ንጣፍ የጥንቱን ዓለም ስልጣኔ በጆሯችን ያንሾካሹካሉ። ፔትራን ስትመለከቱ ላሊበላን ሊያስታውሱ ይችላሉ፤ ሁለቱም ከድንጋይ ተፈልፍለው መሠራታቸው ተመሳሳይ ቢሆንም ፔትራ ወደ ውስጥ (Horizontal) ተፈልፍላ የተሠራች ስትሆን ላሊበላ ደግሞ ወደ ታች (Vertical) ተቆፍሮ የተሠራ ነው።

አጫጭር እውነታዎች

  • የተገነባችበት ዘመን ከ2,000 ዓመታት በፊት ነው።
  • ከአሸዋማ ድንጋይ (Sandstone) ተፈልፍላ የተሠራች ናት።
  • በዩኔስኮ (UNESCO) እ.አ.አ በ1985 በዓለም ቅርስነት ተመዝግባለች።
  • በዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎች ይመጣሉ።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here