እንዴት ሰነበታችሁ የዝግጅታችን ተከታታዮች፤ እትም የእንግዳ ዓምድ የምናስነብባችሁ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሴት ልጅ የቅኔ ሊቅ መሆን እንደምትችል በተግባር ያሳዩትን እማሆይ ዓመተ ማሪያም አሰፋን ነው። እማሆይ ዓመተ ማሪያም በሀይማኖታዊ የቤተክርስቲያን ትምህርት የሊቅነት ማዕረግን ከመቀዳጀታቸው ባለፈ በዘመናዊው ትምህርትም እስከ ማስተርስ ዲግሪ በመጓዝ ጥንታዊውን የግዕዝ ጥበብ በማስተማር ላይ የሚገኙ ታላቅ እናት ናቸው። ከልጅነት እስከ ምንኩስና፣ ከመጻሕፍት ትርጓሜ እስከ ቅኔ የዘለቀውን አስደናቂ ታሪካቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
እማሆይ ዓመተ ማሪያም በመጀመሪያ እንግዳችን ስለሆኑ እያመሰገንን በቅድሚያ ስለ ትውልድዎና ስለ ልጅነትዎ ጅማሮ ቢነግሩን?
እማሆይ ዓመተ ማሪያም እባላለሁ። የተወለድኩት ጥቅምት 16 ቀን 1969 ዓ.ም በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር ደብረ ወርቅ ወረዳ ልዩ ስሙ ቁዴ ኪዳነ ምህርት በሚባል ቦታ ነው። የልጅነት ጊዜዬ የትምህርት ፍቅር የተሞላ ነበር። አባቴ እኔ እንድማር ትልቅ ፍላጎት ነበረው፤ ገና በልጅነቴ በሽኮኮ እያመላለሰ ትምህርት ቤት ይወስደኝ ነበር። ይሁንና አባቴ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ በሞት ቢለየኝም የእርሱን ርእይ እንድፈጽም እግዚአብሔር ረድቶኛል። በወቅቱ ቄስ ደምስ አያሌው የሚባሉ አጎት ነበሩኝ፤ ቆሞስና ታላቅ ሊቅ ነበሩ፤ በልጅነቴ ወንጌል ይገዙልኝና ቃለ ወንጌል እንዳነብላቸው በማድረግ ለመንፈሳዊ ትምህርት መሠረት ጥለውልኛል።
እናቴም በዘመናዊ ትምህርት ስታስተምረኝ ቆይታ እርሷም በድንገት በሞት ተለየችኝ። ከዚያም ከወንድሜ ጋር ሆኜ ለተወሰነ ጊዜ ስወጣ ስወርድ ከቆየሁ በኋላ ከ10ኛ ወደ 11ኛ ክፍል በማልፍበት ወቅት የዓለምን ትምህርት ትቼ ወደ ምንኩስና ሕይወት ለመግባት ወሰንኩ።
ወደ ገዳም የገቡት ገና በወጣትነት ዕድሜዎ ነው? እንዴት ሄዱ? በገዳም የነበረዎት ቆይታስ ምን ይመስል ነበር?
ልጅ ሆኜ ምሥራቅ ጎጃም ደብረ ወርቅ ወረዳ ውስጥ ስላለችው ሀና ኪዳነ ምህረት ገዳም ዝና እሰማ ስለነበር ወደዚያው አመራሁ። እዚያ ስደርስ ገና ሕፃን ነበርኩ። እዚያ ያሉት መነኮሳት ገና ሲያዩኝ “ይህችማ ሕፃን ናት፤ እንዴት አድርገን እንቀበላታለን፤ ቤተሰቦቿም ይቆጡናል” የሚል ስጋት በአእምሯቸው አደረ። በኋላ ግን እዚያው ከገዳሙ አጠገብ ያሉ ገና በ15 ዓመት እድሜያቸው መንነው በወቅቱ እድሜያቸው ወደ 80 ዓመት የሆናቸው መነኩሲት አገኙኝ፤ እርሳቸውም “ቆይ ልጄ እኔ ወደ ሌላ ገዳም እልክሻለሁ፤ እስከዚያ ድረስ ግን ከእኔ ጋር ሱባኤ እንያዝ” ብለው ተቀበሉኝ። እዚያም ፀሎት እንደያዝኩ እዛው ገዳም ውስጥ እናቴ ወለተ ማርያም የሚባሉ በእድሜም ወደ ዘጠና ዓመት አካባቢ የሚሆናቸው ሌላ እናት ነበሩ፤ እርሳቸው ለገዳማውያኑ “ትናንት ሕፃን ናት ብላችሁ ያልተቀበላችኋት ልጅ ለገዳሙ ጠቃሚ ናትና አምጧት፤ በእርሷ እዚህ ገዳም ላይ ብዙ ለውጥ ይታያል” ብለው ባዘዙት መሠረት ሰባት ሆነው መጥተው እግሬ ላይ ወድቀው ይቅርታ ጠይቀውኝ ወደ ገዳሙ አስገቡኝ።
በዚያም የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖልኝ እዚያው መነኮሳቱን እየታዘዘኳቸው ከቆየሁ በኋላ እንደውም በእናታችን ወለተ ሀና ወንበር መቀመጥ አለባት፤ እናት ማድረግም አለብን ተብሎ እመምኔት አድርገው በወንበሩ ላይ ሾመው አስቀመጡኝ። እኔ ግን በጣም ተሰማኝ፤ ገና በቅጡ 18 ዓመት ስላልሞላኝ እንዴት በዚህ ትልቅ ወንበር አቀመጣለሁ ብየ በጣም አለቀስኩኝ። ሌላ ገዳም እሄዳለሁ ብየም ተገለገልኩ። ትምህርት ቤት ነው እያልኩ ስሄድ ሦስት ጊዜ እየመለሱ አምጥተውኛል። እናም በዚህ ሁኔታ ከእኒያ ሴትዮ ጋር እየኖርኩ ሰፊውን ጊዜየን ለገዳሙ እየተላላክሁ እቆይ እና በምትተርፈኝ ትንሽ ሰዓት ወደ እኒያ እናት ተመልሼ የእርሳቸውን ቀለም እማራለሁ። እናም ከእርሳቸው ውዳሴ ማርያም፣ ትምህርተ ህዋትና ህማማተ መስቀል እንዲሁም ሌሎችን ቀለሞች ተምሬያለሁ።
ከገዳም ወጥተው ወደ ሰፊው የቅኔ ጉባኤ ቤት የገቡበት አጋጣሚ እንዴት ነበር?
ከእኒያ እናት ጋር ሆኜ በምትተርፈኝ ሰዓት የሚነግሩኝን ቶሎ እይዝ ነበር። በአንድ ቀን ውዳሴ ማርያምን ጨርሼ ሲያዩኝ በጣም ተገረሙብኝ፤ እንደ ተዓምር ነበር የሆነባቸው። እናም «ልጄ አይንሽ ሳይፈዝ ልብሽ ሳይደነግጥ መያዝ ያለብሽ ለትውልድ የምታስተላልፊው ብዙ ቃለ እግዚአብሔር አለ፤ የቅኔም የመፅሐፍም መምህር ትሆኛለሽ። ስለዚህ ይህ ሀብትሽ ነውና ጉባኤ ቤት ሂጂ» አሉኝ።
ያን ጊዜ የእኒህን እናት አደራ ይዘን ከአንድ ጓደኛየ ጋር በመሆን ከወለተ ሀና ገዳም ወጥተን ወደ ደብረ ድማም ሄድን። በደብረ ድማም መምህር ዲበ ኩሉ ከሚባሉ መምህር ዘንድ ለተወሰነ ጊዜ ቅኔ ተማርኩ። ከዚያም የመጽሐፍ መምህር የሆኑት አንድ አባት «ልጆቼ እኔ ሳልሞት ኑና ከእኔ መፅሐፍ ተማሩ» አሉም፤ እኛም ለአምስት ዓመታት የመጻሕፍትን ትርጓሜን ተማረን አስመሰከርን። በመቀጠልም ወደ መምህር ሰሎሞን ዘንድ ወደ ደቦዛ ሚካኤል፣ ከዚያም ወደ መምህር ፍሬ ስብሐት ሄደን ቅኔ ተማርን። በመጨረሻም ጨጎዴ ሃና ሄጄ ደግሞ ከመምህር ያሬድ ሽፈራው ዘንድ የዋድላ ቅኔን አስመስክሬ መጣሁ፤ ከዚያ በኋላም ወደ ቃራኒዮ መምህር ተስፋ ሥላሴ ዘንድ ሄጄ የዋሸራን ቅኔ ተማርኩ።
የማስተማር አገልግሎትዎ የት ተጀመረ? ምን ፈተናስ ገጠመዎት?
ማስተማር የጀመርኩት በባህር ዳር ከተማ ፔዳ ዩኒቨርሲቲ በስተጀርባ በሚገኘው የተክለ ኃይማኖት ቤተክርስቲያን ነው። መጀመሪያ ላይ እኔ ብቻዬን ከአራቱ ማዕዘን ከሚመጣ ጎረምሳ ተማሪ ጋር እንዴት እሆናለሁ? የሚል ስጋት ነበረኝ። ከዚያም አባ በርናባስ ጋር ወሰዱኝ እና ወደ አቡነ ገሪማ ገዳም ሄጄ እናቶችን እንዳስተምር ላኩኝ። ነገር ግን እናቶች የመማር ፍላጎት ስላልነበራቸው አብሬ ከእነርሱ ጋር አንዳንድ ስራዎችን እየሰራሁ ከቆየሁ በኋላ ግን የቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ የነበሩት መምህር ኃይለ ማርያም «በእኛ ጊዜ የሴት ሊቅ እንዴት ይጠፋል?» በማለት አስጠሩኝና የቅኔና የንባብ ወንበር ሰጡኝ። ከ1999 ዓ.ም ጀምሮም ሕፃናትንና ደቀ መዛሙርቱን በቅኔና በወንጌል እያስተማርኩ እገኛለሁ። እስካሁን በቅኔ ቤት ብዙ ተማሪዎችን፣ በሕፃናት ደረጃ ደግሞ እስከ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን አፍርቻለሁ። ብዙዎች ለትልልቅ ደረጃዎች ደርሰዋል’
መንፈሳዊ እና ዘመናዊ ትምህርቱን እንዴት አጣመሩት? ምን ዓይነት ውጤትስ አስመዘገቡ?
መምህር ኃይለ ማርያም ዘመናዊ ትምህርት እንድማር በጣም ይገፋፉኝ ነበር። እርሳቸው በሞቱ በሦስተኛው ቀን የቀብር ስነ-ስርዓታቸውን ፈጽሜ ማትሪክ ተፈተንኩ። ከዚያም በሂሳብ አያያዝ (Accounting) ዲፕሎማ፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በግዕዝ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሎጅስቲክስ ማኔጅመንት እና በግዕዝ ቋንቋ ሁለት የማስተርስ (MA) ዲግሪዎችን አግኝቻለሁ።ከጀርመን ዩኒቨርሲቲ ከመጡ ዶክተር ጌቴ ከሚባሉ ምሁር ጋር በመሆንም ለጥናትና ምርምር ስራዎች አብረን ሰርተናል።
ስለ ወደፊት ርእይዎ እና ስለ ግእዝ የምርምር ተቋምዎ ግንባታ ቢነግሩን?
ትልቁ ራእዬ ጥንታዊውን የቅኔ አሰጣጥ ከዘመናዊው የመማር ማስተማር ሂደት ጋር በማጣመር ለትውልድ የሚያስተላልፍ የምርምር ተቋም ማቋቋም ነው። ይህንን ለማድረግ በአሜሪካ የሚኖሩ መንፈሳዊ ልጆቼ ግሩምና ኃይለ ሚካኤል ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉልኝ ነው። የመንግሥት አካላትም አስፈላጊውን ቦታ እንዳገኝ ረድተውኛል፤ አሁን ላይ የግንባታ ሥራው ተጀምሯል። ዓላማው ወጣቶች በጥበብና በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ማድረግ ነው።
ለዚህ ሁሉ ስኬትዎ በዋናነት የሚያመሰግኗቸው አካላት እነማን ናቸው?
መጀመሪያ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በመቀጠልም ትምህርቴን እንድቀጥል ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉልኝና ውለታቸው ለማይረሳው ለጋሽ አለማየሁ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው። እንዲሁም መምህር ኃይለ ማርያም፣ በአሜሪካ የሚኖሩት ልጆቼ ግሮምና ኃይለ ሚካኤል እና ለዚህ ክብር እንድበቃ በጸሎታቸውና በምክራቸው የረዱኝን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።
በመጨረሻም ለትውልዱ በተለይም ለሴቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ትምህርት ዕድሜና ጾታ አይገድበውም። እኔ በብዙ ፈተና ውስጥ አልፌ እዚህ የደረስኩት በእግዚአብሔር እርዳታና በጽናት ነው። ሴቶች “እኛም መማር እንችላለን! የሚል እምነት ሊኖራቸው ይገባል። በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል፤ ምክንያቱም ትዕግስትና ጸሎት ካለ የማይደረስበት ግብ የለም። ትውልዱ የቤተክርስቲያንን እውቀትና ጥበብ ጠብቆ እንዲቆይ በትጋት መማር አለበት።
እማሆይ ዓመተ ማሪያም ስለ ነበረን ሰፊ ቆይታና ስላካፈሉን አስደናቂ ታሪክ በጣም እናመሰግናለን።
እኔም አመሰግናለሁ።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


