ትውልድ የመገንባት ውጣ ውረድ

0
85

የእግር ኳስ ስፖርት እውነተኛ ውበት እና ጥበብ የሚጀምረው በግዙፍ ስታዲየሞች ውስጥ ሳይሆን በየሰፈሩ በሚገኙ አቧራማ ሜዳዎች  ነው:: የነገዋ ኢትዮጵያ ኮከብ ተጫዋቾችዋ የሚፈጠሩት ዛሬ ላይ ሌት ተቀን በሚደክሙ ባለዕራይ አሰልጣኞች እጅ ላይ ነው:: በሰሜን ወሎ ዞን መርሳ ከተማ የሚገኘው የቀድሞ ተጫዋች እና የአሁኑ የታዳጊዎች አሰልጣኝ ዳንኤል ዝናቡ ጤናማ ትውልድ እና ተተኪ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ለማፍራት የራሱን አሻራ እያሳረፈ ይገኛል:: ዳንኤል በፕሪሚየር ሊግ መድረክ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በአጠቃላይ ለአምስት በተለያዩ የሊግ እርከን ለሚገኙ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል:: በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ያካበተውን ልምድ በመጠቀምም  የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚረከቡ ታዳጊዎችን  እያሰለጠነ ነው::

የዳንኤል የእግር ኳስ ህይወት እንደ ብዙዎቹ የሀገራችን ኮከቦች ሁሉ የጀመረው በትውልድ መንደሩ መርሳ ነው:: ገና በለጋ የልጅነት ዕድሜው ነበር ለኳስ የተለየ ፍቅር እንዳለው እና ተፈጥሯዊ ክህሎት እንደታደለ ያሳየው:: ክለቦችን ከመቀላቀሉ በፊት በመርሳ ከተማ እና በወረዳው በሚካሄዱ የውስጥ ውድድሮች ላይ ጎልቶ መታየት ጀመረ:: የተጫዋቹን ልዩ ተሰጥኦ እና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያስተዋሉ የአካባቢው የስፖርት ቤተሰቦች በመርሳ እና በደቡብ ወሎ ዞን ሻምፒዮና ላይ እንዲጫወት አደረጉት:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደማቅ አሻራውን በማሳረፍ ገና በወጣትነቱ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ቻለ:: ይህም አጀማመሩ ለደማቁ የእግር ኳስ ህይወቱ ትልቅ መሰረት ጥሏል::

በሻሸመኔ በተካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግ ክለቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ሊግ እንዲቀላቀል ማድረጉን ዳንኤል ያስታውሳል:: ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ለወልዲያ ከነማ በመጫወት አምስት ዓመታትን በብሔራዊ ሊግ አሳልፏል::

ዳንኤል ከወልዲያ ቆይታው በኋላ በተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል:: በ2008 ዓ.ም ወደ ኮምቦልቻ ከነማ ያመራ ሲሆን ከዚያም ወደ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አቅንቷል:: በ2009 ዓ.ም ወደ ደሴ ከነማ በማምራት ቡድኑን መቀላቀል ችሏል:: ደሴ ከነማ ከብሔራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያድግ ምንም እንኳን በጉዳት ምክንያት የተወሰኑ ጨዋታዎች ቢያልፉትም ልምዱን በማካፈል እና ቡድኑን በሥነ ልቦና በማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል::

በ2011 ዓ.ም ዳግም ወደ አሳደገው ክለብ ወልዲያ ከነማ ተመልሶ በከፍተኛ ሊግ መጫወት የጀመረ ቢሆንም በቡድኑ ውስጥ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ክለቡን መልቀቁ አይዘነጋም:: ከዚህ በኋላ ነው ዳንኤል ትኩረቱን አዲስ የትውልድ ግንባታ ላይ ያደረገው:: ወደ ትውልድ መንደሩ መርሳ በመመለስ ወልዲያ አብረውት ያደጉ ወጣቶችን እና የልጅነት ጓደኞቹን በማሰባሰብ ጠንካራ ቡድን ማቋቋም ቢችልም መርሳን ወደ ከፍተኛ ሊግ ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል:: ይህም ዳንኤልን ከተጫዋችነት እንዲገለል አድርጎታል::

አሰልጣኝ ዳንኤል ይህንን በሜዳ ላይ ያካበተውን ዘመናዊ የእግር ኳስ እውቀት እና ክህሎት በመጠቀም በመርሳ ከተማ የሚገኙ እና ለእግር ኳስ ስፖርት ፍላጎት ያላቸውን ህጻናት በመሰብሰብ የራሱን ፕሮጀክት በመቅረጽ ወደ አሰልጣኝነት ሥራ ገብቷል:: እድሜያቸው ከስምንት፣ ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች የሆኑ 20 ታዳጊዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል::

የስፖርት ዘርፉን ለማነቃቃት እና በተለይም እግር ኳስን ከታችኛው መሰረት ጀምሮ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሰልጣኝ ዳንኤል እየተጫወተ ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የመርሳ ከተማ የወጣቶች፣ ስፖርት፣ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ጌታሁን ደርቦ  ይገልጻሉ::

“አሰላለፉ፣ አሰላለጡ፣ መረጃ አሰጣጡ፣ የውድድር ጨዋታ እንዴት እንደሚካሄድ፣ ጨዋታን የሚያነብበት መንገድ በጣም ይለያል” በማለት ታዳጊዎቹ መሰረታዊ የኳስ ቁጥጥርን (Control)፣ ቅብብልን (Pass) እና ኳስ አነዳድን  (Dribble) ጠንቅቀው እንዲያውቁ እያደረገ መሆኑን አቶ ጌታሁን ገልጸዋል::

ይሁን እንጂ መርሳ ከተማ አነስተኛ የገቢ አቅም ካላቸው ከተሞች አንዷ በመሆኗ ለስፖርቱ የሚመደበው በጀት ውስን ነው:: አቶ ጌታሁን “ያለን በጀት አነስተኛ መሆኑ ሙያዊ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ አልቻልንም” ሲሉ  አቶ ጌታሁን ደርቦ ተናግረዋል:: ጉድለቶቹን ለመሙላት በተደረገ ጥረትም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር ወርልድ ቪዥን ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል::

አሁን ላይ ያለው የበጀት እና የቁሳቁስ እጥረት ትልቅ መሰናክል ቢሆንም ወደፊት ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ እቅዶች ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን  የመርሳ ከተማ የወጣቶች፣ ስፖርት፣ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ጠቁሟል:: ጽህፈት ቤቱ ከመንግስት በጀት በተጨማሪ በራሱ ተነሳሽነት ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ከለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ለማሰባሰብም  ዕቅድ ይዟል:: ከሚመደበው መደበኛ በጀት ላይ በመቀነስ ለሰልጣኞቹ የስልጠና የሚሆኑ ኳሶች እና የሜዳ ላይ ኮኖች እንዲሁም ለአሰልጣኙ የሚሆን የስፖርት ቱታ እና ጫማ የማሟላት እቅድ መያዙን ተገልጿል::

“በአካባቢው ያሉ ባለሀብቶች እና ድርጅቶች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል” ይላሉ፤ አሰልጣኙ እና ጽህፈት ቤቱ:: አቧራማው የመርሳ ሜዳ ነገ በፕሪሚየር ሊጉ የሚነግሡ ኮከቦችን እንደሚያፈራ የዳንኤል ላብ እና የአቶ ጌታሁን ምስክርነት  ማረጋገጫዎች ናቸው። በተጨማሪም የከተማዋ ቡድን በብሔራዊ ሊግ ሲሳተፍ ይጠቀምባቸው ከነበሩት የስፖርት ትጥቆች መካከል የተረፉ አስራ አምስት መለያዎችን ለታዳጊዎቹ ድጋፍ ማድረጋቸውን የከተማዋ የወጣቶች፣ ስፖርት፣ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ባለሙያ ገልጸዋል።

አሰልጣኙ ራሱን በሙያ እንዲያሳድግ እና ሕጋዊ የሙያ ፈቃድ እንዲኖረው የከተማው የወጣቶች፣ ስፖርት፣ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፤ እየሰራም ይገኛል:: ዳንኤል ቀጣዩን እና ከፍተኛውን የ “ሲ ላይሰንስ” የአሰልጣኝነት ስልጠና እንዲያገኝ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑም በመርሳ ከተማ የወጣቶች፣ ስፖርት፣ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ተገልጿል::

በአሁኑ ወቅት መርሳ ከተማ ውስጥ ወጣቱ  ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጠ በመሆኑ የዳንኤል የእግር ኳስ ፕሮጀክት ታዳጊዎችን ከዚህ አጥፊ ሱስ በመታደግ እና በስነ ምግባር በማነጽ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። ታዳጊዎቹ ጊዜያቸውን በሜዳ ላይ በማሳለፍ የውድድር መንፈስን፣ የቡድን ሥራን እና ስፖርታዊ ጨዋነትን እየተማሩ ይገኛሉ ተብሏል::

አሰልጣኝ ዳንኤል በመርሳ ከተማ የጀመረው ይህ ታዳጊዎችን የማብቃት ፕሮጀክት በህጻናቱ ላይ ከሚያመጣው የአካል እና የስነ ልቦና ጥንካሬ ባሻገር ወደፊት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን የሚወክሉ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ኮከቦችን የሚያፈራበት ማዕከል እንደሚሆን ይታመናል:: ታዳጊዎቹ አድገው ሀገራቸው ኢትዮጵያ በ2029 ዓ.ም ልታዘጋጅ ላሰበችው የአፍሪካ ዋንጫ ባሕር ዳር እና ወልዲያ ባሉ ግዙፍ ስታዲየሞች ላይ ተሰልፈው ማየት የአሰልጣኙም ሆነ የጽህፈት ቤቱ የጋራ ህልም ነው::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here