እግር ኳስ ከመዝናኛነት አልፎ ጥልቅ የሆነ የሳይንስ፣ የስነ ልቦና እና ታክቲክ ጦርነት ወደሆነበት አስገራሚ ዘመን ላይ ደርሰናል:: ከጥቂት ዐስርት ዓመታት በፊት በነበረው የዓለም እግር ኳስ በአብዛኛው የተመሰረተው በተጫዋቾች ግላዊ ተሰጥኦ፣ በአካላዊ ጥንካሬ እና ቀጥተኛ በሆኑ የማጥቃት መንገዶች ላይ ነበር:: ዛሬ ግን ይህ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ስቴዲየሞች ልክ እንደ ትልቅ የቼዝ ጠረጴዛ የሚቆጠሩበት እና አሰልጣኞች እንደ ጠቅላይ አዛዥ ረቂቅ ርዕዮተ ዓለሞችን የሚያራምዱበት መድረክ ሆኗል።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ እግር ኳስ በእንግሊዝ ሲጀመር ምስቅልቅል እና ቅርጽ የሌለው እንደነበር የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ:: በዚያን ጊዜ ታክቲክ የሚባል ነገር አልነበረም፤ ቡድኖች ኳስን አግኝተው በግል ክህሎት ወደ ፊት እየነዱ (Dribbling) ከመገስገስ ባለፈ የቡድን ቅንጅት አልነበራቸውም:: የመጀመሪያዎቹ የጨዋታ አሰላለፎች አንድ ተከላካይ፣ አንድ አማካይ እና ስምንት አጥቂዎችን (1-1-8) ያካተቱ እንደነበር ይነገራል:: የጨዋታው አላማ በጉልበት ኳስን ወደ ተቃራኒ ግብ ማድረስ ብቻ ነበር:: ሆኖም እ.አ.አ በ1920ዎቹ አጋማሽ ብቅ ያለው የእግር ኳስ የመጀመሪያው ታላቅ የታክቲክ ለውጥ በቀድሞው የአርሴናል አሰልጣኝ ኸርበርት ቻፕማን ቅርጽ እየያዘ መጥቷል:: በወቅቱ የነበረውን ከጨዋታ ውጪ (የኦፍሳይድ) ሕግ መሻሻል ተከትሎ ቻፕማን ታዋቂውን (3-2-2-3) የተሰኘ አሰላለፍ ፈጠረ። ይህ አሰላለፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመከላከል እና በማጥቃት መካከል ሚዛን የፈጠረ፣ የተጫዋቾችን የሜዳ ላይ ስርጭት የተሻለ ያደረገ እና ለቀጣዮቹ ሶስት አሰርት ዓመታት የዓለም የእግር ኳስ መመሪያ ሆኖ ያገለገለ ታላቅ ጅማሮ ነበር።
እ.አ.አ በ1960ዎቹ በጣሊያኖች የካቴናቺዮ (Catenaccio) ወይም ጥብቅ የመከላከል ፍልስፍና በሄሌኒዮ ሄሬራ አሰልጣኝነት አዲስ መልክ ያዘ። ሆኖም የዘመናዊው ማጥቃት ላይ የተመሰረተ እና ውበት ያለው እግር ኳስ እውነተኛ አባት ተደርጎ የሚወሰደው እ.አ.አ በ1970ዎቹ ብቅ ያለው የደች እግር ኳስ ነው። አሰልጣኝ ራይነስ ሚሼልስ እና ዮሃን ክራይፍ ቶታል ፉትቦል (Total Football) የተሰኘ ዓለምን ያስደመመ ፍልስፍና ይዘው መጡ። የቶታል ፉትቦል መነሻ ሀሳብ እጅግ አስደናቂ ነበር፤ ይኸውም ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ያላቸውን የቦታ ገደብ በመስበር አንድ ተከላካይ ወደ ፊት ሲወጣ አጥቂው ወይም አማካዩ የሱን ቦታ ተክቶ የሚሸፍንበት አጨዋወት ነው።
እ.አ.አ በ1980ዎቹ መጨረሻ ጣሊያናዊው አሪጎ ሳኪ የኤሲ ሚላንን ቡድን ሲያሰለጥን የቶታል ፉትቦልን ሀሳብ ከመከላከል ጋር በማዋሃድ ሌላ አብዮት ፈጠረ:: ሳኪ የተጫዋቾችን የሜዳ ላይ ርቀት በማጥበብ በአጥቂው እና በተከላካዩ መካከል ያለው ርቀት ከ25 ሜትር እንዳይበልጥ በማድረግ የዞን መከላከልን በማስተዋወቅ የተጋጣሚን የመተንፈሻ እና የማሰቢያ ጊዜ አሳጠረ። እነዚህ የእግር ኳስ ጽንሰ ሀሳቦች ለዘመናዊ እግር ኳስ መወለድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል::
የእነዚህን የእግር ኳስ ሊቃውንት ንድፈ ሀሳብ ወስዶ፣ አሻሽሎ እና ከዘመኑ ጋር አዋህዶ ዛሬ ላይ ትልቅ የታክቲክ ፈላስፋ ሆኖ ብቅ ያለው ስፔናዊው ፔፕ ጋርዲዮላ ነው:: ጋርዲዮላ የቦታ አያያዝ ፍልስፍናን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ኳስን ከመቆጣጠር ባለፈ ሜዳውን በጂኦሜትሪያዊ ስሌት በመከፋፈል እግር ኳስን ሳይንሳዊ ማድረግ ችሏል:: በጋርዲዮላ ፍልስፍና ውስጥ እያንዳንዱ ተጫዋች ሜዳው ላይ የት መቆም እንዳለበት በግልጽ ይታያል::
ጀርመናዊው የርገን ክሎፕ ጌገንፕሬሲንግ (Gegenpressing) ወይም ኳስ በተነጠቁ በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ውስጥ በከፍተኛ ሀይል መልሶ የመቀማትን ፍልስፍናን አስተዋውቋል:: ይህ ፍልስፍና በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የኳስ አቀጣጣዮች የተሻለው ፈጠራ እንደሆነ ክሎፕ ያምናል:: ይህ ፍልስፍና ተጋጣሚ ቡድን ከራሱ የግብ ክልል ርቆ እንዳይሄድ በማድረግ እና ስህተት እንዲስራ በማስገደድ ላይ የተመሠረተ ነው::
ከዓመታት በፊት አንድ ቡድን 4-4-2 አሰላለፍ ይዞ ወደ ሜዳ ከገባ ጨዋታው እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚሁ ቅርጽ ይቀጥል ነበር። አሁን ግን አሰላለፍ የሚባለው ነገር ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በወረቀት ላይ የሚሰጥ መነሻ መረጃ ብቻ ሆኗል:: አሁን ላይ ያሉ ታላላቅ ቡድኖች በሚከላከሉበት ወቅት 4-4-2 ሆነው ሊታዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ኳስ በሚቆጣጠሩበት ጊዜ አሰላለፉን ወዲያውኑ ወደ 3-2-5 ወይም 2-3-5 ቅርጽ ይቀይሩታል። በዘመናዊው ታክቲክ የግብ ጠባቂዎች ሚናም ተቀይሯል። ጀርመናዊው ኢማኑኤል ኑየር ፈር በቀደደው እና አሁን እነ ኤደርሰን ሞራየስ እና አሊሰን ቤከር በከፍተኛ ደረጃ በሚተገብሩት የስዊፐር ኪፐር (Sweeper-Keeper) ሚና ግብ ጠባቂው የቡድኑ አስራ አንደኛው የሜዳ ተጫዋች ሆኗል። ይህ ደግሞ ጥቃትን ከኋላ ለመመስረት ግብ ጠባቂው እጅግ ወሳኝ የኳስ አቀባይ ሲሆን ተቃራኒ ቡድን ጫና ለማድረግ ሲሞክር የቁጥር ብልጫን ለመፍጠር ያገለግላል::
ተከላካዮችም ቢሆኑ ኳስን አርቀው ከሚመቱ ጉልበተኞች ኳስ መስርተው ወደሚጫወቱ ተጫዋቾች ተሸጋግረዋል። በዚህ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ ከየትኛውም ተጫዋቾች በላይ አስገራሚ ሚናን የተላበሱት የመስመር ተከላካዮች (Fullbacks) ናቸው:: የመስመር ተከላካዮች ቀድሞ የነበረው ተግባር የመስመር አጥቂዎችን መከላከል እና በመስመር ወደ ፊት በመሄድ ኳስን ማሻገር (Crossing) ነበር:: ዛሬ ላይ በጋርዲዮላ ዘመን ፊሊፕ ላም የተሰጠው ሚና በዓለም እግር ኳስ ተስፋፍቷል::
እነ አሽራፍ ሀኪሚ፣ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ እና ጁሬየን ቲምበር ወደ መሀል በመግባት የጨዋታውን ሕግ ቀይረውታል:: ይህ ታክቲክ በመሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫን ይፈጥራል፤ ኳስ ቢነጠቁ ጠንካራ የመከላከል ሽፋን ይሰጣል፡፤ እንዲሁም የክንፍ አጥቂዎች በነጻነት መስመሩን ይዘው አንድ ለአንድ እንዲገናኙ ሰፊ ክፍተት ይፈጥርላቸዋል::
ወደ መሀል ሜዳ ስንሸጋገር ደግሞ ግማሽ ሜዳ (Half-space) የሚባሉትን ወሳኝ ቦታዎች የመቆጣጠር ፉክክር እናገኛለን:: እንደ ኬቨን ዴብሩይነ እና ማርቲን ኦዴጋርድ ያሉ ብሩህ አእምሮ ያላቸው አማካዮች እነዚህን ክፍተቶች (በመስመር እና በመሀል መካከል ያሉ ስውር ቦታዎችን) በመጠቀም ለተቃራኒ ተከላካዮች ከፍተኛ የውሳኔ አሰጣጥ ፈተና ሲፈጥሩ ከዚህ በፊት ተመልክተናል::
የፊት መስመሩም የዚሁ ታክቲካዊ አብዮት ትልቅ ሰለባ መሆኑን የጊቭ ሚስፖርት መረጃ ያመለክታል:: የባህላዊው ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚና በእጅጉ ተቀይሯል:: በምትኩ ሊዮኔል ሜሲ፣ ሮቤርቶ ፊርሚኖ ወይም ሃሪ ኬን በከፍተኛ ደረጃ በተገበሩት የሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር (False 9) ሚና ተተክቷል:: ይህ አጥቂ የፊት መስመሩን ትቶ ወደ መሀል በማፈግፈግ ተከላካዮችን ከቦታቸውእንዲጎትታቸው ይደረጋል:: እንደ ሞሀመድ ሳላህ፣ ኪሊያን ምባፔ እና ቪኒሲየስ ጁኒየር ያሉት ፈጣን አጥቂዎች ደግሞ ከመስመር መስመር ወደ ተፈጠረው የመሀል ክፍተት በከፍተኛ ፍጥነት በመግባት ትልቅ ግብ አነፍናፊዎች ሆነዋል።
በዘመናዊ እግር ኳስ አጥቂዎች ሲከላከሉ ግብ ጠባቂዎች ሳይቀር ደግሞ በማጥቃት ሂደቱ ሲሳተፉ ተመልክተናል:: ትልቁ እና አጓጊው ጥያቄ “ቀጣዩ የታክቲክ ምዕራፍስ ምን ሊሆን ይችላል?” የሚለው ነው:: እግር ኳስ ቆሞ የሚቀር ስፖርት አይደለም፤ አንዱ ያመጣውን እንቆቅልሽ ሌላው ይፈታዋል፤ አዲስ እንቆቅልሽም ይፈጠራል:: ወደፊት በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ ታላላቅ የታክቲክ ለውጦች አንዱ ቦታ አልባ እግር ኳስ (Positionless Football) የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ መተግበር ሊሆን እንደሚችል የቶክ ስፖርት መረጃ አስነብቧል:: ይህ ፍልስፍና የ70ዎቹ የቶታል ፉትቦል የላቀ ቅጂ እንደሆነ የእግር ኳስ ሊቆች ይናገራሉ:: ወደፊት ግብ ጠባቂዎች ኳስ በሚመሰረትበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቡድናቸው በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ላይ ሲጫወት እስከ መሀል ሜዳ ድረስ ዘልቀው በመግባት የቋሚ አማካይነት ሚናን ሊጫወቱ ይችላሉ ብለው የሚተነብዩ የእግር ኳስ ተንታኞችም አሉ:: የቀጣዩ ትውልድ ተጫዋች የማራቶን ሯጭ ትንፋሽ፣ የአጭር ርቀት ሯጭ ፍጥነት፣ የክብደት አንሺ ጉልበት እና የቼዝ ጠበብት አዕምሮን አጣምሮ የያዘ መሆን ግድ ይለዋል ይላል የጊቨ ሚ ስፖርት መረጃ::
በተጨማሪም የቴክኖሎጂ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሚና የነገው የእግር ኳስ ታክቲክ አብዮት ዋነኛ የለውጥ አራማጅ ይሆናል:: አሰልጣኞች በጨዋታ መሃል የተጋጣሚን የደከመ የሜዳ ክፍል እና የተጫዋቾችን የልብ ምት እና የድካም መጠን በስማርት ልብሶች እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ታግዘው ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ በማንበብ አፋጣኝ የታክቲክ እና የቅርጽ ለውጦችን ያደርጋሉ የሚል ግምትም ተቀምጧል:: እንዲሁም እንደ አሜሪካን ሶከር አሰልጣኞች ለተለያዩ የጨዋታው ክፍሎች የተለዩ ስፔሻሊስቶችን (ለምሳሌ የውጪ ውርወራ አሰልጣኝ፣ የማዕዘን ምት አሰልጣኝ፣ የመልሶ ማጥቃት አሰልጣኝ) ይዘው በቡድን ሆነው ውሳኔ የሚያሳልፉበት ዘመን እውን እየሆነ መጥቷል። የሕግ ለውጦችም የታክቲክ ለውጥን ማምጣታቸው አይቀርም፤ ለምሳሌ አምስት ተጫዋቾች የመቀየር ህግ ቋሚ መሆኑ አሰልጣኞች ጨዋታውን በሁለት የተለያዩ ቡድኖች ጉልበታቸውን ሳይቀንሱ ለ90 ደቂቃ እንዲተገብሩ ሰፊ በር ከፍቶላቸዋል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


