“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመስኖ ልማት ላይ በልዩ ትኩረት በመሥራቴ የተሻለ ምርት እያገኘሁ ነው፡፡ በዚህም ልጆቼን በጥሩ ሁኔታ ማስተማር ችያለሁ፤ ተጨማሪ ገቢም እያስገኘልኝ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ለበኵር የሠጡት አርሶ አደር በቀለ አይሸሽም ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ አርባዕቱ እንስሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለመስኖ ልማት የተሳሳተ አመለካከት እንደ ነበራቸዉ ያስታውሳሉ፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ አዋጭ እንደሆነ የተናገሩት አርሶ አደሩ ልማቱን ሲጀምሩ በግብርና ባለሙያዎች ጫና እና ጉትጎታ ነበር:: አሁን ላይ ጥቅሙን ተረድተው ያለማንም ቀስቃሽ በራሳቸው ተነሳሽነት ወቅቱን ጠብቀው እያመረቱ ናቸው:: አርሶ አደሩ አሁን ላይ የክረምቱን ዝናብ ብቻ ሳይጠብቁ የተሰማሩበት መስኖ ልማት ከፍተኛ ጥቅም እያስገኘላቸው በመሆኑ ለሌሎች አርሶ አደሮችም አርዓያ መሆን ጀምረዋል::
እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ የበጋ መስኖ ልማትን በስፋት ማምረት የጀመሩት በ2007 ዓ.ም ነው:: ያኔ በስጋት የተጀመረው የመስኖ ልማት ዛሬ ድረስ በውጤት ታጅቦ ዘልቋል፤ የቤተሰቡን ኑሮም እንዳሻሻለው ይመሰክራሉ::
አርሶ አደር በቀለ በአሁኑ ወቅት ስንዴ፣ ድንች፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ቡና እና አቮካዶ እያመረቱ ነው:: በዚህ ዓመት ከ60 እስከ 70 ኩንታል ከቀይ ሽንኩርት፣ 15 ኩንታል ድንች እና 10 ኩንታል ስንዴ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ ናቸው:: ከዚህ ጎን ለጎንም በሰብል እና በፍራፍሬ የተሸፈነ ማሳቸውን እየተንከባከቡ፤ የደረቀ የመኸር ሰብላቸውን ደግሞ እየወቁ ወደ ቤት እያስገቡ እንደሆነ ነው የነገሩን::
“አሁን ላይ የአካባቢው ማሳ ከክረምት ባልተናነሰ አረንጓዴ ሸማ የለበሰ ያስመሰለው ገጽታ ለዕይታ ይማርካል!”በማለት አርሶ አደሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አሁን በበጋ መስኖ እየተገኘ ካለው በላይ ምርት ለማግኘት በቂ የአፈር ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ማድረግ፣ የተሻሻሉ እና በምርምር የወጡ አዳዲስ ምርጥ ዘሮችን እና በአጠቃላይ ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ግብዓቶችን በወቅቱ፣ በብዛት እና በጥራት መንግሥት ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
ሌላው ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሚገኙ የነገሩን በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ አለላ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ፈጠነ ብርሐኑ ናቸው:: ወደ ልማቱ የገቡትም የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ በመቀበል ነው:: አርሶ አደሩ በበጋ መስኖ ስንዴ የልማት ሥራ ከገቡ ስድስት ዓመታትን አስቆጥረዋል:: በዚህም ከዓመት ዓመት የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን ለበኵር በስልክ ነግረውናል:: በተያዘው የበጋ ወቅት በግማሽ ሄክታር/በሁለት ጥማድ/ መሬታቸው ላይ ስንዴ እንደዘሩ የተናገሩት አርሶ አደር ፈጠነ፤ ከዚህም 40 ኩንታል ምርት አገኛለሁ የሚል ተስፋ አላቸው::
አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት 90 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ከስንዴ በተጨማሪ በበጋው ወቅት ፓፓያ እና አቮካዶ እንደሚያመርቱም ገልፀዋል::
አርሶ አደር ፈጠነ በአመዛኙ በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን በማስታወስ ሌሎች አርሶ አደሮችም በመስኖ ልማቱ በመሳተፍ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የእርሳቸውን ተሞክሮ መነሻ አድርገው ምክር ለግሰዋል::
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የበጋ መስኖ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ዘሩ ገረመው ለበኵር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል:: እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በተያዘው የበጋ ወቅት 50 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ 51 ሺህ 966 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል:: ክንውኑ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ21 ሺህ ሄክታር ብልጫ አለው:: ይህም የሆነው መሬት ፆም ማደር እንደሌለበት ታምኖ ለአርሶ አደሩ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሠራቱ ነው::
በዞኑ ከስንዴ በተጨማሪ ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ቃሪያ እና ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬ እየለሙ ነው:: አትክልት እና ፍራፍሬን ሳይጨምር ከበጋ መስኖ ስንዴ ከሚለማው ውስጥ ሁለት ሚሊዮን 20 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ባለሙያው ገልጸዋል::
ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች ከሚሰጠው ሙያዊ ምክር እና ድጋፍ በተጨማሪ 90 ሺህ 128 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 64 ሺህ 262 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል:: ሰባት ሺህ የሚጠጋ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችም ለአርሶ አደሮች መሠራጨታቸውን ገልፀዋል:: ነገር ግን ከቴክኖሎጂ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የአርሶ አደሩ ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው የበጋ መስኖ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑ ቢታመንም ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ከመንግሥት በተጨማሪ በተለያዩ ፕሮጀክቶች በኩል እንዲቀርቡ እየተሠራ ነው:: ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በስድስት ሺህ 495 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል ተሰብስቧል:: ከዚህም 259 ሺህ 628 ኩንታል ምርት ተገኝቷል::
ዕቅዱ ስኬታማ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት እና የግብርና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ባለሙያው መልዕክት አስተላልፈዋል::
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2018 በበጋ መስኖ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት አቅዷል:: 481 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል:: ከዚህም 51 ሚሊዮን 595 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል:: እስካሁን ስድስት ሚሊዮን 881 ሺህ ኩንታል ምርትም ተሰብስቧል::
የቢሮው መረጃ እንደ ሚያመላክተው ዘንድሮ (2018 ዓ.ም) አርሶ አደሩን ጨምሮ ከአመራር እስከ ባለሙያ የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት የመስኖ ስንዴ ልማትን በተሻለ መልኩ ለመተግበር ቀድሞ ወደ ሥራ ተገብቷል:: ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በጊዜ፣ በወቅቱ፣ በጥራት… ለአርሶ አደሩ ማቅረብ የግድ ነው፡፡ በመሆኑም 467 ሺህ 707 ኩንታል ምርጥ ዘር እና 774 ሺህ 788 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል::
ባለፈው ዓመት (2017 ዓ.ም) 208 ሺህ 236 ሄክታር የሚጠጋ ማሳ በመስኖ ስንዴ በማልማት ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ ኩንታል የስንዴ ምርት እንደተገኘም መረጃው አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ዘንድሮ በበጋ መስኖ ስንዴ 350 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 13 ሚሊዮን 650 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ነው የቢሮው የመስኖ ውኃ አጠቃቀም አግሮኖሚ ባለሙያ አቶ ንጋቴ አለማየሁ ለበኵር የተናገሩት::
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት (መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም) 319 ሺህ 547 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ነው ባለሙያው የተናገሩት:: ቀሪው በበልግ ወራት በዘር የሚሸፈን መሆኑን አስረድተዋል:: ምርታማነትን ለመጨመር 400 ትራክተሮች ለእርሻ ሥራ አገልግሎት ላይ ውለዋል:: ሁለት ሺህ ሞተር ፖምፕ በአዲስ ተገዝተው አገልግሎት እየሰጡ ነው::
የምርት ብክነትን ለመቀነስም ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እየተሠራ ነው:: በመስኖ ልማቱ ላይ የአርሶ አደሩ ዕውቀት፣ አቅም እና ልምድ እያደገ መሆኑንም ጠቁመዋል:: የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የክልሉን የግብርና ዘርፍ ከባህላዊ ወደ ዘመናዊነት እያሸጋገረ ያለ ሲሆን ይህን የተሻለ ጅምር ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል፣ የግብርና ባለሙያዎችን ክትትል በማሳደግ እና ለአርሶ አደሩ ተገቢውን የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ የክልሉን ምጣኔ ሀብት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል::
የአማራ ክልል ለም መሬት፣ በቂ የውኃ ሃብት እና ምቹ የአየር ንብረት ባለቤት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ንጋቴ፤ ይህንን ፀጋ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል::
መረጃ
አዲስ የነዳጅ ዋጋ ተመን ይፋ ሆነ
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒሥቴር ከመጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ አዲስ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ተመን ይፋ አድርጓል።
ሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋን መነሻ በማድረግ ቤንዚን በሊትር 132 ብር ከ18 ሳንቲም፣ ኬሮሲን 146 ብር ከ14 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ 139 ብር ከ84 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 137 ብር ከ03 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 133 ብር ከ45 ሳንቲም እና የአውሮፕላን ነዳጅ 145 ብር ከ23 ሳንቲም እንዲሸጥ ወስኗል። ሚኒሥቴሩ ይህ የዋጋ ማስተካከያ በሁሉም የነዳጅ ማደያዎች ላይ በአስቸኳይ ተፈጻሚ እንዲሆን እና ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግበትም አሳስቧል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


