የከዋክብት ንግሥት

0
149

ከብዙ ዓመታት በፊት፣ ካትሪን የምትባል አንዲት ትንሽ ልጅ ነበረች። ካትሪን ቁጥሮችን በጣም ትወድ ነበር። ደረጃ ስትወጣ ደረጃዎቹን ትቆጥራለች፣ ወደ ገበያ ስትሄድ መንገዱን ትቆጥራለች፣ ማታ ደግሞ ሰማይ ላይ ያሉትን ከዋክብት ትቆጥራለች።

ካትሪን በምትኖርበት አካባቢ ለጥቁር ልጆች የሚሆን ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ ነበር። ነገር ግን አባቷ “ልጄ በጣም ብልህ ናት፣ መማር አለባት!” ብለው ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ሌላ ከተማ ሄዱ። ካትሪንም በትምህርቷ ጎበዝ በመሆኗ ገና በ18 ዓመቷ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ጨረሰች።

በኋላ ላይ ካትሪን “ናሳ” በሚባለው ትልቅ የጠፈር ምርምር ማዕከል ውስጥ መሥራት ጀመረች። በዚያን ጊዜ ኮምፒውተሮች እንደ ዛሬው አልነበሩም። ስለዚህ የጠፈር መንኮራኩሮች ወደ ጨረቃ ሄደው በሰላም እንዲመለሱ መንገዱን በወረቀትና በእርሳስ የምታሰላው ካትሪን ነበረች።

አንድ ቀን አንድ ጠፈርተኛ ወደ ጠፈር ሊሄድ ሲል “ያቺ ብልህ ሴት (ካትሪን) ካላሰላችው እኔ በዚህ መንኮራኩር አልሄድም!” አለ። ካትሪንም ቁጥሮቹን በትክክል አሰላች፣ መንኮራኩሯም በሰላም ሄዳ ተመለሰች።

ካትሪን ቁጥሮችን በመውደዷ እና ጠንክራ በመማሯ፣ ሰዎች ጨረቃ ላይ እንዲረግጡ ረድታለች። “ሁልጊዜ ጥያቄ ጠይቁ፣ መማራችሁንም አታቁሙ” ትላለች ካትሪን።

ምንጭ፡- ሂድን ፊገርስ።

ተረት

ቀበሮ እና ቆቅ

ከዕለታት አንድ ቀን  አንዲት ቀበሮ እና አንዲት ቆቅ ጓደኛሞች ነበሩ። አንድ ቀን ተመካከሩና “አብረን ማሽላ እንዝራ” ተባባሉ።

ማሽላው ደርሶ የሚታጨድበት ጊዜ ደረሰ። ቀበሮዋ ግን ሥራ ስለማትወድና ተንኮለኛ ስለሆነች ቆቅን እንዲህ አለቻት፦ “እኔ ማሽላውን አጭዳለሁ፤ አንቺ ደግሞ በላይ በላዩ እየበረርሽ ‘ጭድ… ጭድ…’ እያልሽ ዝፈኚ” አለቻት። ቆቅም የዋህ ስለነበረች እሺ ብላ መዝፈን ጀመረች።

ቀበሮዋ ግን ማሽላውን አጭዳ ለብቻዋ ለመብላት አሰበች። ማሽላውን ከከመረች በኋላ ለቆቅ እንዲህ አለቻት፦ “እስቲ ተቀመጪ እና ይሄን ክምር ግፊው፤ ከወደቀ ያንቺ ነው፣ ካልወደቀ ግን የኔ ነው” አለቻት። ክምሩ በጣም ትልቅ ስለነበር ቆቅ ብትገፋውም ሊወድቅ አልቻለም።

ቆቅ የቀበሮዋን ተንኮል ተረዳች። ዝም ብላ ቆየችና ቀበሮዋ ወደ ውኃ ስትሄድ፣ ቆቅ ማሽላውን ሁሉ በብልሃት ወደ ሌላ ቦታ አጓጓዘችው። ቀበሮዋ ተመልሳ ስትመጣ ክምሩ ባዶ ሆኖ አገኘችው፡፡

ይህ ተረት የሚያስተምረን ተንኮለኛ መሆን መጨረሻው ኪሳራ መሆኑንና ሰነፍ መሆን ደግሞ መጥፎ እንደሆነ ነው። ሁልጊዜም ለሰዎች ቅን መሆንና ጠንክሮ መሥራት ይሻላል።

ምንጭ፡- የሕዝብ ተረት።

ይሞክሩ

  1. ሳያርስ ይዘራል ሳለቅም ይበላል፡፡
  2. ሁልጊዜ ወደ ፊት ይሄዳል እንጂ ወደ ኋላ አይመለስም፤ ድምፅ የለውም ግን “ቲክ ቲክ” ይላል።
  3. ውኃ ውስጥ ይኖራል ግን ዓሣ አይደለም፤ የሚሄደው በደረቱ ነው ግን እባብ አይደለም። በጀርባው ላይ በጣም ጠንካራ ቤት አለው።

መልስ

  1. ወፍ
  2. ሰዓት
  3. ኤሊ

ነገር በምሳሌ

  • “ካልተማሩ አይመረምሩ፣ ካልዘሩ አያጭዱ”

አንድ ነገር ለማግኘት መጀመሪያ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡

 

  • “ከአጓጉል ሳቅ የለቅሶ ድርቅ”

ለነገሮች ትክክለኛ ቦታና ትርጉም መስጠት ያስፈልጋል።

  • “ሰው በሰው ይለካል፤ ዕንጨት በዕንጨት ይቃኛል።”

ትክክለኛውን ማንነታችንን የምናውቀውና የምንታረመው ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ነው።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመጋቢት 7  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here