ወጣቶች እና ሰላም

0
114

ዛሬ በዓለማችን ላይ ካለው የሰው ኃይል ውስጥ አብዛኛው ቁጥር በወጣቶች የተያዘ ነው:: ወጣቶች የነገ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የዛሬ የሰላም ግንባታ ሞተሮችም ናቸው:: “ሰላም እና ወጣቶች” የማይነጣጠሉ ሁለት የሳንቲም ገጽታዎች ናቸው፤ ምክንያቱም ሰላም ለወጣቶች ዕድገት የሚያስፈልግ ሲሆን ወጣቶች ደግሞ ያንን ሰላም ጠብቀው የሚያቆዩ ብርቱ ኃይሎች ናቸው::

ሰላም ለማንኛውም ሀገር ዕድገትና ብልጽግና ዋነኛው ምሰሶ ነው:: በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላለች ወጣት የበዛባት ሀገር፣ የሰላም መኖር የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ ለመገንባት ወሳኝ ነው:: ወጣቶች የሀገር ዋነኛ የሰው ኃይል ከመሆናቸውም በላይ ለሰላም ግንባታ እና ለአብሮነት ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ::

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተደደር ጋር በመተባበር “የወጣቶች መሪነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት ከሰሞኑ አካሂዷል:: ውይይቱ ወጣቶች ስለ ሰላም መምጣት እና መፅናት ግንባር ቀደሞ የመሪነት ሚናን እንዲጫወቱ እና ዘብ እንደቆሙ ለማስቻል ያለመ ነው::

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዘላለም አረጋ ወጣቶች ነገሮችን በጥበብ እና በብስለት መመልከት እንዳለባቸው ተናግረዋል:: የውይይቱ ዓላማ ወጣቶች የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑንም አንስተዋል::

ምክትል ኃላፊው እንዳሉት አንድ በመሆን የጠላቶችን ሴራ በማፍረስ ለሀገር ግንባታ ታላቅ መሠረትን መጣል ያስፈልጋል:: ወጣቶች የሰላም እና የልማት አምባሳደር መሆንም ይባዋቸዋል፤ በመሆኑም ሰላምን ለማጽናት መትጋት ይገባል:: ወጣቶች ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተው የተማረ ብቻ ሳይሆን የሠለጠነ መሆን ያስፈልጋል ነው ያሉት:: ሥልጣኔ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሆነም ተናግረዋል::

እንደ አቶ ዘላለም ማብራሪያ መንግሥት ለወጣቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፤ ወጣቶች ሰላምን በማጽናት እንዲሁም ልማትን በማልማት ተሳትፎ እና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው:: ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ደግሞ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል:: በምርጫ የሚገኝ ውጤት ተጠያቂነት ያለው ሥርዓትን ስለሚገነባ ወጣቶች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል::

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር የሻምበል አጉማስ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ወጣቶች ለሰላም ያላቸውን ፋይዳ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡ ወጣቶች አዲስ አስተሳሰብን እና ጉልበትን ይዘው የሚመጡ የሕብረተሰብ ክፍል ናቸው::

ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ ልዩነቶችን ማቻቻል እና አዳዲስ የመግባቢያ መንገዶችን መፍጠር ያስፈልጋል:: በተለያዩ ባሕሎች፣ ሃይማኖቶች እና ብሔሮች መካከል ወጣቶች ወዳጅነት በመመሥረትና በመነጋገር የአብሮነት ድልድይ መፍጠር ይችላሉ:: የጋራ መድረኮችን በመፍጠርና በጋራ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ ልዩነቶችን ወደ ጥንካሬ የመቀየር አቅምም አላቸው::

ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢው እንዳመላከቱት በአሁኑ ወቅት ወጣቶች የማኅበራዊ ሚዲያና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ናቸው:: ይህንን በመጠቀም የሰላም መልዕክቶችን ማሰራጨት፣ መልካም ምሳሌዎችን ማስተዋወቅ እና ሕብረተሰቡን ለሰላም ማነሳሳት ይችላሉ:: ሆኖም ቴክኖሎጂን ለጥፋት የሚያውሉ አካላትም ስላሉ ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ነው::

ሰላምን ለማስፈን ለወጣች የሚከተሉት መሠረታዊ ነገሮች ሊሟሉላቸው ይገባልም ብለዋል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት፣ ይህም አድማሳቸውን ያሰፋል፤ የሥራ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፤ ለሰላም ዕሴቶችም ያላቸውን ግንዛቤ ያሳድጋል::

ትምህርት ከጥላቻ አስተሳሰብ ያርቃል፤ ለሰላም ግንባታም ያዘጋጃቸዋል:: የሥራ ዕድል ፈጠራ ደግሞ ሌላኛው ነው፤ ሥራ አጥነት ለወጣቶች ተስፋ መቁረጥ እና ወደ ግጭት የመሳብ ዕድልን ይጨምራል:: መንግሥታት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሥራ ዕድል በመፍጠር ወጣቶች በሀገር ግንባታ ላይ አተኩረው የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ሕይወት እንዲያሻሽሉ ማበረታታት አለባቸው::

የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ ሌላኛው ሊሟላ የሚገባው ጉዳይ ነው፤ ወጣቶች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ውሳኔዎች ላይ እንዲሳተፉ ዕድል መስጠት የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል:: ድምፃቸው እንዲሰማ እና በሀገራቸው ጉዳይ ላይ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ መፍቀድም ወሳኝ ነው::

በመጨረሻም የሰላም ትምህርት እና የአቻ መካሪነት ነው የተጠቀሰው፤ ወጣቶች ስለ ሰላም ባሕል፣ ስለ ግጭት አፈታት እና ስለ ልዩነት አክብሮት በቂ ትምህርት ሊያገኙ ይገባል:: የአቻ መካሪነት ፕሮግራሞች (peer mentorship) ወጣቶች እርስ በርስ በመደጋገፍ የሰላም አምባሳደሮች እንዲሆኑ ይረዳል::

ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የወጣቶችን አቅም በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው:: ለወጣቶች የሰላም ዕድል በመስጠት፣ የሰላም ግንባታው አካል እንዲሆኑ በማድረግ እና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ያላቸውን ብሩህ ተስፋ በማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላምን መገንባት ይቻላል:: ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወጣቶችን በማብቃት ለሰላም ግንባታው የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ ዶ/ር የሻምበል አስረድተዋል::

የውይይቱ ተሳታፊዎች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የበኩላቸውን እንደሚወጡም አንስተዋል:: ወጣት የዓለም ወርቅ ደበላ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም እና ራስን ከጥፋት በመጠበቅ ሰላምን ለማጽናት እተጋለሁ ብላለች:: ወጣቶች እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውን በጥንቃቄ እና በአስተውሎት ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግራለች፡፡ እንደ ወጣትነቷ እና በሴትነቷ ሰላምን  ለማስፈን እና ሀገርን ለመለወጥ በሚደረገው ርብርብ ንቁ ተሳታፊ መሆኗን ገልጻለች፡፡ በቀጣዩ ምርጫም ንቁ ተሳታፊ እንደምትሆን ተናግራ ሰላምን ማስፈን የፓርቲ ሥራ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም መትጋት ይገባዋል ብላለች::

ወጣት ጌታሰው መለሰ በበኩሉ የሰላም ጉዳይ የሚመለከተው አንድ ወገንን ብቻ አለመሆኑን ጠቅሶ ነገር ግን ወጣቶች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ ብሏል፡፡ ለሰላም መስፈን ደግሞ ወጣቱ የውይይትና የመቻቻል ባሕልን ማሳደግ፣ መረጃን በንቃት መመርመር እና የሕግ የበላይነትን ማክበር ይጠበቅበታል ነው ያለው፡፡ ወጣት  የሰላም  ዘብ  ከመሆን  ባሻገር  በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ መሆን እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ በምርጫ ተሳታፊ መሆን አንዱ መሆኑን ጠቅሶ ምርጫ ዜጎች ሰላም እና ደኅንነትን ያስጠብቅልኛል፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያሰፍንልኛል፤ የኢኮኖሚ እና የልማት ተጠቃሚ ያደርገኛል፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ያስከብርልኛል ያሉትን መሪ መምረጥ ጠቀሜታው ለራሳቸው መሆኑን አንስቷል::

 

ማን ናት

የታላላቅ ሰዎች አባባል

– ‘‘ስኬታማ ሰው ለመሆን ሳይሆን ጠቃሚ ሰው ለመሆን ጣር”- አልበርት አንስታይን፦

– ‘‘በአለም ላይ እንዲመጣ የምትፈልገውን ለውጥ ራስህ ሁን”- ማህተመ ጋንዲ፦

– ‘‘ማንኛውም ነገር እስኪሳካ ድረስ የማይቻል ይመስላል”- ኔልሰን ማንዴላ፦

– ‘‘ስኬት መጨረሻ አይደለም፤ ውድቀትም ሞት አይደለም፤ ዋናው ነገር ጉዞውን የመቀጠል ድፍረት ነው”- ዊንስተን ቸርችል፦

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here