በኦማን በተካሄደ ባህላዊ የግመል የውበት ውድድር ላይ ለመካፈል ከተሰባሰቡት መካከል 20 ተሳታፊዎች ሰው ሰራሽ ማጋጌጫ ወይም ማሻሻያ መጠቀማቸው በመረጋገጡ ከተወዳዳሪነት መታገዳቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በያዝነው 2026 እ.አ.አ የካቲት ወር መጨረሻ በኦማን አልሙሳና ከተማ በተካሄደ የግመል የውበት ውድድር ሰው ሰራሽ የከንፈር መሙያ፣ የቅርፅ ማስተካከያ፣ አካል መወጠሪያ… መዋቢያዎች ግመሎች ላይ መከወናቸው ተረጋግጧል፤ በእነስሳት ሀኪሞች፡፡
ከየማእዘናቱ የመጡት አርቢዎች “የምድር እጅግ ውብ ግመል” ማእረግን ለማግኘት ሰው ሰራሽ ማስተካከያዎችን በመገልገላቸው ከተወዳዳሪነት መሰረዛቸው ተጠቁሟል፡፡
ድረ ገጹ እንዳስነበበው የግመል የውበት ውድድር የአረብ ሀገራት ባህል አንዱ አካል ነው፡፡ ባለፉት ውድድሮችም የግመል ባለቤቶች አንፀባራቂ ቆዳ፣ ረዥም ቀጥ ያለ አንገት፣ ግጥም ያለ ከንፈር እና ረዣዥም የዓይን ሽፋሽፍት እንዲኖራቸው ጥረት ማድረጋቸውን ውድድር የተደረገባቸውን ዓመታት ጠቅሶ አስፍሯል፤ ድረ ገጹ፡፡
በዘንደሮው ዓመት በኦማን በተካሄደው ውድድርም ተመሳሳይ ሁነት መከሰቱን የእንስሳት ሀኪሞች በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያና ማስረጃ መረጋገጥ መቻሉ ለንባብ በቅቷል፡፡
ተወዳዳሪዎች በመርፌ በሚሰጥ እድገ ንጥር ወይም “ሆርሞን”፣ የጡንቻ መወጠሪያ አና የመሳሰሉ ነገሮችን አሸናፊ ለመሆን መጠቀማቸው በጤናቸው ላይም አደጋ የሚያደርስ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


