በአሜሪካ ኦሀዮ ግዛት በበርካታ የመንግሥት ቢሮዎች የስልክ እና የበየነ መረብ አገልግሎት መቋረጡን ዩፒአይ ድረ ገጽ አስታውቋል፡፡ ላገልግሎቱ መቋረጥ ምክንያቱም መሬት ውስጥ ጐጆውን የቀለሰ ሽኮኮ መሆኑን ዩፑአይ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
በየካቲት ወር አጋማሽ 2026 እ.አ.አ ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በኦሃዮ ግዛት በበርካታ ቢሮዎች የስልክ እና የበየነ መረብ ግንኙነት ተቋርጦባቸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች የግንባታ ሰራተኞች ፋይበሩን ቆርጠውት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አድሮባቸው ነበር፡፡ በፍተሻው ግን ግምታቸው እውነት ሊሆን አልቻለም፡፡
አስተዳደሩ የችግሩን መንስኤ ለማወቅ የተቋረጠበትን ቦታ ለይቶ ለማስተካከል ያሰማራቸው ባለሙያዎች የዝርጋታ መስመሩን ተከትለው ቦታውን ያገኙታል፡፡ በመሬት ውስጥ ለፋይበር ገመዶች መዘርጊያ በተቆፈረ ቦይ ውስጥ ክፍተት አግኘቶ የገባ “ስኩሪል” አደሴቁኒ ወይም ጅራታም ሽኮከ ለችግሩ መንስኤ ሳይሆን እንደማይቀርም ይገምታሉ፡፡
ባለሙያዎቹ በተከታታይ ባደረጉት ክትትልም ጅራታሙ ሽኮኮ መሳይ “ስኩሪል” የግንኙነት መስመሩን መበጣጠሱን ይደርሱበታል፡፡ ይህንኑም ለበላይ ሀላፊው ያስታውቃሉ፡፡
የግዛቱ የበላይ ኃላፊ ማት ስፕሪንገርም የግንኙነት መሰረተ ልማቱ በተዘረጋበት ቦይ ውስጥ ጐጆ የቀለሰው ጀራታም ሽኮኮ ገመዶችን በመበጣጠስ ግንኙቱን ማቋረጡን አምነው ወደቦዩ የሚያስገቡ ክፍተቶች ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ ማዘዛቸው ታውቋል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


