በኢትዮጵያ በመጭው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል:: የመራጮች ምዝገባ ከበፊቱ የምዝገባም ሂደት በተጨማሪ በዲጂታል መመዝገብ እንደሚቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል:: መራጮችም ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ‘’ምርጫዬ’’ የሚል ስያሜ የተሰጠውን መተግበሪያ ከፕሌይ እና አፕ ስቶር በማውረድ እራሳቸውንና ለመምረጥ ብቁ የሆኑ ቤተሰቦቻቸውን ማስመዝገብ ይችላሉ:: ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም የማይፈልጉ ዜጎችም የመራጭነት ምዝገባቸውን በአካል በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ማከናወን ይችላሉ::
በዲጂታል አሠራር የመራጮች ምዝገባ መካሄዱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ መራጭ አንድ መታወቂያ እንዲኖረው ያደርጋል፤ ይህም በቀጣይ ለሚኖሩ ምርጫዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል::
የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ወደ ተግባር የሚቀየረው በመራጮች ምዝገባ ሂደት ነው። የመራጮች ምዝገባ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል እንዲጎለብት ያደርጋል። የመራጮች ምዝገባ ደግሞ ለሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ መነሻ ተግባራዊ ልምምድ የሚወሰድ ነው።
ዕድሜው 18 እና ከዚያ በላይ ከሆነ፣ በተቀመጡት የመራጭነት ምዝገባ አማራጮች (በምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት፤ “ምርጫዬ” የሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም) እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ድረ-ገጽ (Online) አማካኝነት ምዝገባውን ማከናወን እንደሚቻል የምርጫ ቦርድ መረጃ ያመላክታል::
ለመሆኑ በ“ምርጫዬ” የሞባይል መተግበሪያ እንዴት መመዝገብ ይቻላል? የሚከተሉትን ቅደም ተከተሎች በመከተል ካላቸው መመዝገብ ይቻላል፡-
“ምርጫዬ” የተሰኘውን የመራጮች መመዝገቢያ መተግበሪያ ከ“Play Store ወይም APP Store” በማውረድ በስልክዎ ላይ ይጫኑ፣
በስልክዎ ላይ ከተጫኑት ዝርዝር መተግበሪያዎች ውስጥ “ምርጫዬ” የሚለውን መተግበሪያ ይክፈቱ፣
በመቀጠልም ከተከፈተው የ“ምርጫዬ” መተግበሪያ ላይ የሚጠቀሙበትን ቋንቋ ይምረጡ፣ ቋንቋ መርጠው ከገቡ በኋላ ከሚያገኟቸው ዝርዝሮች ውስጥ “የእርስዎን መገለጫ ይፍጠሩ” የሚለውን ይጫኑ፣
በመቀጠል “በፋይዳ አማካኝነት ወደ መለያ” የሚለውን አማራጭ ይጫኑ፣
የፋይዳ ገጹ ሲመጣልዎ ከፋይዳ መታወቂያዎት ላይ 16 አሃዝ ያለውን ቁጥር (FAN) ካስገቡ በኋላ በስልክዎ የሚላክልዎን ባለስድስት አሃዝ የአንድ ጊዜ ማረጋገጫ ቁጥር (OTP) ያስገቡ፣
መረጃዎን ከፋይዳ ሲያገኙ “ይቀጥሉ” የሚለውን በመጫን መተግበሪያው የሚጠይቅዎትን ቀሪ መረጃ በማስገባት መስማማትዎን በሳጥኑ ውስጥ ምልክት ያድርጉ፣
በመቀጠል ያስገቡትን መረጃ ወደ መተግበሪያው ለመላክ “አስገባ” የሚለውን በመጫን ከመተግበሪያው ቋሚ የመራጭነት መለያ ቁጥር ያገኛሉ፤ ይህ ሊይዙት የሚገባ ቋሚ የመራጭነት መለያ ቁጥርዎም ነው፣
ያስታውሱ! ቋሚ የመራጭነት መለያ ቁጥር አገኙ ማለት ምዝገባዎ ተጠናቋል ማለት አይደለም፤ “ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይመዝገቡ” የሚለውን መጫን ይኖርብዎታል፣
በመቀጠልም በአድራሻዎ መሠረት ቅርብ በሆነ የምርጫ ጣቢያ ለመምረጥ ምርጫ ጣቢያ ዝርዝር ያገኛሉ፣
ከሚያገኙት የምርጫ ጣቢያ ዝርዝሮች ውስጥ የሚቀርብዎን የምርጫ ጣቢያ በመምረጥ “ይመዝገቡ” የሚለውን ይጫናሉ፣
በመረጡት ምርጫ ክልል በኗሪነት ያልዎትን ቆይታ በዓመት እና በወር ያስገባሉ። ያስገቡትን መረጃ ትክክለኛነት በማረጋገጥ በሳጥኑ ላይ ምልክት በማድረግ ያረጋግጡ የሚለውን በመጫን ለምርጫው እራስዎን ይመዘግባሉ፣
በመቀጠል የመታወቂያዎን ዓይነት በመምረጥ የመረጡትን መታወቂያ ፊት እና ጀርባ ፎቶ ማንሣት እና ማያያዝ፣
ከዚያም ለምርጫ ቀን ይዘው የሚመጡት ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል የምርጫ ካርድ ከ48 ሰዓት በኋላ ከመተግበሪያው ያገኛሉ፣
ምርጫ ካርድዎን አትመው ለመያዝ ደግሞ “ወደ ዋና ገጽ ይመለሱ” የሚለውን አማራጭ በመጫን ዋናው ገጽ ላይ የሚገኘውን “ያትሙ” የሚለውን አማራጭ መጫን ይኖርብዎታል።
ዜጎች እነዚህን ሂደቶች ተከትለው በቀላሉ እና በእጅ ስልካቸው በመጠቀም የምዝገባ ሒደቱን የሚያከናውኑበት ምርጫዬ የተሰኘው አማራጭ መቅረቡ ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ ሁሉ ምዝገባቸውን በቀላሉ ለማከናወን ዕድል ይፈጥራል:: ይሁን እንጂ የዲጂታል መራጮች ምዝገባ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ሳይሆን በተመረጡ ጣቢያዎች ላይ ብቻ የሚከናወን መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።
በመሆኑም መራጮች የዲጂታል ምዝገባው የሚካሄደው አስቀድመው ለዚህ ተግባር በተለዩ ውስን ጣቢያዎች ብቻ መሆኑንና በዲጂታል ምዝገባ በማይካሄድባቸው ሌሎች ጣቢያዎች ሁሉ የመራጮች ምዝገባ እንደተለመደው በመዝገብ (በማኑዋል) የሚቀጥል መሆኑን ቦርዱ አስገንዝቧል::
መረጃ
በመራጭነት ለመመዝገብ ፦
ተመዝጋቢው በሚኖርበት የምርጫ ጣቢያ ማንነቱን የሚገልፅ የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት (ያልታደሰም ቢሆን)፣
የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ማቅረብ ካልተቻለ በቅርቡ ፎቶግራፍ ተደርጎበት የተሰጠ እንደ የመንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለለበት ሰነድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያ የመሳሰሉ የመለያ ማስረጃዎች፣
ከላይ የተዘረዘሩት ማስረጃዎች በማይኖሩበት ወቅት መዝጋቢዎች መራጩን ለይተው የሚያውቁት ከሆነ ወይም በገጠር አካባቢ ሲሆን በባህላዊና ልማዳዊ ዘዴ ተመዝጋቢውን ለመለየት የሚቻልበት ሁኔታ ካለ እንዲሁም የምርጫ ጣቢያው በተቋቋመበት ቀበሌ ኗሪ የሆኑ ለረዥም ጊዜ መኖራቸው የተረጋገጠ ሦስት ነዋሪዎች በሚሰጡት ምስክርነት ማስረጃ አልባውን ተመዝጋቢ ለመለየት ከተቻለ ቃለ ጉባኤ ተይዞ ምዝገባው ይከናወናል፡፡
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


