የማይበገረው የሰው ልጅ መንፈስ

0
77

የፓራሊምፒክ መድረክ የሰው ልጅ ጽናት፣ የማይበገር መንፈስ እና ቁርጠኝነት በጉልህ የሚታይበት አካላዊ ጉዳት የህልም እንቅፋት መሆን እንደማይችል በተግባር የሚረጋገጥበት ታላቅ ግዙፍ ስፖርታዊ መድረክ ስለመሆኑ ዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ ድረ ገጽ ያስነብባል፡፡ በዚህ ትልቅ የውድድር መድረክ አካላዊ ጉዳትን አሸንፈው የዓለምን ስፖርት ታሪክ የቀየሩ በርካታ ጀግኖች ተፈጥረው አልፈዋል፤ አሁንም እየተፈጠሩ ነው፡፡

በዓለም የፓራሊምፒክ ታሪክ በማንም ያልተሰበረ እና ወደፊትም ለመስበር እጅግ አዳጋች የሆነ ክብረ ወሰን የጨበጠችው አሜሪካዊቷ ዋናተኛ ትሪሻ ዞር ቀዳሚ የፓራሊምፒክ ስፖርተኛ ናት፡፡ እ.አ.አ በ1964  በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የተወለደችው ትሪሻ  ወደዚህ ዓለም ስትመጣ  አኒሪዲያ በተባለ የዓይን ብሌን ክፍተት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ዐይነ ስውር ሆና ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦቿ ይህንን ተፈጥሯዊ ችግር እንደ ጉድለት እንዲሰማት አላደረጉም፤ በማበረታታት ከጎኗ ቆሙ እንጂ፡፡ ገና በዐስር ዓመቷ በዋና ስፖርት ልምምድ የጀመረችው ትሪሻ የጨለማውን ዓለም ውሃ ውስጥ ያገኘቸውን ነፃነት እና ፍጥነት ወደ ብርሃን መቀየር ችላለች፡፡ ትሪሻ በፓራሊምፒክ መድረክ ላይ መሳተፍ ከመጀመሯ በፊት ትወዳደር የነበረው ሙሉ አካላዊ ጤንነት ካላቸው ዋናተኞች ጋር እንደነበር የሎሪየስ ዶት ኮም መረጃ ያስነብበናል፡፡  እ.አ.አ  በ1980  በሞስኮ ኦሊምፒክ አሜሪካን ወክላ ለመሳተፍ ባደረገችው ማጣሪያ ላይ ያጣችው እጅግ ጠባብ በሆነ ሽርፍራፊ ሴኮንድ ልዩነት እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የትሪሻ የፓራሊምፒክ ጉዞ የጀመረው በ1980 እ.አ.አ ነው፡፡ በኔዘርላንድስ አርነም በተካሄደው ውድድር ገና በ16 ዓመቷ ሰባት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ዓለምን ጉድ አሰኝታለች፡፡ እስከ 2004 እ.አ.አ አቴንስ ፓራሊምፒክ ድረስ 41 የወርቅ፣ ዘጠኝ የብር እና አምስት የነሐስ በድምሩ 55 ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ በታሪክ እጅግ ስኬታማዋ ስፖርተኛ ሆና ስሟ በክብር መዝገብ ሰፍሯል፡፡ የ41 ዓመቷ የቀድሞ ዋናተኛ በሕግ ትምህርት በከፍተኛ ማዕረግ ምሩቅ በመሆን በአሜሪካ የቀድሞ ወታደሮች ጉዳይ መምሪያ ውስጥ በጠበቃነት እያገለገለች እንደምትገኝ የፓራሊምፒክ ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል፡፡

በሁለት የተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ዓለምን ጉድ ያሰኘችው እንግሊዛዊቷ ሳራ ስቶሪን ሌላኛዋ አስደናቂ የፓራሊምፒክ ስፖርተኛ መሆኗን የዓለም አቀፉ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል፡፡ የ39 ዓመቷ የብስክሌት ስፖርተኛ የግራ እጇ በሚገባ ሳያድግ መወለዷን የግል የታሪክ ማህደሯ ያስነብባል፡፡ በ14 ዓመቷ (በ1992ቱ የባርሴሎና ፓራሊምፒክ) ላይ በዋና ስፖርት በመሳተፍ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ የስፖርት ጉዞዋን ጀምራለች፡፡ እስከ 2004 እ.አ.አ አቴንስ ፓራሊምፒክ ድረስ ተወዳድራ 16 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች፡፡  ይሁን እንጂ በ2005 እ.አ.አ በገጠማት እጅግ ከባድ የጆሮ ኢንፌክሽን ምክንያት ወደ ውሃ ውስጥ መግባት እንደማትችል በዶክተሮች ተነገራት፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ተስፋ ሳትቆርጥ የውሃ ዋና ስፖርት በር ሲዘጋባት በባለቤቷ አበረታችነት ፊቷን ወደ  ብስክሌት ስፖርት በማዞር አዲስ ታሪክ መጻፍ ጀመረች:: ሳራ በቅርቡ በተካሄደው የ2024 የፓሪስ ፓራሊምፒክ ላይ በ47 ዓመቷ ተሳትፋ ድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ አይዘነጋም፡፡ በ32ዓመታት የስፖርት ህይወቷ 30 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ምርጥ አትሌት መሆኗንም አስመስክራለች፡፡ የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሳራ በማንችስተር ዩኒቨርሲቲ የክብር ፕሮፌሰር ማዕረግ ተሰጥቷታል፤ በተጨማሪም በእንግሊዝ የዴም (Dame) ከፍተኛ ማዕረግ አግኝታለች፡፡

የዘመናችንን ምርጥ የፓራሊምፒክ ዋናተኛ ብራዚላዊው ዳንኤል ዲያስን ወደ ምድር ሲመጣ የሁለቱም እጆቹ እና የአንዱ እግሩ ክፍሎች ያልተሟሉ ሆነው ነበር፡፡ በልጅነቱ በሚደርስበት መገለል ተስፋ ቆርጦ የነበረው ዳንኤል እ.አ.አ በ2004ቱ የአቴንስ ፓራሊምፒክ ላይ የሀገሩ ልጅ ክሎዶአልዶ ሲልቫን በቴሌቪዥን ሲወዳደር የተመለከተበት ቅጽበት ህይወቱ የተቀየረበት አጋጣሚ መሆኑን ያስታውሳል፡፡ ዳንኤል በውሃ ዋና ስፖርት በቤጂንግ፣ ለንደን፣ ሪዮ ዴጄኔሮ እና ቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ 14 የወርቅ ሜዳሊያዎችን  በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ታሪክ ሠርቷል፡፡ ዳንኤል የሎሪየስ (Laureus) የዓመቱ ምርጥ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኛ ሽልማትን ለሶስት ጊዜያት አሸንፏል፡፡ የ37 ዓመቱ የቀድሞ ዋናተኛ በአሁኑ ወቅት በውሃ ሀብት እና አካባቢ ጥበቃ ምህንድስና የዶክትሬት ዲግሪውን (PhD) አግኝቶ በእንግሊዙ ታዋቂ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ውስጥ በተመራማሪነት እያገለገለ እንደሚገኝ የሎሪየስ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሽልማት እና የኢምፔሪያል ኮሌጅ መረጃ አመልክቷል፡፡

በቼርኖቤል የኑክሌር አደጋ ምክንያት አካል ጉዳተኛ ሆና የተወለደችው አሜሪካዊቷ ኦክሳና ማስተርስ በፓራሊምፒክ ስፖርት ሌላኛዋ ስኬታማ አትሌት ናት፡፡ ኦክሳና በውሃ ዋና ስፖርት በክረምትም ሆነ በበጋ ፓራሊምፒክ ተወዳድራ በርካታ ወርቆችን ያሸነፈች ሁለገብ ጀግና ስፖርተኛ ናት፡፡ ኩባዊቷ ኦማራ ዱራንድም ዐይነስውር የአጭር ርቀት ሯጭ ስትሆን  ከዐስር ዓመታት በላይ በአንድም ውድድር ያልተሸነፈች እና የዓለም ፈጣንዋ ፓራሊምፒያን የሚል ስም ያተረፈች ናት፡፡ አሜሪካዊቷ ዋናተኛ ጄሲካ ሎንግም  31 የፓራሊምፒክ ሜዳሊያዎችን ያሸነፈች ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 18ቱ የወርቅ ሜዳሊያ መሆኑን የግል የታሪክ ማህደሯ ያሳያል፡፡በአጠቃላይም 50 ሜዳሊያዎችን  ሰብስባለች፡፡

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ1968ቱ የቴል አቪቭ ፓራሊምፒክ ላይ የተሳተፈች ሲሆን ከዚያ በኋላ ለበርካታ ዓመታት የተቆራረጠ ተሳትፎ ማድረጓን ፓራሊምፒክ ዶት ኦርግ አስነብቧል፡፡ እ.አ.አ በ2012ቱ የለንደን ፓራለምፒክ ውድድር አትሌት ወንድዬ ፍቅሬ በአንድ ሺህ 500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማምጣቱ አይዘነጋም፡፡ በ2016ቱ የሪዮ ዴጄኔሮ ፓራለምፒክ ውድድርም አትሌት ታምሩ ደምሴ በአንድ ሺህ 500 ሜትር በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያ አሸንፏል፡፡ በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ታሪክ ትልቁ የድል በር የተከፈተው ግን በ2020ው የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው እና በ2024 የፓሪስ ውድድርም ያሸነፈችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ናት፡፡ በ2024ቱ የፓሪስ ፓራሊምፒክ የዓለምን ትኩረት የሳበችው ያየሽ ጌጤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አስደናቂ ብቃት እያሳየች መሆኗን በርካታ የዓለም መገናኛ አውታሮች እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here