ንጽሕና፡- የጤና ዋስትና

0
75

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመላክተው ከ99 በመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን አማኞች ናቸው። የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ አማኞችን ከአምላካቸው ጋር በግብር እንዲገናኙ ማድረግ፣ ማገልገል እና ጤናማ ሆነው በሐሴት እንዲኖሩ ማስቻል ዋና ዓላማቸው ነው ።

ተቋማቱ መሠረታቸው አማኞቻቸው በመሆናቸው  በተለይ የዕምነቱ መገለጫ በዓላት እና መሰል ወቅቶች መሰባሰብ የተለመደ ነው። ከዚህ ባለፈም ፈውስ ለማግኘት በየተቋማቱ ይሰባሰባሉ፣ ለፈውስ መሠረት የሆኑ ሃይማኖታዊ ተግባራትንም ያከናውናሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለቅዱስ ተግባር መሰባሰቡ እንዳለ ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች ወረርሽኞች ሲከሰቱ አደጋው ብዙኃኑን ያካልላል፣ ከባድ ዋጋም ያስከፍላል። የኮሌራ ወረርሽኝ ደግሞ አንዱ ማሳያ ነው።

በአማራ ክልል ወረርሽኙ በተለያዩ ጊዜያት መከሰቱ ይታወቃል፤ በተደረገው ርብርብ በከፍተኛ መጠን መቀነስ ተችሎ ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ከወረርሽኙ ስጋት ነጻ መሆን አልተቻለም።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ ምክክር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በምክክሩም የተለያዩ የዕምነቶች አባቶች እና የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሐሳባቸውን ያካፈሉን የሃይማኖት አባቶች “ወደ ቅዱስ ቦታዎች ለፈውስ የሄደ ሰው እንዴት በንጽሕና ጉድለት በሚመጣ የኮሌራ ወረርሽኝ ይጠቃል? ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት ወረርሽኙን ማጥፋት አለብን” ነው ያሉት።

በተለይ የቤተ ዕምነት መሪዎች የሕዝብ አባቶች እና  መካሪዎች በመሆናቸው ወረርሽኙን ለመግታት የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ነው የገለጹት። “በጋራ በመሥራታችን ውጤት ተገኝቷል፤ ፈውስ ፈልጎ የሄደ ለተጓዳኝ በሽታ እንዳይጋለጥ ማድረግ አለብን” ብለዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ አቶ ፋሲል ታዬ የኮሌራ ወረርሽኝ አማኙን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃ መሆኑን በማንሳት “ወረርሽኙን መከላከል የሃይማኖት ተቋማት ዋና ትኩረት እና ድርሻ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

ዋና ጸሐፊው እንደተናገሩት የፈውስ ቦታዎች የሕመም ማደሪያ መሆን አይገባቸውም። ቦታዎቹን ንጹህ በማድረግ ወረርሽኙን መከላከል ይገባል። የሃይማኖት ተቋማትም ለዚህ አርዓያ መሆን አለባቸው። ግንዛቤ ፈጠራ ላይ በተከናወነው ሥራ ውጤት መገኘቱንም አክለዋል።

ዋና ጸሐፊው ባስተላለፉት መልዕክትም “ታላቅ ታሪክ ያላት፣ የኩራት ምንጭ ሀገር አለችን፤ ታዲያ እንዴት በንጽሕና ጉድለት የሚከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ  ስጋት ሆነብን! ከታሪካችን አኳያ የማይመጥነን በመሆኑ ሁላችንም በቁርጠኝነት ማጥፋት አለብን። ውጤቱ የሚገኘው ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ሲወጣ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

እንደ ዋና ጸሐፊው ገለጻ ኮሌራ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት አጣዳፊ እና ገዳይ በሽታ ነው። ነገር ግን በቀላሉ መከላከል ይቻላል። የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ ደግሞ ዋናው የመከላከያ ዘዴ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ቀላል መንገድ መከላከል እየተቻለ ከተዘናጋን ከባድ ዋጋ ያስከፍላል።

ከሰሞኑ የተካሄደው ምክክር “የኮሌራ ወረርሽኝ ሁኔታ እና ምላሽ አሰጣጥ” በሚል መሪ ሐሳብ ነው። ኮሌራን ከፈውስ ቦታዎች አለፍ ሲልም ከሀገራችን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ደግሞ የምክክሩ ዋና ዓላማ ነው። ዓላማውን ለማሳካትም የመከላከያ ተግባራትን በቁርጠኝነት ማከናወን ይገባል።

በምክክሩ የመወያያ ጽሑፍ ቀርቦ ሐሳብ ተሰጥቷል፤ የመወያያ ጽሑፉን ያቀረቡት ደግሞ በአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና ሌሎች የጤና አደጋዎች ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ አቶ ወንደሰን የኋላ ናቸው፡፡

ባለሙያው እንዳሉት ወረርሽኙን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በትኩረት እየተሠራ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው እና ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑ ስድስት ቦታዎች ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ግንዛቤ ፈጠራ እና የንጽሕና መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ወረርሽኙን ለማጥፋት ወሳኝ ናቸው፤ ይህን ታሳቢ በማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው፤ በዚህም በአርዓያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ውጤቶች መገኘታቸውን አቶ ወንደሰን ተናግረዋል፡፡ ለውጤቶቹ መገኘት በተለይ የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነም አክለዋል።

ምላሽ አሰጣጡ የበርካታ ተቋማትን እና የሃይማኖት አባቶችን የነቃ ተሳትፎ በእጅጉ የሚፈልግ ነው ያሉት ባለሙያው ወረርሽኙ በቅዱስ ቦታዎች ለምን ይከፋል? ሲሉም ያነሳሉ፤ የሕዝብ ጥግግት እና በቂ መሠረተ ልማት አለመኖር ደግሞ በምክንያትንት የጠቀሷቸው ናቸው፡፡

በመሆኑም በቅዱስ ቦታዎች በቂ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት፣ በቂ የውኃ አቅርቦት፣ የግል እና የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ እንዲሁም ፍሳሽ እና ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ወረርሽኙን ለመከላከል ዋና ዋና መንገዶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በእነዚህም ላይ ያሉትን መልካም ጅምሮች በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል።

እንደ አቶ ወንደሰን ማብራሪያ ወረርሽኙን ለመከላል ተሞክሮ የሚሆኑ ተግባራት ተከናውነዋል። ለአብነት ሕግ እና ደንቦች ወጥተው በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል። ተሞክሮውንም ማስፋት ይገባል።

ወረርሽኙን ለመከላከል በትኩረት እየሠሩ ከሚገኙት ተቋማት መካከል የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ አንዱ ነው፤ የቢሮው አማካሪ ወልደ ትንሣኤ መኮንን (ዶ/ር) “ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ መከላከል በእጅጉ ያተርፋል” ነው ያሉት፡፡ ለዚህ ደግሞ ግንዘቤ ፈጠራ ላይ መረባረብ ወሳኝ እንደሆነ ነው ያመላከቱት፡፡

“ታሞ ከመማቀቅ፣ አስቀድሞ መጠንቀቅ” ነባር ኢትዮጵያዊ ብሂል ነው፤ ብሂሉ ደግሞ ችግር ተከስቶ ከባድ ዋጋ ከማስከፈሉ በፊት መከላከል እንደሚገባ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ የኮሌራ ወረርሽኝ ደግሞ የግል አና የአካባቢን ንጽሕና በመጠበቅ ከመከሰቱ በፊት በቀላሉ መከላከል ይቻላል፡፡  ዶክተር ወልደ ትንሣኤ በመልዕክታቸው ያጠናከሩትም ይህንኑ ሐሳብ ነው፡፡

 

መረጃ

የኮሌራ በሽታ ምልክቶች

  • ማስታወክ እና ማስመለስ፦

ኮሌራ መጀመሪያ ደረጃ ላይ ለብዙ ሰዓታት ሊቆይ የሚችል ማስታወክ ሊያጋጥመው ይችላል.

  • ተቅማጥ ፦

በኮሌራ ምክንያት የሚከሰት ተቅማጥ በድንገት ይታይና በፍጥነት ፈሳሽ ይጠፋል፡፡ በኮሌራ ላይ የተመሰረተ ተቅማጥን ለመለየት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ብዙውን ጊዜ ሩዝ ከታጠበበት ውኃ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የገረጣ፣የወተት መልክ ያለው መሆኑ ነው።

  • የሰውነት መሟጠጥ፦

የኮሌራ ምልክቶች መበሳጨት፣ ድካም፣ የዐይን፣ አፍ መድረቅ እና  ከፍተኛ የውኃ ጥማት…

ምንጭ፦  ዶክተር አለ

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here