የሀገር ፍቅር

0
95

እንዴት ናችሁ ልጆች? ልጆች ሀገራችሁን ትወዳላችሁ አይደል? ለመሆኑ የሀገር ፍቅር ምን ማለት ነው? የሀገር ፍቅር  ከቃላት በላይ የሆነ ጥልቅ እና ሕያው ስሜት ሲሆን ትርጉሙም ዜጎች ለተወለዱባት ምድር፣ ለታላቅ ታሪኳ፣ ለሚያምረው ተፈጥሮዋ እና ለአብሮ አደግ ወገኖቻቸው የሚሰጡት ልዩ ክብር እና እንክብካቤ ነው።

ልጆች ሀገራቸውን መውደድ የሚጀምሩት ከቤታቸው እና ከሰፈር ጓደኞቻቸው ጋር ካላቸው ግንኙነት በመነሳት ሲሆን ይህም ስሜት እያደገ ሲሄድ ለሀገር ኩራት እና ለወገን መቆርቆር ሆኖ ይገለጻል። አንድ ልጅ በትምህርቱ ጎበዝ ሲሆን፣ አካባቢውን ከቆሻሻ ሲጠብቅ እና ታላላቆቹን ሲያከብር ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በተግባር እያሳየ ነው ማለት ይቻላል።

የሀገር ፍቅር መሠረቱ የጀግኖች አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን ታሪክ አውቆ ማድነቅ ነው። ልጆች እንደ ዓድዋ ያሉ ታላላቅ የነፃነት ድሎችን እና የጥንት ስልጣኔዎችን ሲሰሙ በሀገራቸው የመኩራት መንፈስ ያዳብራሉ። የሀገርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ መያዝ፣ የሀገርን መዝሙር በስሜት መዘመር እና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል፣ ቋንቋ እና እሴት ማክበር የዚሁ ፍቅር ቀጥተኛ መገለጫዎች ናቸው። ሀገር ልክ እንደ ትልቅ የጋራ ቤት ስለሆነች በውስጧ ያሉትን ወንዞች፣ ተራራዎች፣ ደኖች እና የዱር እንስሳትን መጠበቅም የልጆች ዋነኛ ድርሻ እና የፍቅር ማሳያ ነው።

በተጨማሪም እውነተኛ የሀገር ፍቅር የሚለካው በንግግር ብቻ ሳይሆን በጎ ተግባራትን በማከናወን እና ለጋራ ጥቅም በመቆም ነው። ልጆች ነገ ሀገራቸውን የሚረከቡ እና የተሻለች ዓለምን የሚፈጥሩ መሪዎች እንደመሆናቸው መጠን ዛሬ ላይ እርስ በእርሳቸው ተከባብረው፣ ተረዳድተው እና ተደማምጠው ሲያድጉ ለሀገራቸው ጠንካራ መሠረት ይጥላሉ። ለሀገር መቆርቆር ማለት በወገን ስኬት መደሰት እና ለችግሩም መድረስ በመሆኑ ልጆች ይህንን መልካም ስነ ምግባር ይዘው እንዲያድጉ መርዳት የሁሉም ወላጆች እና መምህራን ኃላፊነት ይሆናል።

ይህ የሀገር ፍቅር ስሜት በልጆች ውስጥ ሲሰርጽ ለሥራ ትጋትን፣ ለሕግ መገዛትን እና ለሌሎች ማሰብን ያመጣል። ሀገር ማለት መሬቱ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያለው ሕዝብ ጭምር በመሆኑ ሰዎችን መውደድ እና መርዳት ትልቁ የሀገር ፍቅር መግለጫ ነው። ልጆች ይህንን ስሜት ይዘው ሲያድጉ ለሀገራቸው ሰላም፣ እድገትና አንድነት ዘብ የሚቆሙ ዜጎች ይሆናሉ።

 

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ የዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት መጽሐፍ

ተረት

ኩሩው አንበሳይሞክሩ

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ለምለም ኮረብታ ላይ የሚኖር ጥቁር አንበሳ ነበር። ይህ አንበሳ በጣም ብልህ እና ኩሩ ሲሆን በዙሪያው ያሉትን እንስሳት ሁሉ በፍቅር እና በአንድነት ያስተዳድር ነበር። በዚያው ጫካ ውስጥ የሚኖሩት ትናንሽ ግልገሎች ደግሞ ሁልጊዜ አንበሳው ለምን ያን ያህል  ጠንካራ እንደሆነ እና ለምንስ በኩራት እንደሚራመድ ይገረሙ ነበር።

አንድ ቀን አንዲት ትንሽ ግልገል ወደ አንበሳው ቀርባ “ጌታዬ፣ ሁልጊዜ በኩራት የምትራመደው እና ለዚህ ጫካ የምትጨነቀው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው። አንበሳውም በፈገግታ እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ልጄ ሆይ፣ ይህ ጫካ የሁላችንም የጋራ ቤት ነው። እዚህ ውስጥ ያሉት ወንዞች ጥማችንን ይቆርጣሉ፤ ዛፎቹ ጥላ ይሆኑናል፤ አፈሩ ደግሞ ምግባችንን ይሰጠናል። ይህንን ምድር መውደድ ማለት ራስን መውደድ ማለት ነው። የሀገር ፍቅር ማለት ደግሞ ይህንን የጋራ ቤታችንን መጠበቅና መንከባከብ ነው” አላት።

አንበሳው ንግግሩን ቀጠለና፣ “ይህ ጫካ የቆመው እኔ ጠንካራ ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ተከባብረንና ተረዳድተን ስለምንኖር ነው። ንቦቹ አበባዎችን ባይንከባከቡ ማር አንበላም ነበር፤ ወፎቹ ባይዘምሩ ጫካው ደስታ አይኖረውም ነበር። ስለዚህ ሀገርህን መውደድ ማለት ጎረቤትህን መውደድ፣ ለደካሞች መቆም እና አካባቢህን በንፅህ እና መጠበቅ ነው” ሲል አስተማራት። ግልገሏም ከዚያን ቀን ጀምሮ ሀገር ፍቅር ማለት ሰንደቅ ዓላማ መያዝ ብቻ ሳይሆን ለጋራ ቤት መልካም ነገርን ማድረግ መሆኑን ተረዳች። ይህ ተረት  የአንድነትን እና የመረዳዳትን ጥቅም ያስተምራል።

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ የቃል ታሪኮች

ይሞክሩ

  1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች በቅደም ተከተል ምን ምን ናቸው?
  2. በዓለም ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ ግዙፉ የየብስ (የምድር) እንስሳ ማን ነው?
  3. የቀን ብርሃን የምትሰጠን እና ተክሎች ማግባቸውን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙ በትን ብርሃን የምትለግሰው ታላቅ ኮከብ ማን ትባላለች?

መልስ

  1. አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ
  2. ዝሆን
  3. ፀሐይ

ነገር በምሳሌ

የታመነ ሰው ከወርቅ ይበልጣል፦

 ሰዎች የሚያምኑትና የማይዋሽ ሰው ከማንኛውም ውድ ስጦታ በላይ ዋጋ አለው።

 

እውነት ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም፦ እውነት መናገር መጀመሪያ ላይ ሊያስፈራ ቢችልም መጨረሻ ላይ ግን ሁልጊዜ አሸናፊ ያደርጋል።

 

እጅ በእጅ ቢተጣጠቡ ይነጻሉ፦

ብቻችንን ከምንሠራው ይልቅ ተረዳድተን የምንሠራው ሥራ ውጤቱ የተሻለና ንጹህ ይሆናል።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመጋቢት 14  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here