በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዝማሪዎች አዝናኝ ዘፋኞች ብቻ አይደሉም:: እንደ ማህበራዊ ተንታኝ፣ የታሪክ መዝጋቢ እና ፈላስፋ ሆነው አገልግለዋል:: የታሪክ ድርሳናት ሆነው ታሪክን መዝግበዋል:: አዝማሪዎች በሰምና ወርቅ ስልት ቅኔን በመጠቀም ስለ ኑሮ፣ ስለ ሞት፣ ስለ ሥልጣን፣ ስለ ፍትህ እና ስለ የሰው ልጅ ባህሪ ያላቸውን ጥልቅ ምልከታ ያንፀባርቃሉ::
ጋዜጣ፣ መጻሕፍት፣መጽሔት፣ ሬዲዮ፣ ቴሊቪዥን እና ማህበራዊ ሚዲያ ከመምጣቱ በፊት አዝማሪዎች የህብረተሰቡ ዓይን እና ጆሮ ሆነው እውቀትን እና መረጃን አስተላልፈዋል::
ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒሊክ” በሚለው መጽሐፉ አዝማሪዎች የጠላት ወረራን ለመከላከል ከሠራዊቱ እኩል ተሰልፈው ወኔ እና ድፍረት ይሰጡ እንደነበር ጽፏል።
“ከሠራዊቱ መካከል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ:: በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹም ዘማቹን እያጫዎቱ ይሄዳሉ:: አብሯቸው የሚሄደው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሯቸዋል:: አዝማሪዎቹም የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይሄዳሉ…” እያለ የአዝማሪዎችን ሚና ይዘረዝራል:: የአዝማሪዎች ሚና ከጦርነት ባሻገር በሌሎች የሕይወት ዘርፎችም ጥልቅ ፍልስፍናዎች የሚያንጸባርቅ ነው::
በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት አዝማሪዎች በጦርነት ላይ ከፍተኛ ወኔ በመስጠት ውለታ ማበርከታቸውን መኖሪያውን በደቡብ ጐንደር ዞን እብናት ከተማ ያደረገው አዝማሪ አበበ መብሬ አጫውቶኛል:: በዚያን ጊዜ በስማዳ ደጃች አጥናፉ አዩ እና ደጃች ታደሰ አብተው ነበሩ:: በመቀጠዋ ፊታውራሪ ደስታ ሸበሽ እና ደጃች ከበደ እንግዳ ነበሩ:: በቋሊሳ ቄስ ረዳ ዋሴ፣ ደጃች በላቸው እና ፊታውራሪ ደምስ ነበሩ:: እንዲሁም በበለሳ ፊታውራሪ ማሩ እና ፊታውራሪ አስፋው ነበሩ:: እነዚህ መሪዎች ጣሊያን ሕዝብን መግደል እና ቤት ማቃጠል ሲጀምር ሕዝብን በማደራጀት ታገሉት:: ያን የትግል ታሪክ ነው አበበ መብሬ ያጫዎተኝ። አዝማሪዎች ይህንን ታሪክ በትውልድ ቅብብሎሽ ይዘውት ቀጥለዋል:: አዝማሪ አበበ መብሬ እሱ በዚያን ጊዜ ባይደርስም በታሪክ የሰማውን፣ አያቱ የተሳተፉበትን፣ አባቱ ያወረሱትን ታሪክ ያውቃል።
በጦርነቱ ጊዜ አዝማሪዎች ይፈለጋሉ:: ድግስ ይዘጋጃል። ለዚህም መኳንንቱ ይሰባሰባሉ:: ባል እና ሚስቱ አዳነ ወልዴ እና ውሽዋ ደብሬ የተባሉ የደብረ ታቦር ታዋቂ አዝማሪዎችን ጠርተው ሙጃ ሮቢት አንፋርጌ ሜዳ ላይ ደጃዝማች ታደሰ አብተው ግብዣ አዘጋጁ ይላል አበበ:: አዝማሪው እና ሕዝቡ ተሰብስቦ መሪዎችን ያወድሳል:: አዝማሪ አበበ መብሬ እንደሚለው አዝማሪ አዳነ ወልዴ ከማሲንቆ ባሻገር ሁለት ፈረንጆችን ድርኳሴ በተባለ ቦታ ላይ በበልጅግ ማርኳል:: ለዚህም ረጅም አልቤን ከሰማኒያ ጥይት ጋር ተሸልሟል:: ባለቤቱ ውሽዋ ደብሬም፣
“የፈረንጅ አለቃ ሄደ ገሰገሰ
መቀጣዋ ከቤ ስማዳ ታደሰ፤
አርብ የተጠመደ ማክሰኞ ተፈታ
የመቀጣዋ ጀግና ፊታውራሪ ደስታ፤
አንድም እያዳ ላይ ሀምሳ ሰው ታረደ
አንድም ዘቀል ሞቃ ሰባ ሰው ነደደ
ይሄንን ሰማና ተነሳ ከበደ፤
አባ ማእበል ከቤ እጁም ቀናሳ ነው
እግሩም ቀናሳ ነው ብሎ ሰው ይንቃል
ጥጥም አይፈትልበት ለተኩስም ይበቃል”
ብላ አወደሰች:: በዚህ ጊዜ ደጃዝማች ከበደ እንግዳ በቅሎዋን ሙሉ እቃዋን እንደተሸለመች አበረከቱላት ሲል አበበ አጫውቶኛል::
አበበ መብሬ ታሪክን እሱ ከኖረበት ዘመን በላይ ከዜማ ጋር በማዜም ታሪክ እየሰነደ ያለ አዝማሪ ነው:: ጥልቅ የሕይወት ፍልስፍናዎችን በግጥሞቹ ያነሳል:: ሕይወት ወራጅ ውኃ ነው:: ከጉዞው በፈቃዱ ለሰከንድ የሚገታ የለም:: ሞት አለ:: ልደት አለ:: ሕጻኑ አርጅቶ ይሞታል:: አበበ አያቶቹን እና ወዳጆቹን በማንሳት በትዝታ ያንጎራጉራል::
ትላልቁ አለቀ እንግዳ የሚሸኘው፤
ይሄንን አውሲያም (ክፉ) ቀን እየተሰቀቀው
ብሎ ሞትን ያዜማል::
የሀገሬ መኳንንት አንዳንዱ ሲነሳ
ከመሸ ማድርበት ሰው አጣሁኝሳ፤
የሀገሬ መኳንንት አንዳንዶች ቀርታችሁ
ምነው እንደ ዶሮ መተካተካችሁ::
ጊዜ በአበበ መብሬ ግጥሞች ውስጥ ትልቅ ጉልበታም ተፈጥሮ ነው:: ይህ ዓለም ከዘር ጋር ወዳጅነት ያለው ቢመስልም እንኳን ሰዎች በሚይዙት ሀብት እና እሴት ክብር እና ሞገስ እንደሚያገኙ ያነሳል:: ይህን ክብር ፍለጋ ሲሉ የሰው ልጆች ከተወለዱበት አፈር፣ ሰፈር፣ መንደር፣ ባህል፣ ቤተሰብ ርቀው ይሰደዳሉ:: የሰው ልጆች ትርጉም ከክብር ጋር የተያያዘ መሆኑን ያነሳል:: ያንን ክብር ፍለጋ ሁልጊዜ መዳከር አለ::
እናቴ ትልቅ ናት ይላል የሰው ሞኝ
አባቴ ትልቅ ነው ይላል የሰው ሞኝ
ትንሹም ትልቅ ነው እንጀራ ሲያገኝ፤
እንጀራ ሆነና ደጉ ቁም ነገሩ
አልቀበር አለ ሰው ሁላ በአገሩ::
ጊዜ አሁንም ጉልበታም ሆኖ በግጥሞቹ ውስጥ ይመጣል:: ከሌለህ የለህም የሚለውን ሐሳብ ያንጸባርቃል::
አልጋ እና ትራሱ አሁን ለምንድን ነው
የሚያዘቃዝቀው የሚያቃናው ቀን ነው፤
ጊዜያትና ወራት ዘንበል ያለ እንደሆን
ለምን ይታገላል ወዳጅ ጠላት ሊሆን፤
ገብስ ይሆናል ጠላ ማር ይሆናል ጠጅ
ጊዜ ለጣለው ሰው መቼ አለው ወዳጅ::
የጊዜ ማብቂያ ምእራፍ የሆነው ሞት በአበበ ግጥሞች ውስጥ አለ:: ሞት ፍትሐዊ ዳኛ ሆኖ ይመጣል:: የሰው ልጆች አኗኗር በየትኛውም መጠን ቢለያይ እኩል የሚያደርጋቸው ከሕይወት በጊዜ አማካይነት የሚቀንስ ያደፈጠ ሞት ይመጣል:: ሰዎች በመኖር ቢለያዩ በሞት እንድ ይሆናሉ::
እኩሉም ሀብታም ነው፣ እኩሉም ደሀ ነው
እኩሉም ረጅም ነው፣ እኩሉም አጭር ነው
እኩሉም ወፍራም ነው፣ እኩሉም ቀጭን ነው
እኩሉም ቀይ ነው፣ እኩሉም ጥቁር ነው
የሚያስተካክለን፣ ግብዐተ-መሬት ነው::
ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚገናኝ ሌላውን የአበበ ሐሳብ ላስቀጥል:: የሰው ልጆች አንዳንድ ጊዜ በፍቅር ብቻ ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነበር:: ነገር ግን ዓለም በፍቅር ብቻ አትኖርም:: ሀብት ውስን ነው:: ስልጣን ያለው ዓለምን ይመራል:: ኃይል ያለው መሪ ይሆናል:: ሰዎችን የሚያጋጫቸው የኃይል የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ ትግል ነው:: ያን ትግል ማሸነፍ ደግሞ ያስከብራል:: የሰዎች ግጭት እና መካሰስ ለክብር እና ለበላይነት ነው:: አሸናፊዎች የሚቀጥሉበት ተሸናፊዎች የሚጠፉበት የዓለም ስርዓት አበበ የሚያነሳውን የአዳም ልጆች መካሰስ አመጣ:: ሟቹ የሰው ልጅ ለመሬት ምን ያጣላዋል ቢልም በሕይወት የመቀጠል ጥያቄ ግን እስከ መቃብር ያሳድደናል::
ሞኝ ነው የአዳም ልጅ
ሞኝ ነው የሔዋን ልጅ
በመሬት ተጣልቶ ዶሴ እየከፈተ
ይጨርሳል ሀብቱን
የኋላ የኋላ ላያጣው መሬቱን::
ምን ያጣላችኋል እኔ አርሰው እኔ አርሰው
ተጨንቆ አይደለም ወይ ምድር ሲገባ ሰው
እኩሉን አንጥፎ እኩሉን ሊለብሰው::
አበበ መንፈሳዊ ሆኖ ዓለምን በቅኔያዊ ግጥሞቹ ተመለከታት:: ግራችሁን ለሚመቷችሁ ቀኛችሁን ስጡ በሚል መነጽር ውስጥ ይህ ሐሳብ ትክክል ነው:: ዓለም ግን ከሕግ እና ስርዓት በተጨማሪ የምትመራበት ሕግ አላት፤ ሀገር በጦርነት ትጸናለች የሚል:: ሕዝብ ለሀገራቸው የሚያደርጉትን ፍልሚያ ትባርካለች:: ግለሰቦችም ይህን ሕግ ይዋሱታል:: ቻርለስ ዳርዊን አሸናፊዎች በሕይወት ይቀጥላሉ እንዳለው ብቻ ሳይሆን ተሽናፊም ይጠፋል:: አበበ የሚለው የሰው ልጅ ተሳስቷል ነው:: የመቃብር መሬቱ ተዘጋጅቶለት ለምን ስለመሬት ይጋደላል ነው የሚለው:: አፈር ተንተርሶ፤ አፈር ለብሶ የሚተኛ የሰው ልጅ ለመሬት ብሎ ባይጣላ መልካም ነበር- ጉዞው ወደ እሱ ነውና::
የሰው ልጆች በመሬት የሚጣሉት መሬትን የመኖሪያ አማራጫቸው ስላደረጉት ነው:: የጠብ ሱስ አልነበረባቸውም:: መጀመሪያ መሬትን ይጠቀሙባታል:: አልምተው፣ አርሰው እና ቆፍረው ሲሳዩዋን ይበሉባታል:: ለዚህም ጸጋየን ዘረፋችሁት ብላ ትቆጣለች:: ከሰው ልጅ ጋር ትቀያየማለች:: ግን ሰው እና መሬት ይህን ጠብ በእርቅ ይፈቱታል:: አበበ
ከመሬትስ ጋራ ታረቅነ በመላ
ፊት እኛ በልተነው ኋላ እሱ ሊበላ
የሚለው ይህን ነው::
መሬት አባት በልቶ
መሬት እናት በልቶ
አክስት አጎት በልቶ
ቢሰራበት ካሳ
እህል አበቀለ ሁሉን የሚያስረሳ::
የሰው ልጅ በሆዱ የሚታለል ደካማ ነውና እናት አባቱን ዘመዱን ከገደለበት ከመሬት ጋር ይታረቃል:: አዝማሪዎች ግጥሞቻቸው ቢጠኑ ይህን መሰል ጥልቅ አተያዮችን የመዘገቡ ናቸው:: የአበበ መብሬ ግጥሞችም ይህን የሚያሳዩ ናቸው።
መረፊያ
ሰባቱ ደጅ አዝማች ስምንተኛው ካሳ
ምርት አደረጋቸው ወቅቷቸው ተነሳ
አዝማሪ አብተው ለደጅ አዝማች ካሳ ( በኋላ አጼ ቴዎድሮስ) ያቀረበው ታሪክ ቀመስ የሙገሳ ግጥም፡፡
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


