የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ብርሐኑ አማረ የታሸጉ ምግብ እና መጠጦችን ሲገዙ መግለጫ ሳያዩ ክፍያ እንደማይፈጽሙ ተናግረዋል:: በግዥ ወቅት ጥንቃቄ በማድረጋቸውም በጤናቸው ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እና የገንዘብ ኪሳራ መታደግ እንደቻሉ ያምናሉ:: በጉዳዩ ላይ የሚመለከተው ተቋም ሁሉ ለህብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ማከናወን እንደሚገባውም አቶ ብርሐኑ ጠቁመዋል::
ሕጉስ ምን ይላል?
በንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ አንድ(1) ላይ “ማንኛውም ነጋዴ በሚሸጣቸው የንግድ ዕቃዎች ላይ መግለጫ መለጠፍ ወይም በተለየ ወረቀት ላይ ጽፎ ለሸማቹ መስጠት አለበት” በሚል ሰፍሯል:: ለሽያጭ የሚቀርቡ የንግድ ዕቃዎች መግለጫ ያላቸው መሆኑን እና የተገለፀውም የንግድ ዕቃ መግለጫ አዋጁ ላይ በተደነገገው መሠረት መሆኑ መረጋገጥ አለበት::
የንግድ ዕቃ መግለጫ በሀገራችን እንዲለመድ እና እንዲስፋፋ ለማድረግ የሚመለከታቸው የሕግ አስፈጻሚ አካላት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ ሐሳባቸውን ለበኵር አጋርተዋል::
ለሸማቹ እና ለንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ፣ ከሸማቾችና ሌሎች ከሚመለከታቸው ሰዎች የሚመጡ ጥቆማዎችን መቀበል፣ ማደራጀት፣ መመርመርና ክስ መመስረት ከተግባራቱ መካከል ተጠቃሾች ናቸው:: የሕግ አስፈጻሚ አካላት የዳኝነት ችሎቱ የሚሰጠውን ውሳኔም የማስፈፀም ኃላፊነት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል::
የንግድ ዕቃ መግለጫ
የንግድ ዕቃ መግለጫ ሲባል በንግድ ዕቃው ላይ የሚፃፍ ወይም የሚለጠፍ ስለ ንግድ ዕቃው ስም፣ አጠቃቀም፣ አያያዝ (አቀማመጥ)፣ ምርቱ መጠቀሚያ ጊዜው ካለፈ ሊያስከትል ስለሚችለው ጉዳት …የያዘ ለሸማቹ ጠቃሚ የሆነ መረጃ ነው::
የንግድ ዕቃዎች መግለጫ የሚዘጋጀው በተለይም ምግብ ነክ ምርቶች የተለያዩ ባህሪያት ስለሚኖራቸው እንዲሁም ለአንዱ ሸማች የሚስማማ ለሌላው ላይስማማ ስለሚችል ሸማቾች የሚገዙትን የንግድ ዕቃ መግለጫ በማንበብ የሚስማማቸው መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገዙ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል:: በመሆኑም ሸማቾች የንግድ ዕቃ በሚገዙበት ወቅት የንግድ ዕቃው ማሸጊያ ላይ የተፃፉትን ወይም የተለጠፉትን መግለጫዎች በጥንቃቄና በተገቢው መንገድ ማንበብ እና መረዳት እንዳለባቸው አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል::
የመግለጫው ጥቅም
* የንግድ ዕቃ መግለጫ ስለ ንግድ ዕቃው ሥም፣ ይዘት፣ ዋጋ፣ የተመረተበትን ሀገር፣ የተመረተበትን ቀን፣ የአገልግሎት ጊዜና መሰል ጠቃሚ የሆኑ አጠቃላይ መረጃዎችን ይሰጣል::
- ሸማቾች ወይም ተጠቃሚዎች የሚገዙትን የንግድ ዕቃ ለማማረጥ ወይም ለማወዳደር ይረዳል::
- ስለንግድ ዕቃው አጠቃቀም፣ አያያዝ፣ አቀማመጥ፣ አወጋገድና በአጠቃቀም ወቅት ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ካለ ስለሚያስከትለው ጉዳትና መሰል ነገሮች ሸማቾች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል::
- በሕግ የተጣለን ኃላፊነት መወጣትን ያረጋግጣል::
- ሸማቹ ለሚገዛው ዕቃ ጥራትና አይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብቱን እንዲገለገልበት ያስችላል::
የንግድ ዕቃ መግለጫ ሊይዝ የሚገባው ነጥቦች
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የንግድ ዕቃ መግለጫ ማሟላት ያለበትን ነጥቦች አስፍሯል:: እነዚህም የንግድ ዕቃውን ሥም፣ የተሠራበትን ወይም የመጣበትን ሀገር፣ ጠቅላላ እና የተጣራ ክብደት፣ መጠን እና ብዛት፣ ጥራት፣ ከምን እንደተመረተ፣ የአሠራር ወይም የአጠቃቀም ዘዴው፣ በአጠቃቀም ወቅት ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች፣ ነጋዴው ስለንግድ ዕቃው አገልግሎት ለገዢው የሚሰጠውን ዋስትና፣ የአምራቹን፣ የአሻጊውን እና የአስመጪውን ሥምና አድራሻ ሊይዝ ይገባዋል::
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የንግድ ዕቃ መግለጫ ከንግድ ዕቃው ላይ በቀላሉ የማይላቀቅ ሆኖ ፅሑፉም የሚታይ፣ ግልፅ እና ሸማቾች በቀላሉ ሊያነቡትና ሊረዱት የሚችሉት እንዲሁም ከምልክት ይልቅ በጽሑፍ የቀረበ አገላለፅ ሊኖረው ይገባል::
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመለከቱትን መስፈርቶች ያሟላ መሆኑን እና የኅብረተሰቡን ጥቅም ለመጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሚኒሥቴሩ በሕዝብ ማስታወቂያ የሚያወጣቸውን ሌሎች ዝርዝሮች መያዝ እንዳለበትም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል::
የአምራቾች እና አስመጪዎች ግዴታ እና ኃላፊነት
አምራቾች የሚያመርቱት የንግድ ዕቃ ለአጠቃቀም አመቺ ወይም ተስማሚ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል:: ይህም ማንኛውም አምራች ሊያገኘው ከሚችለው ትርፍ ጎን ለጎን የሸማቾችን ጥበቃ፣ ደህንነት እና እርካታ ከግምት ያስገባ በሆነ መልኩ መወሰን አለበት::
በመሆኑም በተለይ ምግብ ነክ ምርቶች በበቂ የንግድ ዕቃ መግለጫ ኖሯቸው እንዲመረቱ መደረግ አለባቸው:: የዚህ ኃላፊነት በዋነኝነት ለአምራቹ ወይም ለአቅራቢው የተሰጠ በመሆኑ አምራቾች በዚህ ረገድ ማድረግ የሚኖርባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ ነው::
- ትክክለኛ መረጃ የመስጠት
የንግድ ዕቃ መግለጫ ዋና ጥቅም ስለምርቱ ለሸማቾች መረጃ መስጠት፣ ማስተማር እና በአጠቃቀም ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ ጉዳቶች መጠበቅ በመሆኑ የሚፃፉ ወይም የሚለጠፉ የንግድ ዕቃ መግለጫዎች ሸማቹን የሚያሳስቱ መሆን የለባቸውም:: በመሆኑም የንግድ ዕቃ መግለጫዎች ትክክለኛ እንዲሆኑ ማድረግ የአምራቹ ኃላፊነት እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል::
* ሸማቾችን የመካስ
አምራቾች የሚያመርቷቸው ምርቶች የሸማቾችን ደህንነትና እርካታ የሚጠብቁ እንዲሆኑ ማድረግ በአዋጁ የተቀመጠ ግዴታ ነው:: ይሁንና በምርት ሂደት ውስጥ በሚከሰት ስህተት ሸማቾች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል:: በመሆኑም በአጠቃቀም ወቅት በሸማቾች ላይ ለሚደርስ ጉዳት አምራቾች ተጎጂ ሸማቾችን ለመካስ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆን ይኖርባቸዋል:: ከዚህም በተጨማሪ አስተያየቶችን ለመቀበልና የንግድ ዕቃ መግለጫዎችን በተመለከተ የሚኖሩ ክፍተቶችን ለማሻሻል ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል::
ይህም ሥነ ምግባርን የተላበሰ የንግድ ተግባር ለሸማቾች ጥበቃ ከሚያበረክተው ጥቅም ባሻገር ከሸማቾች ተቀባይነት ስለሚያገኝ ንግዱ ዘላቂነት እንዲኖረው ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ነው::
የሸማቾች ኃላፊነት
- መግለጫዎችን በአግባቡ የማንበብ ልምድ ማዳበር
ከንግድ ዕቃ መግለጫዎች ጋር በተያያዘ ሸማቾች መጀመሪያ ማድረግ የሚገባቸው መግለጫዎችን በጥንቃቄ የማንበብ ልምዳቸውን ማዳበር ነው:: ሸማቾች መግለጫ ያላቸውን የንግድ ዕቃዎች መምረጥና መግለጫዎችንም በሚገባ አንብቦ የመግዛት ልምዳቸውን ካዳበሩ አምራቾች በሚያመርቱት የንግድ ዕቃ ላይ ለሚፅፉት ወይም ለሚለጥፉት መግለጫ ትኩረት እንዲሰጡ ያደርጋል::
- ጥቆማና ግብረ-መልስ መስጠት
ሸማቾች ሊወጡት የሚገባው ሌላው ኃላፊነት በቂ ያልሆኑና አሳሳች መግለጫዎችን ለአምራቹ ወይም ለአቅራቢው አስተያየት (ግብረ መልስ) መስጠትና ከዚህም ጎን ለጎን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥቆማዎችን ማቅረብ ነው::
ሸማቾች ይህን በሚያደርጉበት ወቅት አምራቾች ስለንግድ ዕቃዎች መግለጫ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ከማድረጉም በላይ ጥቆማው የሚደርሰው የመንግሥት አካል መሰል የንግድ ዕቃ መግለጫዎች እንዲስተካከሉና ለሸማቹ ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ይረዳዋል:: ስለሆነም አምራቾች የሚለጥፏቸውን ወይም የሚፅፏቸውን መግለጫዎች ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻሉ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ይሆናል::
- የሸማቾች ማህበራት አባል መሆን
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የሸማቾች ማህበራት ዋና ዓላማ ሸማቾችን ማስተማርና መጠበቅ (መከላከል) መሆኑ ነው:: በመሆኑም ማህበራት አባል በመሆን ራስን ማስተማርና በሂደትም በጋራ የንግድ ዕቃ መግለጫዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህም አምራቾች ለንግድ መግለጫ አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጡና በየጊዜው እንዲያሻሽሉ ያበረታታቸዋል::
- ከመግዛት መቆጠብ
ከላይ ከተገለፁት ተግባራት በተጨማሪ ሸማቹን የሚያሳስቱ የንግድ መግለጫዎች ያሉባቸውን ወይም የንግድ ዕቃ መግለጫ ያልተለጠፈባቸውን ምርቶች ከመግዛት መቆጠብ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም የንግድ ዕቃዎች መግለጫ ካልተለጠፈባቸው የታሸገው ዕቃ ምን እንደሆነ፣ የተመረተበትንና አገልግሎቱ የሚያበቃበትን ጊዜ የምናውቅበትን ሁኔታ… የሚያሳጣን በመሆኑ የንግድ ዕቃ መግለጫ የሌለውን ምርት ገዝተን መጠቀም ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝንበት ዕድል የሚፈጠርበት አጋጣሚ ሊበዛ ይችላል::
ከዚህ በተጨማሪም አምራቾች ወይም አስመጪዎች የሚፅፏቸውን ወይም የሚለጥፏቸውን መግለጫዎች እንዲያሻሽሉ ከማድረጉም በላይ መግለጫዎችን የማይፅፉ ወይም የማይለጥፉ አምራቾችም የንግድ ዕቃ መግለጫ እንዲፅፉ (እንዲለጥፉ) የማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል:: ስለሆነም ሸማቾች እነዚህን ከላይ የተገለፁትን ተግባራት በመፈፀም አምራቾች (አስመጪዎች) የሚሸጧቸውን የንግድ ዕቃዎች መግለጫ እንዲኖርባቸውና መግለጫዎቹም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ እንዲሄዱ ማድረግ ያስችላቸዋል::
የህግ አንቀጽ
የወንጀል ተጠያቂነት
በንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ የተገለፁ የንግድ ዕቃ መግለጫ ይዘትን በተላለፈ መልኩ የተገለፀ እንደሆነ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት ከብር 5,000 (አምስት ሺህ ብር) እስከ ብር 50,000 (ሀምሳ ሺህ ብር) በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና በቀላል እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ አስገንዝበዋል፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


